Thursday, December 7, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየፌዴራል መንግሥት በክልሎች የሚዘረጋቸውን የመሠረተ ልማት አውታሮች ፍትሐዊ ሥርጭት የሚከታተል ኮሚሽን የሚያቋቁም...

የፌዴራል መንግሥት በክልሎች የሚዘረጋቸውን የመሠረተ ልማት አውታሮች ፍትሐዊ ሥርጭት የሚከታተል ኮሚሽን የሚያቋቁም ረቂቅ አዋጅ ቀረበ

ቀን:

ኮሚሽኑ የድጎማና የጋራ ገቢዎች ክፍፍል የሚደረግበትን ቀመር የማዘጋጀት ኃላፊነት ይኖረዋል

በፌዴራል መንግሥት ባለቤትነት በክልሎች ውስጥ የሚዘረጉ የመሠረተ ልማት አውታሮች፣ በክልሎች መካከል የሚኖራቸውን ፍትሐዊ ሥርጭት የሚከታተልና በገለልተኛ ባለሙያዎች የሚዋቀር ኮሚሽን የሚያቋቁም ረቂቅ ሕግ ለፓርላማ ቀረበ።

ረቂቅ ሕጉ እንዲቋቋም የሚጠይቀው ኮሚሽን የመሠረተ ልማቶች ፍትሐዊ ሥርጭትን ተከታትሎ ጉድለቶችንና መስተካከል ይገባቸዋል የሚላቸውን ምክረ ሐሳቦች፣ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት አቅርቦ ውሳኔ እንዲሰጥበት እንደሚያደርግ የሕግ ሰነዱ ያመለክታል።

የሚቋቋመው ተቋም ስያሜ “የፌዴራል ድጎማና የጋራ ገቢዎች ክፍፍል ኮሚሽን” ሲሆን፣ የፌዴራሉ መንግሥት ለክልሎች የሚሰጠውን ዓመታዊ ድጎማ የሚደለደልበት ወይም ለፌዴራሉ መንግሥትና ለክልሎች የጋራ ተብለው በሕገ መንግሥቱ የተመደቡ ገቢዎች በሁለቱ መካከል የሚከፋፈልበትን ቀመር በሚመለከት፣ ተፈላጊውን በጥናት ላይ የተመሠረተ ምክረ ሐሳብ በማዘጋጀት ለፌዴሬሽን ምክር ቤት የማቅረብ ኃላፊነትም ይኖረዋል።

ረቂቅ አዋጁን ያሰናዳው የፌዴሬሽን ምክር ቤት ረቂቁ እንዲፀድቅለት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የላከ ሲሆን፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም በረቂቅ ሕጉ ይዘት ላይ ሐሙስ ኅዳር 4 ቀን 2012 ዓ.ም. የመጀመሪያ ውይይት ካደረገ በኃላ፣ ለዝርዝር ዕይታ ለሕግ ፍትሕና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መርቶታል።

ረቂቁ ኮሚሽኑን ከማቋቋም ባለፈም ክልሎች ከፌዴራል መንግሥት የሚያገኙትን የበጀት ድጎማ ዓይነትና የሚከፋፈሉበትን፣ እንዲሁም ክልሎችና የፌዴራል መንግሥት የጋራ ገቢዎች የሚከፋፈሉበትን መርህ እንደ አዲስ የሚወስንና ክፍፍሉ የሚፈጸምበትን ሥነ ሥርዓት የሚያበጅ ነው።

 ረቂቅ የሕግ ማዕቀፉን ያዘጋጀው ጉዳዩን በተመለከተ ሕገ መንግሥታዊ ሥልጣን የተሰጠው የፌዴሬሽን ምክር ቤት ሲሆን፣ የሕግ ማዕቀፉ የመጀመሪያ ረቂቅ ተጠናቆ ከክልል መንግሥታት ጋር ውይይት እየተደረገበት ነው። እስካሁን የፌዴራል መንግሥት የሚመድበውን የድጎማ በጀት ለክልሎች የሚደለድልበትም ሆነ፣ የጋራ ገቢዎች የሚከፋፈሉበት የአሠራር ሥርዓት ወጥነትና ቅንጅት የጎደለው ነበር፡፡ በዚህም ምክንያት በክፍፍሉ ሚዛናዊነትና ውጤታማነት ላይ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተስተዋሉ የመጡ ክፍተቶችን ለመቅረፍ ይቻል ዘንድ መደበኛ የአሠራር ሥርዓት ተግባራዊ ማድረግ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ፣ አዲስ የሕግ ማዕቀፍ ለማዘጋጀት መቻሉን የረቂቁ መግቢያ ያመለክታል።

በተጨማሪም የክፍፍሉ ሒደት የበለጠ ግልጽነት፣ ፍትሐዊነትና ተጠያቂነት ይሰፍንበት ዘንድ ተቋማዊ አደረጃጀት መፍጠር በማስፈለጉ የሕግ ማዕቀፉ እንዲዘጋጅ ምክንያት መሆኑን ያስረዳል።

በረቂቅ የሕግ ማዕቀፉ መሠረት የፌዴራል መንግሥት ለክልሎች የሚሰጠውን ድጎማ በተመለከተ ሁለት የድጎማ ዓይነቶች ተሰይመዋል። አንደኛው የድጎማ ዓይነት ለጥቅል ዓላማ የሚውል ድጎማ የሚል ስያሜ የተሰጠው ነው፡፡ በዚህ የድጎማ ዓይነት ላይ ምንም ዓይነት ቅድመ ሁኔታ እንደማይቀመጥበትና ክልሎች ከራሳቸው ተጨባጭ ሁኔታ አንፃር ቅድሚያ ለሚሰጧቸው ዓላማዎች የሚያውሉት የበጀት ድጋፍ መሆኑን ሰነዱ ያስረዳል። ጥቅል ድጎማው ለክልሎች የሚከፋፈልበት ቀመር በአሁኑ ወቅት በሥራ ላይ ከሚገኘው የድጎማ ቀመር ጋር ተመሳሳይ ነው።

በመሆኑም የፌዴራል መንግሥት ለክልሎች የሚመድበው ጥቅል ድጎማ የሚከፋፈለው፣ የክልሎችን የወጪ ፍላጎትና ዕምቅ የገቢ አቅም መሠረት በማድረግ እንደሚሆን በረቂቁ ተመልክቷል።

የፌዴራል መንግሥት ለክልሎች የሚሰጠው ሁለተኛው የድጎማ ዓይነት ደግሞ፣ የውስን ዓላማ ድጎማ እንደሚሆን ሰነዱ ይገልጻል። ይህ የድጎማ ዓይነት አንድ የተወሰነ ወይም የተገደበ ዓላማን ለማሳካት ታስቦ ለክልሎች የሚሰጥ የበጀት ድጋፍ እንደሆነ ተጠቅሷል።

ውስን ዓላማ ያለው ድጎማ የሚሰጥበት መርህ በረቂቁ ተዘርዝሮ የተቀመጠ ሲሆን፣ የፌዴራል መንግሥት በክልሎች ወሰን ውስጥ ልዩ ትኩረት ሊሰጣቸው ለሚገቡ አገራዊ ፋይዳ ያላቸውን ጉዳዮች ለማስፈጸም፣ በአንድ ክልል የሚሰጥ አገልግሎት በሌላ ክልል ላይ አዎንታዊ ወይም አሉታዊ ተፅዕኖ በማሳደሩ ምክንያት የሚያስከትለውን ወጪ ለማካካስ፣ ለሴቶች እኩል ተጠቃሚነት፣ ለዘላቂ ልማትና የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋምና የመሠረተ ልማት ክፍተቶችን ለማጥበብ የሚሉት ይገኙበታል።

ይህ ውስን ዓላማ ያለው ድጎማ የሚከፋፈልበትን መርህ ረቂቁ ያስቀመጠ ሲሆን፣ ድጎማው ከመሰጠቱ በፊት ተጠቃሚ ክልሎች ዓላማውን በተመለከተ ከፌዴራል መንግሥት ጋር ስምምነት እንዲፈጽሙ ይጠበቅባቸዋል።

የሥራ አፈጻጸምና የበጀት አጠቃቀም ውጤታማነት፣ እንዲሁም ግልጽነትና ተጠያቂነት የውስን ዓላማ ድጎማው ማከፋፈያ መርሆዎች ተብለው ከተዘረዘሩት መካከል ዋነኞቹ ናቸው።

ረቂቅ የሕግ ማዕቀፉ የፌዴራል መንግሥት ለክልሎች ስለሚሰጠው የድጎማ ዓይነትና ክፍፍሉ የሚፈጸምባቸውን መርሆች አስመልክቶ ከያዛቸው ድንጋጌዎች በተጨማሪ፣ ክልሎችና የፌዴራል መንግሥት የጋራ ገቢዎቻቸውን የሚከፋፈሉበትን መርህና ሥርዓት የተመለከቱ ድንጋጌዎችንም አካቷል።

የጋራ ገቢዎቹ አሁን የሚከፋፈሉበት አሠራር የገቢ ዓይነቶቹን መሠረት አድርጎ በሕግ በተቀመጠ የድርሻ ምጣኔ ወይም በመቶኛ የተሰላ ምጣኔ መሆኑ ይታወቃል።

ለአብነት ያህል ክልሎችና የፌዴራል መንግሥት በማዕድን ዘርፍ ላይ በጋራ የሚጥሉትን የሮያሊቲ ክፍያ የሚከፋፈሉት፣ ረጅም ዓመታት ባስቆጠረው የሮያሊቲ ክፍያ ድንጋጌ ባስቀመጠው ምጣኔ መሠረት ነው፡፡ በዚህ መሠረት የፌዴራል መንግሥት 60 በመቶ ድርሻ ሲኖረው፣ ቀሪው 40 በመቶ ደግሞ የማዕድን ሀብቱ የሚገኝበት ክልል ድርሻ ነው።

አዲስ የተረቀቀው የሕግ ማዕቀፍ የጋራ ገቢዎች ክፍፍል የክልሎችንም ሆነ የፌዴራል መንግሥቱን የወጪ ፍላጎቶችና የገቢ አቅማቸውን ከግምት ውስጥ በማስገባት እንደሚሆን፣ መሠረታዊ መርሆቹም የገቢ ምንጭ፣ የነፍስ ወከፍ እኩልነትና የማመጣጠኛ መርሆዎችን ባማከለ መንገድ እንደሚሆን ያመለክታል።

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...