አገር አቀፍ የስፖርት ምክር ቤት የተመሠረተው ከ1990ዎቹ መጀመሪያ ጀምሮ ቢሆንም፣ ከመንግሥት የካቢኔ አደረጃት ጋር ተያይዞ በሕግ የተሰጠውን ኃላፊነት መወጣት ተስኖት ቆይቷል፡፡ ምክር ቤቱ ከአሁን በፊት የፌደራሉን ስፖርት ኮሚሽን ለማቋቋም በወጣው አዋጅ ቁጥር 692/2003 መሠረት የኮሚሽኑ አንድ አካል ሆኖ ተቋቁሞ የአገሪቱን ስፖርት ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ እንዲመራና እንዲደግፍ በሚል እንደነበር በወቅቱ ሲነገር ነበር፡፡
ስፖርቱን በበላይነት እንዲያስተዳድሩ የሚቋቋሙ መሥሪያ ቤቶችን በሚመለከት የቀረቡ መዛግብት እንደሚያስረዱት ከሆነ፣ የኢትዮጵያ ስፖርት ከቀደምቶቹ መንግሥታት ጀምሮ ወጥ የሆነ የተጠሪነት ወሰን ተበጅቶለት አያውቅም፡፡ አገሪቱን የማስተዳደር ታሪካዊ አጋጣሚ ያገኙ ከቀደምቶቹ ጀምሮ አሁንም ድረስ ስፖርቱ እንደሌሎቹ የልማት ተቋማት ፋይዳው በውል ተለይቶ፣ ወጥነት ያለው መዋቅራዊ አደረጃጀት ሳይበጅለት መቆየቱ ውድቀቱ ብቻ ሳይሆን አሁንም ድረስ በዘፈቀደ እንዲቀጥል ዓይነተኛ መንስኤ ሆኖ መቆየቱ የሚያምኑ በርካቶች ናቸው፡፡
በዋናነት ስፖርቱን እንዲያስተዳድር የሚቋቋመው ተቋም ግልፅ የሆነ የተጠሪነት ወሰን ሳይኖረው፣ አንዴ ከወጣት ሌላ ጊዜ ከባህል፣ ሲያስፈልግ ደግሞ ኮሚሽን ሆኖ ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ እየሆነ መነሻና መድረሻውን ሳያውቅ ዘመን አስቆጥሯል፡፡ ይሁንና በስፖርቱ ላለው ችግር መፍትሔ እንደሚሆን እምነት ተጥሎበት የነበረውና በ1990 ዓ.ም. በአገር አቀፍ ደረጃ የተመሠረተው ብሔራዊ የስፖርት ምክር ቤት ነበር፡፡
ስፖርቱ በኮሚሽን ደረጃ ሆኖ ብሔራዊ ምክር ቤቱን እንዲያስተዳድር በአዋጅ የተሰጠውን ኃላፊነት እንዳለመታደል ሆኖ እንዳይመራ መንግሥታዊ ተግዳሮቶች አላንቀሳቀሱትም፡፡ ምክር ቤቱ ተጠሪ ስለሌለው ሥራውን እንዲያቆም ምክንያት እንደሆነው በኮሚሽኑ የቆዩ ሙያተኞች ይናገራሉ፡፡ መንግሥት የሚያቋቁማቸው የካቢኔ አደረጃጀቶች ከተግዳሮቶቹ ዋና ዋናዎቹ ስለመሆናቸው ጭምር ያስረዳሉ፡፡
እንደ ሙያተኞቹ ስፖርቱ በ2008 ዓ.ም. በኮሚሽን ደረጃ በነበረበት ወቅት ምክር ቤቱን እንደገና ለማቋቋም ሙከራ አድርጎ የነበረ ቢሆንም፣ አደረጃጀቱ ብዙም ሳይቆይ ተመልሶ በሚኒስቴር ደረጃ ወጣቶችና ስፖርት በሚል፣ አሁን ደግሞ ተጠሪነቱ ለባህልና ቱሪዝም ሆኖ የቀጠለበትን ሒደት ይናገራሉ፡፡
የምክር ቤቱ ተጠሪነት አሁንም በግልፅ እንዳልተቀመጠ የሚናገሩት እነዚሁ አስተያየት አስጪዎች፣ ‹‹የኮሚሽኑ ተጠሪነት ለባህልና ቱሪዝም ነው፣ ኮሚሽኑን እንደገና ለማቋቋም የወጣው አዋጅ 692/2003 መሠረት ምክር ቤቱ የኮሚሽኑ አንድ አካል ነው ይላል፡፡ ባለፈው ሐሙስ ኅዳር 4 ቀን 2012 ዓ.ም. በሸራተን አዲስ የብሔራዊ ምክር ቤቱ ዳግም መመሥረቻ ጉባኤ ይፋ ሲደረግ፣ መድረኩን በመምራት የመሪነቱ ድርሻ በዋናነት የባህልና ቱሪዝም ሆኖ ታይቷል፤›› በማለት አሁንም የምክር ቤቱ ጉዳይ ያልጠራ አካሄድ እንደሚስተዋልበት ያስረዳሉ፡፡
በብሔራዊ ምክር ቤቱ ዳግም መመሥረቻ ጉባኤ ይፋ የተደረገው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በተገኙበት መሆኑ፣ መንግሥት ለዘርፉ ልዩ ትኩረት መስጠቱን እንደሚያሳይ መድረኩን በበላይነት የመሩት የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ሒሩት ካሳው (ዶ/ር) በመክፈቻ ንግግራቸው ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡
‹‹የስፖርቱን ሴክተር በተሻለ ደረጃ ለማልማትና ዓለም አቀፋዊ ተወዳዳሪነቱን ለማጎልበት በትኩረት መሥራት የሁሉም ባለድርሻ ኃላፊነት ሊሆን ይገባል፡፡ በዘርፉ የሚስተዋሉ ሕፀፆችን በማረም መሠረቱን የማስፋት፣ ተተኪ ትውልድ የማብቃትና ውጤታማነትን የማረጋገጥ ተግባራት በየደረጃው መከናወን አለበት፡፡ ይሁንና በአንዳንድ አካባቢዎች የስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራዎች የሥጋትና የግጭት ቀጣና እየሆኑ የመጡበት አግባብ ሊታረም ይገባዋል፡፡ ለዚህ የመንግሥት አካሉን ጨምሮ የዘርፉ ሙያተኞችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ማስመር ያለባቸውን በማስመር በቅንጅት መሥራት ይኖርባቸዋል፤›› በማለት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኰንን ለጉባኤው ጠንከር ያለ መልዕክት የያዘ ንግግር ማድረጋቸው ታውቋል፡፡
በዕለቱ የአገር አቀፉን ስፖርት ሪፎርም ፍኖተ ካርታ የሚያሳይ ሰነድ በሚኒስትር ዴኤታው አቶ ሀብታሙ ሲሳይ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል፡፡ በመድረኩ ላይ የክልል ርዕሰ መስተዳድሮች፣ የየክልሉ ስፖርት ኮሚሽነሮች፣ አገር አቀፍ የስፖርት ማኅበራት ፕሬዚዳንቶች፣ የብሔራዊ ፌዴሬሽኖች ጽሕፈት ቤት ኃላፊዎች፣ የታወቁ የስፖርት ሰዎችና ሙያተኞች መታደማቸው ከባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ይፋዊ ድረ ገጽ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡