Sunday, April 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹የውጭ ምንዛሪ ችግር አፈታቱ ኢኮኖሚውን እየገለደ የሚሄድ ከሆነ  ራሳችንን ወደ መብላት ነው የሚወስደን›› አቶ ደረጀ ዘበነ፣ የዘመን ባንክ ፕሬዚዳንት

አቶ ደረጀ ዘበነ ከ20 ዓመታት በላይ በኢትዮጵያ የባንክ ኢንዱስትሪ ውስጥ በማገልገል ይታወቃሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት የዘመን ባንክ ፕሬዚዳንት በመሆን በመሥራት ላይ ናቸው፡፡ ዘመን ባንክን በፕሬዚዳንትነት መምራት ከጀመራቸው በፊት በአዋሽ ባንክ በምክትል ፕሬዚዳንትነት ሠርተዋል፡፡ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክና በወጋገን ባንክ ውስጥም በሙያቸው ካገለገሉባቸው ተቋማት ውስጥ ይጠቀሳሉ፡፡ የጀርመን ኮሜርዝ ባንክ ተጠሪ በመሆን በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ውስጥ የሠሩት አቶ ደረጀ በቢዝነስ አስተዳደር በሕግና በማኔጅመንት ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ዲግሪዎች ያሏቸው አግኝተዋል፡፡ በኢትዮጵያ የፋይናንስ ኢንዱስትሪው በተለይም በቅርቡ ማሻሻያ በተደረገባቸው የፋይናንስ ሕግጋት፣ ከወቅታዊ ኢኮኖሚያዊ ችግር አንፃር በባንኮች ላይ ስላሳደረው ተፅዕኖ፣ የውጭ ዜግነት ላላቸው ኢትዮጵያውያን የፋይናንስ ዘርፉ በመከፈቱና በውጭ ባንኮች መግባትና አንድምታው ላይ፣  እንዲሁም በሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ዳዊት ታዬ ከአቶ ደረጀ ጋር ያደረገው አጭር ቆይታ እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡

ሪፖርተር፡- በአጠቃላይ የፋይናንስ ኢንዱስትሪው በተለይ የአገሪቱ የባንክ ዘርፍ ምን ደረጃ ላይ ይገኛል ማለት ይቻላል? ከየት ተነስቶ የት ደርሳል ተብሎ ሊገለጽ ይችላል?

አቶ ደረጀ፡- በእኔ ዕይታ የኢትዮጵያ የፋይናንስ ኢንዱስትሪ የተወሰኑ ለውጦችን ቢያሳይም፣ ከሌላው ዓለም ኢንዱስትሪ አንፃር ሲታይ ገና ብዙ ሥራ የሚጠይቅ፣ እንዲሁም ተወዳዳሪ የመሆን አቅሙ ገና እንደሆነ ነው የማስበው፡፡

ሪፖርተር፡- ብዙ የሚቀረውና ለመወዳደር የሚያስችለው ቁመና ላይ አይደለም ሲባል እንዴት?

አቶ ደረጀ፡- አንደኛ ኢንዱስትሪው ራሱ ራዕዩ የቱ ጋ እንደሆነና የት ይደርሳል ተብሎ የተገለጸ ነገር የለውም፡፡ ብዥታ ያለበት ነው፡፡ ስለዚህ መንግሥትም ይህንን ዘርፍ ወደ የትኛው አቅጣጫ እንደሚወስደው ግልጽ አይደለም፡፡ ሁለተኛ የኢትዮጵያን የባንክ ኢንዱስትሪ ብናየው በቴክኖሎጂ፣ በሰው ኃይልና በካፒታል እጅግ በጣም ያነሰና ገና ብዙ መሥራት የሚጠይቅ ነው፡፡ ለደንበኞች የሚሰጣቸው አገልግሎቶች እንኳን በጣም ብዙ የሚቀራቸው ናቸው፡፡ በጣም ባህላዊ የሆኑና ቀደምት ባንኮች ሲሠሯቸው የነበሩ ሥራዎች ናቸው እየተከናወኑ ያሉት፡፡ ከብዙ አቅጣጫዎች የኢትዮጵያን ባንኮች ስንመዝናቸው እጅግ በጣም ብዙ ሥራ ይጠይቃል፡፡ እዚህ ደረጃ ላይ ነን ብለን እንኳን ራሳችንን ገምግመን፣ እዚህ ውጤት ላይ ነን ብለን የሚያስደፍር ሥራ እየሠራን ነው አልልም፡፡

ሪፖርተር፡- ምክንያቱ ምንድነው?

አቶ ደረጀ፡- በእኔ ዕይታ እስካሁን ያሉት ባንኮች በምቾት ዞን ውስጥ ነበሩ፡፡ ስለዚህ ምቾት ዞን ውስጥ ስትሆን ደግሞ ያለውን ትቀበላለህ፡፡ ገበያ ውስጥ ያለው የሀብት ችግር ነው፡፡ ሀብቱን ለመሰብሰብ ከለላ አለ፡፡ ይኼ ሀብት ደግሞ ወሳኝ ነው፡፡ ስለዚህ ይኼ በውድድር የሚመራ ቢዝነስ አይደለም፡፡ አሁን በቅርብ ጊዜ በፖሊሲ ለውጥ ምክንያት እርስ በርስ ከሚደረግ ውድድር ባለፈ፣ ሌላ ዓለም ላይ ያለውን ዓይነት ውድድር አይደለም የምታየው፡፡ ምክንያቱም አንዳንዴ ወደ ውድድር ዓለም ስትገባ የሀብት ክምችት ስላለ፡፡ እሱ በራሱ ያግዝሃል፡፡ ውድድሩ ራሱ የከፋ ጫና እንዳያሳድርብህ ያግዝሃል፡፡ ለዚህም አንዱ ትልቁ ማሳያ የሚሆነው የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ አሁን ባለበት ሁኔታ ችግር ላይ እያለ፣ የውጭ ምንዛሪ እጥረቱ በተባባሰበትና አንዳንድ ፋብሪካዎችም ወደ ማቆም እየሄዱ ባሉበት፣ በርካታ ሥራ አጥ በሚኖርበት አገር ውስጥ እንኳን ብዙ ኢንቨስትመንት አይታይም በሚባልበት በዚህ ወቅት እንኳን የባንኮች ትርፍ በአኃዝ ሲታይ እጅግ በጣም የገዘፈ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ላቋርጥዎትና ይኼ ጥያቄ የብዙዎች ነው፡፡ ኢኮኖሚው ችግር ውስጥ ነው እየተባለ የባንኮች ትርፍ እያደገ ነው፡፡ እስኪ ስለዚህ ግልጽ ያድርጉልኝ?

አቶ ደረጀ፡- እዚህ ላይ ነው እንግዲህ ጥያቄዎች የሚነሱት፡፡ እንዲህ ያለውን ነገር ስትመለከተው አንደኛ የባንኮቹ ዋጋ ወሳኝ ናቸው፡፡ በአንድ የሞኖፖሊ ሥርዓት ውስጥ እንደሚኖረው ዋጋ ሰጪዎች እነሱ ናቸው፡፡ ዋጋ ተቀባይ አይደሉም፡፡ ደንበኛው የሚያቀርቡትን አገልግሎት ዓይቶ ሌላ ቦታ ላይ አማራጭ ኖሮትና አመዛዝኖ፣ ይኼኛው ለእኔ የተሻለ ነው ለማለት የሚያስችለው አይደለም፡፡ ይኼ ኢኮኖሚው በሀብት እጥረት ውስጥ መቀመጡን ነው የሚያሳየው፡፡ ለምሳሌ እንኳን የውጭ ምንዛሪ በአገር ውስጥ በሚሽከረከረው ገንዘብ እጥረት አለ፡፡ ከብድር ጋር ተያይዞ ቢል ሲከፈል የራሱ የሆነ ጫና ያመጣል፡፡ የውጭ ምንዛሪ ቅድሚያ የሚሰጣቸው ለእነዚህ ዘርፎች ነው ተብሎ ሲወሰድ፣ በማኑፋክቸሪንግ ላይና በሌሎች ዘርፎች ላይ ጫና ሲመጣ የቀረችውን ሀብት በተመለከተ ባገኙት ልክ የሚፈልጉትን ዋጋ ለመጫን ዕድል ሰጥቷል፡፡ ስለዚህ ይህንን ማስተካከል እስካልቻልን ድረስ አስቸጋሪ ነው፡፡ አብዛኛው የአገራችን ብድር ከንብረት መያዝ ጋር የተያያዘ በመሆኑ፣ ንብረት ያላቸው ደግሞ ንብረት አስይዘው የሚበደሩ ስለሆነ ሰው እስከ መጨረሻ ድረስ ንብረቱን ለማትረፍ ይከፍላል፡፡ ተበዳሪው ምርጫ የለውም፡፡ ሥራ ቢያጣና ትርፍ ቢቀንስበት ንብረቱን ለማዳን እየተንገታገተ ነው ያለው፡፡ ይኼ ነገር በዚህ ሊቀጥል ይችላል ወይ? ለሚለው በደንብ ሊመለስበት የሚገባ ነገር ነውና ከእሱ አንፃር ማየት ይገባናል፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ግን ሳየው ባንኮቹ ለራሳቸው የኢኮኖሚ መቀዛቀዙን ተመልክተው ራሳቸውንም ቢሆን ከአደጋ ለመጠበቅ እያደረጉት ያለ ነገር አለ ብሎ ደፍሮ ለመናገር ያዳግተኛል፡፡ አሁን የከፋው ችግር ግለሰቦችም ሆኑ ቢዝነሶች አቅም በፈቀደ መጠን ያላቸውን ጥሪት አሟጠው መክፈል እስከቻሉ ድረስ ይከፍላሉ፡፡ መክፈል ያልቻሉ ዕለት ግን ሁላችንም ንብረት ይዘን ወደ ገበያ ብንወጣ ባዶ እጃችንን እንገባለን እንጂ፣ የተሻለ ነገር ልናገኝበት የምንችልበት ዕድል አለ ለማለት አያስደፍርም፡፡

ሪፖርተር፡- ስለዚህ ምን ዓይነት መፍትሔ አለ? በመንግሥት ደረጃ መደረግ ያለበት ነገር ምንድነው?

አቶ ደረጀ፡- ችግሮቹን በተለያዩ መንገዶች መፍታት የሚቻልበትን ነገር ማየት ይቻላል፡፡ ይህንን ነገር ተቀራርበን እንዴት መሥራት አለብን የሚለው ውሳኝ ጉዳይ ነው፡፡ ፖሊሲ አውጪዎችም፣ ፖሊሲውን ለማስፈጸም በትግበራ ላይ የሚሳተፉ፣ ፖሊሲው በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ተፅዕኖ የሚያሳርፍባቸው እነዚህ ሁሉ አካላት ቁጭ ብለው መነጋገር ያስፈልጋል፡፡ ይኼ በጣም ሊፈታ የማይችል ችግር ሆኖ አይደለም፡፡ ስለዚህ የትኛው ነው የባሰው? የትኛውን ብናስቀድምና ብናስተካክል ነው ለውጥ ሊመጣ የሚችለው? አደጋውን ማስቀረት የምንችለው? የሚለው ላይ ተነጋግሮ መወሰን ያስፈልጋል፡፡ ለምሳሌ የዋጋ ግሽበቱን እንተውና ብድር ከመክፈል አቅም ጋር አነፃፅረን ስንመለከት፣ የሚከፈለው የወለድ ምጣኔ በአንዳንድ የቢዝነስ ዘርፎች ላይ እጅግ ከፍተኛ ነው፡፡ ይኼ ለባንኮች የቁጥር አሃዝ ቢጨምርላቸውም ኮንሲውመሩን የሚፈታተነው ነው፡፡ ነገር ግን ባንኮች የወለድ ምጣኔ እንዲጨምር ካደረገው አንፃር ግሽበቱን ያመጣው ነው ብለን ለመናገር አይደለም፡፡ ግሽበት ነው ያመጣው ልንል አንችልም፡፡ ምክንያቱም በግሽበቱ ላይ መሠረት ያደረገ የተስተካከለ ዋጋ ስለማናወጣ፣ ነገር ግን ከስድስት ሰባት ዓመታት በፊት የ27 በመቶ የቦንድ ግዥ መመርያ ሲወጣ ባንኮቹ ላይ የገንዘብ መመናመን ጫና ነው ያስከተለው፡፡ ምክንያቱም በሚያበድሩት ብድር ላይ ይህንን ሲያደርጉና በተጨማሪም ለአንድ ዓመት የምታበድሩት ይንንን ያህል ሆኖ 40 በመቶ መቀመጥ አለበት ሲባል፣ በአንድ ዓመት የምትበደረው ብድር ዑደት ፈጣን ስለሆነ ከባንኮቹ ብዙ ገንዘብ የመውሰዱ ዕድል በጣም ሰፊ ነው፡፡ ስለዚህ ይኼ ግሽበቱ በተወሰነ ደረጃ ሊያስታግሰው ይችላል ተብሎ ቢታሰብም፣ ነገር ግን ኢኮኖሚው ደግሞ በአብዛኛው በገቢ ንግድ ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ ባንኮቹ ገበያ ውስጥ ሄደው ተቀማጭ ገንዘብ ለመሰብሰብ የሚደርጉ ትንቅንቅ፣ ብድራቸውን ለማሳደግ በሚያደርጉት ጥረት የምትኖራቸው ሀብት  በጣም አነስተኛ ስለሆነች የሚፈልጉትን ሀብት ተበድረው ያስተላልፉታል፡፡ ስለዚህ ተበድረውም ያንን ሲከፍሉ፣ ተበድረው ደግሞ ይህንን ወደ ተጠቃሚ ወይም ወደ ሸማቹ ያሳልፉታል፡፡ ምክንያቱም በመጨረሻ ከፋይ የሚሆነው ተጠቃሚው የኅብረተሰብ ክፍል ነው፡፡ ይኼንን እንዴት ማስተካከል እንችላለን የሚለውን ማየት አለብን፡፡ አሁን መንግሥትም ያለበትን ሁኔታ እንረዳለን፡፡ ቅድሚያ የሚሰጣቸው ዘርፎች ቅድሚያ እያገኙ፣ የሚያገኙት የውጭ ምንዛሪ ምን አስገኘና ያሉበት ደረጃ ምን ይመስላል ብሎ መፈተሽ ያስፈልጋል፡፡ በአጠቃላይ እንዲህ ባለው አሠራር ምን አገኘን? ምንስ አጣን? ተብሎ ቁጭ ብሎ መታየት አለበት፡፡ በአንድ ጊዜ መውጣት ግን በጣም አስቸጋሪ ነው፡፡ ደረጃ በደረጃ መወጣት ግን ይቻላል፡፡ ምክንያቱም ያንን መንገድ እየተከተልን ስንሄድ ገበያው ውስጥ ያለውን እጥረት ማረጋጋት ከቻልን የወለድ ምጣኔ ወደ ኋላ መመለስ የምንችልበት ዕድል አለ፡፡  

ሪፖርተር፡- የውጭ ምንዛሪ እጥረት ችግሩ አሁንም እንዳለ ነው ብሷልም ይባላል፡፡ እንዲህ ካለው ችግር እንዴት ነው ሊወጣ የሚቻለው?

አቶ ደረጀ፡- የውጭ ምንዛሪ ችግር የሁላችንም ነው፡፡ ነገር ግን የምንፈታበት መንገድ ወደ ተሻለ እየወሰደ ነው ወይ የሚለውን ነገር ግን ቆም ብለን ማሰብ አለብን፡፡ የውጭ ምንዛሪ ችግር አፈታቱ ኢኮኖሚውን እየገደለ የሚሄድ ከሆነ ራሳችንን ወደ መብላት ነው የሚወስደን፡፡

ሪፖርተር፡- እንዴት?

አቶ ደረጀ፡- ለምሳሌ ወደ ወደ ነዳጅና ወደ አንዳንድ ነገሮች የሚሄደውን የውጭ ምንዛሪ ለመቀነስ ምን ዓይነት ስትራቴጂ ነድፈናል የሚለው ነው፡፡ የሚፈለገው አጠቃቀማችን ላይ ሳንሠራ ሰላሳ በመቶ የውጭ ምንዛሪ ወስደን፣ ነዳጅና ቅድሚያ የሚሰጣቸው ተብለው የተለዩት ላይ ብቻ የምናውለው ከሆነ አንድ አቅጣጫ ነው የሚሆነው፡፡ ይኼ መፍትሔ አይሆንም፡፡ ምክንያቱም ሌሎች እንደ ማኑፋክቸሪንግ ያሉ ዘርፎችን እያስራብንና ይህንን በማድረጋችን ሥራ በማቆም ሥራ አጥ የምንፈጥር ከሆነ፣ በኢኮኖሚው ላይ ሌላ ቀውስ ነው የምናመጣው፡፡ ስለዚህ በየተወሰነ ጊዜም እንኳን ቢሆን ጣልቃ መግባት ያስፈልግ ነበር፡፡   

ሪፖርተር፡- ምን ዓይነት ጣልቃ ገብነት?

አቶ ደረጀ፡- ለምሳሌ በየወሩ ከሚገኘው የውጭ ምንዛሪ ላይ 30 በመቶ እየተወሰደ ቅድሚያ ለሚሰጣቸው ዘርፎች እየተሰጠ ነው፡፡ ስለዚህ ሦስት ወራት ቅድሚያ ለሚሰጣቸው፣ ሦስት ወራት ደግሞ ለሌላው ዘርፍ እያደረጉ ጣልቃ የመግባት ሥራዎች ማከናወን ይቻል ነበር፡፡ ከዚህ ጎን ለጎን ደግሞ የነዳጅ አጠቃቀማችን እንዴት ነው መቀነስ የምንችለው? እዚህ ላይ መሥራት ያስፈልጋል፡፡ ከተማው በሙሉ በመኪና  ሲተራመስ እናያለን፡፡ መኪኖቹ በፕሮግራም እንዲንቀሳቀሱ ማድረግ አንዱ መፍትሔ ሊሆን ይችላል፡፡ እንዲህ ያሉትንና ሌሎች የተጠኑ ጥናቶች ጎን ለጎን በማስኬድ መሥራት ይኖርብናል እንጂ፣ ነዳጁን ብቻ በማቅረብ በነበረበት ሁኔታ እንሄዳለን ብንል አያዋጣም፡፡ አገሮች እንደዚህ ዓይነት የውጭ ምንዛሪ ችግር ሲገጥማቸውና ሲንገጫገጭ የሄዱበት መንገድ ይታወቃልና፡፡ አንዳንዴም ከእነሱ መማር አለብን፡፡ ድሆች ነን፡፡ ደኅንነታችንን ለማሸነፍ ደግሞ የተለያዩ አማራጮችን ተከትለን መፍትሔ መፍጠር ካለብን፣ ለዚህ ሁሉ ተቀራርቦ መነጋገሩ ያስፈልጋል ብዬ አምናለሁ፡፡   

ሪፖርተር፡- በቅርቡ የፋይናንስ ዘርፉን ሪፎርም ለማድረግ ከተያዘው ፕሮግራም አንፃር የተለያዩ የፋይናንስ ሕግጋቶች ላይ ማሻሻያዎች ተደርገዋል፡፡ እነዚህ ማሻሻዎች የተባለውን ያህል ናቸው? የሚቀራቸው ነገር የለም?

አቶ ደረጀ፡- እነዚህ የማሻሻያዎቹ መጀመርያ ናቸው፡፡ ኢንዱስትሪው ከየት ተነስቶ የት ድረስ መጣ ተብሎ፣ ወይም ብዙ ነገር አልነበረም ተብሎ፣ ሁሉንም ነገር በአንዴ ከፋፍተን የተጠበቁት ማሻሻያዎች በሙሉ ተደርገዋል ማለት አይቻልም፡፡ ስለዚህ መጀመርያ ማሻሻያቹንም ለማድረግ ግልጽ መሆን የሚገባው፡፡ ለዘርፉ ፍኖተ ካርታ ተሠርቶ ለወደፊት ይኼ ነው መንገዱ እንላለን፡፡ አንዱ ችግራችን ይኼ ነው፡፡ ለምሳሌ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በርካታ ባንኮች ወደ ገበያ እየመጡ ነው፡፡ ስለዚህ ኢትዮጵያ ይህንን ያህል ቁጥር ያላቸው ባንኮች ነው የሚያስፈልጓት? ወይስ የሚመጥኑ ጠንካራና ለአገር ኢኮኖሚ ዋልታና መከታ መሆን የሚችሉ ባንኮች ነው መፍጠር ያለብን? የሚለው ላይ አልሠራንም፡፡ ስለዚህ የተወሰነ ገንዘብ ሰብስቦ ወይም አሁን የሚጠቀሱትን የትርፍ ቁጥሮች መሠረት አድርጎ ባንክ ወደ ማቋቋም ብቻ የሚኬድ ከሆነ፣ ተመልሰን ስህተት ውስጥ እንደገባን ማሰብ ጥሩ ነው፡፡

ምክንያቱም በሌላው ዓለም አንዳየነው ከእኛ በጣም ትልቅ ኢኮኖሚ ያላቸውም አገሮች የባንኮቻቸው ቁጥር በጣም በርካታ አይደለም፡፡ ይልቁኑም ያሉት ባንኮች እየጠነከሩ የገንዘብ፣ የሰውና የካፒታል አቅማቸውን እያደሳደጉ በቴክኖሎጂ ታግዘው ተደራሽነታቸውን እያሰፉ በመሥራት፣ በጣም ተወዳዳሪና ጠንካራ የሆኑ ባንኮችን መፍጠር ይቻላል፡፡ እዚህ አፍሪካ ውስጥ እንኳን ደቡብ አፍሪካን ብናይ ጠንካራ ባንኮች ፈጥራ ከራሷ አልፋ ለሌሎች የአፍሪካ አገሮች እያወጣች ነው፡፡ የባንኮቿን አጥር ስናይ ግን በጣም ትንሽ ናቸው፡፡ ስለዚህ አሁን እየተደረጉ ያሉ ማሻሻያዎችን ማየት ያለብን እንደ ጅማሮ ነው፡፡ የሚቀጥሉም አሉ፡፡ የፋይናንስ ሪፎርሙን ተከትሎ ይመጣሉ ብለን የምንጠብቃቸው ማሻሻያዎችም አሉ፡፡ አንደኛ ማዕከላዊ ባንኩም ያለበትን ሁኔታ ግምት ውስጥ ማስገባትም ተገቢ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡፡ በአንድ ጊዜ ሁሉንም ማሻሻያዎች ያደርጋል ማለት በጣም ከባድ ነው፡፡  

ሪፖርተር፡- በአሁኑ ወቅት ያለነው የቢዝነስ መቀዛቀዝና ኢኮኖሚውም በሚፈለገው ደረጃ ያለ መራመድ በባንክ ኢንዱስትሪው ላይ ተፅዕኖ አልፈጠረም ማለት ይቻላል?

አቶ ደረጀ፡- የባንክ ኢንዱስትሪው ፈተናው ገና እየጀመረ ነው ብዬ ነው የማስበው፡፡ ቀደም ብዬ የገለጽኩልህም ነገር ይህ ነው፡፡ ሰዎች መሄድ የሚችሉበት ደረጃ ድረስ ነው የሚሄዱት፡፡ መንገዱ እስከ ወሰዳቸው ድረስ ሄደው እስኪቆሙ ድረስ ይታገላሉ፡፡  አንድ ቦታ ላይ ግን ይቆማሉ፡፡ እያየን ያለነው ይኼንን ነው እንጂ ባንኮች አልተፈተኑም ማለት አይቻልም፡፡ ኢኮኖሚው መቀዛቀዝ ሲጀምር ብድር አከፋፈል ላይ በራሱ ተፅዕኖ ያሳርፋል፡፡ የብድር አከፋፈል ላይ ብቻ ሳይሆን ቢዝነሱ እየቀዘቀዘ ሲሄድ፣ ባንኮቹ ከገበያው ለሚያገኙት የሚያገኙት እየደከመ ነው የሚሄደው፡፡ ስለዚህ እንዲህ ያሉ ችግሮች ተላልፈው ሲመጡ ወደ ባንኮች የሚሻገር ከሆነ፣ ለኢኮኖሚው አደገኛ ነው የሚሆነው፡፡ የባንክን ትርፍ ባለፈው ዓመት ሪፖርት ከተደረገው ቁጥር አንፃር የምናገር ከሆነ ስህተት ነው ብዬ ነው የማስበው፡፡ በደንብ እየተፈተኑ ነው፡፡ ፈተናው ምን ያህል ከባድ ነው የሚለው ላይ እንደ ሁኔታው መመለስ ካልሆነ በቀር፣ የፈተናዎቹ ምልክቶች እየመጡ ናቸው ብዬ አምናለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- የፋይናንስ ሕግጋትን ከማሻሻል አንፃር ውሳኔ ከተላለፉባቸው ዓብይ ጉዳዮች አንዱ፣ የውጭ ዜግነት ያላቸው ኢትየጵያውያን በየትኛውም የፋይናንስ ዘርፍ እንዲገቡ መፍቀዱ ነው፡፡ በእነዚህ የፋይናንስ ተቋማት ውስጥ ኢንቨስት ሲያደርጉ ግን፣ በውጭ ምንዛሪ መሆን እንዳለበት ተደንግጓልና በዚህ ላይ ያለዎት ምልከታ ምንድነው?

አቶ ደረጀ፡- የአዋጁ ዕይታ ይሆናል ብዬ የማስበው የሌላ አገር ዜግነት ያላቸው ኢትዮጵያውያን በውጭ ዜግነታቸው ኢንቨስትመንታቸው፣ ገበያቸው፣ ወይም ክፍያቸው በውጭ ምንዛሪ ስለሆነ በውጭ ምንዛሪ አክሲዮን ይግዙ የሚል ነው ዕሳቤው፡፡ ይህንን በማድረጋቸው በኢኮኖሚ ላይ ትልቅ የውጭ ምንዛሪ ግኝት ይኖራል ተብዬ ብጠየቅ፣ እኔ በጣም እጠራጠራለሁ፡፡ አንደኛ ብሩ ራሱ ያለው የመግዛት አቅም ሲታይ፣ በጣም ጥቂት በሆነች የውጭ ምንዛሪ በርከት ያለ አክሲዮን ሊገዛ የሚቻልበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ ስለዚህ በዚህ ደረጃ የውጭ ምንዛሪ ችግራችንን እናቃልላለን ተብሎ አይታሰብም፡፡ ግን ኢትዮጵያውያን ነበሩና በዚህ ዘርፍ በአገራቸው በዚያ መንገድ ኢንቨስት ያድርጉ መባሉ አግባብ ያለው ነው፡፡ ምክንያቱም እዚህ ያለ ገንዘብ ዞሮ በእነሱ ስም ከሚደረግ በተወሰነ መልኩ ይህን ለመለየት መደረጉ ብዙም ችግር አለው ብዬ አላስብም፡፡ አንዳንድ ሰዎች በዕውቀታቸው ሊያግዙ ይችላሉ ሲሉ እሰማለሁ፡፡ በዚህ ደረጃ ምን ያህል ኢትዮጵያውያን የፋይናንስ ዘርፉን መለወጥ ይችላሉ የሚለው መረጃ የለኝም፡፡ ነገር ግን አንድም ሰው ቢሆን የተሻለ ውቀት ካለው ለመለወጥ ያግዛል ብዬ አምናለሁ፡፡ ከዚህ አንፃር ምን ያህል የሰው ኃይልና ካፒታል ያደርጋል ለሚለው ወደፊት የምናየው ነው፡፡ ካፒታልን በተመለከተ ግን እጅግ በጣም ሰፊ ነገር ይመጣል ብዬ አላምንም፡፡ ነገር ግን ለእነሱ በመፈቀዱ ወገኖቻችን በመሆናቸው እንደ ኢትዮጵያዊ በጣም ደስ ይለኛል፡፡ እጅግ የተለየ ለውጥ በፋይናንስ ዘርፍ ያመጣሉ ብዬ ግን አላምንም፡፡

ሪፖርተር፡- የውጭ ባንኮች ከመግባታቸው አንፃርስ ምን አንድምታ ይኖረዋል ብለው ያስባሉ?

አቶ ደረጀ፡- የውጭ ባንኮች ከግለሰብ ኢንቨስተሮች የተለዩ ናቸው፡፡ እነሱን የምናይበት አንዱ መንገድ በምን ዓይነት ሁኔታ ይገባሉ የሚለው ነው፡፡ የውጭ ባንኮች ቢገቡ ይዘው የሚመጡት ነገር ይኖራል፡፡ የተሻለ ቴክኖሎጂ፣ የተሻለ የሰው ኃይል፣ የተሻለ ካፒታል ይዘው ይመጣሉ፡፡ በዘርፉ ውስጥ ከፍተኛ ውድድር እንዲኖር ያደርጋሉ፡፡ ደንበኞች የተለያዩ አገልግሎቶችን እንዲያገኙ አማራጭ ይፈጠራል፡፡ ይህ ትልቅ ዕገዛ ነው፡፡ ሁሉም ነገር ደግሞ ውድድር የሚያመጣ ከሆነ ተጠቃሚው የተሻለ አገልግሎት የሚያገኝበት ዕድል ሰፊ ይሆናል፡፡  

ሪፖርተር፡- ግን እንዲህ ዓይነት ዕድሎች ይዘው የሚመጡ ከሆነ የኢትዮጵያ ባንኮች ዕጣ ፈንታ ምን ሊሆን ይችላል? የተወዳዳሪነት አቅማቸው አይፈተንም?

አቶ ደረጀ፡- የኢትዮጵያ ባንኮች ከእነሱ ጋር መወዳደር ይችላሉ ብሎ ደፍሮ የሚናገር ሰው ካለ ለራሱ እተዋለሁ፡፡ የእኔ እምነት ግን አይችሉም የሚል ነው፡፡ ይህንኑ ሐሳቤን ቀድሜ የገለጽኩልህ ይመስለኛል፡፡ እውነቱ ይኼ ከሆነ ምን መደረግ አለበት ለሚለው መልስ መስጠት ያስፈልጋል፡፡ መቼም ሁሉም ነገር ሽግግር ስለሆነ በተወሰነ ደረጃ አክሲዮኖችን እየገዙ ቢመጡ በማኔጅመንቱም ላይ ተሳትፎ ስለሚኖራቸው በዕውቀት፣ ይዘውት በሚመጡት ካፒታልና በተለያዩ አገሮች የሚተገበሩ የተለያዩ አሠራሮችን በቀላሉ የማሸጋገር ሁኔታዎች ሊፈጠሩ ይችላሉ፡፡ በዚህ የኢትዮጵያ የባንክ ዘርፍ እንዲሻሻል ይረዳዋል ብዬ አምናለሁ፡፡ አለበለዚያ ሁሌ በተዘጋንበት ተቀምጥን ራሳችንን ትልቅ ነን ብለን የምናስቀምጥ ከሆነ አስቸጋሪ ነው፡፡ ስለዚህ የውጭ ባንኮች በተወሰነ ደረጃ በኢትዮጵያ የባንክ ኢንዱስትሪ ውስጥ ቢሳተፉ ለተቋማቱ የተሻለ ዕድል ይፈጥርላቸዋል፡፡ ራሳቸውን እንዲመለከቱ ይረዳል፣ እንድንማርም ያግዘናል፡፡ ወጣ ብለን ስንመለከት እኮ የእኛና የሌሎች አገሮች የፋይናንስ ዘርፍ አደረጃጀት ምን ያህል ልዩነት እንዳለው እንገነዘባለን፡፡ የውጭ ባንኮች ደረጃ በደረጃ መግባታቸው ጠቃሚ ነው፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ከውጭ ይገቡ የነበሩ 38 ዓይነት ምርቶች እንዳይገቡ ዕግድ ተጣለ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ 38 ከውጪ የሚገቡ ምርቶች ላይ ዕገዳ...

በወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የተሰበሰበው ከፍተኛ ሀብት ጥቅም ላይ እየዋለ አይደለም ተባለ

በኢትዮጵያ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የተሰበሰበው የተቀማጭ ገንዘብ መጠን...

በደቡብ አፍሪካ የተጀመረውን የሰላም ንግግር አሜሪካንን ጨምሮ ተመድና ኢጋድ እየታዘቡ ነው

ለሰሜን ኢትዮጵያ ግጭት ሰላማዊ መፍትሔ ለማምጣት በአፍሪካ ኅብረት አማካይነት...

ኢትዮጵያ በ2023 የሚኖራት የውጭ ምንዛሪ ክምችት ለ18 ቀናት ግዢ መፈጸሚያ ብቻ እንደሚሆን አይኤምኤፍ ተነበየ

ኢትዮጵያ በ2023 የሚኖራት የውጭ ምንዛሪ ክምችት ለ0.6 ወር ወይም...