Tuesday, July 23, 2024

ከ144 ቀናት በኋላ የተጠናቀቀው የሰኔ 15 ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ግድያ ምርመራ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ቅዳሜ ሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ.ም. በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ዋና ከተማ ባህር ዳር ውስጥ ያልታሰበና ያልተገመተ፣ በተለይ ለክልሉ ሕዝብ እጅግ ከባድና አስደንጋጭ አደጋ መድረሱ ይታወሳል፡፡ አደጋው የክልሉን ሕዝብ ያስደነገጠና ግራ ያጋባ ነበር፡፡ አደጋው በክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ላይ የተፈጸመ የግድያ ወንጀል መሆኑ ይታወሳል፡፡ ክልሉን በፕሬዚዳንትነት እንዲመሩ ከተሾሙ አራት ወራት ያልሞላቸው የምጣኔ ሀብት ምሁሩ አምባቸው መኮንን (ዶ/ር)፣ የእሳቸው ልዩ አማካሪ አቶ ዕዘዝ ዋሴና የክልሉ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ አቶ ምግባሩ ከበደ በጥይት ተደብድበው መሞታቸውም በወቅቱ መገለጹ አይዘነጋም፡፡ በተቀራራቢ ሰዓት ምሽት ላይ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታ ማዦር ሹም ጄኔራል ሰዓረና ጓደኛቸው መሆናቸው የተነገረው ጡረተኛው ሜጀር ጄኔራል ገዛዒ አበራ በአዲስ አበባ በጄኔራል ሰዓረ መኖሪያ ቤት ውስጥ በግል ጠባቂያቸው መገደላቸው፣ በወቅቱ ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍል በከፍተኛ ሁኔታ አስደንግጦ ነበር፡፡

የከፍተኛ ባለሥልጣናቱ ድንገተኛ ሞት ግራ ያጋባው ሕዝብ ግራ ገብቶት በመንቆራጠጥ ላይ እያለ፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽሕፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊ አቶ ንጉሡ ጥላሁን፣ ‹‹በባህር ዳር ከተማ የተደረገው ወይም የተፈጸመው ድርጊት መፈንቅለ መንግሥት ነው፤›› አሉ፡፡ ምንም እንኳን በተለይ የሰው ሕይወት ያውም ከፍተኛ ሕዝብ የሚኖርበትን ክልል የሚመራ አካል በድንገተኛ ሁኔታ መገደሉ እየታወቀ፣ ሳይጣራና አመላካች ፍንጮች ከሕግ ድንጋጌ ጋር ተመዝነው ምን ዓይነት ወንጀል እንደሆነ ለማወቅ በማይቻልበት ቅፅበት ‹‹የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ነው፤›› መባሉ ግራ ቢያጋባም፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በሙሉ ወታደራዊ ዩኒፎርም በቴሌቪዥን በሰጡት መግለጫ፣ በባህር ዳር የተፈጸመው ድርጊት መፈንቅለ መንግሥት መሆኑን ማረጋገጣቸው ይታወሳል፡፡

በመቀጠልም በባህር ዳር ከተማ የክልሉ የፀጥታ ቢሮ ምክትል ኃላፊ የነበሩትን ብርጋዴር ጄኔራል ተፈራ ማሞን ጨምሮ ከ277 በላይ ተጠርጣሪዎች መታሰራቸው ተነገረ፡፡ በአዲስ አበባ ከተማም የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የሕዝብ ግንኙነትና የምክር ቤት አባል አቶ ክርስቲያን ታደለን ጨምሮ 140 ተጠርጣሪዎች ታሰሩ፡፡ በባህር ዳርና በአዲስ አበባ ከተሞች ከከፍተኛ የመንግሥትና ወታደራዊ ባለሥልጣናት ግድያ ጋር ተያይዞ የታሰሩ ከ300 የሚበልጡ ተጠርጣሪዎች ድርጊቱ ከተፈጸመበት ሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ አራት ወራት በሚደርስ እስራት ከቆዩ በኋላ፣ አብዛኛዎቹ ከመታወቂያ ዋስ እስከ አሥር ሺሕ ብር በሚደርስ ዋስትና ከእስር እንዲፈቱ ተደረገ፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ በባህር ዳርና በአዲስ አበባ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት የግድያ ተጠርጣሪዎች ላይ ሲደረግ የነበረው ምርመራ መጠናቀቁንና ክስ ለመመሥረት አስፈላጊው መረጃ መገኘቱን የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ፣ የአማራ ክልል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ (በአቶ ምግባሩ ከበደ የተተኩት) እና የፌዴራል ፖሊስ በጋራ በመሆን ኅዳር 3 ቀን 2012 ዓ.ም. መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

የወንጀል ድርጊቱ ከተፈጸመ ከ144 ቀናት ቆይታ በኋላ የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ አቶ ብርሃኑ ፀጋዬ፣ የፌዴራል ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነር ጄኔራል ተኮላ አይፎክሩና የአማራ ክልል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ አቶ ገረመው ገብረ ጻድቅ ኅዳር 3 ቀን 2012 ዓ.ም. በጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ዋና መሥሪያ ቤት መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

አጠቃላይ የወንጀል ሒደቱንና ላለፉት አምስት ወራት የተደረጉትን የምርመራ ዓይነቶችና የተገኘውን ውጤት በሚመለከት ሰፊ ማብራሪያ የሰጡት፣ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ብርሃኑ ፀጋዬ ናቸው፡፡ አቶ ብርሃኑ እንዳስረዱት፣ ሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ.ም. በአማራ ክልል ከፍተኛ ባለሥልጣናትና በአዲስ አበባ ከተማ በጠቅላይ ኤታ ማዦር ሹም ላይ የተፈጸመው የግድያ ወንጀል ምርመራ ተጠናቋል፡፡ ስለወንጀሉ ዓላማ ሲያብራራ፣ ድርጊቱ መንግሥትን በኃይል ለማስወገድና ሥልጣንን በኃይል ለመቆጣጠር ታቅዶ የተፈጸመ መፈንቅለ መንግሥት ነው ብለዋል፡፡ በአማራ ክልል የመንግሥትና የፓርቲ አመራሮች ላይ ዕርምጃ በመውሰድ፣ ክልሉን ለመቆጣጠር የተለያዩ ዝግጅቶች መደረጋቸውን፣ ወንጀሎቹ የሚፈጸሙባቸውን ቦታዎች አስቀድሞ በመለየት፣ ጥቃቱን  መፈጸም የሚችል የሰው ኃይል በማዘጋጀትና አመራር በመስጠት፣ በዕቅድ የተፈጸመ ወንጀል መሆኑን አብራርተዋል፡፡

ዋና ዓቃቤ ሕግ ብርሃኑ የወንጀል ድርጊቱን አፈጻጸም እንዳስረዱት፣ በባህር ዳር ከተማ በርዕሰ መስተዳድሩ ቢሮ ላይ፣ በክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን እንደ ሥጋት የሚታዩትን የፖሊስ አመራሮች መኖሪያ ቤትና በሌሎች ላይ ጥቃት ተፈጽሟል፡፡ የአዴፓ ጽሕፈት ቤት፣ የክልሉ የእንግዳ ማረፊያ፣ እንዲሁም በአዲስ አበባ የመከላከያ የበላይ ኃላፊዎች ላይ ተልዕኮ በመስጠት የተፈጸመ ወንጀል መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የክልሉን ርዕሰ መስተዳደር የወንጀሉ ዋና አቀነባባሪ ብርጋዴር ጄኔራል አሳምነው ጽጌና ከእሳቸው ጋር የነበሩት ሻምበል መማር ጌትነት፣ ሻምበል ታደሰ እሸቴና ሻለቃ አዱኛ ወርቁ በዋናነት የወንጀሉን ተግባር ለመፈጸምና ለማስፈጸም የተመለመሉ መሆናቸውን አቶ ብርሃኑ ገልጸዋል፡፡ አምባቸው መኮንን (ዶ/ር)ን በሚመለከት ከላይ የተጠቀሱት አካላት የክልሉን ልዩ ኃይል በብርጋዴር ጄኔራል አሳምነው መሪነት በርዕሰ መስተዳድሩ ቢሮ ሦስተኛ ፎቅ ላይ በመሄድ ወደ መሰብሰቢያ አዳራሽ ለመግባት ሲሞክሩ፣ የርዕሰ መስተዳድሩ አጃቢዎች እንዳይገቡ እንደከለከሏቸው፣ በዚህ ጊዜ አጃቢዎችን በመግደል ወደ ስብሰባ አዳራሽ መግባታቸውን ጠቁመዋል፡፡ በተመሳሳይ የርዕሰ መስተዳድሩ ልዩ ረዳት የአቶ ዕዘዝ ዋሴን አጃቢ ትጥቅ በማስፈታትና በማሰር ወደ አዳራሹ ገብተው፣ አምባቸው መኮንንን (ዶ/ር) የተለያየ የሰውነት ክፍላቸውን በጥይት በመደብደብና ደረጃ ላይ ጎትተው በመጣል፣ ሕይወታቸው እንዲያልፍ መደረጉን አቶ ብርሃኑ ተናግረዋል፡፡ አቶ ዕዘዝም በተመሳሳይ ጥቃት ተፈጽሞባቸው ሕይወታቸው እንዲያልፍ መደረጉንና የክልሉ ዋና ዓቃቤ ሕግ የነበሩት አቶ ምግባሩ ከበደም የተመቱ ቢሆንም፣ ለጊዜው ሕይወታቸው ባለማለፉ ወደ ሕክምና ተወስደው ዕርዳታ እየተደረገላቸው (አዲስ አበባ በሪፈራል መምጣታቸው ይታወሳል)፣ ሕይወታቸው ማለፉንም አክለዋል፡፡

እነዚህ የተጠቀሱት ድርጊቶች በሰነድ፣ በቴክኒክ ምርመራና በሰዎች ማስረጃ የተረጋገጡ መሆናቸውንም አቶ ብርሃኑ ጠቁመዋል፡፡ ወንጀሉ የተፈጸመበትን ቦታ በሚመለከት የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽንና የፖሊስ አመራሮችን በሚመለከት አቶ የማነ ታደሰ፣ ሃምሳ አለቃ አበበ መልኬ፣ ሃምሳ አለቃ ስለሺ ከበደ፣ ሃምሳ አለቃ ስለሺ ጌታቸውና ሌሎች 17 የልዩ ኃይል አባላትን በመያዝ ጥቃቱን ማድረሳቸውንም አቶ ብርሃኑ ገልጸዋል፡፡ በክልሉ ፖሊስ አመራር መኖሪያ ቤት ላይም ጥቃት በመፈጸም፣ በሰውና በንብረት ላይ ጉዳት ማድረሳቸውን አስረድተዋል፡፡ የአዴፓ ጽሕፈት ቤትን ሃምሳ አለቃ አየነው ታደሰ የተባሉ 17 የልዩ ፖሊስ አባላትን በመያዝ በፈጸሙት ጥቃት በሰውና በንብረት ላይ ጉዳት ማድረሳቸውን፣ የክልሉን እንግዳ ማረፊያ ደግሞ ሻምበል ውለታው አባተ 25 የልዩ ፖሊስ አባላትን በመያዝ ባደረሱት ጥቃት፣ በሰውና በንብረት ላይ ጉዳት ማድረሳቸውን አቶ ብርሃኑ ተናግረዋል፡፡ ሁሉም ከብርጋዴር ጄኔራል አሳምነው የተሰጣቸውን ተልዕኮ በመፈጸም፣ 15 ሰዎች መገደላቸውንና 20 ሰዎች የአካል ጉዳት እንደደረሰበቸው፣ እንዲሁም ከፍተኛ በሆነ ሀብት ላይ ጉዳት ማድረሳቸውንም አክለዋል፡፡

የወንጀል ድርጊቱን ለመፈጸም የተለያዩ የጦር መሣሪያዎችን፣ ሰነዶችን፣ የኤሌክትሮኒክስ መሣሪያዎችን፣ ተንቀሳቃሽ ስልኮችንና የሰው ምስክሮችን ለምርመራ መጠቀማቸውን የተናገሩት ዋና ዓቃቤ ሕጉ፣ 114 ክላሽኒኮቭ ጠብመንጃዎች፣ ሦስት ብሬልና አራት ማካሮብ ሽጉጦች ለፎሬንሲክ ምርመራ ቀርበው፣ 11 ክላሽኒኮቭ ጠብመንጃዎች፣ አንድ ብሬልና አንድ ማክሮቭ ሽጉጥ ለወንጀል ተግባር ከተተኮሱ ጥይቶች ጋር ተመሳሳይ መሆናቸውን ማረጋገጥ እንደተቻለ ገልጸዋል፡፡ በተጠርጣሪዎች ቢሮና መኖሪያ ቤት በተደረገ ብርበራ የተለያዩ የሰነድ ማስረጃዎች፣ ተንቀሳቃሽ ስልኮች፣ ኤሌክትሮኒክስ መሣሪያዎች፣ የተለያዩ የውጭ አገሮች ገንዘቦች በኤግዚቢትነት መያዛቸውን አክለዋል፡፡ ተጠርጣሪዎቹ በወቅቱ ያደረጉት የእርስ በርስ የስልክ ግንኙነትም በማስረጃነት መያዙንም ጠቁመዋል፡፡ ተጠርጣሪዎቹን በተሳተፉበት የወንጀል ዓይነት መለየት መቻሉን ተናግረው፣ ሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ.ም. አምባቸው መኮንን (ዶ/ር)ን በመጠበቅ ላይ የነበሩ አራት አባላትና የክልሉ አመራሮች የቅርብ አጃቢ የነበሩ ስምንት አባላት በቁጥጥር ሥር በማዋል ምርመራ መከናወኑንም ገልጸዋል፡፡  

ሌሎች 70 ተጠርጣሪዎች ላይ የመያዣ ትዕዛዝ በማውጣት የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን 31 ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ሥር መዋሉን፣ 39 ተጠርጣሪዎች ግን እስካሁን አለመያዛቸውን አቶ ብርሃኑ አብራርተዋል፡፡ አቶ ብርሃኑ በዝርዝር እንደገለጹት፣ 22 ተጠርጣሪዎች የባንክ ሒሳባቸው ታግዶ እየተጣራ ነው፡፡ ከ147 ሰዎች ላይ የቃል ማስረጃ በባህር ዳር መቀበል ተችሏል፡፡ የሰነድና የቴክኒክ ምርመራ፣ እንዲሁም ወንጀሉ መፈጸሙን የሚያስረዳ ማስረጃ ተሰብስቦ መጠናቀቁን ተናግረዋል፡፡

ወንጀሉን ለመፈጸም ስለተደረገው ዝግጀት ያብራሩት ዋና ዓቃቤ ሕጉ፣ ዝግጅቱ የተጀመረው በሚያዝያ ወር 2011 ዓ.ም. ነው፡፡ ብርጋዴር ጄኔራል አሳምነው ጽጌና አንዳንድ የክልሉ ‹‹አክቲቪስት ነን ባዮች›› ራሳቸውን ለኅብረተሰቡ ብቸኛ ተቆርቋሪ በማድረግ፣ ‹‹እኔና የተወሰኑ ሰዎች በምናደርገው እንቅስቃሴ ብቻ ነው ለውጥ የሚመጣው፤›› በማለትና ኅብረተሰቡን የተሳሳተ ግንዛቤ በማስጨበጥ፣ እንዲሁም በአገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች እየተስተዋሉ ያሉ የጽንፈኝነትና የአክራሪነት ድርጊቶችን በመጠቀም፣ አንዱ አመራር እንዲጠላና ሌላው አመራር ተወዳጅ እንዲሆን በማድረግ፣ ኢመደበኛ አደረጃጀቶችን በመጠቀምና የተወሰኑ የፖለቲካ ድርጅቶች አደረጃጀቶችን በመከተል እነሱ የተበደሉና ጉዳት የደረሰባቸው በማስመሰል፣ ሕዝቡን ሥጋት ውስጥ ሲከቱ መክረማቸውን አብራርተዋል፡፡

የክልሉን ገዥ ፓርቲ (አዴፓ) አሠራር፣ ዓላማና አመራሮችን በማንቋሸሽ፣ የተገኘውን ለውጥ የራሳቸው አድርገው በመውሰድ፣ በፌዴራልና በክልል መንግሥት መካከል ያለውን ግንኙነት በመጥፎ መልክ በመሳልና በማስቀመጥ፣ የክልሉ መንግሥት ሥልጣንና ተግባራት በሕገ መንግሥቱ ተለይቶ መሰጠታቸው እያወቁ፣ ያንን በመጣስ የተለያዩ ሕገወጥ ተግባራት መፈጸማቸውን አስረድተዋል፡፡ የስለላ ተቋማትን የማደራጀት፣ የመምራትና የማሠልጠን ተግባራት የፌዴራል መንግሥቱ ሥልጣን ብቻ መሆኑን ሕገ መንግሥቱ ቢደነግግም፣ ከተለያዩ አካባቢዎች ሠልጣኞችን በመመልመልና ሥልጠና በመስጠት ለሰባት ሳምንታት 110 ለሚሆኑ ሰዎች ሥልጠና መስጠታቸውን አቶ ብርሃኑ ገልጸዋል፡፡ የሥልጠናው ይዘት፣ የክትትል አስፈላጊነት፣ ዓይነትና ዘዴዎች፣ የመረጃ ትንተናና አሰባሰብ ሥልጠና፣ የሥውር ጦርነት አስፈላጊነትና መከሰቻ መንገዶችን፣ የማውደም ሥልጠናዎችን፣ የሥነ ልቦናና የኢኮኖሚ ጦርነትን የሚመለከቱ ሥልጠናዎችን መስጠታቸውንም፣ ከተገኙት የሰነድና የተለያዩ ምርመራዎች ለማወቅ መቻላቸውን ገልጸዋል፡፡

መፈንቅለ መንግሥቱን ለማሳካት አደገኛ የሆነ አደረጃጀትና ሥልጠና ማድረጋቸውንም አክለዋል፡፡ ፖለቲካዊ፣ ወታደራዊ፣ ባህላዊና የከተማ አደረጃጀት የመሳሰሉት ሥልጠናዎች መሰጠታቸውንና ዝግጅት ማድረጋቸውንም ተናግረዋል፡፡ ሥልጠናውን ከወሰዱ በኋላ በአዲስ አበባ፣ በአሶሳ፣ በሐዋሳ፣ በአፋርና በተለያዩ የአማራ ክልል አካባቢዎች መሰማራታቸውንም አቶ ብርሃኑ ተናግረዋል፡፡ ሌላው በእነ ብርጋዴር ጄኔራል አሳምነው የተመለመሉት ከተለያዩ ተቋማት በተለያየ የሥነ ምግባር ችግር ከሥራቸው የተባረሩና በራሳቸውም ፈቃድ ሥራቸውን የለቀቁ የመከላከያ ሠራዊት አባላት ሲሆኑ፣ በተለይ ቀደም ብሎ በነበረው የመፈንቅለ መንግሥት ተሳትፎ በወንጀል ሳይከሰሱ በሥነ ምግባር ጉድለት የተባረሩትን የልዩ ኃይል አባል በማድረግና ተጨማሪ ሥልጠና በመስጠት፣ ለወንጀል ድርጊቱ ተሳታፊ እንዲሆኑ መደረጉን ዋና ዓቃቤ ሕጉ አስረድተዋል፡፡ ከአጎራባች ክልሎች ጋር በተለያዩ ጊዜያት የተፈጠሩ ግጭቶችን በመምራትና በማስተባበር፣ ሕዝቡን እርስ በርሱ በማጋጨትና ለዋናው ዓላማቸው ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር ሲሠሩ እንደነበርም አክለዋል፡፡

መፈንቅለ መንግሥቱ ከተሳካ በኋላ ተቃውሞ ሊነሳባቸው ይችላል ብለው በሰጉባቸው የተለያዩ ቦታዎች ላይ የታጠቁ አባላቶቻቸውን በማስታጠቅና በማስቀመጥ፣ ዕርምጃ የሚወሰዱባቸውን የዞንና የወረዳ አመራሮችን በመለየት ተዘጋጅተው እንደነበርም በምርመራ መረጋገጡን አስረድተዋል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ በጠቅላይ ኤታ ማዦር ሹሙ ጄኔራል ሰዓረ መኮንንና ሜጀር ጄኔራል ገዛዒ አበራ ላይ የተፈጸመውን ግድያን በሚመለከትም በዋናነት በብርጋዴር ጄኔራል አሳምነው ጸጌ መሪነት የተፈጸመ መሆኑን ጠቁመው፣ ኃላፊዎቹ ሲመቱ ሠራዊቱ በብሔር ተከፋፍሎ ሊበተንና ሊዳከም እንደሚችል፣ በዚህ ምክንያትም ከፍተኛ ግጭት ሊፈጠር የሚችል መሆኑን በማቀድ መንቀሳቀሳቸውን አቶ ብርሃኑ ገልጸዋል፡፡ ወታደራዊ ኃይሉ ከተዳከመና ከተበተነ አገሪቱንና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ሊያስጠብቅ የሚችል ኃይል ሊኖር ስለማይችል፣ የፌዴራል መንግሥትን መቆጣጠር ቀላል ነው የሚል ቀቢፀ ተስፋ በመያዝ የወንጀል ድርጊቱ መፈጸሙንም አክለዋል፡፡

ጄኔራል ሰዓረንና ሜጀር ጄኔራል ገዛኢን ለመግደል የተደረገውን ዝግጅት በሚመለከት ዋና ዓቃቤ ሕጉ እንደገለጹት፣ አንድ የመከላከያ ሠራዊት አባል የሆነ አሥር አለቃ በመመልመል ከብርጋዴር ጄኔራል አሳምነው ጋር ጎንደር ተገናኝተዋል፡፡ ሥልጣን ከተቆጣጠሩ በኋላ ሥልጣንና ገንዘብ እንደሚሰጠው ቃል ተገብቶለት ለጊዜው የተወሰነ ገንበዘብ ተሰጥቶታል ብለዋል፡፡ ተጨማሪ ተልዕኮዎችን ለማስፈጸም አሥር አለቃው ወደ መከላከያ ተመልሶ ሌላ አባል መመልመሉንም አስረድተዋል፡፡ ከመከላከያ የተመለመሉት አባላት የተሰጣቸው ዋና ተልዕኮ፣ ጠቅላይ ኤታ ማዦር ሹምና ሌሎች ከፍተኛ ኃላፊዎች ላይ ዕርምጃ እንዲወሰድ መሆኑንም አክለዋል፡፡ በቅድሚያ ጄኔራል ሰዓረ መኮንንና ጄኔራል ብርሃኑ ጁላ ላይ ዕርምጃ ለመውሰድ የመጀመርያው ተልዕኮ እንደተሰጣቸው የገለጹት አቶ ብርሃኑ፣ ጄኔራል ሰዓረ ላይ ዕርምጃ እንዲወሰድ ተልዕኮ የተሰጠው የግል ጠባቂያቸው መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ የግል ጠባቂያቸውን የመለመለው በጎንደር ተገኝቶ ተልዕኮ የወሰደው አሥር አለቃ በባህር ዳር የሚፈጸመው ተልዕኮ እንደተሳካ ስልክ ደውሎ ሲያሳውቀው፣ ተጠርጣሪው አሥር አለቃ መሳፍንት ጥጋቡ በሁለቱ ከፍተኛ መኮንኖች ላይ ግድያ መፈጸሙን አስረድተዋል፡፡

ጥቃቱ ከተፈጸመ በኋላ ጄኔራል ብርሃኑ ጁላ በሥፍራው መገኘታቸው ስለማይቀር በእሳቸወም ላይ ጥቃት እንዲፈጸም ተልዕኮ ተሰጥቶ እንደነበር በምርመራ መታወቁን አቶ ብርሃኑ ገልጸዋል፡፡ በአጋጣሚ በሥፍራው ባለመገኘታቸው ተልዕኮው ሳይሳካ መቅረቱንም ተናግረዋል፡፡ የታሰበው የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ በመከላከያ ሠራዊት መኮንኖች ላይ ግድያ የሚፈጽሙና የመረጃ ሥራ መሥራት የሚችሉ አካላትን በመመልመል በክልሉ ልዩ ኃይል ውስጥ ከሠለጠኑ በኋላ፣ በሦስት ሻምበል በማደራጀት ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን በኃይል ለማፍረስ ወታደሮችንና ሽፍቶችን በማስታጠቅ ድርጊቱን መፈጸማቸውን ምርመራዎች እንደሚያሳዩ አስረድተዋል፡፡ ድርጊቱን ለመፈጸም እንዲችሉ ከባለሀብቶችና ከተለያዩ አካላት የገንዘብ መዋጮ በመሰብሰብ፣ የቡድንና የነፍስ ወከፍ መሣሪያዎችን በማስታጠቅ፣ ዕርምጃ ለመውሰድ ቦታዎችንና ሰዎችን በመለየትና ሥምሪት በመስጠት የተሠራ የወንጀል ድርጊት መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

ወንጀሉ በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ባሉ ኃላፊዎች ላይ የተፈጸመ፣ ሁሉን ዓይነት ጥንቃቄ በማድረግ የመንግሥት መደበኛ ሥራዎችን ለመሥራት በማስመሰል ከፍተኛ ዝግጅት ሲደረግ እንደነበርም አቶ ብርሃኑ ተናግረዋል፡፡ የወንጀል ድርጊቱ ውስብስብና በመንግሥት ተቋማትና ኃላፊዎች ላይ የተወሰደ መሆኑን በመጠቆም፣ ምርመራው ረዥም ጊዜ የወሰደበትን ምክንያትም አስረድተዋል፡፡ በሁለቱም ቦታዎች የተጀመረውን ምርመራ በማጠናቀቅ፣ በወንጀሉ የተሳተፉ ተጠርጣሪዎችን እንደ ተሳትፏቸው በመለየት፣ የወንጀል ክስ መዘጋጀቱንም ይፋ አድርገዋል፡፡ በአጠቃላይ በወንጀል ሒደቱ ውስጥ በባህር ዳር 277 ተጠርጣሪዎችን፣ በአዲስ አበባ 140 ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ሥር በማዋል ምርመራ መካሄዱንም ገልጸዋል፡፡

በባህር ዳር ከታሰሩት ውስጥ 45 ተጠርጣሪዎች የወንጀል ተሳትፏቸው አነስተኛ በመሆኑ ወደ ምስክርነት በማዞር፣ በሌሎቹ ላይ ለጊዜው የተገኘው ማስረጃ ሊያሳስራቸው በቂ ባለመሆኑና በቀጣይ ይጣራል ተብሎ በዋስትና መፈታታቸውን ተናግረዋል፡፡ በ47 ተጠርጣሪዎች ላይ ቀዳሚ ምርመራ ፍርድ ቤት ተወስዶ በአጠቃላይ በ55 ተጠርጣሪዎች ላይ ባህር ዳር ክስ ለመመሥረት ዝግጅት መጠናቀቁን አቶ ብርሃኑ አስታውቀዋል፡፡ በአዲስ አበባ አጠቃላይ በተፈጠረው ግድያ የተጠረጠሩ 140 ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር ቢውሉም፣ አምስት ተጠርጣሪዎች ምንም እንኳን ከጉዳዩ ጋር ተያያዥነት ቢኖረውም፣ ከሌሎች በመለየት በጦር መሣሪያ ዝውውር እንዲታይና ክስ ተመሥርቶ በሒደት ላይ መሆኑን በመወሰን ክስ ተመሥርቶ በሒደት ላይ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ 61 ተጠርጣሪዎች በዋስ እንዲወጡ መደረጉንና 13 ተጠርጣሪዎች ግን የተጠረጠሩበት የወንጀል ድርጊት፣ በዓቃቤ ሕግ ማስረጃ ምዘና ሒደት ሊያስከስሳቸው እንደሚችል በመታመኑ፣ ክስ እንደተዘጋጀባቸው አስረድተዋል፡፡

በአጠቃላይ በአዲስ አበባ የግድያ ወንጀል በተጠረጠሩ 13 ግለሰቦች፣ በባህር ዳር ከተማ በተፈጸመው የግድያ ወንጀል ደግሞ  55 ተጠርጣሪዎች ላይ ክስ ለመመሥረት ዝግጅት መጠናቀቁን ዋና ዓቃቤ ሕግ አቶ ብርሃኑ አብራርተዋል፡፡ በባህር ዳር ከተማ ኃላፊነታቸውን ባልተወጡ 15 ተጠርጣሪዎች ላይም ለብቻው መዝገብ ተከፍቶ ገና ምርመራ እየተደረገ መሆኑንም አክለዋል፡፡ በወንጀል ምርመራው የፌዴራል ፖሊስ መርማሪዎች፣ የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕጎች፣ የአማራ ክልል የፖሊስ መርማሪዎች፣ የክልሉ ዓቃቤ ሕግ፣ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት፣ የኢንፎርሜሽንና መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ፣ የመከላከያ ሠራዊት ባለሙያዎችና የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን መሳተፋቸውንም ገልጸዋል፡፡

ጠቅላይ ዓቃቤ ሕጉ የሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ.ም. በባህር ዳርና በአዲስ አበባ ከተማ የተፈጸመውን ግድያ በሚመለከት ምርመራው መጠናቀቁንና በሁለቱ አካባቢዎች በአጠቃላይ 68 ተጠርጣሪዎች ላይ ክስ መዘጋጀቱን ከገለጹ በኋላ፣ በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ የተገኙ በርካታ ጋዜጠኞች ተጨማሪ ማብራሪያ የሚፈልጉ ጥያቄዎችን ለመጠየቅ የፈለጉ ቢሆንም፣ ‹‹ከአራት ጋዜጠኞች በላይ አንቀበልም›› በማለት ጠቅላይ ዓቃቤ ሕጉ ገደብ በመጣላቸው፣ ግልጽ ሊደረጉ የሚገቡ ጥያቄዎችን ማንሳት አልተቻለም፡፡ በተለይ ጄኔራል ሰዓረ መኮንንና ጓደኛቸውን በመኖሪያ ቤታቸው ግድያ በመፈጸም የተጠረጠረው የግል ጠባቂያቸው አሥር አለቃ መሳፍንት የመከላከያ ሠራዊት አባል በመሆኑና ዕርምጃም ወስዷል ተብሎ የተጠረጠረው በወታደራዊ መኮንኖች ላይ በመሆኑ፣ መከሰስ ያለበት በወታደራዊ ፍርድ ቤት ከመሆኑ አንፃር ግልጽ ሊደረግ የሚገባው ጥያቄ እንደነበር በርካታ ወገኖች እያነሱ ይገኛሉ፡፡ ሌሎችም በርካታ ለኅብረተሰቡ ግልጽ መደረግ ያለባቸው ጥያቄዎች ቢኖሩም፣ ገደብ በመጣሉ ምንም ማድረግ አልተቻለም፡፡ ጋዜጠኞች በመግለጫ ላይ የሚገኙት የተነገራቸውን ብቻ ይዘው እንዲመለሱ ሳይሆን፣ ተጨማሪ ማብራሪያ የሚያስፈልጋቸው ነገሮች ካሉ ለሚመለከተው አካል (ኃላፊ) በማንሳት፣ ግልጽነት መፍጠር ከመሆኑ አንፃር ‹‹ጥያቄ አለኝ›› እያሉ መገደብ ተገቢ አለመሆኑንም አስተያየት ሰጪዎች እየገለጹ ነው፡፡ በተፈቀደላቸው አራት ጋዜጠኞች (ሁለቱ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ጋዜጠኞች ናቸው) ከተነሱት ጥያቄዎች መካከል፣ ምርመራው ገለልተኛና ነፃ ሆኖ ስለመካሄዱ የተነሳውን ጥያቄ ምላሽ የሰጡት የአማራ ክልል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ አቶ ገረመው ገብረ ጻድቅ ሲሆኑ፣ ነፃና ገለልተኛ በሆነና በግልጽ ችሎት መካሄዱን፣ ለተጠርጣሪዎች ጭምር የሚጠቅም ማስረጃ በዓቃቤ ሕግና በፖሊስ ምርመራ መገኘቱን ገልጸዋል፡፡ ሌላው ዓቃቤ ሕግና የፀጥታ አካላት ከፖለቲካ ነፃ ሆነው እንዲሠሩ በደንብ ተደንግጎ መለየታቸውም አንዱ የገለልተኛነታቸው ማረጋገጫ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ የባህር ዳርና የአዲስ አበባ ግድያ እንዴት ሊገናኝ እንደሚችል ለተነሳውም ጥያቄም፣ የተሰባሰቡ ማስረጃዎች ግንኙነት እንዳላቸው ማሳየታቸውን ጠቁመው፣ እንዴት እንደሚገናኙ በፍርድ ቤት ክርክር ወቅት የሚጣራ መሆኑንም አቶ ገረመው አስረድተዋል፡፡

ባለው ሁኔታ ግን ክስ ለመመሥረት የሚያስችሉ የግንኙነት ማስረጃዎች መገኘታቸውን አክለዋል፡፡ በፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ምክትል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ አቶ ገለታ ሥዩምና የፌዴራል ፖሊስ ባልደረባ ኮሚሽነር ጄኔራል ተኮላ አይፎክሩ በተመሳሳይ ሁኔታ ገለልተኛ በሆኑ ከ60 በላይ አባላት የተጣራ ምርመራ መሆኑንና ነፃ፣ ገልተኛና ፕሮፌሽናል መንገድ ሁኔታ መጣራቱን ተናግረዋል፡፡      

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -