Tuesday, November 28, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የኢትዮጵያ ባንኮች በሶማሌላንድ መንቀሳቀስ የሚችሉበት የሕግ ረቂቅ ተዘጋጀ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በአሁኑ ወቅት ወኪል ባንክ በመክፈት በሶማሌላንድ እየተንቀሳቀሰ የሚገኘውን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጨምሮ፣ ሌሎችም የንግድ ባንኮች በአገሪቱ ቅርንጫፍ ከፍተው መንቀሳቀስ የሚችሉበትን የሕግ ረቂቅ ማዘጋጀቱን የሶማሌላንድ ማዕከላዊ ባንክ ይፋ አደረገ፡፡

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በሶማሌላንድ ቅርንጫፍ ለመክፈት ፍላጎት እንዳሳየ የገለጹት የአገሪቱ ባለሥልጣናት፣ ለሶማሌላንድ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተላከው ረቂቅ ሕግም የግል ባንኮች በአገሪቱ መንቀሳቀስ የሚችሉበትን መብት የሚሰጥ ከመሆኑም ባሻገር፣ ከሸሪዓ ወይም ከወለድ አልባ አገልግሎት ባሻገር ወለድ ላይ የተመሠረተ አገልግሎት ለማቅረብ የሚፈልጉም ሊገቡ የሚችሉበት ዕድል ሊፈጠር እንደሚችል፣ የሶማሌላንድ ማዕከላዊ ባንክ ዳይሬክተር ጄኔራል አህመድ ሐሰን አርዎ አስታውቀዋል፡፡ ይሁን እንጂ ረቂቅ ሕጉ ወለድ የሚያስከፍሉ ባንኮችን በተመለከተ፣ በፓርላማ በሚወሰነው መሠረት ፈቃድ እንደሚሰጥ ገልጸዋል፡፡

በኢትዮጵያና በሶማሌላንድ ማዕከላዊ ባንኮች መካከል ድርድር እየተካሄደ እንደሚገኝ ሲገለጽ፣ ንግድ ባንክ በበኩሉ ቅርንጫፍ ለመክፈት መዘጋጀቱን ከጥቂት ሳምንታት በፊት ማስታወቁ ይታወሳል፡፡

የባንከ ኦፍ ሶማሌላንድ ኃላፊ እንደገለጹት፣ አገሪቱ የውጭ ብድር ማግኘት የምትችልበት ዕድል ባለመኖሩ አብዛኛው በአገሪቱ የሚንቀሳቀሰው ካፒታል በዜጎች ጥረትና ከውጭ በሚኖሩ የዳያስፖራ አባላት የሚመነጭ ሀብት ነው፡፡ በውጭ የሚኖሩ የሶማሌላንድ ዜጎችና ተወላጆች ብዛት አንድ ሚሊዮን ሲገመት፣ ባለፈው ዓመት ብቻ በባንኮች በኩል በቀጥታ የላኩት የሐዋላ ገንዘብ 1.6 ቢሊዮን ዶላር እንደነበር ጠቁመዋል፡፡ በአንፃሩ በአገሪቱ የሚኖሩ ዜጎች ብዛት ከአምስት ዓመታት በነበሩ መረጃዎች መሠረት 4.6 ሚሊዮን ይገመታል፡፡

ከውጭ በባንኮች በኩል የሚላው የሐዋላ ገቢ እያደገ መምጣቱን ያስታወቁት ዳይሬክተር ጄኔራል አህመድ ሐሰን አርዎ፣ አገራቸው በዶላር የሚደረጉ ክፍያዎችን ወደ ሶማሌላንድ ሽልንግ እንዲቀንሱ የማድረግ እንቅስቃሴ ላይ ብትሆንም፣ በዶላር ወደ ውጭ የሚደረጉ ክፍያዎች ላይ ምንም ዓይነት ገደብ እንዳላስቀመጠች አስታውቀዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት አብዛኛው ከ100 ዶላር በላይ የሆኑ ክፍያዎች በዶላር ይስተናገዳሉ፡፡ ከ100 ዶላር በታች ዋጋ ያላቸው ክፍያዎች ግን በሽልንግ እንዲካሄዱ መወሰኑን ገልጸዋል፡፡ የሽልንግ የመግዛት አቅም እያደገ በመምጣቱ ባለፈው ዓመት አንድ ዶላር በ10,300 የሶማሊላንድ ሽልንግ የሚመነዘርበት ምጣኔ በአሁኑ ወቅት ወደ 8,300 ዝቅ ማለቱን አስታውሰዋል፡፡ ይህ አኃዝ ይበልጡን እየቀነሰ በመምጣት ደሃውና በአብዛኛው ግብይቱን በሽልንግ ላደረገው የአገሪቱ ዜጋ ከዋጋ ጫናና ከኑሮ ውድነት እንዲያንሰራራ አጋዥ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ይህም ሆኖ በአገሪቱ የሚንቀሳቀሱ የሌሎች አገሮች ዜጎች ያለ ገደብ ገንዘባቸውን በውጭ ምንዛሪ ማንቀሳቀስና ወደሚፈልጉት አካባቢ ማስተላለፍ የሚችሉበት ነፃ የፋይናንስ ሥርዓት በመኖሩ፣ በርካታ የንግድ ተቋማት ቀስ በቀስ እየገቡ እንደሚገኙ ዋቢ ያደረጉት በድንበር አካባቢ የሚገኙ የኢትዮጵያ ባንኮችን ነው፡፡ ቶጎ-ውጫሌ በተሰኘው የድንበር ከተማ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ጨምሮ በትንሹ ከአሥር የሚበልጡ የንግድ ባንኮች ቅርንጫፍ ከፍተው ያንቀሳቅሳሉ፡፡ ይህም የሆነው ሶማሌላንድ በዶላር የክፍያና የልውውጥ እንቅስቃሴ ላይ ምንም ዓይነት ገደብ ስለማትጥል ነው ብለዋል፡፡

ከባንኮቹ መበራከት ባሻገር በአሁኑ ወቅት ከተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስና ከሌሎች አቅራቢያ አገሮች ጭነቶችን በገፍ የሚያስገቡ የኢትዮጵያ ነጋዴዎችም፣ ከበርበራ ወደብ በቀጥታ ወደ ቶጎ-ውጫሌ የሚያጓጉዙ ነጋዴዎች ቁጥር እየተበራከተ መምጣቱን አብራርተዋል፡፡ 

የኢትዮጵያ ነጋዴዎች በብዛት ጭነቶቻቸውን በቶጎ-ውጫሌ ሲያጓጉዙም የወደብ አገልግሎት ክፍያ ከመፈጸም በቀር የቀረጥና የታክስ ግዴታ ስለማይጣልባቸው፣ በበርበራ ወደብ በኩል ወደ ድንበር ሸቀጦችን በገፍ እያስገቡ እንደሚሸጡ አስረድተዋል፡፡ በርካታ የኤሌክትሮኒክስ ምርቶችም ቶጎ-ውጫሌ ከተማን ሲያጥለቀልቁ፣ በርካታ አልባሳትና መጫሚያዎችም በብዛት በየሱቁ ይታያሉ፡፡

ምንም እንኳ በርካታ የኢትዮጵያ ነጋዴዎች በብዛት ሶማሌላንድን ቢያዘወትሩም በሕጋዊነት የተመዘገቡ፣ በንግድና በኢንቨስትመንት መስክ ተመዝገበው የሚነግዱ እንደሌሉ ሚስተር ሐሰን አርዎ ይናገራሉ፡፡ ከታክስ ዕፎይታ ባሻገር የአሥር በመቶ ታክስ ብቻ በምትጥለው አገራቸው በርካቶች ኢንቨስት እንዲያደርጉ የጠየቁ ሲሆን፣ በተለይም በዓሳ ሀብት መስክ ካላት ሀብት አኳያ ለኢትዮጵያ ገበያ ተስማሚ ምርት ማቅረብ የሚችሉ ኩባንያዎች ቢኖሩ፣ ለሁለቱም አገሮች ትልቅ ጥቅም እንደሚኖረው አብራርተዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት በርካታ ሕጎች እየወጡና የነበሩትም እየተሻሻሉ በመሆናቸው፣ እ.ኤ.አ. ከ2020 ጀምሮ የኢትዮጵያ ባለሀብቶች ወደ ሶማሌላንድ በመሄድ ኢንቨስት ቢያደርጉ የበለጠ ተጠቃሚ እንደመሆኑ ኃላፊው ያምናሉ፡፡ ምንም እንኳ በሕጋዊ መንገድ የተመዘገቡ ነጋዴዎችና ኢንቨስተሮች የሉም ይባል እንጂ የከፍተኛ ትምህርት አገልግሎት የሚሰጡ የኢትዮጵያ ተቋማት ይገኛሉ፡፡ አድማስ ዩኒቨርሲቲ፣ ኒው ጄኔሬሽን ዩኒቨርሲቲ፣ ጅማ ዩኒቨርሲቲና ሌሎችም ይጠቀሳሉ፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድም ጥቂት የቲኬት ሽያጭ ቢሮዎች አሉት፡፡

ይህም ሆኖ ሶማሌላንድ ዕውቅና ልታገኝ ባለመቻሏ በርካታ ጫናዎች እንዳሉባት ይታወቃል፡፡ የማዕከላዊ ባንኩ ኃላፊ እንደገለጹት፣ አገሪቱ ትልልቅ የመሠረተ ልማት አውታሮችን ለመገንባት የሚያስፈልጋትን ብድርም ሆነ የሚያስፈልጋትን ያህል የዕርዳታ ድጋፍ ማግኘት አልቻለችም፡፡ ይህንን ተከትሎም በርካታ ባለሀብቶችም ሆኑ የውጭ ባንኮች ወደ አገሪቱ መግባት እንዳልቻሉ ይታመናል፡፡ አብዛኛው የአገሪቱ የመንገድና የሌሎች መሠረተ ልማቶችም ከፍተኛ ጥገናና መስፋፋት ቢያስፈልጋቸውም፣ በፋይናንስ ዕጦት ከተማዋን ጨምሮ የበርካታ አካባቢዎች መንገዶች ምቹ አይደሉም፡፡

የመንግሥት ትልቁ ወጪ ከደኅነት በተጨማሪ ለደመወዝና ለመሳሰሉት የሚውል በጀት ላይ የተመሠረተ እንደሆነም ተገልጿል፡፡ መንግሥት በአብዛኛው ነፃ ገበያ ላይ የተመሠረተ ኢኮኖሚ የሚከተል በመሆኑ፣ አብዛኛው የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ በገበያው ፍላጎትና አቅርቦት ላይ የተመሠረተው ነው፡፡

ባንክ ኦፍ ሶማሊላንድ የሚቆጣጠራቸው ዳሃብሺል ኢንተርናሽናል ባንክ፣ ዳር ሰላም ባንክ፣ እንዲሁም ፕሪሚየር ባንክ የተባሉ የግል ባንኮች ሲኖሩ ከሦስቱ ትልቁ ዳሃብሺል የተሰኘው ነው፡፡ በጥቅሉ የሦስቱ ባንኮች የተጣራ ሀብት መጠን 171 ሚሊዮን ዶላር እንደሆነ የማከላዊ ባንኩ መረጃ ያሳያል፡፡ ከባንኮቹ ባሻገር 16 የሐዋላ ገንዘብ ማስላለፍ አገልግሎት የሚሰጡና ሁለት የአነስተኛ ገንዘብ አቅራቢዎች፣ የታካፉል ወይም የሸሪዓ ሥርዓትን የሚያሟሉ ሦስት የመድን ሰጪ ድርጅቶች፣ ሁለት የሞባይል ክፍያ አገልግሎት ሰጪዎችና 357 የውጭ ምንዛሪ ወኪሎች በሶማሌላንድ እንደሚንቀሳቀሱ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች