Sunday, June 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየሲዳማ ሕዝበ ውሳኔ ድምፅ አሰጣጥ ዛሬ ይካሄዳል

የሲዳማ ሕዝበ ውሳኔ ድምፅ አሰጣጥ ዛሬ ይካሄዳል

ቀን:

ለዓመታት ሲንከባለል እንደቆየ የሚነገርለትን የሲዳማ ብሔር የክልልነት ጥያቄ ምላሽ የሚሰጠው የሲዳማ ሕዝበ ውሳኔ ድምፅ አሰጣጥ ዛሬ ረቡዕ ኅዳር 10 ቀን 2012 ዓ.ም. በመላው ሲዳማ ዞን ይከናወናል፡፡ ከ2.3 ሚሊዮን በላይ መራጮች ድምፅ ይሰጣሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ከተመሠረተ የመጀመርያው የክልልነት ሕዝበ ውሳኔ የሆነው የሲዳማ ሕዝበ ውሳኔ ውጤት በኋላ፣ የመጀመርያው አዲስ የፌዴራል መንግሥቱ አባል ክልል ሊመሠረት ይችላል፡፡

የሲዳማ የክልልነት ጥያቄ ሐምሌ 11 ቀን 2010 ዓ.ም. በዞኑ ምክር ቤት ከፀደቀ በኋላ ለደቡብ ክልል ምክር ቤት ቢቀርብም፣ በሕገ መንግሥቱ መሠረት የክልሉ ምክር ቤት በአንድ ዓመት ውስጥ ሕዝበ ውሳኔ ማግኘት ባለመቻሉ ተደጋጋሚ ግጭቶች ተከስተዋል፡፡ በተለይ በ2010 ዓ.ም. በሲዳማ ብሔር ዘመን መለወጫ በዓል በጨምበላላና ዞኑ የራሱን በራሱ ክልልነቱን ያውጃል ተብሎ ሲነገር ቆይቶ፣ ሐምሌ 11 ቀን 2011 ዓ.ም. የተፈጠሩ ግጭቶች ያስከተሉት ከፍተኛ ዕልቂት የሚታወስ ነው፡፡

የዞኑ አስተዳደርና የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች የክልልነት ጥያቄው ምላሽ እንዲሰጠው በሰላማዊ ሠልፎች ሲጠይቁ መቆየታቸው የሚታወቅ ቢሆንም፣ በተለይ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሐምሌ 10 ቀን 2011 ዓ.ም. ሕዝበ ውሳኔውን በአምስት ወራት ውስጥ ለማድረግ በወሰነ ማግሥት የተከሰተው ግጭትና ዕልቂት ብዙዎችን አሳዝኗል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድም በሪፎርም ሥራ በመወጠሩ ምክንያት ሕዝበ ውሳኔውን በፍጥነት ማድረግ እንደማይቻል ጠቅሶ ባወጣው መርሐ ግብር መሠረት፣ የሲዳማ ሕዝበ ውሳኔ ከቀድሞው የተቆረጠለት ቀን በአንድ ሳምንት ተራዝሞ ዛሬ ይካሄዳል፡፡

መደበኛው የዞኑ የመንግሥት ሥራዎችንና ትምህርትን እስከ ዓርብ ኅዳር 12 ቀን 2012 ዓ.ም. ድረስ የሚያቋርጠው ሕዝበ ውሳኔ በ1,692 የምርጫ ጣቢያዎች የሚከናወን ሲሆን፣ ከ2.3 ሚሊዮን በላይ መራጮች ድምፅ ለመስጠት ተመዝግበዋል፡፡ ድምፅ በሚሰጥበት ወቅት በ200 ሜትር ክልል ውስጥ ከተፈቀደላቸው አካላት በስተቀር መገኘት የማይቻል ስለሆነ፣ ለምርጫው ስኬት ሲባል በመላው የሲዳማ ዞንና የሐዋሳ ከተማ የሞተር ብስክሌቶች እንዳይንቀሳቀሱ ታግደዋል፡፡

የሲዳማ የክልልነት ጥያቄን ተከትሎ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል በርካታ የክልልነት ጥያቄዎች በዞን ምክር ቤቶች ፀድቀው ወደ ክልል ምክር ቤት የተላለፉ ሲሆን፣ ምናልባትም በቀጣይ ሌሎች ክልሎችን የሚመሠርቱ ሕዝበ ውሳኔዎች ሊኖሩ እንደሚችሉም ይገመታል፡፡

እነዚህን ጥያቄዎች እያስተናገደ የሚገኘው የደቡብ ክልል መንግሥትና ፓርቲው የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ደኢሕዴን) የጥያቄዎቹን መነሻና ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ምላሽ ለመስጠት በባለሙያዎች በማስጠናት፣ ግኝት መሠረትም ሦስት ምክረ ሐሳቦች መቅረባዠው ይታወሳል፡፡ ክልሉን እንዳለ ማስቀጠል፣ ክልሉን በሁለት ወይም ከአምስት ባልበለጡ ክልሎች መክፈል ወይም የክልልነት ጥያቄዎች ለአገራዊ ደኅንነት አደጋ እየፈጠሩ የሚቀጥሉ ከሆነ ላልተወሰነ ጊዜ ጥያቄዎቹን ማቆየት የሚሉ ምክረ ሐሳቦች በጥናቱ ቀርበው እንደነበር አይዘነጋም፡፡

የክልሉ መንግሥትና ደኢሕዴን ለሲዳማ ዞን ክልልነት በመስጠት ሌሎችን ባሉበት ማስቀጠል፣ ነገር ግን በአንድ የክልል ከተማ ማዕከልነት ከመታጠር በርካታ ማዕከላት እንዲኖሩ የሚል ምርጫ ማድረጉ፣ ይሁንና ይኼንን የደኢሕዴን ውሳኔ የወላይታና የካፋ ዞን አመራሮች መቃወማቸው ይታወሳል፡፡

የሲዳማን ሕዝበ ውሳኔ ድምፅ አሰጣጥ በሰላም ለማጠናቀቅ በቂ ዝግጅት መደረጉን፣ የዞኑ አስተዳደር አስታውቋል፡፡ ከኅብረተሰቡ ጋር ተከታታይ ውይይት ሲደረግ እንደነበር የገለጸው አስተዳደሩ፣ ምንም ዓይነት የፀጥታ ሥጋት እንደማይኖር አስረድቷል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አወዛጋቢው የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ጉዳይ

በኢትዮጵያ የሕገ መንግሥት ማሻሻል ጉዳይ ከፍተኛ የፖለቲካ ውዝግብ የሚቀሰቀስበት...

 መፍትሔ  ያላዘለው  የጎዳና  መደብሮችን  ማፍረስ

በአበበ ፍቅር ያለፉት ስድስት ዓመታት በርካቶች በግጭቶችና በመፈናቀሎች በከፍተኛ ሁኔታ...

የተናደው ከቀደምቱ አንዱ የነበረው የአዲስ አበባ ታሪካዊ ሕንፃ

ዳግማዊ አፄ ምኒልክ በ19ኛው ክፍለ ዘመን መገባደጃ መናገሻ ከተማቸውን...

የአከርካሪ አጥንት ሕክምናን ከፍ ያደረገው ‘ካይሮፕራክቲክ’

በአፍሪካ ከጀርባ ሕመም ጋር በተያያዘ በርካታ ሰዎች ለከፍተኛ የአካል...