Thursday, June 20, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ኢትዮጵያና ሶማሌላንድ የቴሌኮምና የኤሌክትሪክ ኃይል  ስምምነት ሊያደርጉ ነው

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

1.5 ቢሊዮን ዶላር የንግድ ግንኙነትን የሚገዛ  ስምምነት እንደሚፈረም ይጠበቃል

በኢትዮጵያና በሶማሌላንድ መካከል የበርበራ ኮሪደር ስምምነት ውስጥ ከሚካተቱ ስምምቶች መካከል በቴሌኮምና በኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት መስክ ለሚዘረጋው ግንኙነት፣ በሁለቱ መንግሥታት መካከል ስምምነት ሊደረግ መታቀዱ ተገለጸ፡፡

የሶማሌላንድ ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ሚኒስትር አብዲላሂ አቦከር ኦስማን ለኢትዮጵያ ጋዜጠኞች እንዳስታወቁት፣ በሁለቱ አገሮች መካከል በተደረሰው የበርበራ ኮሪደር ስምምነት መሠረት የወደብ አጠቃቀምን ጨምሮ የመንገድ፣ የቴሌኮም፣ እንዲሁም የኤሌክትሪክ ኃይል ግንኙነትም ይካተታል፡፡

በመሆኑም በኤሌክትሪክ ኃይል መስክ ኢትዮጵያ የ100 ሜጋ ዋት ኤሌክትሪክ ኃይል ለሶማሌላንድ ለማቅረብ መስማማቷን፣ ይህ ስምምነት ወደ ተግባር እንዲመጣ የሚያግዙ ስምምነቶች በቅርቡ እንደሚፈርሙ ሚኒስትሩ አስታውቀዋል፡፡ ሶማሌላንድ በግልና በመንግሥት አጋርነት የሚተዳደር የአገልግሎት ዘርፍ ዘርግታለች፡፡ አብዛኛውን የኤሌክትሪክ አገልግሎት የሚያቀርቡት የግል ኩባንያዎች ናቸው፡፡ የኤሌክትሪክ ኃይል ፍጆታ ወጪም ውድ እንደሆነ፣ ከዚህ በተጨማሪም ሶማልቴል የተሰኘው የሶማሌላንድ የግል ቴሌኮም ኩባንያ፣ ኢትዮ ቴሌኮም፣ እንዲሁም የኦማን ቴሌኮም ኩባንያ በመሆን በሦስቱ መካከል በሚደረገው ስምምነት የቴሌኮም አቅርቦትን ለማስፋፋት የሚቻልባቸው ሥራዎች እንደሚካሄዱ የገለጹት የሶማሌላንድ ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ሚኒስትር፣ እነዚህን ሥራዎች የሚመራ የሁለቱ አገሮች የበይነ ሚኒስትሮች ኮሚቴ ተዋቅሮ እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ አስታውቀዋል፡፡ በሶማሌላንድ በኩል በተለይ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦቱ የሚተዳደርበት ብሔራዊ የኃይል ማስተላለፊያና ማሠራጫ ቋት ግንባታ ሥራ ይከናወናል ብለዋል፡፡ የቴሌኮምና የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦቱን የግልና የመንግሥት ተቋማት በጋራ የሚሠሩበት፣ የግንባታ፣ የኦፕሬሽንና የሥርጭት ሥራን ማዕከል ያደረገ አሠራር እንደሚዘረጋም አብራርተዋል፡፡  

ከዚህ ጎን ለጎን የወደብ ማስፋፊያ ግንባታ እየተካሄደበት የሚገኘው የበርበራ ወደብ የ440 ሚሊዮን ዶላር ፕሮጀክትም እ.ኤ.አ. በ2021 እንደሚጠናቀቅ ሲጠበቅ፣ ከተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስና ከእንግሊዝ መንግሥት በተገኘ የ110 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍም፣ ከበርበራ እስከ ቶጎ-ውጫሌ እስከተሰኘው የድንበር ከተማ የሚዘረጋው መንገድም ጥገናውና አዲስ ግንባታው በዚያው ዓመት እንደሚጠናቀቅ አብራርተዋል፡፡

.ኤ.አ. በ2005 እና በ2016 የበርበራ ወደብን እንደ ትራንዚት ወደብ፣ እንዲሁም እንደ መሸጋገሪያ ወደብ የመጠቀም ስምምነቶች በሁለቱ መንግሥታት መካከል መፈረሙን ሚኒስትሩ አስታውሰዋል፡፡ በመወጪው ታኅሳስ ወር የሶማሌላንድ ልዑክ ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት፣ ከትራንስፖርትና ከገንዘብ ሚኒስትሮች በተጨማሪ ከሌሎችም የሁለቱ አገሮች ግንኙነቶች ላይ ተጠሪ ከሆኑ የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ጋር እንደሚነጋገር ይጠበቃል፡፡

እንዲህ ያሉትን ሥራዎች በሁለቱ መንግሥታት መካከል የሚያሳልጥ የሁለትዮሽ የንግድ ስምምነት ለመፈረራረም እንቅስቃሴዎች መጀመራቸው ሲገለጽ፣ በአብዛኛው ለኢትዮጵያ እንዳደላ የሚነገርለትን የንግድ እንቅስቃሴ ለማቀላጠፍ ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጠር ተስፋ እንዳላቸው ሚኒስትሩ አስታውቀዋል፡፡ በሁለቱ አገሮች መካከል በዓመት እስከ 1.5 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት የንግድ ልውውጥ እንደሚካሄድ የሶማሌላንድ ባለሥልጣናት ይገልጻሉ፡፡ ከዚህ ውስጥ 700 ሚሊዮን ዶላር የሚገመት የንግድ ሚዛን ጉድለት እንደሚታይበት ይጠቀሳል፡፡ ከኢትዮጵያ በአብዛኛው ጫት፣ አትክልትና ፍራፍሬ፣ የቁም እንስሳትና መሰል ምርቶች በብዛት ይላካሉ፡፡ ከእነዚህ ውስጥ እስከ 27 በመቶውን የሚሸፍነው የጫት ወጪ ንግድ ሲሆን፣ በቀን ከ800 ሺሕ ዶላር ያላነሰ ግብይት እንደሚፈጸም ይታመናል፡፡

ይህም ሆኖ በርካታ ኢትዮጵያውያን በሶማሌላንድ በስደተኛነት እንደሚኖሩ፣ አብዛኞቹም የራሳቸውን ጥቃቅንና አነስተኛ ንግድ ሥራ በመክፈት እንደ ፀጉር ቤት፣ ምግብ ቤት በመክፈትና በሌሎችም የንግድ ሥራዎች ውስጥ ተሰማርተው ይገኛሉ፡፡ በርካታ ቁጥር ያላቸውም በትልልቅ ሆቴሎችና አገልግሎት መስጫዎች በጥበቃ ሥራ፣ በቤት ውስጥ ሠራተኛነትና በመሳሰሉት ተቀጥረው ይሠራሉ፡፡ ምን ያህል ኢትዮጵያውያን በሶማሌላንድ ውስጥ ይኖራሉ ለሚለው ጥያቄ ይህ ነው የሚል ምላሽ ማግኘት ያስቸግራል፡፡ እንደ ባለሥልጣናቱ ገለጻ የሶማሌላንድ ሕግ ጥምር ዜግነትን ስለሚፈቅድ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ እንደ ኢትዮጵያዊ፣ ሶማሌላንድም እንደ አገሬው እየሆኑ የሚኖሩ በርካቶች ናቸው፡፡ ይህም ቁጥራቸውን በቀላሉ ለመለየት አዳጋች እንደሚያደርገው ቢገለጽም፣ አብዛኞቹ ግን ያለ ሕጋዊ ሰነድ ወይም ፓስፖርት እንደሚኖሩ ይነገራል፡፡

በተመድ የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽን በኩል ተመዝግበው በሶማሌላንድ እንደሚኖሩ ከስምንት ዓመታት በፊት ይፋ የተደረጉ መረጃዎች ሕጋዊ የስደተኛነት መሥፈርት አሟልተው የሚኖሩት ቁጥራቸው 2,000 እንደነበር፣ በአንፃሩ አብዛኞቹ ኢትዮጵያውያን እንደሆኑ በሚነገረው መሠረት እስከ 80 ሺሕ የሚደርሱ ሰነድ የሌላቸው ስደተኞች በሶማሌላንድ እንደሚኖሩ ሲነገር፣ በሐርጌሳ የሚኖሩ ቢያንስ 30 ሺሕ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በተመድ ስደተኞች ኮሚሽን እንደሚደገፉ ያምናሉ፡፡ ይህም ሆኖ በአብዛኛው እንደሚነገረው፣ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በሶማሌላንድ ሕዝብ ዘንድ ጥሩ ተቀባይነት እንዳላቸው ይናገራሉ፡፡ ይህም ሆኖ ዘር ተኮር ፖለቲካው ሶማሌላንድ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንንም እየነካካቸው እንደሚገኝና በኢትዮጵያ የሚፈጸመው ጥቃት እዚያም ተከትሏቸው እንደመጣ የሚናገሩ አሉ፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች