ካሜሮን እ.ኤ.አ. በ2021 ለሚያስተናግደው የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ በባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም የአይቮሪኮስት (ዝሆኖቹ) አቻውን ያስተናገደው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን (ዋሊያዎቹ) በምድብ ማጣሪያው የመጀመርያውን ሦስት ነጥብ ያስመዘገበበትን ውጤት አግኝቷል፡፡
ኅዳር 9 ቀን 2012 ዓ.ም. በተካሄደው ጨዋታ በእንግዳው ቡድን ከ1ለ0 ተመሪነት በሱራፌል ዳኛቸውና አምበሉ ሺመልስ በቀለ አማካይነት ባስቆጠራቸው ሁለት ጎሎች 2 ለ1 አሸንፏል፡፡
በነጥብ ጨዋታ ሽንፈት ያላስተናገደው የባህር ዳር ስታዲዮም ዋሊያዎቹ በሜዳቸው የሚያደርጓቸውን ሁለት ጨዋታዎች ማለትም የኒጀርና የማዳጋስካር ጨዋታዎችን እንደሚያስተናግድ ይጠበቃል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በአሠልጣኝ አብርሃም መብርሃቱ እየተመራ እስካሁን ካደረጋቸው ስድስት የነጥብ ጨዋታዎች ሦስት ጊዜ ሽንፈትን ሲያስተናግድ፣ ሦስት ጊዜ ነጥብ ሲጋራና አንድ ጊዜ ማሸነፉ ይታወቃል፡፡