Monday, May 29, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትየፕሪምየር ሊጉ የክልል ጨዋታ የፀጥታ ጥበቃ አጥጋቢ ምላሽ አላገኘም

የፕሪምየር ሊጉ የክልል ጨዋታ የፀጥታ ጥበቃ አጥጋቢ ምላሽ አላገኘም

ቀን:

የኢትዮጵያ ጥሎ ማለፍ ዋንጫ ተሰረዘ

የዘንድሮ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ኅዳር 21 ቀን 2012 ዓ.ም. እንደሚጀምር አዲስ የተዋቀረው ዓብይ ኮሚቴ ኅዳር 6 ቀን በአዳማ በነበረው የዕጣ ማውጣት ሥነ ሥርዓት ላይ አስታውቋል፡፡

ዓብይ ኮሚቴው ተሳታፊ ክለቦች በተገኙበት በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ውሳኔ ያስተላለፈ ሲሆን፣ በክልል ከተሞች የሚከናወኑ ጨዋታዎች የፀጥታ ጥበቃ ጉዳይ ግን አጥጋቢ ምላሽ አለማግኘቱን ገልጿል፡፡ ዓብይ ኮሚቴው የ2012 ዓ.ም. የመተዳደሪያ ደንቡን ለክለቦች አቅርቧል፡፡ በዚህም ለውድድሩ ቅድመ ሁኔታ ብሎ ካቀረባቸው መስፈርቶች መካከል የክለቦች ምዝገባ፣ የተሳታፊ ክለቦች መጫወቻ ሜዳዎች ዝግጁነትና የመወዳደሪያ ሥፍራዎች የፀጥታ ጉዳይ በዋናነት ቢቀመጡም፣ የክልል የፀጥታ ኃይሎች ኃላፊነት የመቀበል ጉዳይ ጥያቄ ውስጥ መውደቁ ተገልጿል፡፡

ውድድሮችን በክልሎች ማከናወን ለበርካታ ክለቦች ሥጋት እንደሆነ በተሳታፊ ክለቦች ሳይቀር ሲነሳ የነበረ ጉዳይ ቢሆንም፣ በአንፃሩ የክልል የፀጥታ ተቋሞች ፈጣን ምላሽ ለመስጠትና ኃላፊነት ለመውሰድ ወደኋላ መሸሻቸው ከወዲሁ ጥርጣሬ ፈጥሯል፡፡ 

ቀደም ብሎ በክልሎች ውድድር ለማድረግ አዳጋች በመሆኑ፣ በተለይ በተመልካቾች መካከል የሚፈጠሩ አለመግባባቶች በዋነኝነት ሲነሱ ቢከርሙም፣ ከዚያ በላይ ደግሞ በፀጥታ አስከባሪዎች ቸልተኝነት የሚደርሰው አድሎነት በዋናነት ሥጋት ፈጥሯል፡፡

የዘንድሮውን ውድድር ለመጀመር ከወዲሁ ከሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ምክክር ሲያደርግ የሰነበተው ስፖርት ኮሚሽን፣ ክለቦችና የከተማ አስተዳደሮች እንዲሁም የፀጥታ አካላት ኃላፊነት እንዳለባቸው በአዳማ ባሰናዳው ሥልጠና ላይ አስገንዝቧል፡፡ ውድድሩን በሰላማዊ መንገድ ለማከናወን በየክለቡ ውስጥ የሚገኙ ሁሉም አካላት ኃላፊነት እንዳለባቸው ተጠቅሷል፡፡

የተለያዩ የውጭ አገር የተመልካቾች አያያዝ ልምድ ወደ አገር ውስጥ በማምጣትና ከደጋፊዎች ማኅበር አንድ አንድ ሰው በመምረጥ በቅድመ ጨዋታ ላይ ውይይት ለማድረግ ማቀዱን ዓብይ ኮሚቴው አስታውቋል፡፡

የውድድሩን ፀጥታ ጉዳይ በተመለከተ በአዳማ ውይይት ላይ የተገኙት የክለብ አመራሮች እንዲሁም ባለድርሻ አካላት ለችግሩ መንስኤ መፍትሔ ሲያስቀምጡ ቢስተዋሉም ተግባራዊነቱ ላይ ግን ባለማተኮራቸው በባለሙያዎች ተተችተዋል፡፡

ከዚህ ቀደም በፀጥታ ጉዳይ ላይ ለመምከር በተለያዩ መድረኮች ላይ ከመሳተፍ ባሻገር አለመግባባቶች ሲፈጠሩ ‹‹ጆሮ ዳባ ልበስ›› ብለው ከማለፍ ውጪ ተግባር ላይ እምብዛም እንደሆኑ ይጠቀሳል፡፡

ምንም እንኳ ዘንድሮ ውድድሩ ክለቦች በመረጡት ዓብይ ኮሚቴ መመራቱን ተከትሎ ከዚህ ቀደም የሚስተዋሉና ተመልካቾችን ለጠብ የሚጋብዙ ጉዳዮች ይቀንሳሉ ተብሎ ቢገመትም፣ በክለቦች መካከል የተፈጠሩ ቁርሾዎች መወገድ እንዳለባቸው ብዙኃን አስተያየት የሰጡበት ነው፡፡

ውድድሩ ኅዳር 22 ተጀምሮ ሰኔ 15 እንደሚጠናቀቅ መርሐ ግብር ቢወጣለትም የአገሪቷ ነባራዊ ሁኔታ ግን ሊጉን ለመጀመር ወሳኝነት እንዳለው በመድረኩ ተጠቁሟል፡፡

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራ አስተያየት ከሆነ፣ በክልል ከፀጥታ ኃይሎች ጋር መነጋገር ቢጀምሩም የተወሰነ መጓተቶች አሉ፡፡ በክልል የሚከናወኑ ውድድሮችን ፀጥታ ማስከበር መንግሥታዊ ኃላፊነት በመሆኑ የሚመለከተው አካል እየሠራበት ይገኛል ብለዋል፡፡

በውድድሩ ደንብ ላይ በአዳማ ሲመክር የነበረው ዓብይ ኮሚቴ የኢትዮጵያ ጥሎ ማለፍ ዋንጫ እንዳይካሄድ ክለቦች በዘጠኝ ድምፅና በአምስት ተቃውሞ መወሰናቸውን ገልጿል፡፡ ወልዋሎ ዓዲግራትና ስሑል ሽረ ባልተገኙበት ውሳኔ መሠረት በዚህም መሠረት በሊጉ አንደኛና ሁለተኛ የሚወጡ ክለቦች ቀጥታ ወደ አፍሪካ ሻምፒዮንስ ሊግና ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ይገባሉ፡፡

በፕሪሚየር ሊግ ዕጣ አወጣጥ መሠረትም የመጀመርያ ሳምንት ጨዋታ መርሐ ግብር አዳማ ከፋሲል፣ ወልቂጤ ከቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ሰበታ ከተማ ከወልዋሎ፣ ስሑል ሽረ ከኢትዮጵያ ቡና፣ ጅማ አባ ጅፋር ከባህር ዳር ከተማ፣ መቐለ ከሃድያ  ሆሳዕና እንዲሁም ሐዋሳ ከተማ ከድሬዳዋ በሚያደርጉት ጨዋታ ይጀምራል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመስቀል አደባባይ የመግቢያ ክፍያ ለምን?

ወጣቶች፣ ሕፃናትና አረጋውያን ሳይቀሩ መንፈሳቸውን የሚያድሱበት እንዲሁም ሐሳባቸውን በነፃነት...

በሕገ መንግሥቱ የተዋቀረው ‹‹የብሔር ፖለቲካ›› እና ‹‹ሥርዓቱ›› ያስከተለው መዘዝና መፍትሔው

(ክፍል አራት) በዓቢዩ ብርሌ (ጌራ) ባለፈው ጽሑፌ (በክፍል ሦስት) አሁን ያለው...

የኢትዮጵያ ኅብረተሰብና የመንግሥት መሪ ምሥል

በበቀለ ሹሜ በ2015 ዓ.ም. መጋቢት ወር ውስጥ ይመስለኛል በ‹ሸገር ካፌ›...

ዩኒቨርሲቲዎችን ራስ ገዝ ያደረገው አዋጅ የፍትሐዊነት ጥያቄ አስነሳ

በቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት ስምንት ዩኒቨርሲቲዎችን ራስ ገዝ በማድረግ ተቋማዊና...