Sunday, March 26, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትአትሌቲክስ ፌዴሬሽን አቋርጦት የነበረው የአሜሪካዊ ማናጀር ውል አደሰ

አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አቋርጦት የነበረው የአሜሪካዊ ማናጀር ውል አደሰ

ቀን:

25 ሺሕ ዶላር እንዲቀጣ ወስኗል

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ‹‹ለተቋሙ ሕገ ደንብ ተገዥ አልሆኑም›› በሚል የውል ማቋረጥ የዲሲፕሊን ዕርምጃ የወሰደባቸው የአሜሪካዊ ማናጀር ሚስተር ሁሴን ማኪን ዕገዳ ማንሳቱ አስታወቀ፡፡ ፌዴሬሽኑ ዕገዳውን ያነሳው ሚስተር ሁሴን ማኪ ይቅርታ ከመጠየቃቸውም በላይ በማናጀርነት የሚያስተዳድሯቸው በርካታ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች መኖራቸውን ግምት ውስጥ በማስገባት ጭምር እንደሆነ ገልጿል፡፡

ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ሰኞ ህዳር 8 ቀን 2012 ዓ.ም. በጽሕፈት ቤቱ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ፣ የአሜሪካዊ ሚስተር ሁሴን ማኪ ዕገዳ ቢነሳም ለሌሎች ማስተማሪያ እንዲሆን 25,000 ዶላር እንዲቀጣ መወሰኑን ገልጿል፡፡

በመግለጫው ላይ ውሳኔውን ያሰሙት የብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንት ኮማንደር ደራርቱ ቱሉ እንደገለጹት፣ ሚስተር ሁሴን ማኪ ከ120 በላይ ስመ ጥር አትሌቶችን ይዘው ለ13 ዓመታት ያህል ከኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ጋር ሲሠሩ ቆይተዋል፡፡ በቆይታቸው በአገሪቱ ዋና ዋና ቦታዎች የታዳጊ አትሌቶች ፕሮጀክት (Kids Athletics Project) ያላቸው ከመሆኑ ባሻገር አዲስ አበባ ውስጥ ቢሮ ከፍተው እየሠሩ ይገኛሉ፡፡ ኦሊምፒክን ጨምሮ በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናና በሌሎችም ታላላቅ መድረኮች ውጤታማ የሆኑ አትሌቶችን ለአገሪቱ ማፍራታቸው ከግምት መግባቱን የገለጹት ምክትል ፕሬዚዳንቷ፣ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ይቅርታቸውን ተቀብሎ፣ ቅጣታቸውን ወደ ገንዘብ በመለወጥ 25,000 ዶላር እንዲከፍሉ መወሰኑን፣ ይሁንና ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ቅጣቱ በቂ ነው ብሎ ባያምንም ሌሎች እንዲማሩበት ውሳኔው ተላልፏል ብለዋል፡፡

የፌዴሬሽኑን ውሳኔ መነሻ በማድረግ በዕለቱ ከተነሱ ጥያቄዎች መካከል፣ ሰርኩላር በተላለፈ ማግሥት ውሳኔው በይቅርታ የሚቀለበስ ከሆነ፣ በቀጣይ በተቋሙ በማናጀሮችና በአትሌቶቹ መካከል በሚኖረው የተጠሪነት ወሰን ላይ የሚኖረው ተፅዕኖ እንዴት ይታያል? ባለፉት ዓመታት ተመሳሳይ የዲሲፕሊን ጥሰቶች ሲፈጸሙ ዕርምጃ ባለመውሰዱ ፌዴሬሽኑ ‹‹ጥርስ የሌለው አንበሳ›› ሲባል መቆየቱን፣ ይህ የአሁኑ ውሳኔም እንደማይፀና ብዙዎች እየተናገሩ ሳለ ነው የተቀለበሰው፣ ከዚህ አንፃር ውሳኔው ለሌሎች መማሪያ መሆን አለመሆኑን ማረጋገጫው ምንድነው? የሚሉት ይጠቀሳሉ፡፡

‹‹ፌዴሬሽኑ ባለው ተቋማዊ አሠራር ለእንዲህ ዓይነቱ ጥፋት ከእንግዲህ ትዕግሥት አይኖረውም፤›› በማለት ኮማንደር ደራርቱና የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው አባል በዛብህ ወልዴ (ዶ/ር) በመተጋገዝ ማብራሪያ ሰጥተው፣ አሁንም ቢሆን ፌዴሬሽኑ ይቅርታውን ሊቀበል የቻለው ጥፋቱ በዋናነት ከአትሌቶቹም ገፋፊነት የተፈጠረ መሆኑ ጭምርን በመረዳቱ ነው ብለዋል፡፡ 

አሜሪካዊ ሁሴን ማኪ በበኩላቸው ለተፈጠረው ስህተት ይቅርታ ጠይቀው፣ ስህተቱ በእሳቸው ሙሉ ፍላጎት ላይ አለመመሥረቱንና አትሌቶቹ በውድድሩ ለመሳተፍ ከነበራቸው ጉጉት የተነሳ መሆኑን ተናግረው፣ ለወደፊቱ እንደማይደገም ማረጋገጫ ሰጥተዋል፡፡ የማናጀሩ ተወካይና አሠልጣኝ አቶ ሃጂ አዴሎ ቅጣት እንደማያስተምር ገልጸው የተሻለ የሚሆነው ግን በሆደ ሰፊነት ተነጋግሮና ተግባብቶ መሥራቱ አስፈላጊ ይሆናል ብለዋል፡፡  

ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ በዶሃው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ በማራቶን ውድድር ተሳትፈው የነበሩ አትሌቶች ከማገገሚያው ሦስት ወራት በፊት ውድድር እንዳያደርጉ ቢወስንም፣ ኤሊት ስፖርት ማኔጅመንት የተወሰኑ አትሌቶችን በኒውዮርክ ሲቲ ማራቶን ላይ ማሳተፉን ተከትሎ ፌዴሬሽኑ ከማናጀሩ ሁሴን ማኪ ጋር የነበረውን ውል እንዳቋረጠ መዘገባችን ይታወሳል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለፋይናንስ ዘርፉ ብቃት ያለው የሰው ኃይል የማፍራት የቤት ሥራን የማቃለል ጅማሮ

የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ እያደገ ለመሆኑ ከሚቀርቡ ማስረጃዎች ውስጥ  የግል...

የምድር ባቡርን የሚያነቃቃው የመንግሥት ውሳኔ

በኢትዮጵያ ወደብ አልባነት ላይ የተደመረውን የሎጀስቲክስ ችግር ለመፍታት ግዙፍ...

የፓርላማ አባላት ስለሰላም ስምምነቱ አፈጻጸም ግልጽ መረጃ የለንም አሉ

‹‹ሕወሓትን ለፍረጃ አብቅተውት የነበሩ ጉዳዮች በአብዛኛው መልክ ይዘዋል›› ሬድዋን...