በአገሪቱ የፖለቲካ ትርክቶች፣ ንግግሮችና ውይይቶች መሀል ጎልተው ከሚወጡ ጥያቄዎች መሀል የብሔራዊ ዕርቅና አገራዊ መግባባት የሚለው ሐሳብ አንዱና ዋነኛው ነው፡፡ ይህ ጥያቄ ለበርካታ ፖለቲከኞች የአፍ ማሟሻ አጀንዳ ነው፡፡ በተለይ የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) የደርግ መንግሥት አሸንፎ ሥልጣኑን ከተቆጣጠረ ጀምሮ በተደረጉ የፖለቲካ ድርድሮችና ውይይቶች ላይ ጎልቶ ተሰምቷል፡፡
ባለፉት ዓመታት አብዛኛው የተቃውሞ ጎራው ፖለቲከኞች ለአገሪቱ ህልውናና የፖለቲካ ምኅዳር መዳበር አንዱና ዋነኛው ጉዳይ የነበሩ በደሎች ላይ ጥልቅ ውይይት በማድረግ ለችግሩ ሁነኛ መፍትሔ ለመስጠት የብሔራዊ ዕርቅ አጀንዳን በተደጋጋሚ ያነሱ የነበረ ሲሆን፣ ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ ደግሞ ‹ማን ከማን ተጣልቶ ነው የሚታረቀው?› በሚለው አቋሙ በመፅናት አጀንዳውን ወደ ጎን ገሸሽ ሲያደርገው ነበር፡፡
ፖለቲከኞች በተለይ የደቡብ አፍሪካንና የሩዋንዳን ጉዳይ እንደ ምሳሌ በማንሳት፣ በአገሪቱ ዘላቂ ሰላም ለማምጣት መጀመርያ ብሔራዊ ዕርቅ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ሲወተውቱ ነበር፡፡
የብሔራዊ ዕርቅን የሚያቀነቅኑ ቡድኖችና ግለሰቦች በተለይ ባለፉት ዘመናት በአገሪቱ ለተከሰቱ ልዩነቶችና መቋሰሎች አንድ መፍትሔ ሳይበጅለት ስለአገር ማውራትም ሆነ መወያየት ከችግሩ እንዳንወጣ ያደርገናል በማለት፣ የአጀንዳውን አስፈላጊነት ከመሞገት አልቦዘኑም፡፡ ነገር ግን ለዚህ ውትወታቸው ከመንግሥት ሲሰጥ የነበረው ምላሽ ተመሳሳይ እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ወደ ሥልጠን ከመጡ ወዲህ ደግሞ አጀንዳው በከፍተኛ ሁኔታ እየተቀነቀነ የሚገኝ ሲሆን፣ የመንግሥት አቋምም የመለሳለስ አዝማሚያ እያሳየ ነው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ምንም እንኳ ብሔራዊ ዕርቅ የሚለውን አጀንዳ በተለየ ሁኔታ አንስተው ባያቀነቅኑትም፣ ወደፊት በጋራ ለመጓዝ ግን ያለፈውን በመተው በአዲስ አስተሳሰብና በፍቅር መሥራት እንደሚገባ በተለያዩ አጋጣሚዎች ሲናገሩ ተስተውሏል፡፡
ብሔራዊ ዕርቅ መከናወኑ ለአገሪቱ ሰላም ሁነኛ መሣሪያ እንደሆነ የሚሞግቱ ወገኖች፣ በተለይ ደግሞ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የሚፈጠሩ ግጭቶችንና አመረጋጋቶችን እንደ ማሳያነት በማውሳት ሰላም እንዲመጣ የብሔራዊ ዕርቅ አጀንዳ ጊዜ የማይሰጠው ጉዳይ እንደሆነ እየገለጹ ነው፡፡
ከዚህ አንፃር የተለያዩ ቡድኖችና ግለሰቦች ስለሰላም መወያየትና ስለአገሪቱ የሰላም ሁኔታ የተለያዩ የውይይት መድረኮችን በማሰናዳት ላይ ይገኛሉ፡፡ የእንዲህ ዓይነት መነሳሳት ውጤት የሆነ የውይይት መድረክ ባለፈው ሳምንት ሐሙስ ኅዳር 4 ቀን 2012 ዓ.ም. በጁፒተር ሆቴል ተካሂዶ ነበር፡፡
የውይይት መድረኩን ያዘጋጀው ከአንድ ዓመት በፊት ስለኢትዮጵያ ጉዳይ ያገባናል በሚሉ የግለሰቦች ስብስብ አማካይነት የተቋቋመው የሐሳብ ማዕድ ነው፡፡ ውይይቱም ‹‹ዕርቀ ሰላምና ከብሔራዊ መግባባት›› በሚል ርዕስ ሲሆን፣ ‹‹ከዚህ አንፃር ምን ልንሠራ እንችላለን?›› የሚል ዓላማ አንግቦ የተከናወነ መድረክ ነበር፡፡
በዕለቱ ለውይይት የሚሆን መነሻ ሐሳብ ያቀረቡት ታዋቂው የሰላምና ደኅንነት ምሁር ህዝቅያስ አሰፋ (ፕሮፌሰር) ሲሆኑ፣ ግጭት እንዴት ይፈጠራል? እንዴትስ ይፈታል? የግጭት አፈታት ዘዴዎችን ሥራ ላይ ለማዋል ምን ያስፈልጋል? ለወደፊት የሰላም ሥራ ለማቀድ ምን መደረግ አለበት? የሚሉ ሐሳቦች ላይ ያላቸውን የካበተ ልምድ በማውሳት ለተወያዮች ጥልቅ የሆነ ገለጻ አድርገዋል፡፡
ፕሮፌሰሩ ከዳበረ ልምዳቸው በመነሳት በተለይ በግጭት አፈታት ዘዴዎች ላይ ዘለግ ያለ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ ‹‹ስለሰላም በተደጋጋሚ የምናወራው በአገራችን የማያባራ ግጭት በመኖሩ ነው፤›› በማለት ገለጻቸውን የጀመሩት ፕሮፌሰሩ፣ ‹‹መፍትሔውንም ራሳችን ቁጭ ብለን መፈለግ አለብን እንጂ ፈጣሪን ጨምሮ ወደ ሦስተኛ ወገን ማስተላለፍ አይበጅም፤›› ሲሉ ጠቁመዋል፡፡
በዚህም መሠረት በተለያየ ደረጃ ስለሚገኝና የተሳትፎን መጠን መሠረት ያደረገ የግጭት አፈታት ሒደት ምን እንደሚመስል አስረድተዋል፡፡ ከግጭት አፈታት አንፃር የዜጎች ተሳትፎ ከፍተኛ እንደሆነ በመጥቀስ፣ እያንዳንዱ የግጭት አፈታት እንዴት አሳታፊ ወይም ደግሞ ከልካይ እንደሆነም አስረድተዋል፡፡
ከተሳትፎ አንፃር የጥቂቶችን ተሳትፎ የሚይዘው የግጭት አፈታት ዘዴ በኃይል (Force) መፍታት ሲሆን፣ ይህም ማለት የጦር መሣሪያ ወይም ሌላ ጉልበትን በመጠቀም ሌላውን ወገን በማስገደድ የሚከናወን የግጭት አፈታት ዘዴ ነው ብለዋል፡፡
እንዲህ ባለው የግጭት አፈታት ወቅት ኃይል ወይም ጉልበት የሌለው ወገን መፍትሔ ለመፈለግ ያለው ተሳትፎና ድርሻ ዝቅተኛ በመሆኑ፣ በኃይለኛው ወይም በጉልበተኛው ወገን የቀረበውን የመፍትሔ ሐሳብ መቀበል ብቸኛ አማራጭ እንደሚሆን አስረድተዋል፡፡
ስለዚህ ኃይልን በመጠቀም የሚደረግ የግጭት አፈታት ዘዴ ዋነኛው መንገዱ ኃይል በመሆኑ፣ በግጭቱ የተሳተፉ ሁሉም ወገኖች ለመፍትሔው የሚኖራቸው ተሳትፎ እጅግ ዝቅተኛ እንደሆነ በመግለጽ በኢትዮጵያም እየተስተዋለ ያለው አካሄድ ይህ መሆኑንና ‹‹ሰላምን ለማምጣት የብዙዎች የመፍትሔ ሐሳብ እየተደመጠ አይደለም፤›› በማለት፣ የሁሉንም ባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ወሳኝነት በአፅንኦት ገልጸዋል፡፡
ሌላኛው የግጭት አፈታት ዘዴ ደግሞ ፍርድ (Adjudication) መሆኑን፣ ኃይልን በመጠቀም ከሚደረገው መፍትሔ የመፈለግ መንገድ አንፃር የተሳትፎ መጠኑ ከፍተኛ ቢሆንም፣ ነገር ግን የመጨረሻ ውሳኔ የሚሰጠው በሦስተኛ ወገን ማለትም በዳኛ በመሆኑ የተሳትፎ መጠኑ ለተዋንያኑ የተተወ እንዳልሆነ አስረድተዋል፡፡
በዚህም መሠረት ራሳቸው የችግሩ ባለቤቶች ለችግራቸው መፍትሔ ራሳቸው የማይሰጡ ከመሆኑ አንፃር፣ ይህም ቢሆን ውስንነት እንዳለው አውስተዋል፡፡
በመሆኑም ከሁለቱም ግጭት አፈታቶች የተሻለው ግን በራሱ መሉ ያልሆነውን ሌላ የግጭት አፈታት ዘዴ መኖሩን ጠቁመዋል፡፡ ሦስተኛው የግጭት አፈታት ዘዴ ደግሞ ግልግል (Arbitration)፣ በአብዛኛው በፍርድ ከሚሰጥ የግጭት አፈታት ጋር ተመሳሳይነት እንዳለው አመላክተዋል፡፡
ከፍርድ የሚለየው ዋነኛ ነጥብ ግን በግጭት ውስጥ ያሉት ወገኖች እንዲገላግላቸው የሚፈልጉትን ወገን የመመረጥ ሚና መጫወታቸውን ነው፡፡ በዚህም መሠረት መፍትሔ ለመፈለግ በሚደረገው ጥረት ውስጥ የተዋናዮቹ የተሳትፎ መጠን ሰፋ እንደሚል አስረድተዋል፡፡
ከዚህ ከፍ ያለ የተሳትፎ መጠን ያለው የግጭት አፈታት ዘዴ ደግሞ ድርድር (Negotiation) ሲሆን፣ የዚህኛው መንገድ ደግሞ ችግር ያለባቸው ወገኖች ቁጭ ብለው አብረው በመሥራትና በመነጋገር ለችግራቸው መፍትሔ የሚፈልጉበት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
በዚህኛው የግጭት አፈታት ዘዴ በችግሩ ላይ የተሳተፉ ወገኖች አንድ ላይ ተቀምጠው ለሁሉም ወገን የሚበጅ መፍተሔ ለማምጣት የሚደራደሩ በመሆናቸው፣ የተሳትፎ መጠኑ ከፍተኛ እንደሚባል ገልጸዋል፡፡
ምንም እንኳን የተሳትፎ መጠኑ ከሌሎቹ የግጭት አፈታት ዘዴዎች አንፃር ከፍተኛ ቢሆንም፣ ሁሉንም በግጭት የተሳተፉ ወገኖችን ማወያየት ግን በጣም ከባድ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ሁለቱንም ወገኖች ወደ ጠረጴዛ ለማምጣትና ለውይይት ማዘጋጀት ከፍተኛ ጥረት የሚጠይቅ ሥራ መሆኑን፣ ባለድርሻ አካላቱን ለማምጣት ከተቻለ ግን ካለው የተሳትፎ መጠን አንፃር ግጭቶችን ለመፍታት ዓይነተኛ ሚና እንደሚጫወት አስረድተዋል፡፡
ከዚህ በመቀጠል የተሻለ የተሳተፎ መጠን ያለው የግጭት አፈታት ዘዴ ደግሞ ሽምግልና (Mediation) መሆኑን፣ የዚህን የእንግሊዝኛ ቃል ሽምግልና ከማለት ይልቅ አስታራቂ የሚለው የተሻለ እንደሚሆን ምሁሩ ገልጸዋል፡፡
ይህንንም ሲያብራሩ ‹ሜድየሽን› ማለት በሁለት ወገኖች ተመርጦ ሁለቱ ወገኖች ያሉባቸውን ችግሮች እንዲፈቱ የመርዳት ሚና የሚጫወትና የመወሰን ሥልጣን የሌለው አካል ነው፡፡ ሽምግልና ላይ ግን ለመሸምገል የተቀመጠው አካል የዳኝነት ሚና የሚጫወት በመሆኑ፣ ሽምግልና ለማለት ያስቸግራል በማለት አስታራቂ የሚለው ለእንግሊዝኛው ቃል ቀረብ የሚል ትርጉም እንዳለውም አውስተዋል፡፡
ይኼኛው የግጭት አፈታት ዘዴ ግጭቶችን በውይይት ከመፍታት የሚለየው ሦስተኛ ወገንን የሚጋብዝ በመሆኑ ሲሆን፣ የባለድርሻ አካላት የተሳትፎ መጠን ግን ከውይይት የተሻለና ከፍተኛ እንደሆንም ገልጸዋል፡፡
ከዚህ አንፃር በግጭት ውስጥ ያሉ ወገኖች መፍትሔ ለማምጣት የሚመርጡት የግጭት አፈታት ዘዴ ውይይት ነው? ወይስ አስታራቂነት የሚለው የበርካቶች ጥያቄ መሆኑን አክለዋል፡፡
እንዲህ ላሉ ጥያቄዎች ውይይት በጣም ጥሩ የግጭት መፍቻ ዘዴ ቢሆንም፣ አስቸጋሪውና ከባዱም ዘዴ እንደሆነ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ ይህን ዘዴ ከባድና አስቸጋሪ ከሚያደርጓቸው ምክንያቶች ደግሞ የውይይቱን ሥርዓት ወይም አካሄድ መወሰን ላይ መግባባት ከባድ ስለሚሆን፣ ሁለቱም ወገኖች ለማሸነፍ ስለሚፈልጉና መደማመጥ ስለማይኖር መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ከዚህ ሁሉ በላይ ይህን ዘዴ ከባድ የሚያደርገው ግን ውይይቱን የሚጀምረው ማን ነው? የሚለውን ለመመለስ አስቸጋሪ እንደሆነ፣ ምክንያቱም መጀመርያ የእንወያይ ጥሪ የሚያቀርበው ወገን እንደ ደካማ ስለሚታይ ጥሪ የቀረበለት አካል ጥሪውን ከመቀበል ይልቅ፣ ተቀናቃኜ አሁን ደክሟል ከሚል ዕሳቤ በመነሳት አሁን ነው ማጥቃት በሚል ውሳኔ በመጓዝ ግጭቶች ሊባባሱ ይችላሉ በማለት አብራርተዋል፡፡
በመጨረሻ የቀረበው የግጭት አፈታት ዘዴ ደግሞ ዕርቅ (Reconciliation) ነው፡፡ ይህ የግጭት አፈታት ዘዴ በግጭት ወቅት የተፈጠረውን ችግር ከመፍታት በዘለለ፣ የተፈጠሩ ማኅበራዊ ስንጥቆችን እስከ ወዲያኛው መፍትሔ ማበጀት ላይ ስለሚያተኩር መሆኑን አውስተዋል፡፡
በሽምግልናና በዕርቅ መሀል ያለው ልዩነት ደግሞ ሽምግልና በሁለቱ ወገኖች የሚነሳውን ችግር አስመልክቶ መፍትሔ መስጠት ላይ የሚያተኩር ሲሆን፣ ዕርቅ ግን አድማሱን ከሽምግልና አስፍቶ በግጭቱ ወቅት የተጎዳውን፣ የተፈናቀለውንና የተዋረደውን የኅብረተሰብ ክፍል ላይ የተፈጠረውን ስብራት እንዴት እንጠግነው የሚለው ላይ የሚያተኩር ነው ብለዋል፡፡
ከዚህ አንፃር ምንም እንኳን ግጭቱ አንዴ ቢፈታም የተበጠሰውን ዝምድና እንዴት መጠገን ይቻላል? ቂምን፣ ጥላቻን፣ ፍርኃትን፣ ሐዘንና የመሳሰሉትን የግጭቱ ጠባሳዎችን እንዴት ማረቅ ይቻላል የሚለው ጉዳይ ላይ ትኩረት ሰጥቶ የሚከናወነው የግጭት አፈታት ዘዴ ዕርቅ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
ዕርቅ ችግሮችን ከመፍታት ባለፈ የማኅበረሰብ ጠባሳንና ቁስሎችን የማከም ከፍተኛ ኃይል ያለው የግጭት አፈታት ዘዴ እንደሆነ የሚስማሙት በርካቶች ሲሆኑ፣ በቅጡ ተግባር ላይ ከዋለም አዲስ ምዕራፍ ለመክፈት ዓይነተኛ ሚና እንደሚጫወት ተገልጿል፡፡
እነዚህን የግጭት አፈታት ዘዴዎችን በትንተና ካቀረቡ በኋላ ለኢትዮጵያ ሰላም መምጣት የሁሉም አካላት ሚናንና ተሳትፎን እንደሚጠይቅ የገለጹ ሲሆን፣ ካላቸው ዓለም አቀፍ ልምድና ተሞክሮ በመነሳት የኢትዮጵያን ችግር ለመፍታት የጎደለው ፍላጎት ማጣት መሆኑን አስረግጠው ተናግረዋል፡፡
‹‹የአገራችንን ችግር ለመፍታት የጎደለው የፍላጎት ማጣት ጉዳይ ነው፡፡ ፍላጎት ማምጣት ከተቻለ የኢትዮጵያ ችግር ከሌላው ዓለም አንፃር ከባድ አይደለም፤›› በማለት ሁሉም ባለድርሻ አካላት ሰላም የማስፈን ፍላጎታቸውን እንዲያዳብሩና ወደ ጠረጴዛ እንዲመጡ ጥሪ በማቅረብ ገለጻቸውን አጠናቀዋል፡፡