Monday, December 4, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በስምንት ሚሊዮን ዶላር ወጪ የሚታደሰው የባህር ዳሩ ግራንድ ሆቴል

ተዛማጅ ፅሁፎች

በጣና ሃይቅ ዳርቻ ላይ የሚገኘው የባህር ዳሩ ግራንድ ሆቴል ሁለት ዓመት ከፈጀ ድርድር በኋላ ከራዲሰን ሆቴል ግሩፕ ጋር የማኔጅመንት ኮንትራት ተፈራረመ፡፡ በዚህም መሠረት ሆቴሉ በስምንት ሚሊዮን ዶላር ወጪ ዕድሳት ከአንድ ዓመት በኋላ ወደ ሥራ እንደሚገባ ታውቋል፡፡

የፊርማ ሥነ ሥርዓቱ የተካሄደው ሐሙስ ህዳር 4 ቀን 2012 ዓ.ም. ሲሆን፣ የሆቴሉ ስያሜ ወደ ‹‹ራዲስን ባህር ዳር›› መቀየሩ ተገልጿል፡፡ ድርድሩ የተካሄደው በኦዚ ዓለም አቀፍ የሆቴል ፕሮጀክት አማካሪዎች ባለቤት አቶ ቁምነገር ተከተል እንደሆነም ታውቋል፡፡

የሆቴሉ ባለቤት ወ/ሮ ትልቅ ሰው ገዳሙ በፊርማ ሥነ ሥርዓቱ ወቅት እንደገለጹት፣ የራዲሰን ወደ ባህር ዳር መምጣት ለአገሪቷ ፋይዳው ሰፊ ነው፡፡    ‹‹ራዲሰንን ወደ ባህር ዳር ሳመጣው ከእኔ በላይ ለአገሬ ትልቅ ፋይዳ ይኖረዋል በማለት ነው፡፡ ይህም ሲባል ከውጭ ምንዛሪ አንፃር እንዲሁም ከቱሪስት ፍሰቱ አኳያ ትልቅ ሚና የሚጫወት ይሆናል፤›› ብለዋል፡፡

የራዲሰን ሆቴል ግሩፕ የሆቴል ማኔጅመንቱን ለ20 ዓመታት እንደሚመሩት የገለጹት ወ/ሮ ትልቅ ሰው፣ ንብረትነቱ ግን ሙሉ በሙሉ የእሳቸው እንደሚሆን ተናግረዋል፡፡ በቀጣይም ሌሎች ሆቴላቸውን ከራዲሰን ጋር ለማፈራረም እንዳሰቡ ወ/ሮ ትልቅ ሰው አሳውቀዋል፡፡

በስምንት ሚሊዮን ዶላር ወጪ የሚታደሰው የባህር ዳሩ ግራንድ ሆቴል

 

ዕድሳቱ ከስድስት እስከ ዘጠኝ ወራት ጊዜ እንደሚወስድና ሙሉ ለሙሉ ወደ ሥራ ለመግባት የአንድ ዓመት ጊዜ እንደሚፈጅ የገለጹት አቶ ቁምነገር፣ ዕድሳቱ በሁለት ተከፍሎ እንደሚያካሄድ ጠቁመዋል፡፡

ይህንንም ሲያብራሩ የመጀመሪያው በ6.5 ሚሊዮን ዶላር ወጪ የሚከናወነው የሆቴሉ ዕድሳት ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ የሆቴሉን አካባቢ የማልማት ሥራ እንደሆነና ወጪውም 1.5 ሚሊዮን ዶላር እንደሚፈጅ ተናግረዋል፡፡ በአጠቃላይ በስምንት ሚሊዮን ዶላር እንደሚታደስ ገልጸዋል፡፡

ይህ ባለ17 ወለል ሕንፃ ሆቴል ከዕድሳቱ በኋላ 125 መኝታ ክፍሎችን በማካተት ሥራ እንደሚጀምርም አክለዋል፡፡ በዓለም ላይ ከ1‚400 በላይ ሆቴሎች በሥሩ የሚያስተዳድረው ራዲስን ሆቴል ግሩፕ፣ በኢትዮጵያ ከሚያስተዳድራቸው ሆቴሎች ይኼኛው አራተኛው እንደሆነ ግሩፑ አስታውቋል፡፡

የራዲሰን ሆቴል ግሩፕ ምክትል ፕሬዚዳንት ኤሊ ዮንስ፣ በቅርብ ዓመታት ኢትዮጵያ እያስመዘገበች ያለችውን ከፍተኛ የቱሪዝም ዕድገት በማውሳት በገበያው አራተኛ ሆቴላቸውን በማቅረባቸው ደስተኛ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች