ካሜሮን እ.ኤ.አ. በ2021 ለምታስተናግደው የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ በምድብ 11 የተደለደለው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን፣ የአይቮሪኮስት አቻውን ባለፈው እሑድ በባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም አስተናግዶ 2 ለ 1 በሆነ ውጤት ማሸነፉ፣ አዲስ አበባን ጨምሮ በአራቱም አቅጣጫ ብሔራዊ ስሜት የሚያጠናክር አስተያየት ተጠናክሮ እንደቀጠለ ይገኛል፡፡ ብሔራዊ ቡድኑ የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጨምሮ በሌሎችም ተመሳሳይ መድረኮች ተደጋጋሚ ሽንፈቶችን ሲያስተናግድ መቆየቱና ጠንካራውን የአይቮሪኮስት ብሔራዊ ቡድን ያሸንፋል የሚል ግምት ባለመኖሩ ውጤቱ ከነድክመቱ በብዙዎች ዘንድ እንዲወደስ መነሻ ሆኗል የሚሉ አልጠፉም፡፡
የመጀመሪያውን የምድብ ጨዋታ ከሜዳው ውጪ በማዳጋስካር 1 ለ 0 በሆነ ጠባብ ውጤት የተሸነፈው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን፣ ከማዳጋስካር ቡድን ወቅታዊ አቋምና የእግር ኳስ ደረጃ በመነሳት ውጤቱ ለዋሊያዎቹ ቀጣይ ተጋጣሚ ለአይቮሪኮስት ግምት እንዲሰጠው ሆኖ ቆይቷል፡፡ ይሁንና ዋሊያዎቹ ማራኪ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴን ጨምሮ “ዝሆኖቹ” በሚል ቅጽል ስም የሚታወቁትን ድል ነስተዋል፡፡
ድሉ በነጥብ ጨዋታ ሽንፈት ገጥሞት በማያውቀው የባህር ዳር ስታዲየም መሆኑ፣ የኢትዮጵያ ቡድን በሜዳው የሚያደርጋቸውን ቀሪ ሁለት ጨዋታዎች (ኒጀርና ማዳጋስካር) በዚሁ ሜዳ እንደሚሆንም ይጠበቃል፡፡ ዓለም አቀፉ የባህር ዳር ስታዲየም ደረጃውን በሚመለከት የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) እንዲያሟላ ቅድመ ሁኔታ ካስቀመጠለት መካከል ብዙውን አሟልቶ የሚቀረው ተጨዋቾች ከመልበሻ ቤት ወደ ስታዲየሙ በሚወጡበት ጊዜ ከተመልካቾች መከላከያ አጥር ብቻ እንደሆነ ለመታዘብ ተችሏል፡፡
በብሔራዊ ቡድኑ ተደጋጋሚ ሽንፈት ምክንያት ዋና አሠልጣኙ ኢንስትራክተር አብርሃም መብርሃቱን ቆይታን ጥያቄ አስነስቶበት መቆየቱ ይታወሳል፡፡
ሪፖርተር በዚህ ጉዳይ ያነጋገራቸው አስተያየት ሰጪዎች፣ አሠልጣኙ በአፍሪካ በእግር ኳስ ደረጃዋ ከቀዳሚዎቹ ተርታ በሆነው አይቮሪኮስት ላይ ያስመዘገቡት ውጤት እንደተጠበቀ፣ ቡድናቸው አሁንም ወጥ የሆነ የቡድን ቁመና ክፍተት በሰፊው ይስተዋልበታል፡፡ አሠልጣኙ የቡድኑን ኃላፊነት ከተረከቡ ማግሥት ጀምሮ ያደረጓቸውን የወዳጅነት ጨዋታዎችን ጨምሮ የቡድናቸው ቅርፅ የተለያየ ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ በቀናት ልዩነት ከማዳጋስካርና ከአይቮሪኮስት ጋር ያደረጓቸው ጨዋታዎች ጥንካሬውም ሆነ ክፍተቱ ብቻ የተጠቀሟቸው ተጨዋቾች ጭምር ቡድኑ የሚከተለው እንቅስቃሴና የአጨዋወት ዘይቤ እንዲህ ነው ብሎ በእርግጠኝነት ለመናገር አያስችልም፤” የሚሉ ናቸው፡፡
የምድቡ ማጣሪያ ሦስተኛ ጨዋታ በመጪው ነሐሴ ወር ነው፡፡ ይህ ደግሞ ለአሠልጣኝ አብርሃምና ረዳቶቻቸው ቀደም ሲል የቡድናቸው ክፍተቶች ተብለው የተጠቀሱትን ለማስተካከል እንዲጠቀሙበት ጥሩ አጋጣሚ ይፈጥርላቸዋል የሚሉት እነዚሁ አስተያየት ሰጪዎች የሰሞኑ ድጋፍ ቀጣይነት ይኖረው ዘንድ ሊታሰብበት እንደሚገባ ጭምር ይመክራሉ፡፡
ኢንስትራክተር አብርሃምና ስብስባቸው ከአፍሪካ ዋንጫ ምድብ ማጣሪያ ጎን ለጎን አፍሪካውያን በውስጥ ሊጎቻቸው የሚጫወቱ ተጨዋቾች ብቻ ከሚሳተፉበት የአፍሪካ አገሮች ዋንጫ (ቻን) ውጪ የሆኑት በምሥራቅ አፍሪካዊቷ ሩዋንዳ ተሸንፈው መሆኑ ይታወሳል፡፡ አሠልጣኙ ለቡድናቸው ሽንፈት ምክንያት ብለው በወቅቱ ያስቀመጡት፣ ከያዟቸው ተጨዋቾች ዘጠና በመቶ ወጣቶች እንደመሆናቸው ኢንተርናሽናል የጨዋታ ልምድ አስፈላጊነትን ነው፡፡
አሠልጣኙ ከቻን ማጣሪያ ውጪ ከሆኑ በኋላ ለ2021 የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ የተጠቀሙባቸው ተጨዋቾች በግብፅ ሊግ እየተጫወተ ከሚገኘው ሽመልስ በቀለ ውጪ ቀሪዎቹ በብሔራዊ ቡድን ተሳትፎም ሆነ በዕድሜ በአብዛኛው በወጣት ደረጃ የሚታዩ ናቸው፡፡ ቡድኑ ምንም እንኳ በምድብ ማጣሪያው የመጀመሪያ ጨዋታ ሽንፈት ቢገጥመውም፣ በሁለተኛው ጨዋታ ያውም በአይቮሪኮስት ላይ ያስመዘገበው ውጤትና አሠልጣኙ በልጆቹ የወሰዱት ቁርጠኝነት ሊያስመሰግናቸው ይገባል የሚሉ አልጠፉም፡፡
ዋና አሠልጣኙ የቡድናቸው ውጤታማነት ቀጣይነት የሚኖረው፣ በአገሪቱ ሊጎች የሚጫወቱ ተጨዋቾች ተሳትፎ እንደተጠበቀ ሆኖ በውጪ የሚጫወቱ ፕሮፌሽናሎችን መጠቀም ግድ እንደሚል ተናግረዋል፡፡ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ በዚህ ረገድ የሚኖረውን ሒደት በአፋጣኝ ማሟላት እንደሚጠበቅበትም እየተነገረ ይገኛል፡፡
ድሉን ተከትሎ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ባለፈው ረቡዕ በስካይ ላይት ሆቴል ለልዑካን ቡድኑ በአጠቃላይ 800,000 ብር ሸልሟል፡፡ ሽልማቱ ለዋና አሠልጣኙ አብርሃም 30,000 ብር፣ ለቡድኑ ቋሚና ተቀይረው ለተጫወቱ 14 ተጨዋቾችና ረዳት አሠልጣኞች 25,000 ብር እንዲሁም የቡድኑን ሹፌር ጨምሮ ለተቀሩት ተጨዋቾችና ልዑካን አባላቱ ለእያንዳንዳቸው 20,000 ብር መሆኑ ታውቋል፡፡