Monday, December 4, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ለዘጠነኛው ዓለም አቀፍ የጥራጥሬና ቅባት እህሎች ኮንፍረንስ ከ350 በላይ ተሳታፊዎች መመዝገባቸው ተገለጸ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ኅዳር 19 እና 20 ቀን 2012 ዓ.ም. እንደሚካሄድ በሚጠበቀው ዘጠነኛው ዓለም አቀፍ የጥራጥሬና ቅባት እህሎች ኮንፍረንስ ከ350 በላይ ተሳታፊዎች እንደተመዘገቡ ተገለጸ፡፡ ይህ የተገለጸው ዓርብ ኅዳር 12 ቀን 2012 ዓ.ም. በንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ቢሮ በተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ነው፡፡

ኮንፍረንሱ የተዘጋጀው የኢትዮጵያ ጥራጥሬ፣ ቅባት እህሎችና ቅመማ ቅመም አዘጋጅቶ ላኪዎች ማኅበር ከንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ነው፡፡

የኢትዮጵያ ጥራጥሬ፣ ቅባት እህሎችና ቅመማ ቅመም ላኪዎች ማኅበር የቦርድ ፕሬዚዳንት አቶ ኃይለ በርሄ እንደገለጹት፣ እስካሁን በጠቅላላው 360 ተሳታፊዎች ተመዝግበዋል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ከ20 የተለያዩ አገሮች (ቻይና፣ ህንድ፣ የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ፣ ፓኪስታን፣ ሱዳን፣ ናይጄሪያ፣ ሲውዘርላንድ፣ እስራኤል የመሳሰሉት) የተመዘገቡ 110 ተሳታፊዎች ሲገኙበት፣ 250 የእርሻ ግብዓትና ማሽነሪ አቅራቢዎችም እንደሚሳተፉ ይጠበቃል ተብሏል፡፡

ዓለም አቀፍ ገዥዎችን፣ የአገሪቱን የዘርፍ ምርት ላኪዎችን፣ የእርሻ ምርት ግብዓት አቅራቢዎችን፣ ከፍተኛ የመንግሥት ተቋማትና የተለያዩ አገልግሎት ሰጪዎችን በአንድ መድረክ በማገናኘት የንግድና የሥራ ትስስርን መፍጠር፣ የዘርፉንና የማኅበሩን የሥራ እንቅስቃሴ ማስተዋወቅ፣ ቢዝነስ ግንኙነቱን ማጠናከርና ከአምራች አገሮች ጋር የልምድ ልውውጥ ማድረግ የኮንፍረንሱ ዋና ዓላማዎች መሆናቸውን አቶ ኃይለ በርሄ ገልጸዋል፡፡

 ጥራጥሬና የቅባት እህሎች ከቡና ቀጥሎ ከፍተኛ ግብይት እንደሚፈጽምባቸው በማውሳት የዶላር ምንዛሪ ከማምጣት አንፃር ኮንፍረንሱ ዓይነተኛ ሚና እንዳለው ገልጸዋል፡፡

ለዘጠነኛ ጊዜ የሚካሄደው ኮንፍረንስ ‹‹ስትራቴጂያዊ የቢዝነስ ግንኙነትን ማበልፀግ›› በሚል መሪ ቃል የሚካሄድ ሲሆን፣ የሚቀጥለው ዓመት የሰሊጥና የፍራፍሬ የግብይት ሒደት፣ አቅርቦት እንዲሁም ፍላጎት ምን ይመስላል በሚለው ላይና ምን ዓይነት የግብይት ስትራቴጂ መከተል አለብን በሚለው ላይ አቅጣጫ የሚያሳይ መሆኑን አቶ አሰፉ ሙሉጌታ በንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የውጭ ንግድ ማስፋፊያ ዳይሬክቶሬት ጄኔራል ዳይሬክተር ገልጸዋል፡፡

አቶ አሰፋ በቅባት እህሎችና ጥራጥሬው የአፈጻጸም ሁኔታ ላይም ገለጻ ሰጥተዋል፡፡ እሳቸው እንዳሉት በ2011 ዓ.ም. በቅባት እህሎች ላይ አነስተኛ አፈጻጸም ታይቷል፡፡ በ2011 ዓ.ም. 42 ሺሕ በላይ ቶን ለመላክ ታቅዶ የተሳካው 260 ሺሕ ቶን ብቻ መሆኑንና የዕቅዱ 61 በመቶ ብቻ መሳካቱን ገልጸዋል፡፡

የአምናውን አፈጻጸም ከ2010 ዓ.ም. ጋር ሲያነፃፅሩት ከ20 በመቶ በላይ ቅናሽ የነበረበት እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ይህንንም በዋጋ ሲገልጹት 503 ሚሊዮን ዶላር ታቅዶ የተገኘው 388 ሚሊዮን ዶላር እንደሆነ፣ ይኼም የዕቅዱን 77 በመቶ ያሳካ መሆኑንና ከታቀደው ሰባት በመቶ ያነሰ አፈጻጸም ማሳየቱን አውስተዋል፡፡

የጥራጥሬ ሰብሎች ላይ ከዕቅዱ አኳያ የተሻለ አፈጻጸም በ2011 ዓ.ም. መታየቱን የገለጹት አቶ አሰፋ፣ 486 ሺሕ ቶን ለማከናወን ታቅዶ 458 ሺሕ ቶን መከናወኑና የዕቅዱን 94 በመቶ ማሳካቱን ገልጸዋል፡፡ በዋጋ ደረጃ ሲገለጽ 316 ሚሊዮን ዶላር ለማስገባት ታቅዶ፣ 265 ሚሊዮን ዶላር መገኘቱንና ይሄም የዕቅዱን 83.9 በመቶ መከናወኑ ተመልክቷል ብለዋል፡፡

አቶ አሰፋ የ2012 በጀት ዓመት ዕቅድን ሲያብራሩ፣ ‹‹ከቅባት እህሎች 353‚676 ቶን በመላክ 471 ሚሊዮን ዶላር በላይ ለማግኘት ያቀድን ሲሆን፣ ከጥራጥሬም እንዲሁ ከ500 ሺሕ በላይ በመላክ ወደ 315 ሚሊዮን ዶላር ለማግኘት አቅደናል፤›› ብለዋል፡፡

ይኼንንም ለማሳካትና በቀጣይም ለሌሎች ሥራዎች መሠረት ለመጣል ይኼ ኮንፍረንስ ይረዳናል ብለው እንደሚያስቡም አክለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች