Monday, May 20, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የበርበራ ወደብ የመጀመሪያ ማስፋፊያ ግንባታ በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ እየተከናወነ እንደሚገኝ ተገለጸ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ተጨማሪ 270 ሚሊዮን ዶላር የሚጠይቁ የኮንቴይነር ማቆያ ግንባታዎች ይካሄዳሉ

ከአንድ ወራት በፊት ማስፋፊያው በይፋ የተጀመረውና በ442 ሚሊዮን ዶላር በጀት የሚገነባው የበርበራ ወደብ ማስፋፊያ ግንባታ፣ በታቀደለት የጊዜ ሰሌዳ መሠረት እየተካሄደ እንደሚገኝ የሶማሌላንድ ወደብ ባለሥልጣን አስታወቀ፡፡

በሁለት ምዕራፎች ተከፍሎ በመጀመሪያው ምዕራፍ በ100 ሚሊዮን ዶላር እየተካሄደ የሚገኘው የማስፋፊያ ግንባታ፣ በአሁኑ ወቅት መድረስ በሚጠበቅበት የግንባታ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ የባለሥልጣኑ ዋና ኃላፊ ሚስተር ሰዒድ ሐሳን አብዱላሒ አስታውቀዋል፡፡ የማስፋፊያ ግንባታው እስከ 500 ሜትር ርዝመት ያላቸውን ሦስት ትላልቅ መርከቦች በአንድ ጊዜ ለማስተናገድ የሚያስችለው አቅም እንደሚኖረው ይጠበቃል፡፡ በአሁኑ ወቅት ከ600 ሜትር በላይ ያለውን የወደቡ የመርከብ ማስተናገጃ (ደርዝ ወይም ኪ) ላይ ተጨማሪ የ800 ሜትር ግንባታ በማካሄድ በአንድ ጊዜ ሦስት ትልልቅ ዓለም አቀፍ መርከቦችን የማስተናገድ አቅም ይኖረዋል ብለዋል፡፡

በመሆኑም በመጀመሪያው ምዕራፍ ግንባታ የወደቡን የመርከብ ማስተናገጃ ወይም ደርዝ በ250 ሺሕ ካሬ ሜትር እንደሚያሰፋው ተገልጿል፡፡ በአሁኑ ወቅት ያለው የወደቡ አቅም 150 ሺሕ ባለ 20 ጫማ ኮንቴይነሮችን የሚያስተናገድ ሲሆን፣  ወደ 450 ሺሕ ባለ 20 እና ባለ 40 ጫማ ጥምር ኮንቴይነሮች ወደ ማስተናገዱ ያሳድገዋል ተብሏል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በአሁኑ ወቅት ያለውን 25 ሺሕ ቶን ሸቀጥ በተለይም የምግብ ሸቀጦችን የማስተናገድ አቅሙን፣ ወደ 40 ሺሕ ቶን እንደሚያሳድገውም ይጠበቃል፡፡

ይሁን እንጂ ከመጀመሪያው የ400 ሜትር የመርከብ ማስተናገጃ የወደብ ግንባታ በተጨማሪ ሁለተኛው ማስፋፊያ የሚካሄደው የመጀመሪያው የወደብ ማስፋፊያ 70 በመቶ ጥቅም ላይ ሲውልና ውጤቱ ሲረጋገጥ እንደሆነ ያብራሩት ኃላፊው፣ ለሁለተኛው ምዕራፍ የ400 ሜትር ማስፋፊያና የኮንቴይነር ማስተናገጃ ተርሚናል ግንባታ ብሎም በወደቡ ለሚካሄዱ አዳዲስ የአገልግሎት ማዕከላትና መሰል ግንባታዎች 270 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ ተጨማሪ ኢንቨስትመንት እንደሚያስፈልግ ሚስተር አብዱላሒ ገልጸዋል፡፡

በበርበራ ወደብ እንዲሁም በበርበራ ኮሪደር እየተካሄዱ ከሚገኙ ሥራዎች መካከል የመንገድ ግንባታና የኤርፖርት መልሶ ግንባታ ሥራዎች ይገኙበታል፡፡ በአሁኑ ወቅት በ110 ሚሊዮን ዶላር ከበርበራ ወደብ እስከ ኢትዮጵያ ድንበር ቶጎ ውጫሌ የሚዘረጋ መንገድ ግንባታ እየተካሄደ እንደሚገኝ ተዘግቧል፡፡ ከመንገዱ ባሻገር ከዓመታት በፊት በሩስያውያን አማካይነት በበርበራ የተገነባው ወታደራዊ የአውሮፕላን ማረፊያ፣ በተባበሩት ዓረብ መንግሥታት የጦር ሰፈር ከመሆን በተጨማሪ የንግድና የመንገደኞች አውሮፕላኖችም እንዲገለገሉበት የሚያስችል ግንባታ እየተካሄደበት እንደሚገኝ ተብራርቷል፡፡ 

የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ ኩባንያ የሆነው ዲፒ ወርልድ የበርበራ ወደብን የማስተዳደር ኃላፊነትን ከሶማሌላንድ መንግሥት ከተረከበ በኋላ ብዙም ሳይቆይ በተደረገው የሦስትዮሽ ድርድርና ስምምነት መሠረት፣ ኢትዮጵያ የ19 በመቶ ድርሻ ከወደቡ በመግዛት መቀላቀሏ ይታወሳል፡፡ ዲፒ ወርልድ በበኩሉ የ51 በመቶ ሲይዝ፣ የሶማሌላንድ መንግሥት ቀሪውን 30 በመቶ ድርሻ በመያዝ ወደቡን የማስፋፋት ሥራዎች እንደሚሠሩ አስታውቀው ነበር፡፡ ኢትዮጵያ የ110 ሚሊዮን ዶላር ኢንቨስትመንት በማካሄድ የወደብ ተጠቃሚነት ዕድሏን እንደምታስፋፋ ይጠበቃል፡፡

በአሁኑ ወቅት ለኢትዮጵያ አማራጭ የወደብ አገልግሎት መስጠት እንደሚችሉ የሚታመንባቸው የኬንያው ላሙ፣ የሱዳኑ ፖርት ሱዳን ከጂቡቲ ወደብና ከሶማሌላንድ በርበራ ወደብ ጋር እየተቀናቀኑ ይገኛሉ፡፡ ምንም እንኳ በአሁኑ ወቅት የበርበራ ወደብ ካለፈው ዓመት ጀምሮ የሚያስተናግዳቸው የኮንቴይነር ጭነቶች ብዛት በ40 በመቶ ጭማሪ ቢያሳዩም፣ አብዛኛውን ጭነት በወደቡ በኩል የሚያስተናግደው የዓለም የምግብ ፕሮግራም መሆኑ ታውቋል፡፡ የግል አስመጪዎች ብዙም እየተቀጠሙበት ባይሆንም የተወሰኑ ወደ ድንበር አቅራቢያ ድረስ ዕቃዎቻቸውን በማምጣት እስከ ጅግጅጋና ድሬዳዋ የሚያዳርሱ አስመጪዎች በተወሰነ ደረጃ እየተገለገሉበት እንደመጡ ተብራርቷል፡፡ ከኢትዮጵያ በበርበራ ወደብ በኩል ወደ ሌሎች አገሮች የሚላክ ሸቀጥ ግን የሁለቱን መንግሥታት ብቻም ሳይሆን፣ ላኪዎች የሚያገኙትን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ መረጃ እንደሚፈልጉ ይታመናል፡፡

ይህም ይባል እንጂ ከአዲስ አበባ እስከ በርበራ ወደብ ያለው ርቀትና ከአዲስ አበባ እስከ ጂቡቲ ያለው የመንገድ ርቀት እኩል ነው የሚሉት የበርበራ ወደብ ኃላፊ፣ እንደውም ከበርበራ እስከ ኢትዮጵያ ድንበር ያለው መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥም ሜዳማ መሆኑ ለተሽከርካሪዎች ተመራጭ እንደሚያርገው ይተማመናሉ፡፡

አብዛኛው የኢትዮጵያ ነጋዴ ወደ በርበራ ወደብ ያልመጣው አንድም ተገቢውን መረጃ የሚሰጠው ስላላገኘ እንደሆነ ገልጸው፣ የወደብ ማስፋፊያውና የኮሪደሩ የመንገድ ግንባታ አለመጠናቀቅም ሌላው ምክንያት እንደሚሆን አስታውቀዋል፡፡ ከወራት በኋላ የመንገዱም ሆነ የወደብ ማስፋፊያ ግንባታው ስለሚጠናቀቅ ይህንኑ ለማሳወቅ የኢትዮጵያ አስመጪና ላኪዎች በአዲስ አበባና በሌሎችም ከተሞች በመዘዋወር የሚያስተዋውቅ ልዑክ እንደሚንቀሳቀስ ገልጸዋል፡፡ 

 ከእነዚህ ወደቦች በተጨማሪ የአሰብ ወደብም ተፎካካሪ ሆኖ መምጣቱ የኢትዮጵያን የባህር በር ተጠቃሚነት አማራጭ እንዳስፋፋው ሲገለጽ ቢቆይም፣ አገሪቱን ፈታኝ የጂኦፖለቲካዊ ፍጥጫ ውስጥ እንደከተታት የሚገልጹ አሉ፡፡ እስካሁን ከ95 በመቶ ያላነሰውን የኢትዮጵያን ወጪና ገቢ ንግድ የምታስተናግደው ጂቡቲ፣ ይኸው ድርሻ እንደሚኖራት በመተማመን አዳዲስ ወደቦችን እንደገነባች ትገልጻለች፡፡ አብዛኞቹም ከቻይና መንግሥት በብድር የተገኙና አንዳንዶቹም በኢትዮጵያ መንግሥት ዋስትና ጭምር የተገነቡ ናቸው፡፡ ይሁን እንጂ ከኢትዮጵያ ወጪና ገቢ ንግድ ውስጥ 30 በመቶውን የበርበራ ወደብ ለማስተናገድ በሚችልበት አቅም እየተገነባ እንደሚገኝ ባለሥልጣናቱ ሲገልጹ፣ የተቀረው መጠን ለጂቡቲ እንደሚቀርላት ይታሰብ ነበር፡፡ ሆኖም ሳይታሰብ ዕርቅ ያወረደችው ኤርትራ ይህንን የሁለቱን ወደቦች ድርሻ በማዛባት፣ ፖለቲካዊ ሚዛኑ እንዳይናጋ ሥጋት አሳድሯል፡፡

በብርሃኑ ፈቃደ፣ ሐርጌሳ፣ ሶማሌላንድ

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች