Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናበጄኔራል ሰዓረ መኮንን ግድያ የተጠረጠረውን የግል ጠባቂ ጨምሮ በ13 ተጠርጣሪዎች ላይ ክስ...

በጄኔራል ሰዓረ መኮንን ግድያ የተጠረጠረውን የግል ጠባቂ ጨምሮ በ13 ተጠርጣሪዎች ላይ ክስ ተመሠረተ

ቀን:

የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታ ማዦር ሹም ጄኔራል ሰዓረ መኮንንና ጡረተኛውን ሜጀር ጄኔራል ገዛዒ አበራን በመግደል የተጠረጠረው የጠቅላይ ኤታ ማዦር ሹሙ የግል ጠባቂ አሥር አለቃ መሳፍንት ጥጋቡን ጨምሮ፣ በ13 ተጠርጣሪዎች ላይ ክስ ተመሠረተ፡፡

የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ብርሃኑ ፀጋዬ ኅዳር 4 ቀን 2012 ዓ.ም. በሰጡት መግለጫ ባሳወቁት መሠረት ሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ.ም. በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ፕሬዚዳንት፣ ልዩ አማካሪና ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ፣ እንዲሁም የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታ ማዦር ሹምንና ጓደኛቸውን ጨምሮ 15 ሰዎችን በመግደል የተጠረጠሩና ለመክሰስ በቂ መነሻ ማስረጃ ተገኝቶባቸዋል ከተባሉት 68 ተጠርጣሪዎች ውስጥ በአዲስ አበባ በፌዴራል ዓቃቤ ሕግ አማካይነት ክስ የተመሠረተባቸው 13 ግለሰቦች፣ ዓርብ ኅዳር 12 ቀን 2012 ዓ.ም. ፍርድ ቤት ቀርበው የተመሠረተባቸው ክስ ተነቦላቸዋል፡፡

ተከሳሾቹ የጄኔራል ሰዓረ መኮንን የግል ጠባቂ አሥር አለቃ መሳፍንት ጥጋቡ፣ አቶ አስጠራው ከበደ፣ አቶ ሲሳይ አልታሰብ፣ አቶ አበበ ፈንታ፣ አቶ አስቻለው ወርቁ፣ አቶ ተሾመ መለሶ፣ አቶ ዓለምኔ ሙሌ፣ አቶ ከድር ሰኢድ፣ አቶ አየለ አስማረ፣ አቶ አማረ ካሴ፣ አቶ ፋንታሁን ሞላ፣ የአብን ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልና የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ክርስቲያን ታደለና አቶ በለጠ ካሳ ናቸው፡፡  

በተከሳሾቹ ላይ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አንደኛ ፀረ ሽብር ወንጀል ችሎት ክስ ያቀረበው ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ፣ ተከሳሾቹ የወንጀል ሕግ ቁጥር 32 (1ሀ እና ለ)፣ 38 እና 238 (2) ድንጋጌን በመተላለፍ የወንጀል ድርጊት መፈጸማቸውን ገልጾ የክስ ዝርዝር አቅርቧል፡፡

ተከሳሾቹ በኃይል፣ በአድማና በሕገወጥ መንገድ መፈንቅለ መንግሥት ማካሄድ የሚያስችል አደረጃጀት መፍጠራቸውን፣ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን በኃይል ለመለወጥም ከሚያዝያ ወር 2011 ዓ.ም. ጀምሮ የአማራ ክልል መንግሥት ሥራ አመራር ኢንስቲትዩት ውስጥ ተልዕኳቸውን የሚፈጽሙበትን ዘዴና ሁኔታ፣ ‹‹የፀጥታ ክትትል ኦፊሰር ሥልጠና›› በሚል ሽፋን አባላት መመልመላቸውን፣ መንግሥትን በሥውር የሥነ ልቦና ጦርነትና በኢኮኖሚ ጦርነት በማካሄድ አደረጃጀት ሲፈጥሩ መቆየታቸውን ዓቃቤ ሕግ በክሱ አስረድቷል፡፡ መፈንቅለ መንግሥት ማካሄድ የሚያስችላቸውን አደረጃጀት ከፈጠሩ በኋላ፣ በአማራ ክልል በሚገኙ ዞኖችና ከክልሉ ውጪ በኦሮሚያ፣ በአዲስ አበባና በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልሎች ውስጥ አባሎቻቸውን መመደባቸውንም በክሱ ጠቁሟል፡፡

የተመደቡት አባላት በተመደቡበት አካባቢ የታጠቁና ዓላማውን በመደገፍ ሊንቀሳቀሱ የሚችሉ አካላትን በመመልመል በግልና በቡድን የማኅበራዊ ሚዲያዎች በመጠቀም፣ ሕዝቡ በክልልም ሆነ በፌዴራል አመራሮች ላይ አመኔታ እንዲያጣ በማድረግ ሥርዓቱ በኃይል እንዲቀየር ሲንቀሳቀሱ እንደነበር ዓቃቤ ሕግ በክሱ ገልጿል፡፡

በአማራ ክልል አመራሮች ላይ ጥቃት ሲፈጸም ከፌዴራል ተቋማት የመከላካያ ሠራዊት አመራሮችን በመግደል ሠራዊቱን መበተንና የሚፈጸመውን ጥቃት መከላከል ስለማይችሉ፣ በቀላሉ ሥልጣን ለመቆጣጠር ይቻላል ብለው ዝግጅት ሲያደርጉ እንደነበርም በክሱ ተገልጿል፡፡

በመሆኑም ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን በኃይል ለማፍረስ በአማራ ክልል የፀጥታና ደኅንነት ኃላፊ ብርጋዴር ጄኔራል አሳምነው ጽጌ በመመራት ሰኔ 15 ቀን 2012 ዓ.ም. የክልሉን ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አምባቸው መኮንን (ዶ/ር)፣ የክልሉን ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ምግባሩ ከበደ፣ የክልሉን ሕዝብ አደረጃጀትና የፕሬዚዳንቱ አማካሪ አቶ ዕዘዝ ዋሴን፣ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ደግሞ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታ ማዦር ሹም ጄኔራል ሰዓረ መኮንንና ሜጀር ጄኔራል ገዛዒ አበራን በመግደል መሳተፋቸውን ክሱ ይገልጻል፡፡ በክልሉ ፖሊስ ኮሚሽንና የተለያዩ አመራሮች መኖሪያ ቤቶችና በአዴፓ ጽሕፈት ቤት ላይ ጥቃት በመፈጸም ለመቆጣጠር ጥረት ማድረጋቸውንም አክሏል፡፡ ተከሳሾቹ በተለያዩ የማኅበራዊ ትስስር ገጾችና ባደራጁት ኃይል ጥቃቱ እንዲፈጸም በመንቀሳቀስ ድርጊት ላይ መካፈላቸውን ጠቁሟል፡፡

የጄኔራል ሰዓረ መኮንን ጠባቂ አሥር አለቃ መሳፍንት ቀኑና ወሩ ባልታወቀ በሚያዝያ ወር 2011 ዓ.ም. ጽጌ በተባለ ግለሰብ አማካይነት ከብርጋዴር ጄኔራል አሳምነው ጋር መገናኘቱን የሚገልጸው የዓቃቤ ሕግ ክስ፣ ‹‹ጄኔራል ሰዓረ መኮንን የአማራ ሕዝብን እያስገደለ ነው፡፡ ለአማራ ሕዝብ የማይጠቅሙ አመራሮችን በማስወገድ ክልሉን እንቆጣጠራለን፡፡ ስለዚህ ጄኔራል ሰዓረን መግደል አለብህ፡፡ ሌላም ደፋርና ቆራጥ ሰው ፈልገህ ታገናኘኛለህ፤›› በማለት ተልዕኮ እንደተሰጠው ዓቃቤ ሕግ በክሱ አስረድቷል፡፡

ጠባቂውም ተልዕኮውን በመቀበል ለዓቃቤ ሕግ አንደኛ ምስክር ሆኖ የተቆጠረን ግለሰብ በማግኘት፣ ‹‹ብርጋዴር ጄኔራል አሳምነው ጄኔራል ሰዓረን እንድገድል ተልዕኮ ሰጥቶኛል፡፡ አንተ ደግሞ ምክትል ጠቅላይ ኤታ ማዦር ሹሙን ጄኔራል ብርሃኑ ጁላን ትገድላለህ፣ እነዚህ ጄኔራሎች፣ የክልሉና ፌዴራል የተለያዩ አመራሮች የአማራን ሕዝብ እየጎዱት ነው፡፡ አመራሮቹ ላይ ዕርምጃ ሲወሰድ ሠራዊቱ እንዳይከላከል ጠቅላይ ኤታ ማዦር ሹሞቹን ገድሎ ሠራዊቱን መበተን አለብን፤›› በማለት ማሳመኑን ክሱ ይገልጻል፡፡ ምስክር ሆኖ የተቆጠረው ግለሰብም በሐሳቡ በመስማማት በግንቦት ወር 2011 ዓ.ም. ወደ ጎንደር በመሄድ፣ ከብርጋዴር ጄኔራል አሳምነው ጋር ተገናኝተው ተልዕኮ እንዲቀበል ማድረጉን ዓቃቤ ሕግ በክሱ ገልጿል፡፡

በባህር ዳር አመራሮች ላይ ዕርምጃ እንደተወሰደ ለአሥር አለቃ መሳፍንት እንደሚነገረውና በጄኔራል ሰዓረ ላይ ዕርምጃ ሲወሰድ ሁኔታውን ለማየት ሲሰባሰቡ ጄኔራል ብርሃኑ ጁላን እንዲገድል ተልዕኮ ቢሰጠውም፣ ጄኔራል ሰዓረ መኮንንና ጓደኛቸውን የገደለው አሥር አለቃ መሳፍንት በቁጥጥር ሥር በመዋሉና ለምስክሩም ባለመንገሩ ተልዕኮው መክሸፉን ክሱ ይገልጻል፡፡ ሌሎቹም ተከሳሾች ከሕግ ውጪ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ለማፍረስ በማሰብ ከአማራ ክልል መደበኛ የፀጥታ መዋቅር ውጪ የአማራ የስለላና ደኅንነት ድርጅት (አሳድ) የሚል ተቋም በመገንባት፣ ጠላት ተብለው የተፈረጁ የፖለቲካ ኃይሎች (ሕወሓትና ኦዴፓ)ን ለመሰለልና መንግሥትን ለማዳከም የኃይል ዕርምጃ ለመውሰድ ሥልጠናና የተግባር ልምምድ በመውሰድ ተልዕኮ ተቀብለው ሲንቀሳቀሱ እንደነበር ዓቃቤ ሕግ በክሱ ገልጿል፡፡

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ሥራ አስፈጻሚ አባልና የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ክርስቲያን ታደለም ሕገ መንግሥቱን ለመናድና በሕዝብ ላይ ሁከት ለመፍጠር በማሰብ በባህር ዳር፣ በደብረ ታቦር፣ በጎንደርና በወልዲያ ከአካባቢዎች ሲንቀሳቀስ እንደነበር ዓቃቤ ሕግ በክሱ ጠቅሷል፡፡ በተጠቀሱት አካባቢ የሚገኙትን ተወካዮች በማግኘት፣ ‹‹በአማራ ክልል አመፅና ብጥብጥ መነሳት አለበት፡፡ ሱዳን የተፈጠረውን ዓይነት ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት በኢትዮጵያም መካሄድ አለበት፡፡ ይህ እንዲሆን መጀመርያ የክልሉ መዋቅርን ማፍረስ አለብን፡፡ በተለይ አዴፓ ኃላፊዎችን፣ የደኅንነትና የፀጥታ መዋቅሩን ልንመታ ይገባል፡፡ የገንዘብና የትጥቅ ድጋፍ ከውጭም ከውስጥም ማግኘት አለብን፡፡ ከባለሀብቶችና ከውጭ አካላት ጋር ቀጥታ ትስስር በመፍጠር የህቡዕ አደረጃጀቱን በትጥቅ ማጠናከር ይገባል፡፡ ከፀጥታው ትጥቅ እንቀማ፡፡ ወጣቱን ለአመፅ ማነሳሳትና ማዘጋጀት አለብን፡፡ ህቡዕ አደረጃጀትን በመፍጠር በዩኒቨርሲቲዎች አመፅ እንዲነሳ መሥራት አለብን፡፡ በክልሉ ሌላ ተፎካካሪ ፓርቲ መንቀሳቀስ የለበትም፤›› በማለት ተልዕኮ መስጠቱን ዓቃቤ ሕግ በክሱ በዝርዝር አስረድቷል፡፡

ተከሳሾቹ በአጠቃላይ ከሚያዝያ ወር 2011 ዓ.ም. ጀምሮ፣ ‹‹የኮሚሽን ጋጋታ የወልቃይትን ጥያቄ አይመልስም፡፡ በኃይል መሬቱን ማስመለስ አለብን፡፡ የአዴፓን አመራሮች ማመን አያስፈልግም፡፡ ሕዝቡ መዘጋጀት አለበት፤›› በማለትና በቡድን በመደራጀት ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን በኃይል ለማፍስ ሲንቀሳቀሱ እንደነበር ዓቃቤ ሕግ በክሱ አብራርቷል፡፡ ተከሳሾቹ በወንጀሉ በቀጥታ በመሳተፍ፣ የተፈጸመው ወንጀል ውጤት እንዲያገኝና ሕዝቡም ደግፎ እንዲቆም በመቀስቀስና በድርጊቱም የ17 ሰዎች ሕይወት ማለፉን፣ 20 ሰዎች የአካል ጉዳት እንደ ደረሰባቸውና በርካታ ንብረት እንዲወድም በማድረጋቸው ሕገ መንግሥትና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት ላይ የሚደረግ ወንጀል ክስ እንዲመሠረትባቸው ዓቃቤ ሕግ በክሱ አብራርቶ ገልጿል፡፡ ተከሳሾቹ የተጠቀሰባቸውን የወንጀል ሕግና ድርጊት መከላከል ሳይችሉ ቀርተው ‹‹ወንጀለኛ›› የሚባሉ ከሆነ፣ ከዕድሜ ልክ እስከ ሞት ድረስ ሊያስቀጣ የሚችል መሆኑን የወንጀል ሕግ ቁጥር 238 (2) ድንጋጌ ያስረዳል፡፡

ተከሳሾቹ ክሱ ተነቦላቸው ማንነታቸው ከተረጋገጠ በኋላ በጠበቃ ስለመወከላቸው ፍርድ ቤቱ ጠይቋል፡፡ ጠቆር ያለ ግራጫ ቱታ ለብሶና ነጠላ ጫማ አድርጎ በልዩ ኮማንዶዎችና የፌዴራል ፖሊስ ተከቦ የቀረበው አሥር አለቃ መሳፍንት፣ የግራ ዓይኑ ጉዳት ደርሶበታል፡፡ ‹‹አዎ፣ እሺ›› ከማለት ያለፈ ፈታ ብሎ መናገር አይችልም፡፡ ለ12 ተከሳሾች የቆሙት ሦስት ጠበቆች ለእሱም የሕግ አገልግሎት ሊሰጡት ፈቃደኛ መሆናቸውን በመግለጻቸው፣ ፍርድ ቤቱ መስማማት አለመስማማቱን ጠይቆት ቢቆሙለት እንደሚስማማ ገልጿል፡፡ ጠበቆቹም ለፍርድ ቤቱ ተከሳሹ የት እንደታሰረ ስለማያውቁ፣ ለመጠየቅና የተሟላ የሕግ ድጋፍ እንዲያደርጉለት የታሰረበት ቦታ የት እንደሆነ እንዲገለጽላቸው ትዕዛዝ እንዲሰጥላቸው አመልክተዋል፡፡

ሌሎቹ ተከሳሾች ደግሞ በብርበራ ወቅት የተወሰዱባቸው የተለያዩ ንብረቶች መኖራቸውን ጠቁመው፣ አሁን ፖሊስ ምርመራውን ጨርሶ ዓቃቤ ሕግ ክስ በመመሥረቱ ንብረቶቻቸው ለቤተሰቦቻቸው እንዲመለሱላቸው ጠይቀዋል፡፡ አያያዛቸውን በሚመለከትም ሥጋት እንዳለባቸው ተናግረው፣ ቀጥሎ የሚቆዩት በማረሚያ ቤት በመሆኑና እዚያም ሥጋት ስላላቸው ፍርድ ቤቱ ጥብቅ ትዕዛዝ እንዲሰጥላቸው ጠይቀዋል፡፡

ፍርድ ቤቱም የግራ ቀኙን ትዕዛዝ ከሰማ በኋላ ንብረትን (በኤግዚቢት የተያዘውን) በሚመለከት አቤቱታቸውን በጽሑፍ እንዲያቀርቡ፣ ማረሚያ ቤትም ተከሳሾችን በጥብቅ ክትትል በአግባቡ እንዲጠበቅ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡ ስለአሥር አለቃ መሳፍንት ግን ምንም ያለው ነገር የለም፡፡ የክስ መቃወሚያ ለመቀበል ለታኅሳስ 1 ቀን 2012 ዓ.ም. ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...