Sunday, March 26, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየቀድሞ የጤና ጥበቃ ሚኒስትርን ጨምሮ ታዋቂ የጨው ነጋዴዎችና ኃላፊዎች ተከሰሱ

የቀድሞ የጤና ጥበቃ ሚኒስትርን ጨምሮ ታዋቂ የጨው ነጋዴዎችና ኃላፊዎች ተከሰሱ

ቀን:

የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ለሁለተኛ ጊዜ ካቢኔያቸውን ሲያቋቁሙ የጤና ጥበቃ ሚኒስትር አድርገው ሾመዋቸው የነበሩት ይፍሩ ብርሃን (ፕሮፌሰር) በሌሉበት ጨምሮ፣ ታዋቂ የጨው ነጋዴዎች ማኅበር ኃላፊዎች የሙስና ወንጀል ክስ ተመሠረተባቸው፡፡

ይፍሩ (ፕሮፌሰር) የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ሆነው በሚሠሩበት ወቅት የማይገባ ጥቅም ለማግኘት ወይም ለማስገኘት፣ እንዲሁም በሌላው ላይ ጉዳት እንዲደርስ በማሰብ ጥራቱን ያላሟላና በሕዝብ ጤና ላይ ጉዳት የሚያደርስ ጨው ለገበያ እንዲሠራጭ መፍቀዳቸውን፣ ወይም ትዕዛዝ መስጠታቸውን ዓቃቤ ሕግ የመሠረተው ክስ ያስረዳል፡፡

የኢትዮጵያ የምግብ፣ መድኃኒት፣ ጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለሥልጣን በሕገወጥ መንገድ የተገኘን የጨው ማቀነባበርና ማምረት ብቃት ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት አዋጁ ቁጥር 661/2002 አንቀጽ 48 እና 49፣ እንዲሁም በመመርያ ቁጥር 5/2004 አንቀጽ 30 እና 34 መሠረት በግልጽ የተሰጠውን ሥልጣንና ኃላፊነት ተጠቅሞ በመስክ ጉብኝት ላይ ቁጥጥር ማድረጉን ክሱ ያብራራል፡፡

በመስክ ጉብኝቱም ያገኘውን ግድፈት መሠረት በማድረግ ለአፋር ጨው ማቀነባበሪያና ማምረቻ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ተሰጥቶት የነበረውን የጨው ማምረት የብቃት ማረጋገጫ ምስክር ወረቀት፣ ከመጋቢት 27 ቀን 2009 ዓ.ም. ጀምሮ የጨው ምርት እንዳያሠራጭ ለጊዜው ማገዱንም ዓቃቤ ሕግ በክሱ ጠቁሟል፡፡

ዕግዱን በሚመለከት የሚቀርብ ቅሬታ ካለ ለባለሥልጣኑ መሥሪያ ቤት በተዘረጋው የቅሬታ አቀራረብ፣ አፈታት ሥርዓትና መመርያ አንቀጽ 34 እና 38 መሠረት በቅሬታ ኮሚቴ ሊታይ እንደሚገባም አክሏል፡፡ ነገር ግን ይፍሩ (ፕሮፌሰሩ) ሚያዝያ 17 ቀን 2009 ዓ.ም. በተጻፈ ደብዳቤ ለአፋር ጨው ማቀነባበሪያና ማምረቻ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር፣ ዕግዱ እንዲነሳና ለሦስት ወራት የዕፎይታ ጊዜ እንዲሰጠው በማድረጋቸው ባለሥልጣኑ የወሰደው ዕርምጃ ተግባራዊ እንዳይሆን፣ ጥራቱን ያልጠበቀና ለጤና ጎጂ የሆነ ጨው ለገበያ እንዲያውል ማድረጋቸውን ክሱ ይገልጻል፡፡  

ይፍሩ (ፕሮፌሰር) ባነሱት ዕግድ ተጠቃሚ መሆናቸው የተገለጸው ደግሞ ታዋቂው የጨው ነጋዴና አከፋፋይ ሐጂ ሰዒድ ያሲን ዓሊ መሆናቸውንም ዓቃቤ ሕግ በክሱ ገልጿል፡፡

ዓቃቤ ሕግ ክሱን የመሠረተው የአፋር ጨው ማምረቻ አክሲዮን ማኅበር የሥራ አመራር ቦርድ አባላት አቶ ሙሉጌታ ሰይድ፣ አቶ ተፈሪ ዘውዱ፣ አቶ ወንዱ አንተ፣ አቶ ዓባይነህ ጥላሁን፣ ሰይድ ኤሮ (ዶ/ር) እና አቶ ናደው ታደሰ የማኅበሩ ሥራ አስኪያጅ አቶ ሀብቱ ሐጎስ፣ ዋና አከፋፋይና ነጋዴ ሐጂ ሰዒድ ያሲን፣ አቶ ይስማሸዋ ሥዩም፣ አቶ ሳድቅ መሐመድ፣ ይፍሩ ብርሃን (ፕሮፌሰር) ያልተያዙ፣ አቶ አማረ አሰፋ ያልተያዙና አቶ አረጋ አስፋው ናቸው፡፡

ሐጂ ሰዒድ፣ አቶ ይስማሸዋና አቶ ሳድቅ ከቦርድ አባላትና ሥራ አስኪያጁ ጋር የማይገባ ግንኙነት በመፍጠር በአክሲዮን ማኅበሩ ጥቅምና መብት ላይ ጉዳት ለማድረስ፣ የማይገባ ጥቅም ለማግኘት ከአክሲዮን ማኅበሩ ጋር በተመሳሳይ ንግድ ለተሰማራው አፋር ጨው ማቀነባበሪያና ማምረቻ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር የማይገባ ጥቅም እንዲያገኝ ማድረጋቸውን የዓቃቤ ሕግ ክስ ያብራራል፡፡

በአፋር ክልል አፍዴራ ወረዳ የሚገኘውንና ከኩባንያው የተከፈለ ካፒታል 83.3 በመቶ የሚሆነው አክሲዮን ድርሻ የመንግሥት የልማት ድርጅት የሆነው የኢትዮጵያ የማዕድን፣ ነዳጅና ባዮፊውል አክሲዮን ማኅበር የሆነውን የአፋር ጨው ማምረቻ አክሲዮን ማኅበር የግል ይዞታ 9,900 ካሬ ሜትር ይዞታ ሥልጣናቸውን ተጠቅመው፣ የአፋር ጨው ማቀነባበሪና ማምረቻ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ፋብሪካ እንዲገነባበት ማድረጋቸውን ክሱ ይገልጻል፡፡ የአፋር ጨው ማምረቻ አክሲዮን ማኅበር የጨው ማቀነባበሪያ ፋብሪካ ለመገንባት ህንድ ከሚገኘው የውጭ ኩባንያ ጋር ቢዋዋልም ተከሳሾቹ የአዋጪነት ጥናት ከተጠናና ዲዛይን ለመሥራት ዝግጅት ሲደረግ ማስቆማቸውንና ይህም የተደረገው ሐጂ ሰዒድን፣ አቶ ይስማሸዋና አቶ ሳድቅ ኃላፊ የሆኑበት የአፋር ጨው ማቀነባበሪያና ማምረቻ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበርን ለመጥቀም መሆኑንም ክሱ ይገልጻል፡፡ ተከሳሾች የአፋር ጨው ማቀነባበሪና ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማምረቻ ማኅበርን ያላግባብ ተጠቃሚ በማድረግ የሙስና ወንጀል መፈጸማቸውንም ጠቁሟል፡፡

አቶ ሀብቱና ሐጂ ሰዒድ በመንግሥት በኩንታል 257.95 ብር ጥሬ ጨው እንዲሸጥ በንግድ ሚኒስቴር ቢወስንም፣ እነሱ ግን ከተመን በታች ኩንታል በ140 ብር ለአቶ ሀብቱ ሐጎስ መሸጣቸውን፣ ሐጂ ሰዒድ ደግሞ ከአቶ ሀብቱ ሐጎስ ጋር በመመሳጠር የመንግሥትን ግብር ጨምሮ ‹‹ሰዒድ ያሲን ቢዝነስ›› በሚባል ድርጅታቸው ስያሜ በመጠቀም 12.9 ሚሊዮን ብር ጉዳት እንዲደርስ ማድረጋቸውን ክሱ ይገልጻል፡፡ በአጠቃላይ ተከሳሾቹ ሥልጣናቸውን ያላግባብ በመጠቀም የሙስና ወንጀል፣ የፀና ፈቃድ ሳይኖራቸው በነዳጅ ንግድ ሥራ ላይ ተሰማርቶ መገኘት ወንጀል፣ የምግብ ደኅንነትና ጥራት አጠባበቅ ወንጀል፣ በወርቅ፣ በጥሬ ገንዘብና በውጭ አገር ገንዘብ በሕገወጥ መነገድ ወንጀል በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ክስ ተመሥርቶባቸዋል፡፡  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለፋይናንስ ዘርፉ ብቃት ያለው የሰው ኃይል የማፍራት የቤት ሥራን የማቃለል ጅማሮ

የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ እያደገ ለመሆኑ ከሚቀርቡ ማስረጃዎች ውስጥ  የግል...

የምድር ባቡርን የሚያነቃቃው የመንግሥት ውሳኔ

በኢትዮጵያ ወደብ አልባነት ላይ የተደመረውን የሎጀስቲክስ ችግር ለመፍታት ግዙፍ...

የፓርላማ አባላት ስለሰላም ስምምነቱ አፈጻጸም ግልጽ መረጃ የለንም አሉ

‹‹ሕወሓትን ለፍረጃ አብቅተውት የነበሩ ጉዳዮች በአብዛኛው መልክ ይዘዋል›› ሬድዋን...