Wednesday, February 28, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናኢትዮጵያ ሶማሌላንድን ገሸሽ ያደረገ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ጀምራለች በማለት ሥጋት እንደገባቸው ባለሥልጣናቱ ገለጹ

ኢትዮጵያ ሶማሌላንድን ገሸሽ ያደረገ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ጀምራለች በማለት ሥጋት እንደገባቸው ባለሥልጣናቱ ገለጹ

ቀን:

በሶማሌላንድ የኢትዮጵያ ተሰናባች ቆንስላ ጄነራልን የሚተካ ተሿሚ አልተመደበም

የድንበር ደኅንነት ሥጋት ፈጥሯል

ለዓመታት በኢትዮጵያና በሶማሌላንድ መካከል የፀናው ግንኙነት በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) አስተዳደር ወቅት ትኩረት ተነፍጎታል ያሉ የሶማሌላንድ ባለሥልጣናት፣ ኢትዮጵያ ሶማሌላንድን ያገለለ አካሄድ መከተል መጀመሯ እያሳሰባቸው መምጣቱን አስታወቁ፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ሰሞኑን በሶማሌላንድ ጉብኝት እያደረጉ ለሚገኙ የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች እንደተገለጸው፣ የኢትዮጵያ መንግሥት በአፍሪካ ቀንድ እያደረገ ያለው እንቅስቃሴ የሚደገፍ ቢሆንም፣ ሶማሌላንድን ገሸሽ የማድረግ አዝማሚያ እየታየበት ስለመሆኑ ስሞታ ቀርቦበታል፡፡ የሶማሌላንድ ባለሥልጣናት ማሳያ ከሚያደርጓቸው ነጥቦች መካከል በኤርትራ፣ በሶማሊያና በኢትዮጵያ መካከል የተደረገው የሦስትዮሽ ስምምነት ሶማሌላንድን ወደ ጎን ማለቱን ነው፡፡

በሶማሌላንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና ዓለም አቀፍ ትብብር ዳይሬክተር ጄኔራል አብዲናሲር አህመድ ሄርሲ ምንም እንኳ ሶማሌላንድ በኢትዮጵያ ላይ ሙሉ እምነት ቢኖራትም፣ የኢትዮጵያ ሁኔታ ግራ እንደሚያጋባቸው ተናግረዋል፡፡ በኢትዮጵያ እየተካሄዱ የሚገኙ የሪፎርም ዕርምጃዎችን በተስፋ እንደሚጠበቁ ያስታወቁት ሚስተር ሄርሲ፣ ይህም ይባል እንጂ የኢትዮጵያ ወቅታዊ የፖለቲካ ትኩሳት አገራቸውን እንደሚያሠጋት አልሸሸጉም፡፡

በሶማሌላንድ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ከፍተኛ አማካሪና የሚኒስትሪ ልዩ ረዳት ሞሐመድ ኦማር ሐጂ በበኩላቸው፣ የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙት ፖሊሲ እየተለወጠ መሆኑን እንደሚያውቁና ይዘቱ ምን እንደሚሆን ለመረዳት እንደሚጓጉ ገልጸው፣ ኢትዮጵያ ከሶማሌላንድ ጋር ቀድሞ የነበራትን ዓይነት ትኩረት እያሳየች እንዳልሆነ አስታውቀዋል፡፡ እንደ እኚህ ባለሥልጣን ሁሉ፣ በሚኒስትሩ ከፍተኛ የፖሊሲ አማካሪ የሆኑት ሞሐመድ ኤ. ሞሐመድ (ባራዋኒ) ተመሳሳይ ሐሳብ አንፀባርቀዋል፡፡

ከመስከረም ወር ጀምሮ የሥራ ጊዜያቸውን ባጠናቀቁት ቆንስላ ጄነራል ምትክ እስካሁን ሌላ ተሿሚ አለመመደቡ፣ ኢትዮጵያ ከሶማሌላንድ ጋር የነበራትን ጥብቅ የዲፕሎማሲ ግንኙነት አሁን ቸል እያለችው ለመምጣቷ በማሳያነት እየቀረበ ነው፡፡

ኢትዮጵያ ከጎረቤት በላይ እህት አገር ነች የሚሉት እነዚህ ባለሥልጣናት፣ ከዲፕሎማሲ ግንኙነት ቸልተኝነት ባሻገር በኢትዮጵያ ወገን ሥጋት የደቀነባቸው ሌላም ጉዳይ በባለሥልጣናቱ ተጠቅሷል፡፡ ሁለቱ አገሮች የሚዋሰኑበት ድንበር ከ745 ኪሎ ሜትር በላይ ሲሆን፣ የድንበሩን ፀጥታና ሰላም ለማስጠበቅ ከፍተኛ በጀት እንደምትመድብ የምትገልጸው ሶማሌላንድ፣ በኢትዮጵያ በኩል ያለው ዝምታና ግልጽ ያልወጣ ቸልታ ሥጋቷን እንዳባባሰው አስታውቃለች፡፡

ሶማሌላንድ እ.ኤ.አ. ከጃኑዋሪ 2020 ጀምሮ ተግባራዊ የሚደረግ 500 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ በጀት ስታፀድቅ፣ ከዚህ ውስጥ እስከ 40 በመቶ ለፀጥታ ሥራዎች እንደሚውል ባለሥልጣናቷ ይናገራሉ፡፡ በፀጥታ ጉዳዮች ኢትዮጵያ ሥልጠናን ጨምሮ በርካታ ድጋፎች ለሶማሌላንድ ታደርግ እንደነበር ይታወቃል፡፡ ይህ ድጋፍ አሁንም እንደሚቀጥል፣ በሁለቱ አገሮች መካከል የሚታየው ጊዜያዊ ሁኔታ ወደነበረበት ጥብቅ ግንኙነት እንደሚመለስ በሶማሌላንድ የኢንፎርሜሽን፣ ባህልና ብሔራዊ መምርያ ዳይሬክተር ጄነራል ሙክታር ሞሐመድ ዓሊና ሌሎቹም ባለሥልጣናት ያምናሉ፡፡

የዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ገጽታው ባልለየበት ሁኔታም ቢሆን በአገሮቹ መካከል ያለው የንግድ ግንኙነት እያደገና እየተጠናከረ መምጣቱ ይነገራል፡፡ በአሁኑ ወቅት በሁለቱ አገሮች መካከል እስከ 1.5 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት ዓመታዊ የንግድ ልውውጥ እንዳለ ሲመገት፣ አብዛኛው ወደ ኢትዮጵያ ያደላ ነው፡፡ ከዚህ የንግድ እንቅስቃሴ ውስጥ ከኢትዮጵያ የሚላከው የጫት መጠን ትልቁን ድርሻ ይይዛል፡፡ የጫት ድርሻው ከ27 በመቶ ያላነሰ ድርሻ እንደሚይዝ ሲገለጽ፣ አትክልትና ፍራፍሬ፣ የቁም እንስሳት፣ መጫሚያና ሌሎችም ሸቀጦች ወደ ሶማሌላንድ ይጫናሉ፡፡ በአንፃሩ ወደ ኢትዮጵያ ከሚላኩት ጥቂት ሸቀጦች መካከል ጨውና የሳሙና ምርቶች ይጠቀሳሉ፡፡

ይህንን ግንኙነት የሚያሻሽሉ ሕጋዊ የንግድ፣ የኢንቨስትመንትና የባንክ ሕጎችን በማውጣት የኢትዮጵያ ባለሀብቶች ወደ ሶማሌላንድ እንዲመጡ ለማድረግ ዕቅድ መያዛቸውን ባለሥልጣናቱ ይገልጻሉ፡፡

ኢትዮጵያውያን በሶማሌላንድና በሶማሊያ መካከል ያለውን የድንበር ብቻም ሳይሆን የአመለካከት ልዩነት ሊገነዘቡልን ይገባል የሚሉት ሶማሌላንዶች፣ እ.ኤ.አ. ከ1991 ጀምሮ የራሳቸውን አገርና መንግሥት እንደ መሠረቱ፣ እስካሁንም ኢትዮጵያን ጨምሮ የዓለም አገሮች ዕውቅና እንዲሰጧቸው በመጠባበቅ ላይ እንደሚገኙ ያስረዳሉ፡፡ 

በብርሃኑ ፈቃደ፣ ሐርጌሳ፣ ሶማሌላንድ

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ወደ መኖሪያ ቤታቸው ሲገቡ ባለቤታቸው በቴሌቪዥን የሚተላለፈውን ዜና በመደነቅ እየተመለከቱ አገኟቸው]

እንዲያው የሚደንቅ ነው እኮ። ምኑ? ዜና ተብሎ በቴሌቪዥን የሚተላለፈው ነገር ነዋ፡፡ ምኑ...

በኦሮሚያ የሚፈጸሙ ግድያዎችና የተጠያቂነት መጥፋት

የካቲት 11 ቀን 2016 ዓ.ም. ቢሾፍቱ አቅራቢያ በሚገኘው የዝቋላ...

የኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋይ ገበያ ከሚያስፈልገው ካፒታል ውስጥ 90 በመቶውን ሰበሰበ

እስካሁን 15 ባንኮች የመዋዕለ ንዋይ ገበያው ባለድርሻ ሆነዋል የኢትዮጵያ መዋዕለ...

አዲሱ የንብ ባንክ ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ማቀዱ ተሰማ

አዲሱ የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር...