Thursday, June 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየአዲሱ ፓርቲ ውህደት ከፕሮግራሙና ከሕገ ደንቡ ጋር ፀደቀ

የአዲሱ ፓርቲ ውህደት ከፕሮግራሙና ከሕገ ደንቡ ጋር ፀደቀ

ቀን:

‹‹ውህደቱ በአገራችን የፖለቲካ ታሪክ አዲስ የአስተሳሰብ ለውጥና ዕመርታ የሚያመጣ ነው››

የኢሕአዴግ ምክር ቤት

‹‹በውህደት ሰበብ ሕወሓትን ለማፍረስ የሚያስችል ሕጋዊ ሥልጣን የለንም››

የሕወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ

የኢሕአዴግ ምክር ቤት ዓርብ ኅዳር 12 ቀን 2012 ዓ.ም. ምሽት ባወጣው መግለጫ፣ ከኅዳር 11 እስከ 12 ቀን 2012 .ም. ባደረገው ስብሰባ በፓርቲው ውህደት፣ በፕሮግራምና ሕገ ደንብ ላይ በዝርዝር ተወያይቶ ውሳኔዎች ማስተላለፉን አስታወቀ፡፡ አዲሱ ውህድ ፓርቲ ብልፅግና ፓርቲ የሚል ስያሜ እንደተሰጠው ይታወሳል፡፡

ኢሕአዴግ አገር መምራት ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ባለፉት ሦስት አሥርት ዓመታት በማኅበራዊ፣ኢኮኖሚያዊናፖለቲካዊ መስኮች በርካታ ለውጦችን ያስመዘገበ ድርጅት መሆኑን ገልጾ፣ ‹‹ይሁን እንጂ በስኬቶቹ ልክ በርካታ ጉድለቶችም የተስተዋሉበት መሆኑን መገምገማችን ይታወሳል፡፡ በተለይም በብሔራዊ ማንነትና በአገራዊ አንድነት መካከል ሚዛን ጠብቆ በመሄድ፣ ማኅበራዊ ፍትሕን በማረጋገጥ፣ እውነተኛ ፌዴራላዊ ሥርዓት በመገንባት ረገድ ጉድለቶቹ የበዙ ነበሩ፤›› ብሏል፡፡ ‹‹እንዲሁም አርብቶ አደሩን የአገራችንን ክፍል የወከሉ ድርጅቶችአጋር› በሚል አግላይ አሠራር በአገራቸው ዕጣ ፈንታ ላይ ቀጥተኛ ውሳኔ የማይሰጡ የሩቅ ተመልካች እንዲሆኑ ተደርገው ቆይተዋል፡፡ በመሆኑም ኢሕአዴግ ለውጡን መምራት የሚችል፣ ሁሉም ኢትዮጵያውያን የሚወከሉበት፣ ሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች አንዳችም ልዩነት ሳይደረግባቸው እኩል የሚሳተፉበት፣ ዘመኑን የዋጀ የነገ ፓርቲ በመሆን እውነተኛ ኅብረ ብሔራዊ ፌደራላዊት ኢትዮጵያ ዕውን እንድትሆን ለማድረግ ራሱን ፈትሾ የአደረጃጀት፣ የአሠራርና የፕሮግራም ማሻሻያ ማድረግ የግድ እንደሚለው በየጊዜው ሲካሄዱ በነበሩ ጉባዔዎችና ድርጅታዊ መድረኮች አቅጣጫ ሲቀመጥ ቆይቷል፤›› ሲል ምክር ቤቱ በመግለጫው ገልጿል፡፡

በድርጅቱ 11 መደበኛ ጉባዔ የፓርቲ ውህደት አጀንዳ አንኳር ከነበሩት የውይይት አጀንዳዎች ተጠቃሽ እንደነበር፣ በጉባዔውም የውህደት ሒደቱ ከሚገባው በላይ የተጓተተ መሆኑን በመገምገም ጥናቱ በፍጥነት ተጠናቆ ወደ ተግባር እንዲገባ ውሳኔ መተላለፉ እንደሚታወስ፣ የኢሕአዴግ ምክር ቤትም ጥናቱን እንዲፋጠን በማድረግ ተከታትሎ በማስፈጸም ኃላፊነቱን እንዲወጣ አቅጣጫ ተቀምጦ እንደነበር እንደሚታወቅ ምክር ቤቱ በመግለጫው አክሏል። በዚህ መሠረት ጥናቱ በዘርፉ ልምድና የካበተ ዕውቀት ባላቸው ምሁራን ተካሂዶ ለየብሔራዊ ድርጅቶች ሊቃነ መናብርት፣ ለሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴናማዕከላዊ ኮሚቴዎች ቀርቦ ውይይትና አስተያየቶች ተሰጥተውበት እየዳበረ እንዲመጣ መደረጉን አስረድቷል። የኢሕአዴግ ኦዲትና ቁጥጥር ኮሚሽንም ውህደቱ በሁሉም ብሔራዊ ድርጅቶች አባላትና አመራር ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነት ያገኘ፣ እንዲሁም በድርጅቱ መተዳደሪያ ደንብ መሠረት የተከናወነ ስለመሆኑ በተናጠል ባደረገው ጥናት ያረጋገጠይህም ለምክር ቤቱ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል ሲል አስታውሷል።

በመጨረሻም የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ከኅዳር 6 እስከ 8 ቀን 2012 .ም. ባደረገው መደበኛ ስብሰባ በጥናቱ ላይ ዝርዝር ውይይት አድርጎ በአብላጫ ድምፅ ካፀደቀው በኋላ ውሳኔ እንዲሰጥበት ለምክር ቤቱ ማስተላለፉን፣ ምክር ቤቱም በአሠራሩ መሠረት ለሁለት ቀናት ባካሄደው ውይይት የውህደት ውሳኔ ሐሳቡን፣ የፓርቲውን ፕሮግራምና ሕገ ደንብ በዝርዝር ካየና ካዳበረ በኋላ በሙሉ ድምፅ ማፅደቁን አስረድቷል።

ምክር ቤቱ ውህድ ፓርቲው በኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ ምግባር አዋጅ መሠረት ቀሪ ሒደቶችን በፍጥነት አጠናቆ የቆመላቸውን ዓላማዎች ወደሚያሳካባቸው ተጨባጭ ሥራዎች እንዲሸጋገር የሚያስችሉትን አቅጣጫዎችም ማስቀመጡን አስታውቋል። የኢሕአዴግ ምክር ቤት ይህን ውሳኔ ሲያስተላልፍ እስካሁን የነበረው የኢሕአዴግ አደረጃጀትና ፕሮግራም የአቃፊነት ጉድለት የሚታይበት በመሆኑ የባለቤትነትና የባይተዋርነት አሠላለፍን እንደፈጠረ፣ ይህም ድርጅቱንና አገሪቱን ወደ ከፋ ክፍፍል ያመራና ፅንፈኝነትን እየወለደ የሄደ መሆኑን በመገንዘብ አቃፊ የፖለቲካ አቅጣጫን መከተል እንዳለበት በማመን መሆኑን በመግለጫው ገልጿል፡፡ ለተፈጠረውም አገራዊ ችግር መፍትሔው ሁሉም ኢትዮጵያውያን ባለቤት የሆኑበት፣ በአገራቸው ጉዳይ ራሳቸው የሚወስኑበት ኅብረ ብሔራዊ ፓርቲ መገንባትና የቡድንና የግለሰብ መብቶች ተጣጥመው የሚሄዱበት የፖለቲካ ዓውድ መገንባት መሆኑን ምክር ቤቱ እንዳመነበት አስረድቷል።

‹‹ውህደቱ በአገራችን የፖለቲካ ታሪክ አዲስ የአስተሳሰብ ለውጥና ዕመርታ የሚያመጣ የአንድነት፣ የአብሮነትና የእኩልነት መንፈስን የሚፈጥር ነው። የፓርቲ ውህደቱ ሁሉንም የሚያካትት፣ ተደራሽና ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በማንነቱ ሳይገደብ የሚሳተፍበትን ሁኔታ በመፍጠር ጠንካራ ኅብረ ብሔራዊ ፌዴራላዊ ሥርዓት ዕውን ማድረግ ያስችላል፤›› ያለው ምክር ቤቱ፣ ‹‹በተጨማሪም የቡድንና የግል መብትን፣ እንዲሁም ብሔራዊ ማንነትንና ኢትዮጵያዊ አንድነትን በማጣጣም በሕገ መንግሥታችን ላይ የተቀመጠውን አንድ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ የመገንባት ራዕይ ዕውን ለማድረግ የሚያስችል ነው፤›› ሲል አክሏል።

ውህድ ፓርቲው የበለፀገች ኢትዮጵያን ዕውን በማድረግ ግዙፍ የዓላማ ማዕቀፍ ውስጥ የሕዝቦች መሠረታዊ ፍላጎቶችን በዘላቂነት ለማሟላት ጥራትና ቀጣይነት ያለው ዕድገት በማስመዝገብና ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት ያለው ኢኮኖሚ በመገንባት ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ፣ የሕዝቦችን ድህነትን፣ ዕርዛትንና ኋላቀርነትን ቀርፎ ሁሉን አቀፍ ብልፅግና በኢትዮጵያ ዕውን ሆኖ ለማየት የሚሠራ ፓርቲ ነው በማለት ምክር ቤቱ በመግለጫው አስረድቷል። ለዴሞክራሲ ባህል ማበብ አስፈላጊ የሆኑ ባህልና ተቋማት በመገንባት፣ የሕዝቦች ነፃነትና እኩልነት ተረጋግጦ፣ ሁሉም ኢትዮጵያውያን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶቻቸው ተከብረውላቸው፣ ኅብረ ብሔራዊ አንድነት የተረጋገጠባት ፌዴራላዊት ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ በፅኑ መሠረት ላይ ማቆም ፓርቲው ከሚታገልላቸው ቁልፍ አጀንዳዎች አንዱ መሆኑን ጠቁሟል። በማኅበራዊ ልማት መስክም መልካም አገራዊ እሴቶችና ባህሎችን በማዳበር በሥነ ምግባር የታነፀ ትውልድ ማፍራት፣ ለኑሮ ምቹ የሆነ አካባቢን መፍጠር፣ የማኅበረሰብ ጤና ተጠብቆ፣ ጥራት ያለው ትምህርት ለሁሉም እንዲዳረስና በሕዝቦች መካከል አዎንታዊ ሰላም ተፈጥሮ፣ ሁለንተናዊ ብልፅግና እንዲረጋገጥ የሚተጋ መሆኑን ገልጿል። ለመላው የድርጅቱ አባላትና ደጋፊዎች፣ ለአጋር ድርጅቶች አመራርና አባላት፣ ለተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች በሙሉና ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጥሪ በማቅረብ መግለጫውን ደምድሟል።

ይህ በዚህ እንዳለ የሕወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ ረቡዕ ኀዳር 10 ቀን 2012 ዓ.ም. ለኢሕአዴግ ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት በላከው ደብዳቤ፣ ምክር ቤቱ የውህደት አጀንዳውን ተወያይቶ የመወሰን ሕጋዊና ፖለቲካዊ ሥልጣን ስለሌለው በውይይቱ ላይ እንደማይገኝ አስታውቆ ሳይገኝ ቀርቷል፡፡ የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ኅዳር 6 ቀን 2012 ዓ.ም. የውህደት ጥናት ላይ ለመወያየት በሚል ባካሄደው ስብሰባ፣ አጀንዳውን ስቶ ባልተሠጠው ሥልጣን የኢሕአዴግ እናትና አጋር ድርጅቶችን እንዲዋሀዱ በአብላጫ ድምፅ መወሰኑን አስታወሷል፡፡ ሕወሓት በዚያ ስብሰባ ላይ በስድስት ተሳታፊዎቹ ቢወከልም የተቃውሞ ድምፅ ማሰማቱ አይዘነጋም፡፡

ሕወሓት እንደሚለው የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የውህድ ፓርቲ ጥናት ላይ ለመወያየት የያዘውን አጀንዳ ወደ ጎን በማለት ወደ ውህደት እንሻገር በሚል ያስተላለፈው ሕጋዊ ያልሆነ ውሳኔ በምክር ቤቱ ተደግሟል፡፡ ‹‹ከዚህም በተጨማሪ የሕወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ በጥናቱ ውጤት ላይ እንዲወያይ ተወስኖ እያለ ምንም ዓይነት ውይይት ሳይደረግ በጥድፊያ የምክር ቤቱ ስብሰባ መጠራቱ ተገቢ ባለመሆኑ፣ በውህደት ሰበብ ሕወሓትን ለማፍረስ የሚያስችል ሕጋዊ ሥልጣን ስለሌለን በኢሕአዴግ ምክር ቤት ስብሰባ ላይ ተገኝተን የሕወሓትን መዋሀድ ለመወሰን አንችልም፤›› ብሏል፡፡ ‹‹የሕወሓት ዕጣ ፈንታ ሊወሰን የሚችለው በየደረጃው ውይይት ከተደረገበት በኋላ በሕወሓት ጉባዔ ብቻ በመሆኑ፣ በአሁኑ ስብሰባ ላይ ለመሳተፍ የማንችል መሆኑን እናሳውቃለን፤›› ሲል አቋሙን አስታውቋል፡፡ የኢሕአዴግ ምክር ቤት ውሳኔ ከተሰማ በኋላ ግን ወደ ማተሚያ ቤት እስከሄድንበት ቅዳሜ አመሻሽ ድረስ ከሕወሓት በኩል ተጨማሪ ነገር አልተሰማም፡፡      

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በአዲስ አበባ በድምቀት ተከበረ

የአዛርባጃን ኤምባሲ  የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በትላንትናው ዕለት አከበረ። ሰኞ...

የመንግሥትና የሃይማኖት ልዩነት መርህ በኢትዮጵያ

እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች የሃይማኖት ተቋማት አዎንታዊ ሚና የጎላ...

ሐበሻ ቢራ ባለፈው በጀት ዓመት 310 ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ

የአንድ አክሲዮን ሽያጭ ዋጋ 2,900 ብር እንዲሆን ተወስኗል የሐበሻ ቢራ...