Thursday, December 7, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

አቢሲኒያ ባንክ ለኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት ጽሕፈት ቤት ማስፋፊያ በለቀቀው ቦታ ምትክ አዲስ ይዞታ አገኘ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ለኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ፕሬዚዳንት ጽሕፈት ቤት ማስፋፊያ ግንባታ ይዞታውን በቀረበለት ጥያቄ መሠረት ለማስተላለፍ የተስማማው አቢሲኒያ ባንክ፣ በምትኩ ከዋቢ ሸበሌ ሆቴል ጎን 10,329 ካሬ ሜትር ቦታ እንዲሰጠው የአዲስ አበባ ከተማ ካቢኔ እንደወሰነለት አስታወቀ፡፡

በቦሌ አፍሪካ ጎዳና የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ፕሬዚዳንት ጽሕፈት ቤት ይፈልጋቸዋል የተባሉትና በባንኩ ይዞታ ሥር የነበሩት ቦታዎች ሦስት የነበሩ ሲሆን፣ በእነዚህ ይዞታዎቹ ላይ የሕንፃ ግንባታ ለማካሄድ ዝግጅት ሲያደርግ እንደነበር አይዘነጋም፡፡ ሆኖም በእነዚህ ቦታዎች ላይ ለፕሬዚዳንቱ ጽሕፈት ቤት ማስፋፊያ  ለማከናወን በመታቀዱ በስምምነት ቦታውን እንዲለቁና ተለዋዋጭ ቦታ እንደሚሰጠው ከአዲስ አበባ አስተዳደር በቀረበለት ጥያቄ መሠረት፣ በስምምነት ቦታውን ለቆ ተለዋጭ ቦታ እንዲያገኝ ተፈቅዶለታል፡፡

ባንኩ ቅዳሜ ኅዳር 13 ቀን 2012 ዓ.ም. ባካሄደው ጠቅላላ ጉባዔ ላይ እንደተመለከተው፣ በስምምነት የሚለቀቀው ቦታ በአጠቃላይ 7,280 ካሬ ሜትር ስፋት ያለው ነው፡፡ የባንኩ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ አቶ መሠረት ታዬ እንደገለጹት፣ ባንካቸው ፍላሚንጎ አካባቢ ያሉትን ይዞታዎቹን ለኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት ጽሕፈት ቤት በማስተላለፍ፣ በምትኩ ከዋቢ ሸበሌ ሆቴል ጎን ያለ ቦታ እንዲተካለት ውሳኔ ተሰጥቷል፡፡

አቶ መሠረት በዚህ ጉዳይ ላይ በሰጡት ተጨማሪ ማብራሪያ፣ የባንኩ ይዞታዎች በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ወረዳ 07 ሦስት የይዞታ ካርታ ሲኖራቸው፣ ስፋታቸውም በአጠቃላይ 7,280 ካሬ ሜትር ነው፡፡ በእነዚህ ይዞታዎቹ ላይ ግንባታ ለማስጀመር ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ ነበር ብለዋል፡፡ ሆኖም ባንኩ በስምምነት ይዞታውን እንዲለቅና በምትኩም አንድ ወጥ የሆነ ሰፊ ይዞታ የሚሰጠው መሆኑን በመግለጽ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባቀረበው ጥያቄ መሠረት፣ በስምምነት  ለመልቀቅ ባንኩ መስማማቱም አስታውሰዋል፡፡

በቀረበው ጥያቄ መሠረት ባንኩ የተሻለ ተጠቃሚ እንዲሆን ለማድረግ ከባንኩ ቦርድ፣ ከከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችና ከከፍተኛ ባለአክሲዮኖች ጋር ምክክር በማድረግ አማራጭና ተስማሚ ሊሆን የሚችለውን ቦታ በመምረጥ ለአስተዳደሩ ቀርቦ አዎንታዊ ምላሽ መገኘቱንም አቶ መሠረት ገልጸዋል፡፡

ለባንኩ ተስማሚ የተባለውና በምትክ እንዲሰጠው የተጠየቀው ቦታ ሜክሲኮ አደባባይ ዋቢ ሸበሌ ሆቴል ጎን ያለው ቦታ እንደነበር፣ በዚህ ጥያቄ መሠረት የተፈለገው ቦታ እንደተወሰነላቸው አስረድተዋል፡፡ ይህንን ቦታ ለማግኘት በርካታ ባንኮች ጥያቄ አቅርበው እንደነበር ያስታወሱት የቦርድ ሊቀመንበሩ፣ በቶሎ የማግኘቱ ሁኔታ ቀላል አልነበረም ብለዋል፡፡ ሆኖም በባንኩ ከፍተኛ ባለአክሲዮኖችና በአመራሩም ያላሰለሰ ክትትል በምትክነት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ ውሳኔ እንዳሳለፈ ለጠቅላላ ጉባዔው አሳውቀዋል፡፡

በምትክ እንዲሰጣቸው ውሳኔ የተሰጠበት ቦታ ባንኩ ከለቀቀው ቦታ ጋር ሲነፃፀር 3,049 ካሬ ሜትር በተጨማሪነት ለባንኩ የተገኘ መሆኑም ገልጸዋል፡፡ ‹‹የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በባንካችን ስም የባለቤትነት የይዞታ ካርታ አዘጋጅቶ ለማስረከብ በሒደት ላይ በመሆኑ በአጭር ጊዜ ይጠናቀቃል ብለን እናምናለን፤›› ያሉት አቶ መሠረት፣ ‹‹የይዞታ ማረጋገጫውን በቅርቡ እናገኛለን የሚል እምነት አለኝ፤›› ብለዋል፡፡

አቢሲኒያ ባንክ ይዞታ ሥር የነበሩት ሦስት ቦታዎች ጉዳይ አሁን በዚህ ደረጃ መቋጫ ማግኘቱ ይገለጽ እንጂ፣ ጉዳዩ ዓመታትን ያስቆጠረ ምልልስ የተደረገበትና  የተለያዩ ውሳኔዎች ሲሰጥበት የነበረ መሆኑ ይታወሳል፡፡

ከአራት ዓመታት በፊት የአቢሲኒያ ባንክ ከይዞታው ላይ በመቀነስ፣ ለኦሮሚያ ፕሬዚዳንት ጽሕፈት ቤት እንዲሰጥ በአዲስ አበባ አስተዳደር ተወስኖ እንደነበርም አይዘነጋም፡፡ ይህ ውሳኔ አግባብ አይደለም በማለት ባንኩ አቤት በማለቱ ውሳኔው ተሸሮለት ነበር፡፡ አሁን ግን እንደ አዲስ በተደረገ ስምምነት ቦታውን ሙሉ ለሙሉ ለቆ ተለዋጭ ቦታ እንዲሰጠው በተደረገው ድርድር፣ ምትክ ቦታ ለማግኘት የሚያስችል ውሳኔ አግኝቷል፡፡ ባንኩ ከአራት ዓመታት በፊት ከይዞታው ተቀንሶ እንደማይወሰድበት ካረጋገጠ በኋላ፣ በቦታው ላይ ባለ 19 ፎቅ ሕንፃ ግንባታ ለማካሄድ ሲዘጋጅ እንደነበር ይታወሳል፡፡

አቢሲኒያ ባንክ አንጋፋ ከሚባሉት የግል ባንኮች አንዱ ሲሆን፣ ከ23 ዓመታት በላይ በፋይናንስ ኢንዱስትሪው ውስጥ የቆየ ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች