Monday, June 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየጥላቻ ንግግርና የሐሰተኛ መረጃ ሥርጭትን ለመከላከል የተረቀቀው ሕግ ቅጣት ጠንካራ እንዲሆን የፓርላማ...

የጥላቻ ንግግርና የሐሰተኛ መረጃ ሥርጭትን ለመከላከል የተረቀቀው ሕግ ቅጣት ጠንካራ እንዲሆን የፓርላማ አባላት ጠየቁ

ቀን:

የረቂቅ ሕጉ የተፈጻሚነት ወሰን እንዲሰፋም ጠይቀዋል

 በኢትዮጵያ የጥላቻ ንግግርና ሐሰተኛ መረጃ ሥርጭትን ለመከላከል የተረቀቀው የወንጀል ሕግ ቅጣቶች አነስተኛ በመሆናቸው፣ አስተማሪ ሊሆኑ በሚችሉ ጠንካራ ቅጣቶች እንዲሻሻል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ጠየቁ፡፡

በፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ተረቆ በሚኒስትሮች ምክር ቤትን ይሁንታን ያገኘው የጥላቻ ንግግርና የሐሰተኛ መረጃ ሥርጭት ረቂቅ አዋጅ ማክሰኞ ኅዳር 16 ቀን 2012 ዓ.ም. ለሕዝብ ተወካዮች የቀረበ ሲሆን፣ በምክር ቤቱ ሁለት አባላት ከቀረበ ሥጋት አዘልና የሕጋዊነት ጥያቄ በስተቀር በርካቶቹ ረቂቅ ሕጉን በመደገፍ አስተያየቶቻቸውን ሰጥተዋል፡፡

ይህም የጥላቻ ንግግርና ሐሰተኛ መረጃን ለመከላከል ለሕግ አውጪዎቻቸው የወንጀል ድንጋጌዎችን የያዙ ሕጎችን ያቀረቡ አገሮች ከሕግ አውጪ ምክር ቤቶቻቸው ጠንካራ ተቃውሞን ተጋፍጠው ያፀደቁ ስለመሆናቸው፣ ረቂቅ ሕጉን ለማዘጋጀት በተሞክሮነት የተጠቀሱት ኬንያ፣ ፈረንሣይና ጀርመን እንዲሁም የሌሎች በርካታ አገሮች ተሞክሮ ያስገነዝባል፡፡

እንደዚህ ዓይነት ሕጎች መሠረታዊ የሆነውን የመናገርና የሚዲያ ነፃነት ይጨፈልቃል የሚል ጠንካራ ሙግት ከእነዚህ አገሮች ሕግ አውጪ ምክር ቤቶች መቅረቡን፣ እስካሁንም ተመሳሳይ ሙግት በበርካታ አገሮች እየተነሳ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ግን ረቂቅ አዋጁን ከመደገፍ አልፈው፣ የተፈጻሚነት ወሰኑ ጠባብ እንደሆነ በመግለጽ መካተት ይገባቸዋል ያሏቸውን የማሻሻያ ሐሳቦች ሰንዝረዋል፡፡

ከሞላ ጎደል ሁሉም ሐሳብ የሰነዘሩ የምክር ቤቱ አባላት ረቂቅ ሕጉ የዘገየ ካልሆነ በስተቀር፣ አገሪቱ አሁን ላለችበት ፖለቲካዊ ሁኔታ መፍትሔ እንደሚሰጥ እምነታቸውን ገልጸዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በረቂቅ ሕጉ የተቀመጡት ቅጣቶች ዝቅተኛ መሆናቸውን በመጥቀስ፣ ጠንካራ ቅጣት እንዲቀመጥ ሲሉ ጠይቀዋል፡፡

እንደ ጥላቻ ንግግር ወይም ሐሰተኛ ተወስደው ክልከላ የማይደረግባቸውን ልዩ ሁኔታዎችን ረቂቅ ሕጉ አካቷል፡፡ እነዚህም ልዩ ሁኔታዎች መረጃው የትምህርት ወይም ሳይንሳዊ ምርምር አካል ከሆነ፣ የዜና ዘገባ፣ ትንታኔ ወይም የፖለቲካ ትችት አካል ከሆነ፣ እንዲሁም የኪነ ጥበብ፣ ትወና ወይም መሰል የሥነ ጥበብና የሃይማኖት አስተምህሮ አካል እንደሆኑ በረቂቁ ተመልክቷል፡፡

የምክር ቤቱ አባላት ግን እነዚህን ልዩ ሁኔታዎች በመቃወም ሃይማኖታዊ አስተምህሮዎች፣ የዜና ዘገባዎች፣ የምርምር ሥራዎች፣ የፖለቲካ ትችቶች፣ የኪነ ጥበብ ውጤቶች የግጭት መንስዔ ሆነው ሳለ በዚህ መልክ ተለይተው ክልከላ እንዳደረግባቸው መቀመጡ ተገቢነት የለውም፣ ሊስተካከል ይገባል ሲሉ ተከራክረዋል፡፡

በተጨማሪም የቀረበው ረቂቅ ግጭትን ለመከላከል ብቻ ዓላማ ማድረጉ ውስንነት ያለበት በመሆኑ፣ የተፈጻሚነት ወሰኑ እንዲሰፋና የውጭ ኢንቨስትመንት ወደ አገር እንዳይገባ ተፅዕኖ ያላቸው ሐሰተኛ መረጃዎችን የሚለቁ አካላትንም እንዲያካትት ጠይቀዋል፡፡

አንድ የምክር ቤቱ አባል ግን ረቂቁ በሕገ መንግሥቱና ሕገ መንግሥቱ በተቀበላቸው ዓለም አቀፍ ሕጎች ጥበቃ የተደረገለትን የመናገር ነፃነት የሚጥስ እንዳይሆን ሥጋት እንዳለባቸው በመግለጽ፣ ከመፅደቁ በፊት ጥንቃቄ እንዲደረግ ጠይቀዋል፡፡ እኚህ አባል በሰጡት አስተያየት ሕገ መንግሥቱ ለመናገር ነፃነት ልዩ ጥበቃ እንደሚያደርግ፣ ይኸውም በዋናነት ከብሔራዊ ደኅንነት አንፃር የተቀመጠ ገደብ መሆኑን በማንሳት የቀረበው ረቂቅ ይህንን ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌ የሚጥስ እንዳይሆን ጥንቃቄ መደረግ እንዳለበት ገልጸዋል፡፡

በምክር ቤቱ የመንግሥት ረዳት ተጠሪ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ጫኔ ሺመካ በበኩላቸው የቀረበው ረቂቅ አዋጅ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት በሕገ መንግሥቱ ጥበቃ የተደረገለት ቢሆንም፣ ይህ መብት ገደብ ሊጣልበት እንደሚችል ሕገ መንግሥቱ የሚደነግግ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የጥላቻ ንግግርና የሐሰተኛ መረጃ ሥርጭት በአገሪቱ እየተበራከተ በመምጣቱ ዘላቂ መፍትሔ ካልተበጀለት ለአገሪቱ ሰላምና ደኅንነት ትልቅ አደጋ መሆኑን የገለጹ ሲሆን፣ በቅርቡም በሐሰተኛ መረጃ ሥርጭት ግልጽ ሳቢያ በሰው ሕይወትና በንብረት ላይ ጉዳት መድረሱን እንደ ማሳያ አውስተዋል፡፡

ረቂቅ አዋጅ ከአባላቱ የተነሳውን ጨምሮ ዝርዝር ውይይት እንዲደረግበት ለሕግ፣ ፍትሕና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በዋናነት ተመርቷል፡፡

የጥላቻ ንግግር ማለት “ሆን ብሎ የሌላን ሰው፣ የተወሰነ ቡድንን ወይም ማኅበረሰብን፣ ብሔርን፣ ሃይማኖትን፣ ቀለምን፣ ፆታን፣ አካል ጉዳተኝነትን፣ ዜግነትን፣ ስደተኝነትን ወይም ቋንቋን መሠረት በማድረግ እኩይ አድርጎ የሚስል፣ የሚያንኳስስ፣ የሚያስፈራራ፣ መድልዎ እንዲፈጸም፣ ወይም ጥቃት እንዲፈጸም የሚያነሳሳ ጥላቻ አዘል መልዕክት” እንደሆነ ረቂቁ ይገልጻል፡፡ በመሆኑም የጥላቻ ንግግርን በአደባባይ ወይም ለሕዝብ በሚደረግ ንግግር፣ በኪነ ጥበብ ሥራ፣ በጽሑፍ፣ በምስል፣ በድምፅ ቅጂ ወይም በቪድዮ፣ በብሮድካስት፣ በየጊዜው በሚወጣ የኅትመት ውጤት ወይም በማኅበራዊ ሚዲያ፣ ወይም በሌሎች ማናቸውም መገናኛ መንገዶች ለሕዝብ መልዕክቱ እንዲደርስ ማድረግ የወንጀል ድርጊት መሆኑን ረቂቅ አዋጁ ትርጓሜ ይደነግጋል፡፡ አደገኛ የሐሰት መረጃ ማለት ደግሞ “ፍሬ ነገር ወይም አንኳር ይዘቱ ውሸት መሆኑን እያወቀ ወይ ማወቅ ሲገባው ሁከት ወይም ግጭት የማነሳሳት፣ ወይም ጥቃት እንዲደርስ የማድረግ ዕድሉ ግልጽ በሆነ መንገድ ከፍ ያለ መረጃን በማናቸውም መንገድ ማሠራጨት” እንደሆነ በረቂቁ ትርጓሜ ተሰጥቶታል፡፡

የጥላቻ ንግግርን የተመለከቱ ወንጀሎች መፈጸም እስከ ሦስት ዓመት በሚደርስ ቀላል እስራት ወይም ከመቶ ሺሕ ብር ያልበለጠ መቀጮ እንደሚያስቀጣ፣ በጥላቻ ንግግሩ የተነሳ በግለሰብ ወይም በቡድን ላይ ጥቃት የተፈጸመ ወይም የተሞከረ ከሆነ ቅጣቱ እስከ አምስት ዓመት የሚደርስ ጽኑ እስራት እንደሚሆን ይደነግጋል፡፡ በሌላ በኩል አደገኛ ሐሰተኛ መረጃ ማሠራጨትን በተመለከተ የተደነገገውን ድርጊት የተላለፈ እንደነገሩ ሁኔታ እስከ አንድ ዓመት በሚደርስ ቀላል እስራት ወይም ከሃምሳ ሺሕ ብር ያልበለጠ መቀጮ እንደሚጣልበት፣ ድርጊቱን የፈጸመው ከአምስት ሺሕ በላይ ተከታይ ባለው የማኅበራዊ ሚድያ ገጽ ከሆነ ወይም በብሮድካስት አገልግሎት ወይም በየጊዜው በሚወጣ የኅትመት ውጤት ከሆነ፣ ሦስት ዓመት በሚደርስ ቀላል እስራት ወይም ከ100,000 ብር ያልበለጠ መቀጮ እንደሚጣል ይደነግጋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...