Monday, April 15, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ኢትዮጵያን ከአፍሪካ ሁለተኛዋ የኤሌክትሮኒክ ግብይት መድረክ የሚያደርጉ ስምምነቶች ተፈረሙ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በኢትዮጵያ ሰሞኑን ይፋዊ የሥራ ጉብኝት ባደረጉት ግዙፉ የኤሌክትሮኒክ ግብይት ተቋም አሊባባ ግሩፕ ዋና ዳይሬክተር ቻይናዊው ጃክ ማ አማካይነት  በኢትዮጵያ መንግሥትና በአሊባባ መካከል የተፈረሙ ሦስት ስምምነቶች፣ ኢትዮጵያ ከሩዋንዳ በመቀጠል በአፍሪካ የኤሌክትሮኒክስ ዓለም ግብይት መድረክ (Electronic World Trade Platform) ማዕከል እንድትሆን ያስችሏታል ተባለ፡፡

‹‹WTP›› በመባል የሚጠራው ይኼ የግብይት ማዕከል በግል ድርጅቶች መሪነት የሚካሄድና በርካታ ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ እንደሆነ የተነገረ ሲሆን፣ የኤሌክትሮኒክ የንግድ ግብይትን ለማቀላጠፍና ሕጎችን ውጤታማ ለማድረግ የሚያግዝ የመንግሥትና የግል ዘርፍ የትብብር ማዕቀፍ መሆኑም ይነገርለታል፡፡

ትኩረቱ በተለይም ለአነስተኛ የንግድ ሥራዎች እንደሆነ የሚነገርለት ይኼ የግብይት መድረክ፣ ውጤታማ የፖሊሲና የንግድ ሥራ ከባቢ እንዲኖር በማድረግ ድንበር አቋራጭ የኤሌክትሮኒክስ ንግድ ለማቀላጠፍ ያግዛል ተብሏል፡፡

በኢትዮጵያ መንግሥትና በአሊባባ መካከል የተደረሰው ስምምነትም፣ የዚህ መድረክ ማዕከል በኢትዮጵያ እንዲቋቋም ያስችላል ተብሏል፡፡

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ከአሊባባ ጋር በመተባበር ባወጣው መግለጫ የዚህ ማዕከል መቋቋም የድንበር አቋራጭ ንግድ እንዲኖር፣ እንዲሁም የተቀላጠፈ የሎጂስቲክስ አገልግሎትና የተሟላ አገልግሎት እንዲፈጠር ለማድረግ፣ የኢትዮጵያ መካከለኛና አነስተኛ የንግድ ድርጅቶች የቻይናና ሌሎች ገበያዎችን መድረስ እንዲችሉ የአቅም ግንባታ ሥልጠና ለማስገኘት ያስችላል ብሏል፡፡

በእስያ በቻይናና ማሌዥያ፣ እንዲሁም በአውሮፓ በቤልጂየም፣ በአፍሪካ በሩዋንዳ ተመሳሳይ ማዕከላት መቋቋማቸውን የሚጠቅሰው መግለጫው፣ የማዕከላት ቁጥር ሲበዛ በማዕከላቱ መካከል የሚደረገው የንግድ ልውውጥ እንደሚያድግ ተስፋ እንደተደረገና ለነጋዴዎችም የተሻለ ዓለም አቀፍ ዕድሎችን እንደሚያስገኙ መግለጫው ያስረዳል፡፡

በስምምነቱ መሠረት በመጀመርያ የባለ ብዙ ተግባር የዲጂታል የንግድ ማዕከል ተገንብቶ የኢትዮጵያ ምርቶች ወደ ዓለም ገበያ መግባት የሚያስችላቸውን በር መክፈት እንደሆነ በመግለጽ፣ ይኼም ለድንበር አቋራጭ ንግዶች በማዕከልነት እንደሚያገለግልም በመግለጫው ተመልክቷል፡፡

ኢትዮጵያን በመጪዎቹ አሥር ዓመታት በዲጂታል ኢኮኖሚ ከአፍሪካ አምስት አገሮች መካከል አንዷ ለመሆን የታሰበውን ዕቅድ እንሚያግዝ ተገልጿል፡፡

አሊባባ በዓለም ግዙፍ ከሚባሉት የኤሌክትሮኒክስ ንግድ ግብይት ተቋማት መሀል አንዱ መሆኑ ይነገርለታል፡፡   

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች