አደገኛ አደንዛዥ ዕፅ በኢትዮጵያ ሲያዘዋውሩ የተገኙ 24 የውጭ አገር ዜግነት ያላቸው ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር እንደዋሉ፣ የፌራዴል ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ፡፡
አገሪቱ ከሌሎች አገሮች ጋር ባላት የዲፕሎማሲ ግንኙነት ላይ ችግር እንዳይፈጥር በመሥጋት፣ የግለሰቦቹ ማንነትም ሆነ ዜግነት አልተገለጸም፡፡ ግለሰቦቹ የተያዙት ባለፉት ሦስት ወራት በተለያዩ ጊዜያት ዕፆቹን ለማስወጣት ሲሞክሩ መሆኑን፣ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን የሩብ ዓመት ሪፖርት ያሳያል፡፡
59 ኪሎ ግራም ካናቢስ፣ 95 ኪሎ ግራም የሚመዝን 168 ጥቅል ኮኬይን፣ እንዲሁም 1.4 ሚሊ ሊትር ፈሳሽ ኮኬይን በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ሊያስወጡ ሲሉ መያዛቸው ተገልጿል፡፡
የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ወንጀል መከላከል ዘርፍ ከኦሮሚያ ፖሊስ ጋር በመቀናጀት በ2012 ዓ.ም. የመጀመርያው ሩብ ዓመት ሻሸመኔ አካባቢ ባካሄደው ዘመቻ፣ የተያዙ አደገኛ ዕፆች እንዲወገዱ ማድረጉን ይፋ አድርጓል፡፡ በዘመቻው በተሽከርካሪ ሊጓጓዝ የነበረ ከ595 ኩንታል የሚበልጥ፣ እንዲሁም በ135 ሔክታር መሬት ላይ የለማ የካናቢስ ማሳ እንዲወገድ ማድረጉም ተገልጿል፡፡
አደገኛ ዕፆችን በአገር ውስጥ በድብቅ የሚያበቅሉ ሕገወጦች የተሻለ ገንዘብ እንደሚያገኙበትና ለአርሶ አደሮችም በመንገር እንዲስማሙ እንደሚያደርጉ፣ የኮሚሽኑ ሪፖርት ያሳያል፡፡ እህል አምርተው ከሚያገኙት ገንዘብ የተሻለ በካናቢስ እንደሚያገኙ የተነገራቸው አርሶ አደሮች ማሳቸውን በካናቢስ እየተኩ መሆኑንም አስታውቋል፡፡
በአዲስ አበባም ለመልሶ ማልማት ፕሮግራም ታጥረው በቆዩ ቦታዎች ላይ ካናቢስ በቅሎ መገኘቱንና መወገዱንም አስታውቋል፡፡ ካናቢስ ሲበቅልባቸው ነበሩ የተባሉ ታጥረው የቆዩ ቦታዎች፣ የከተማ አስተዳደሩ ዕርምጃ የወሰደባቸው እንደሆኑ ተገልጿል፡፡