Sunday, June 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትከዘንድሮ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ምን ይጠበቃል?

ከዘንድሮ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ምን ይጠበቃል?

ቀን:

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የዓመቱን መርሐ ግብር እሑድ ኅዳር 21 ቀን 2012 ዓ.ም. ይጀምራል፡፡ ከብዙ ውጣ ውረዶች በኋላ በ16 ክለቦችና በአዲስ ዓብይ ኮሚቴ የሚመራው ውድድር ካለፉት ጊዜያት መሻሻልን ያሳያል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ዘንድሮ 22ኛ ዓመቱን ያስቆጠረው ሊጉ፣ ከተወዳዳሪ ክለቦች በተመረጡ ሰባት የዓብይ ኮሚቴ አባሎች ይመራል፡፡ በተለይ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በብጥብጥ እየታጀበ የመጣው ፕሪሚየር ሊግ፣ በዘንድሮ የውድድር ዘመን በተመልካቾች መካከል አለመግባባቶች እንዳይፈጠሩ የተሳታፊ ክለቦች የደጋፊ ማኅበሮች የተለያዩ መድረኮች እያዘጋጁ ውይይት ሲያደርጉ ቆይተዋል፡፡

በውድድሩ ላይ ተጋርጦ የነበረው የተመልካቾች አለመግባባትና ሁከት ክለቦችን እንዳሻቸው ከቦታ ወደ ቦታ ተዘዋውረው እንዳይጫወቱ ሲያደርጋቸው መቆየቱ ይታወሳል፡፡

በተመልካቾች መካከል የተፈጠረውን ቁርሾ ተከትሎም አንዱ ክለብ ወደ ሌላኛው ክለብ ክልል ሄዶ ጨዋታ እንደማያደርግ አቋሙን ያሳወቀም አልታጣም ነበር፡፡

በርካታ ክሶችን ሲያስተናግድ የቆየው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን፣ አምና የነበረው ሁከት ዳግም እንዳይፈጠር በሚል ሐሳብ የውድድር ፎርማት በመቀየር የክለቦችን ቁጥር ወደ 24 ከፍ በማድረግና በአክሲዮን ይዞ የሚተዳደሩበትን ንድፈ ሐሳብም ለመገናኛ ብዙኃን ይፋ ማድረጉ ይታወሳል፡፡

ምንም እንኳ ክለቦች በአዲስ ሊዋቀር በነበረው ፎርማት ውስጥ ለመካተት ፍላጎት ያሳዩ ክለቦች ቢኖሩም፣ ጠለቅ ያለ ውይይት ከተደረገበት በኋላ 16 ብቻ የሚሳተፉበትን በዓብይ ኮሚቴ እየተመሩ ሊቀጥሉ ይችላል የሚለው ላይ ከስምምነት ተደርሶ በነበረው እንዲቀጥል ተደርጓል፡፡

በዘንድሮው ከዚህ ቀደም የነበሩ ችግሮችና አለመግባባቶች በጥቂቱም ቢሆን ይቀነሳሉ የሚሉ አስተያየቶች እየተሰነዘሩ ይገኛል፡፡ ለዚህም ማሳያነት በተለያዩ የክልል ከተሞች የተደረጉት የከተማ ዋንጫ ውድድሮች መልካም ጎናቸው ጎልተው መታየታቸው ፍንጭ ሆነዋል፡፡

በተለይ ደግሞ በአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ውድድር ላይ ለግማሽ ፍጻሜ ለመድረስ በተገናኙት የከተማዋ ተፎካካሪ ክለቦች ቅዱስ ጊዮርጊስና ኢትዮጵያ ቡና ተመልካቾች መካከል የተስተዋለው መከባበርና ሥነ ሥርዓት ለክልል ክለብ ደጋፊዎች እንደማሳያ መወሰድ እንዳለበት የብዙኃን አስተያየት ሆኖ ቆይቷል፡፡

ሁለቱ ክለቦች ጨዋታ ሲኖራቸው በከተማዋ ነዋሪ ላይ ሽብር ከመፍጠሩም ባሻገር በስታዲየም ውስጥ የሚፈጠረው መጨናነቅና መሰዳደብ ተመልካቾችን ትዝብት ውስጥ የሚከት ነበር፡፡

የሁሉም ክለቦች ደጋፊ ማኅበር ፕሬዚዳንቶች በጥምረት የመሠረቱትን ማኅበር ተከትሎ፣ እንደዚህ ዓይነት ችግሮች ዳግም እንዳይከሰቱ አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረጋቸውን ገልጸዋል፡፡

በደጋፊ ማኅበሮች እየተከናወኑ ያሉት መልካም ተግባሮች እንዳሉ ሆነው፣ በእግር ኳስ ሜዳዎች ላይ ለሚስተዋሉ ብጥብጦች ምክንያቶችን መለየት እንደሚያስፈልግ ይነገራል፡፡

እ.ኤ.አ. 2016 በአውሮፓ ዋንጫ ማጣሪያ ውድድር ላይ እንግሊዝ ከሩሲያ ባደረገችው ጨዋታ ላይ በርካታ ተመልካቾች ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡ ከ30 በላይ ተመልካቾች ለከፋ ጉዳት የዳረገው ይኼ ጨዋታ፣ በእግር ኳስ ላይ ለሚያጋጥሙ ብጥብጦች አምስት የመፍትሔ ሐሳቦች በቢቢሲ ዘገባ ተጠቅሰው ነበር፡፡

ቢቢሲ በዘገባው ካስቀመጣቸው አምስት ነጥቦች አንደኛው ተመልካቾች መጠጥ ጠጥተው ወደ ስታዲየም እንዳይገቡ ማገድ ሲሆን፣ ውድድር ከመጀመሩ 24 ሰዓት በፊት የትኛውም ተመልካች መጠጥ ጠጥቶ እንዳይገባ የሚለው ቀዳሚ ነው፡፡

ሁለተኛው መፍትሔ ተደርጎ የተወሰደው ደግሞ ጨዋታን ቀደም ብሎ መጀመር ሲሆን፣ ይኼም ተመልካቾች ጠጥተው ወደ ስታዲየም እንዳይገቡ ያደርጋቸዋል የሚል ነው፡፡

ሦስተኛው መፍትሔ ተደርጎ የተቀመጠው ጨዋታዎችን ያለተመልካቾች ማድረግ ሲሆን፣ ይህም ክለቦቻቸው ላይ የሚያጋጥመውን ጉዳት ታሳቢ ስለሚያደርጉ ከሁከት ይቆጠባሉ የሚል አስተያየት ነው፡፡

ቢቢሲ በዘገባው አራተኛ መፍትሔ ብሎ ያስቀመጠው በስታዲየም የተመልካቾችን መቀመጫ ቦታቸውን የተለያዩ ቦታ ማድረግ ነው፡፡ የመጨረሻው መፍትሔ ተደርጎ የተቀመጠው፣ ለተመልካቾች በትምህርት የተደገፈ ሥልጠና መስጠት የሚለው ነው፡፡ በዚህም እ.ኤ.አ. 1980 የቤልጂየም ሊግ ለተመልካቾች ሥልጠና መስጠቱንና ለውጥ ማምጣት መቻሉን እንደማሳያነት ተጠቅሷል፡፡

እሑድ የሚጀምረው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ፣ ክለቦች በክልሎች በነፃነት ተንቀሳቅሰው ጨዋታቸውን ለማድረግ የክልል የፀጥታ ኃይሎች፣ የከተማ አስተዳደር አመራሮች፣ የደጋፊ ማኅበርና የክለብ አመራሮች አስፈላጊውን ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለባቸውና ከዚህ ቀደም በፌዴሬሽኑ ንዝህላልነት ሲያጋጥም የነበረውን ፀብ አጫሪ ድርጊቶች የሊጉ ዓብይ ኮሚቴ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባው ማሳሰቢያ ተሰጥቷል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አወዛጋቢው የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ጉዳይ

በኢትዮጵያ የሕገ መንግሥት ማሻሻል ጉዳይ ከፍተኛ የፖለቲካ ውዝግብ የሚቀሰቀስበት...

 መፍትሔ  ያላዘለው  የጎዳና  መደብሮችን  ማፍረስ

በአበበ ፍቅር ያለፉት ስድስት ዓመታት በርካቶች በግጭቶችና በመፈናቀሎች በከፍተኛ ሁኔታ...

የተናደው ከቀደምቱ አንዱ የነበረው የአዲስ አበባ ታሪካዊ ሕንፃ

ዳግማዊ አፄ ምኒልክ በ19ኛው ክፍለ ዘመን መገባደጃ መናገሻ ከተማቸውን...

የአከርካሪ አጥንት ሕክምናን ከፍ ያደረገው ‘ካይሮፕራክቲክ’

በአፍሪካ ከጀርባ ሕመም ጋር በተያያዘ በርካታ ሰዎች ለከፍተኛ የአካል...