[ለክቡር ሚኒስትሩ አንድ የባንክ ኃላፊ ስልክ ደወለላቸው]
- ሰላም ክቡር ሚኒስትር?
- ዛሬ ከየት ተገኘህ?
- ሪፖርት ላደርግ ነዋ፡፡
- ምኑን?
- ግዥውን ነዋ፡፡
- የምኑ ግዥ?
- የመስታወቱን ነዋ፡፡
- እሺ፡፡
- ክቡር ሚኒስትር በቃ ተተኮስን፡፡
- እንዴት?
- እንቅልፍ አልወስድ ብሎኛል፡፡
- ለምን?
- ሳስበው ነዋ፡፡
- ምኑን?
- ብልፅግናችንን፡፡
- ፓርቲውን ማለትህ ነው?
- ከፓርቲው በፊት እኛ ልንበለፅግ ነው፡፡
- እንዴት?
- በቃ ሁሉን ነገር በእኔ ጣሉት፡፡
- አልገባኝም፡፡
- ውጭ ካሉት አቅራቢዎች ጋር ተነጋግሬያለሁ፡፡
- ስለምኑ?
- ስለመስታወት ግዥው፡፡
- እሺ፡፡
- ጨረታውን በእነሱ ልክ እንሰፋዋለን፡፡
- ከዚያስ?
- ከዚያማ ተውት ክቡር ሚኒስትር፡፡
- እንዴት?
- አሁን የአገሪቱ ሁኔታም ጥሩ አይደለም፡፡
- ምን እያልክ ነው?
- አማራጭ አገር ሊኖረን ይገባል፡፡
- ምን?
- እውነቴን ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ባለፈው አለቃችን ያሉትን አልሰማህም እንዴ?
- ለዚያ እኮ ነው አማራጭ አገር ያስፈልገናል የምልዎት፡፡
- ምን ማለት ነው?
- እንደዚህ ዓይነት አጋጣሚ ሲገኝ መብላት አለብን፡፡
- እ…
- ብልፅግናን በተግባር ነው ማሳየት ያለብን፡፡
- ይኼ እኮ ስርቆት ነው፡፡
- ማን ነው ያለው?
- ምንድነው ታዲያ?
- እኛ ፕሮፌሽናል ሥራ ነው የምንሠራው፡፡
- የምን ሥራ ነው?
- ጨረታ እናወጣለን፡፡
- እሺ፡፡
- ከዚያም ግዥውን እንፈጽማለን፡፡
- ዋናው ጥያቄ እንዴት የሚለው ነው?
- ስነግርዎት ማንም ጥያቄ የማያነሳበት ሒደት ነው የሚኖረው፡፡
- እ…
- እኔው ራሴ ሄጄ ነኝ ዕቃውን የምመርጠው፡፡
- ከዚያስ?
- ከዚያማ እኛም እንቀበላለን፡፡
- ኮሚሽን፡፡
- እ…
- ለዚያውም…
- እ…
- በዶላር!
[ለክቡር ሚኒስትሩ አንድ ባለሀብት ስልክ ደወለላቸው]
- ምነው ክቡር ሚኒስትር?
- ምን ሆንክ?
- ምን አደረግናችሁ?
- ምን እያልክ ነው?
- ዜናውን ሰምቼ እኮ ነው፡፡
- የምን ዜና?
- ሊገቡ ነው የሚለውን ነዋ፡፡
- ውህዱ ውስጥ ነው፡፡
- ኧረ እኔ ስለውህዱ ምን አገባኝ?
- ታዲያ ምንድነው የምታወራው?
- ኧረ የውጭ ኩባንያዎቹን ነው ያልኩዎት፡፡
- የት ነው የሚገቡት?
- የዘይትና የስኳር ንግድ ውስጥ ነዋ፡፡
- ምን ችግር አለው?
- እኛ እኮ እዚህ የደረስነው በዚህ ንግድ ነው፡፡
- እሱማ ይታወቃል፡፡
- ታዲያ እኛ ላይ ምነው ጨከናችሁ?
- እናንተ ናችሁ እንጂ ጨካኝ የሆናችሁት፡፡
- እንዴት?
- ይኸው በየቀኑ ሕዝቡ ላይ ዋጋ እየጨመራችሁበት ታስመርሩታላችሁ፡፡
- እ…
- እሱም አልበቃ ብሏችሁ ለጤንነት ተስማሚ ያልሆነ ምርት እያመጣችሁ ትቸበችባላችሁ፡፡
- ቢሆንም ክቡር ሚኒስትር…
- ምን ቢሆንም ትለኛለህ?
- አይቆጡ እንጂ ክቡር ሚኒስትር?
- ለምን አልቆጣ?
- ምን አጠፋሁ?
- ስንት ዓመት ዘይት ስትነግድ ፋብሪካ እንኳን ለመገንባት ምንም ፍላጎት አታሳይም?
- ያው አያዋጣም እኮ፡፡
- ስለዚህ አንተ ስለራስህ እንጂ ስለሕዝቡ አታስብም፡፡
- እዚህ አገር ስለሕዝብ የሚያስብ አለ እንዴ?
- እሱስ ልክ ነህ፡፡
- ታዲያ እኔን ከሌሎቹ እንዴት ልለይ እችላለሁ?
- ስለዚህ አሁን ከውጭ እናስገባለን፡፡
- እ…
- ለሕዝቡ የሚያስቡ የውጭ ነጋዴዎችን እናስመጣለን፡፡
- እነሱስ ቢሆን ለሕዝቡ ያስባሉ ብለው ነው?
- እሱን የምናየው ይሆናል፡፡
- ግን በዚህ ጊዜ መሆኑ ያሳዝናል ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ለምን?
- ስለብልፅግና እየተወራ እኛ ላይ ጫና መፍጠሩ ተገቢ አይደለም፡፡
- ለእናንተ ብልፅግና አይገባም፡፡
- ምንድነው የሚገባው?
- ማረሚያ ቤት!
[ክቡር ሚኒስትሩ ከደላላ ወዳጃቸው ጋር ተገናኝተው ምሳ እየበሉ ነው]
- ምን ይጨመር ክቡር ሚኒስትር?
- እየበላሁ እጨምራለሁ፡፡
- ምን ነካዎት ክቡር ሚኒስትር?
- ምነው?
- ጊዜው የብልፅግና ነው፡፡
- እሱማ ልክ ነው፡፡
- ስለዚህ ገበታው መትረፍረፍ አለበት፡፡
- እ…
- ክቡር ሚኒስትር መቼም ኢሕአዴግ ፈርሷል፡፡
- ያው እሱን አፍርሰን አይደል ብልፅግናን የምናቋቁመው፡፡
- ስለዚህ የኢሕአዴግ ሥርዓትም ፈርሷል ማለት ነው፡፡
- ምን ጥያቄ አለው?
- አዩ ኢሕአዴግ በወሬ እንጂ በተግባር ስለሌለበት እኛ በብልፅግና ለየት ማለት አለብን፡፡
- እንዴት?
- የምናወራውን በተግባር ማሳየት አለብን፡፡
- ምን እያልከኝ ነው?
- ብልፅግናን በተግባር ማሳየት አለብን፡፡
- እ…
- ለእሱ ደግሞ ከሕዝቡ በፊት መሪዎቹ በተግባር ማሳየት አለባቸው፡፡
- ማለት?
- መበልፀግ አለብዎት፡፡
- እንዴት?
- እኔ ጥሩ ስትራቴጂ እየነደፍኩ ነው፡፡
- ምን ዓይነት ስትራቴጂ?
- እርስዎ የሚበለፅጉበትን ነዋ፡፡
- እኮ እንዴት?
- ከበርካታ የውጭ ኩባንያዎች ጋር እየተነጋገርኩ ነው፡፡
- እ…
- ወደዚህ ለመምጣት አሰፍስፈው እየጠበቁ ነው፡፡
- እና?
- እናማ ከሚመጡት ሁሉ ጋር በሽርክና እንሠራለን፡፡
- እ…
- ክቡር ሚኒስትር ምነው ደነገጡ?
- የምትነግረኝ ነገር ነዋ ያስደነገጠኝ፡፡
- ስነግርዎት ብልፅግናን በተግባር ማሳየት አለብን፡፡
- ሥልጣን ላይ የተቀመጥነው እኮ ሕዝቡን ለማበልፀግ ነው፡፡
- አንድ ነገር ልንገርዎት ክቡር ሚኒስትር?
- ምን?
- እኛ ካልበለፀግን ሕዝቡ አይበለፅግም፡፡
- እ…
- ሁሉ ነገር መጀመር ያለበት ከመሪዎች ነው፡፡
- እሱማ ትክክል ነው፡፡
- ስለዚህ ብልፅግናም በእርስዎ መታየት አለበት፡፡
- አሁን የምትነግረኝ አካሄድ ግን ትክክል አይመስለኝም፡፡
- እንዴት?
- በዚህ መንገድ ብንበለፅግ ባለፀጋ አንባልም፡፡
- ታዲያ ምንድነው የምንባለው?
- ባለጌ!
[ለክቡር ሚኒስትሩ የቀድሞ ሚኒስትር ስልክ ደወሉ]
- ምን ፈለግክ?
- ተው እንጂ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- አንዋሀድም አላችሁ አይደል እንዴ?
- ታዲያ በማናውቀው ፕሮግራም እንዴት እንዋሀዳለን?
- የእናንተ ፕሮግራምማ የትም አላስኬደንም፡፡
- ይኼ ሁሉ ልማት በምን መጣ ታዲያ?
- አሁን አገሪቱን ማስቀጠል አልቻለም፡፡
- የእኛን ታሪክ ለማጥፋት ነው ይኼ ሁሉ ሩጫ?
- የእናንተን ጥፋት ለማረም ነው እንጂ፡፡
- እ…
- ይኸው በጭቆና አንገቱን ያስደፋችሁትን ሕዝብ ቀና ልናደርገው ነው፡፡
- በምን?
- በብልፅግና ነዋ፡፡
- የእናንተማ ዓላማ ገብቶናል፡፡
- ምንድነው?
- አሃዳዊ ሥርዓት ማምጣት ነዋ፡፡
- አሃዳዊው ሥርዓትማ የእናንተ ነበር፡፡
- እንዴት?
- እናንተ አልነበራችሁ እንዴ አገሪቱን ከዳር እስከ ዳር በእጅ አዙር ስትገዙ የበራችሁት፡፡
- እ…
- ያበለፀጋችሁትም ራሳችሁ እንጂ ሕዝቡን አይደለም፡፡
- ግድ የለም ጊዜ ጥሎን ነው፡፡
- አሁን እናንተን ማንም አይፈልጋችሁም፡፡
- እ…
- በአዲሱ ፓርቲ ያላችሁን ቦታም በሐራጅ ሸጠነዋል፡፡
- ቀለዱ ክቡር ሚኒስትር?
- እውነቴን ነው፡፡
- ችግር የለም፡፡
- ለማንኛውም ብልፅግና የእናንተን ሥርዓት ገርስሶታል፡፡
- የእኛ ሥርዓት ምንድነው?
- ጨፍላቂ!