Wednesday, June 12, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ኪንና ባህልቅኔያዊ ሥዕል

ቅኔያዊ ሥዕል

ቀን:

በሔለን ተስፋዬ

ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ኩነቶች በሥነ ሥዕል፣ በሙዚቃ፣ በሥነ ጽሑፍ፣ በፊልምና በቴአትር ይገለጻሉ፡፡ በኢትዮጵያም በርካታ ሠዓሊያን የተለያዩ መድረኮችን በመጠቀም ሐሳባቸውን፣ ትዝብታቸውን፣ ትዝታቸውን፣ ኑሮዋቸውን፣ አካባቢያቸውን በሥዕል ያጋራሉ፡፡

በቅርቡ በጣሊያን ባህል ማዕከል ሠዓሊ፣ ቀራፂና ዲዛይነር ሚሊዮን ብርሃኔ የሣለቻቸውን ሥዕል በዕይታ አቅርባለች፡፡ ወጣቷ ‹‹ሥዕላዊ ቅኔ›› በሚል ርዕስ 40 የሚሆኑ የሥዕል ሥራዎቿን አቅርባለች፡፡

- Advertisement -

በፈጣሪ ትዕዛዝ መሠረት ከፍጥረታት ከእያንዳንዱ ሁለት ሁለት በመርከቡ በማስገባት ፍጥረትን ከጥፋት ውኃ የታደገው ታላቁ ሰው ኖህ በ‹‹ሥዕላዊ ቅኔ›› ለዕይታ ከቀረቡት አንዱ ነው፡፡

“የኖህ መርከብ” ከዘመኑ የፖለቲካ ውጥንቅጥ ይታደገን ዘንድ ሐሳባዊ ምኞቷን በሥዕሏ አሥፍራለች፡፡

‹‹የመጀመርያ ሰው፣ የፍጥረታት ሁሉ አባት አዳም›› በዚህ ዘመን ቢኖር ያለውን  የሰው ጭካኔና ግፍ ተመልክቶ እንደ ገና ወደ ፈጣሪው የመልሰኝ ተማፅኖውን የሚያሳይ ሥዕል ሌላኛው ሥራዋ ነው፡፡

ቅኔያዊ ሥዕል

‹‹በሥዕላዊ ቅኔ›› የሥዕል ጋለሪ የኖህ መርከብ ላይ ቅዱሳን መላዕክት የተሣሉበት መንገድ በአገራዊ አሣሣል ዘይቤ ነው፡፡

ሰዎች ሐሳባቸውን በጽሑፍና በሌሎች መንገድ እንደሚገልጹት እርሷም  የሚሰማትን ሐሳብ በሥዕሎቿ ‹‹ሥዕላዊ ቅኔ›› የሥዕል ዓውደ ርዕይ ለማሳየት መብቃቷን ነግራናለች፡፡

እንቅልፍ፣ ሕይወት፣ ጉዞ ትምህርት ቤት፣ ካፌ፣ ሰብሰብ ያሉ ሰዎች ሲያንቀላፉ የሚታይበት ሌላው ሥዕሏ ነው፡፡ ወጣቷ ይሄን የታዘበችውንና ሁልጊዜ የሚታየውን ነገር በሥዕሎቿ እንዳሰፈረች ገልጻለች፡፡

ከእንቅልፍ ጋር በተያያዘ ብቻ እስከ ሰባት የሚደርሱ ሥዕሎችን ለዕይታ ያቀረበች ሲሆን ከእነዚህ አንዱ፣ ‹‹ለፍተሻ ይተባበሩ!›› የሚል ጽሑፍ ያለበት ሥዕል ነው፡፡ በሥዕሉ ጥበቃው (የሚፈትሸው) እንቅልፍ ሸለብ አድርጎት ይታያል፡፡

‹‹እንቆቅልሽ›› በሚል ስያሜ የተሣሉ ሥዕልሎችም ለዕይታ ቀርበዋል፡፡ እነዚህ ሥዕሎች የሰው ልጆችን የሚያሳዩ ቢሆንም፣ ሰው ቅኔ እንደሆነ ለማሳየት የተሞከረበት ይመስላል፡፡ ሠዓሊ ሚሊዮን ‹‹በእንቆቅልሽ፣ የሰው ልጅ ማንነትና ባህሪ ስንት ነው? አንድ ሰው በአሥር የተለያዩ ቦታዎች አሥር ዓይነት ሰው የሚሆንበት አጋጣሚዎች አሉ፡፡ በሌላ በኩል ሰውን አውቀዋለሁ ማለት ከባድ ነው፣ የሰው አመል እቤት ውስጥ ሌላ፣ ውጭ ሌላ፣ ሥራ ቦታ ሌላ፣ ለማሳየት ሞክሬአለሁ፤›› ብላለች፡፡

በ‹‹ሥዕላዊ ቅኔ›› ከተካተቱት ሥዕሎች መካከል የከተማ ገፅታና መኖሪያ ቤቶች ይገኙበታል፡፡

እነዚህ መኖሪያ ቤቶች እጅግ የደከሙ፣ በዚህ የኑሮ ደረጃ ዲሽ የተሰቀለባቸው፣ ነዋሪዎቹ ቢቸገሩም ዲሽ ስላላቸው የተለያዩ መረጃዎችን ማግኘት እንደሚችሉ መልዕክት ለማስተላለፍ ታስቦ መሣሉን ተናግራለች፡፡

‹‹የራስ ምሥል›› በሚለው ርዕሷ ሠዓሊዋ የራሷን ምሥል አካታለች፡፡ ሴት ልጅ አበባ ናት፣ ትውልድ እንዲቀጥል የምታደርግ ናት፣ ውበት ናት፣ እጅግ አስፈላጊ ናት፣ አስፈላጊ ባትሆን ኖሮ አዳም ብቻውን በኖረ ነበር፡፡ ‹‹ምንም እንኳን ሥዕሉ እኔ ልሁን እንጂ ብዙ ሴቶችን የሚገልጽ ሥዕል ነው፤›› ስትልም ሚሊዮን ትገልጻለች፡፡

‹‹ጎረቤታሞቹ ሌላኛው የሥዕል ሥራዋ ነው፡፡ የተለዩ ግንደ ቆርቁሮች ውስጥ የሚኖሩ ወፎች እጅግ ቀለማቸው የሚያምር ውበት አለው፡፡ ነገር ግን ቀለማቸው የተለያየ ነው፡፡ የሚያወጡት ድምፅ የተለያየ ነው፡፡ ነገር ግን አንዱ የሌላው ድምፅ ይወደዋል፡፡ አንዱ የሌላውን ቀለም ይወደዋል፡፡ ምክንያቱም አንደኛው ያለው ሌላኛው ጋር ስለማይገኝ የሚል ሐሳብ እንዳለው ተናግራለች፡፡

ሥዕሉ የኢትዮጵያን ብሔረሰቦች የሚያሳይ ነው የምትለው ወጣቷ፣ የተለያየ ቀለም፣ ዘር፣ ሃይማኖት፣ ቋንቋ ቢኖርም፣ ውበት ነው፤ ምክንያቱም ሁሉም አንድ ዓይነት ቢሆን ኖሮ ሕይወት አሰልቺ ይሆን ነበር ብላለች፡፡

በሥዕሎቹ ‹‹እኔ የምኖረውን፣ የኔ የሆነውም፣ ስሜቴን አናግራለሁ፤›› የምትለው ሚሊዮን፣ አንድ ሰው ሕይወት ከሌለው በድን እንደሚሆን ሁሉ ሥዕል ሐሳብ ከሌለው በድን (ባዶ) ይሆናል፡፡ ስለሆነም በሥዕሎቹ ሐሳብ እንዲገለጹ አድርጌያታለሁ ስትል ገልጻለች፡፡

‹‹ሥዕሎቼ ቅኔ ናቸው›› ስትልም፣ ስለአንድ ነገር ብቻ እንደማያወሩ፣ ስለሕይወት፣ ስለመኖር፣ ጥያቄ፣ መልስ፣ ሒደትን የያዘው የሕይወት ጥያቄ፣ ቅኔያዊ በሆነ መንገድ በሥዕል ሥራዎቹ መገለጹን ታክላለች፡፡

አንድ ሰው ሐሳቡን በጽሑፍ፣ በሙዚቃ ሊገልጽ ይችላል የምትለው ሠዓሊዋ፣ የሷ ቅኔ መቀኛ፣ ታሪክን መንገሪያ፣ ሐዘንና ምኞት መግለጫ ሥዕል እንደሆነ ነግራናለች፡፡ እና ስኬታማም እንደሆነች ነግራናለች፡፡

በ‹‹ሥዕላዊ ቅኔ›› የሥዕል ጋለሪ ካነበበቻቸው መጻሕፍት የአንዱ ደራሲ መጨረሻ ምን እንደሆነ የሁል ጊዜ ጥያቄዋ በመሆኑ በሥዕል አጋርታለች፡፡

ደራሲና ጋዜጠኛ በዓሉ ግርማ ይሙት፣ ይኑር፣ ጠፍቶ ይቅር ወይም ሌላ የራሷን መላ ምት በሥዕሏ አስፍራለች፡፡ የደራሲና ጋዜጠኛ በዓሉ ቦልስዋገን መኪና፣ የመጻሕፍቱ ግንጥልጣይ በንፋስ ሲወሰድ መቅረፀ ድምፅ፣ ደራሲው የት እንደደረሰ የተነገሩ የተለያዩ መላ ምቶች ታይተውበታል፡፡ ሠዓሊ ሚሊዮን ከዚህ ቀደም በተለያዩ ጋለሪዎች ሦስት ዓውደ ርዕይ ማቅረቧን የነገረችን ሲሆን ‹‹ሥዕላዊ ቅኔ›› አራተኛ ሥራዋ ነው፡፡ በቀጣይ የቅርፃ ቅርፅ ሥራዎቿን ይዛ ብቅ እንደምትል ገልጻለች፡፡

በአገሪቱ የተለያዩ ሠዓሊዎች ቢኖሩም፣ ሥራዎቻቸውን የሚያቀርቡበት ቦታ ባለመኖሩ ወረፋ በመጠበቅ ሥዕሎቻቸው ለሕዝብ ዕይታ ሳይበቁ እንደሚቀር ተናግራለች፡፡

በተለይ የጣሊያን ባህል ማዕከልና ጎተ ኢንስቲትዩት ሥዕሎችን እንዲያሳዩ እንደሚያግዙ እንደ አገር ግን ትልቅ ሥራ እንደሚጠበቅ ጠቁማለች፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...