ስኳር አልባ የለስላሳ መጠጦች ለገበያ አቀረበ
ኮካ-ኮላ ኩባንያ መንግሥት ለሽያጭ ከሚያቀርባቸው የስኳር ፋብሪካዎች መካከል የተወሰኑትን ለመግዛት መዘጋጀቱን አስታወቀ፡፡ የግዥ ፍላጎቱን ለመንግሥት በማስታወቅ የጨረታ ሒደቱ ይፋ የሚደረግበትን ጊዜ እየተጠባበቀ መሆኑ ገልጿል፡፡
የኮካ-ኮላ ኩባንያ ቢቨሬጅ አፍሪካ እህት ኩባንያ የሆነው ኢስት አፍሪካ ቦትሊንግ አክሲዮን ማኅበር ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዳሪል ዊልሰን ለሪፖርተር እንዳስታወቁት፣ ኮካ-ኮላ የጥሬ አቅርቦት ፍላጎቱን በአገር ውስጥ ለማሟላት ካለው ፍላጎት በመነሳት የስኳር ፋብሪካ ለመግዛት መወሰኑን አስታውቀዋል፡፡
ምንም እንኳ ዋነኛ የሥራ ዘርፉ የለስላሳ መጠጦችን በመጥመቅ ለገበያ ማቅረብ ቢሆንም፣ የጥሬ ዕቃ ዕጥረት እየፈጠረበት ካለው ጫና በመነሳት በፋብሪካ ግዥ ከሚፎካከሩ ትልልቅ ኩባንያዎች አንዱ ሆኗል፡፡ የትኞቹን ፋብሪካዎች እንደሚገዛ በዝርዝር ባይጠቅሱም፣ የቀረቡትን አማራጮች የኮካ-ኮላ ፋብሪካዎች ከሚገኙባቸው አካባቢዎች በቅርብ ርቀት የሚገኙና አመቺ የተባሉት ላይ እንደሚያነጣጥር ሚስተር ዊልሰን አስታውቀዋል፡፡ ከስኳር ፋብሪካ ግዥ በተጨማሪ የፕላስቲክና የብርጭቆ ጠርሙስ ማምረቻዎችን የመክፈት ሐሳብ እንዳለውም ገልጸዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት የስኳር አቅርቦት ችግር በምርት ሒደቱ ላይ ፈተና የደቀነበት ኮካ-ኮላ ፋብሪካ፣ በኮታ በሚሰጠው ድልድል መሠረት አብዛኛውን አቅርቦት ከውጭ በማስገባት ይሸፍናል፡፡ ለምርት ከሚያስፈልገው ውስጥ ከ30 እስከ 40 በመቶውን ብቻ ከአገር ውስጥ እንደሚያገኝ ሚስተር ዊልሰን ይገልጻሉ፡፡
ለመጪዎቹ አምስት ዓመታት በኢትዮጵያ የ300 ሚሊዮን ዶላር ኢንቨስትመንት እንደሚያካሂድ ያስታወቀው ኮካ-ኮላ ፋብሪካ፣ በአሁኑ ወቅት በሰበታ ከተማ በ70 ሚሊዮን ዶላር ኢንቨስትመንት በኢትዮጵያ ትልቁን የለስላሳ መጠጦች ማምረቻ ፋብሪካ ግንባታ ማስጀመሩ ይታወቃል፡፡ በተመሳሳይም በሐዋሳ ከተማ አዲስ ማምረቻ ለመገንባት መሬት መረከቡን ሚስተር ዊልሰን አስታውሰዋል፡፡
ለሁለቱ ፋብሪካዎች በጠቅላላው ከ150 ሚሊዮን ዶላር ያላነሰ በጀት መመደቡን የኮካ-ኮላ ኩባንያ ኃላፊዎች ከዚህ ቀደም አስታውቀው እንደነበር መዘገባችን ይታወሳል፡፡ በሰበታ የሚገነባው ፋብሪካ በ14 ሔክታር መሬት ላይ የሚንሰራፋና በቀን 70 ሺሕ ሳጥን ለስላሳ የማምረት አቅም ያለው ግዙፍ ፋብሪካ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ከ60 ዓመታት በላይ የዘለቀው ኮካ-ኮላ፣ በአዲስ አበባና በድሬዳዋ ብቻ የነበሩትን ፋብሪካዎች አድማስ በማስፋት ከሁለት ዓመት ተኩል በፊት ወደ ባህር ዳር በማቅናት ሦስተኛውን የማምረቻ ፋብሪካ ወደ ሥራ ማስገባቱ አይዘነጋም፡፡
በሌላ ዜና ስኳር አልባ የለስላሳ ምርቶችን ያስተዋወቀው ኮካ-ኮላ፣ እ.ኤ.አ. በ2020 ከሚያመርታቸው መካከል የሰባት በመቶ ሽፋን የሚይዙ ስኳር የሌላቸው የኮካ-ኮላ፣ የስፕራይትና የፋንታ ምርቶችን ለገበያ አቅርቧል፡፡ እነዚህ ምርቶች ምንም ዓይነት ከሸንኮራ አገዳም ሆነ ከስኳር ድንች ካሉ ሥራ ሥር ምርቶች ከሚገኝ የስኳር ምርት ሙሉ በሙሉ ነፃ ሆነው፣ በአንፃሩ እንደ መጠጦቹ ዓይነት ተለይተው የተቀመሙ ግብዓቶች የተካተቱበት፣ አስፓርታም የተሰኘ ማጣፈጫ የተካተተባቸው ምርቶች በተጠቃሚው ዘንድ በተደጋጋሚ ይቀርቡ ከነበሩ ጥያቄዎች በመነሳት ለገበያ እንዳቀረባቸው ኮካ-ኮላ አስታውቋል፡፡