Friday, June 2, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

ከስህተት የማይማሩ ወደ ውድቀት ይንደረደራሉ!

መሳሳት የጥፋተኝነት ምልክት አይደለም፡፡ የሚሠራ ይሳሳታል፡፡ ሳይሠሩ ስህተት ላይ የሚያተኩሩ መኖራቸውም ይታወቃል፡፡ ስህተት አነፍናፊ ይባላሉ፡፡ የሚሠራ መሳሳቱ አዲስ ነገር አይደለም፡፡ ትልቁ ጥፋት ስህተትን መደጋገም ነው፡፡ ከሌሎች ስህተት አለመማርም ሌላው ጥፋት ነው፡፡ ብልህ በተቻለ መጠን የሚማረው ከሌሎች ስህተት ሲሆን፣ ሞኝ ግን ከራሱም አይማርም፡፡ በዚህ ዘመን ሞኝነት በጣም ያስገምታል፡፡ ከቤተሰብ ጀምሮ እስከ ትምህርት ቤት፣ ከሥራ ገበታ እስከ መንግሥት አመራር ድረስ በሥራ ወቅት የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶችን በብልኃት ማለፍ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ብልኃት የሚያስፈልገው ስህተትን ለመቀነስ ብሎም ለማስወገድ ነው፡፡ ብልህ ሰው አብረውት ከሚኖሩ ወይም ከሚሠሩ ሰዎች ጋር በግልጽ ይነጋገራል፣ ችግሮችን በአግባቡ ይፈታል፣ ልምምድ ይለዋወጣል፣ መተማመንን ያዳብራል፡፡ በየትኛውም የሥራ መስክም ሆነ በፖለቲካ፣ በኢንቨስትመንትም ሆነ በመንግሥት አመራር ላይ ያሉ ሰዎች ስህተትን የሚያስወግዱት በብቁና በንቁ አማካሪዎች በመመራት ነው፡፡ ‹‹መካር የሌለው ንጉሥ ያለ አንድ ዓመት አይነግሥ›› እንዲሉ፣ በብልህ አማካሪ የማይታገዙ ለተደጋጋሚ ስህተትና ቀውስ ይዳረጋሉ፡፡ ብዙ ጊዜ ችግሮች የሚያጋጥሙት በዚህ ምክንያት ነው፡፡

እንዳለመታደል ሆኖ ከአነስተኛ የሥራ ከባቢ እስከ ትልቁ የመንግሥት መዋቅር ድረስ፣ አድርባይነትና አስመሳይነት የተፀናወታቸው ግለሰቦችና ቡድኖች ለስህተት መፈጠር መንስዔ መሆን ብቻ ሳይሆን ለመደጋገም ምክንያት ይሆናሉ፡፡ ተሳስተው ከሚያሳስቱ ጀምሮ ሆን ብለው የስህተት አዙሪት የሚፈጥሩ ለተበላሸ ውሳኔም ሰበብ ይሆናሉ፡፡ በዚህ ምክንያት ለሥራ መበደልና ለመተማመን መጥፋትም ትልቁን ድርሻ ይይዛሉ፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጠንካራ ቁመና የማይኖራቸው በአስመሳዮች ስለሚከበቡ ነው፡፡ የመንግሥት አሠራር ለብልሽት የሚዳረገው ውሸታሞችና አጭበርባሪዎች ስለሚበዙ ነው፡፡ አነስተኛ የንግድ ተቋምም ሆነ ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ የሚያንቀሳቅስ ኢንቨስትመንት የሚንገዳገዱት፣ የሥራ ሳይሆን የጥፋት መልዕክተኞች ሰለባ ሲሆኑ ነው፡፡ በእንዲህ ዓይነት ሰዎች እግር ተወርች የተያዙ መንግሥታትም ለውድቀት ይዳረጋሉ፡፡ ሕዝብና መንግሥት፣ ሠራተኛና ቀጣሪ፣ የፖለቲካ ፓርቲና ደጋፊ፣ ወዘተ የሚቃቃሩት ለስህተት የሚዳርጉ ውሳኔዎች ሲበዙ ነው፡፡ በአስመሳዮችና በአድርባዮች ሳቢያ የሚደርሱ ጥፋቶች በንቁ ዓይን ካልታዩ ለቀውስ ይዳርጋሉ፡፡ ከቀውስ ለማገገም የሚፈጀው ጊዜ፣ ጉልበትና ገንዘብ በጣም ከፍተኛ በመሆኑ ኪሳራው ከባድ ነው፡፡

የኢትዮጵያን አጠቃላይ ሁኔታ በወፍ በረር ስንመለከተው ችግራችን የሚጀምረው ከቤተሰብ ነው፡፡ ቤተሰብ ሰላማዊና የተረጋጋ ሕይወት የማይመራ ከሆነ ለማኅበረሰቡ የሚያቀርበው የተንጋደደ ሰብዕና ነው፡፡ ወሬ ከሚበዛበት ቤተሰብ ውስጥ ወሬኞች እንደሚፈጠሩ ሁሉ፣ ተንኮል ከሚጎነጎንበት ቤተሰብ ውስጥ መሰሪዎች ይገኛሉ፡፡ ሌብነት፣ ሐሜት፣ ክፋት፣ ሴራ፣ ወዘተ የዚህ ውጤት ናቸው፡፡ ማኅበረሰቡም እነዚህን ችግሮች ማረቅ ካልተቻለው የላይኛው እርከን ድረስ ጦሱ ይከተላል፡፡ የሥራ ከባቢዎችም ብዙ ጊዜ ችግር የሚገጥማቸው እንዲህ ዓይነት ሰብዕና የተላበሱ ሰዎች ሲቆጣጠሯቸው ነው፡፡ እነዚህ የኃላፊዎችን የመወሰን ድርሻ ጭምር በመውሰድ ወይም የተጣመመ መረጃ በማቅረብ መሰናክል ይፈጥራሉ፡፡ የትምህርት ተቋማት ሊያርቁዋቸው ያልቻሉ ሰብዕናዎች ሲበዙ ደግሞ ጦሱ ለአገር ይተርፋል፡፡ በተለያዩ የኃላፊነት እርከኖች ላይ የሚቀመጡ ሰዎች ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ የሚገባቸው የመሰሪዎች ሰለባ እንዳይሆኑ ነው፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የንግድና የኢንቨስትመንት፣ የትምህርት፣ የሙያና የሲቪል ማኅበረሰቦች፣ በየደረጃው ያሉ የመንግሥት አመራሮች፣ ወዘተ ለስህተቶች መደጋገም መንስዔ ከሆኑ ግለሰቦችና ስብሰቦች ራሳቸውን ማፅዳት አለባቸው፡፡ ካልሆነ ግን ለከፍተኛ ችግር ይጋለጣሉ፡፡

ኢትዮጵያ ላለፉት ሃምሳ ዓመታት በላይ ሥቃይዋን የምታየው በሥርዓት መመራት ባለመቻሏ ነው፡፡ በመንግሥትም፣ መንግሥታዊ ባልሆኑም ሆነ በግል ተቋማት ከፍተኛ የሆነ ደካማነት የሚታየው ከብቃትና ከክህሎት ይልቅ ለማይጠቅሙ ነገሮች ቅድሚያ ስለሚሰጥ ነው፡፡ ብሔርን፣ እምነትን፣ መደብን፣ የጥቅም ተጋሪነትንና የመሳሰሉትን የሚያስቀድሙ መቧደኖች ትኩረት እያገኙ የአገሪቱ ተቋማት በአመዛኙ የአድርባዮች፣ የአስመሳዮች፣ የሐሜተኞች፣ የወሬኞችና የአሉባልተኞች መጫወቻ ሆነዋል፡፡ ከፍተኛ የሰው ኃይል፣ የተፈጥሮ ሀብት፣ ተስማሚ የአየር ፀባዮች፣ በርካታ የቱሪዝም መስህቦች፣ ወዘተ ያሏት አገር የድህነት መጫወቻ ለምን ሆነች? ከፍተኛ የውጭ ዕዳ አናቷ ላይ ለምን ያናጥራል? የኤክስፖርት ገቢዋ እያሽቆለቆለ የገቢ ንግዷ ከመጠን በላይ ተለጥጦ የንግድ ሚዛኑ ለምን ተዛባ? በጥላቻና በክፋት የተተበተበው ፖለቲካ ለምን አይቀየርም? ከተቋማት ይልቅ ለምን የግለሰቦች ተክለ ሰብዕና ይገዝፋል? የሕግ የበላይነት ተረጋግጦ ፍትሕ ለምን ለሁሉም ተደራሽ አይሆንም? አሁንም ድረስ መንግሥትና ፓርቲ ለምን ይቀላቀላሉ? ወዘተ ብለን ዋነኛ የሚባሉ ውስን ጥያቄዎችን ስናነሳ መልሱ ግልጽ ነው፡፡ ከስህተት ለመላቀቅ አለመቻል ዋነኛውን ድርሻ ይይዛል፡፡

ከስህተት ወደ ስህተት የሚደረገው ጉዞ እየቀጠለ ከሄደ መቆሚያው የት እንደሚሆን ለማወቅ ያዳግታል፡፡ የፖለቲካ ችግራችን ወደ እምነት ተቋማት ሲጓዝ እያየን ነው፡፡ ዕለታዊ ግለሰባዊ አለመግባባቶች ወደ ብሔርና ሃይማኖት ጠብ ሲቀየሩ እናስተውላለን፡፡ ከአገር ይልቅ ማንነት ውስጥ መደበቅ እየተለመደ ነው፡፡ አጥፊን በሠራው ሳይሆን በብሔሩ ወይም በእምነቱ ምክንያት የምንደግፈው ከሆነ ትልቅ ስህተት ነው፡፡ የሠራን የምናመሠግነው በውጤቱ ሳይሆን በብሔሩ ወይም በእምነቱ ከሆነ ይህም ትልቅ ስህተት ነው፡፡ ሠራተኛን የምንመዝነው በአፈጻጸሙ ሳይሆን ስሜታችን በመራን ከሆነ ሌላው ስህተት ነው፡፡ በአጠቃላይ ለ21ኛው ክፍለ ዘመን የማይመጥኑ ውሳኔዎች አገር እየጎዱ ነው፣ ትውልድንም እየገደሉ ነው፡፡ ምክንያታዊነት እየጠፋ ስሜታዊነት የበላይነት ሲይዝ ከፍተኛ የሆነ ችግር ይፈጠራል፡፡ ሹመት በብሔር፣ የባንክ ብድር በብሔር፣ መሬት በብሔር፣ የሥራ ቅጥር በብሔር፣ ወዘተ እየሆነ የደረሰው ጥፋት እየታወቀ ሃይማኖት ሲቀላቀልበት አደገኛ ነገር ይፈጠራል፡፡ በመሆኑም ከትንሽ ቢሮ ጀምሮ እስከ ትልቁ የመንግሥት አስፈጻሚ አካል ድረስ ከአስመሳዮችና ከአድርባዮች ማፅዳት ያስፈልጋል፡፡ አጉል መቧደንም ሆነ ጉድኝት መጨረሻው አያምርም፡፡ ለብቃት፣ ለክህሎት፣ ለልምድና ለሥነ ምግባር የሚሰጠው ዝቅተኛ ግምት በፍጥነት ይቀየር፡፡ ለስህተት የሚዳርጉ አማካሪዎችና ምክሮች እየበዙ ነው፡፡ አገር የደኸየችው፣ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ መሠረት መጣል ያልቻለችው በስህተት መንገድ ላይ መመላለስ ስለበዛ ነው፡፡ ስህተትን መደጋገም ደግሞ የሚያንደረድረው ወደ ውድቀት ነው!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

የተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅን የሚተካ ረቂቅ ተዘጋጀ

ከቫት ነፃ የነበረው የኤሌክትሪክ ኃይል ገደብ ተቀመጠለት የገንዘብ ሚኒስቴር ከሃያ...

ብሔራዊ ባንክ ለጥቃቅንና አነስተኛ ብድሮች ዋስትና መስጠት ሊጀምር ነው

ኢንተርፕራይዞችን ብቻ የሚያገለግል የፋይናንስ ማዕከል ሥራ ጀመረ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ...

አዋሽ ባንክ ለሁሉም ኅብረተሰብ የብድር አገልግሎት የሚያስገኙ ሁለት ክሬዲት ካርዶች ይፋ አደረገ

አዋሽ ባንክ ለሁሉም የኅብረተሰብ ክፍሎች በዘመናዊ መንገድ ብድር ማስገኘት...

መንበሩ ካለመወረሱ በስተቀር መፈንቅለ ሲኖዶስ መደረጉን ቤተ ክህነት አስታወቀ

ቅዱስ ሲኖዶስ ከነገ ጀምሮ ውይይት እንደሚጀምር ተነገረ ‹‹እኛ ወታደርም ሆነ...
- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በአዲስ አበባ በድምቀት ተከበረ

የአዛርባጃን ኤምባሲ  የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በትላንትናው ዕለት አከበረ። ሰኞ...

የመንግሥትና የሃይማኖት ልዩነት መርህ በኢትዮጵያ

እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች የሃይማኖት ተቋማት አዎንታዊ ሚና የጎላ...

ሐበሻ ቢራ ባለፈው በጀት ዓመት 310 ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ

የአንድ አክሲዮን ሽያጭ ዋጋ 2,900 ብር እንዲሆን ተወስኗል የሐበሻ ቢራ...

የባንኮች ብድር አሰጣጥ ፍትሐዊና ብዙኃኑን ያማከለ እንዲሆን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አሳሰበ

ባንኮች የብድር አገልግሎታቸውን በተቻለ መጠን ፍትሐዊ፣ የብዙኃኑን ተጠቃሚነት ያማከለና...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የፖለቲካ ምኅዳሩ መላሸቅ ለአገር ህልውና ጠንቅ እየሆነ ነው!

የኢትዮጵያ ፖለቲካ ምኅዳር ከዕለት ወደ ዕለት የቁልቁለት ጉዞውን አባብሶ እየቀጠለ ነው፡፡ በፖለቲካ ፓርቲዎች የእርስ በርስ ግንኙነትም ሆነ በውስጠ ፓርቲ ዴሞክራሲ የሚታየው መስተጋብር፣ ውል አልባና...

የመኸር እርሻ ተዛብቶ ቀውስ እንዳይከሰት ጥንቃቄ ይደረግ!

ክረምቱ እየተቃረበ ነው፡፡ የክረምት መግቢያ ደግሞ ዋናው የመኸር እርሻ የሚጀመርበት ጊዜ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ከእርሻው ክፍለ ኢኮኖሚ 70 በመቶ ያህሉን የሰብል ምርት የምታገኘው በመኸር እርሻ...

የሕዝቡን ኑሮ ማቅለል እንጂ ማክበድ ተገቢ አይደለም!

መንግሥት አገር ሲያስተዳድር ለበርካታ ወጪዎቹ ገንዘብ ስለሚያስፈልጉት አስተማማኝ የገቢ ምንጮች ሊኖሩት ይገባል፡፡ በጀት ሲይዝም ሆነ ወጪዎቹን ሲያቅድ ጠንቃቃ መሆን ይኖርበታል፡፡ ወቅቱ ለመጪው ዓመት በጀት...