Tuesday, July 23, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ስኳር ፋብሪካዎችን ለመግዛት ዳንጎቴን ጨምሮ በርካታ ገዥዎች የጨረታ ጊዜውን እየጠበቁ ነው

ተዛማጅ ፅሁፎች

የስኳር ዋጋን የሚወስን ቦርድ እንደሚቋቋም ተገልጿል

የአገር ውስጥ ኩባንያዎች መንግሥት ድጋፍ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል

መንግሥት ከሚሸጣቸው 13 የስኳር ፋብሪካዎች ውስጥ ስድስቱን ከአራት ወራት በኋላ ወደ ግል ለማዘዋወር መዘጋጀቱን ሲያስታውቅ፣ ዳንጎቴ ግሩፕን ጨምሮ በርካታ ኩባንያዎች የጨረታውን ሒደት በመጠባበቅ ላይ እንደሚገኙ ተገለጸ፡፡

የገንዘብ ሚኒስቴር ከፍተኛ አማካሪ ብሩክ ታዬ (ዶ/ር) ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በግዥ ሒደቱ የሚሳተፉ የአገር ውስጥና የውጭ ኩባንያዎች ፍላጎቶቻቸውን እንዲያስታውቁ በተደረገው ጥሪ መሠረት በርካታ ኩባንያዎች ጨረታው የሚወጣበትን ጊዜ በመጠባበቅ ላይ ናቸው፡፡ ፍላጎቶቻቸውን ካስታወቁ መካከል ከኬንያ፣ ከአልጄሪያ፣ ከሞሪሸየስ፣ ከተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ፣ ከሳዑዲ ዓረቢያ፣ ከኳታር፣ ከናይጄሪያና ከሌሎችም የተውጣጡ ኩባንያዎች ጨረታው የሚከፈትበትን ቀን እየጠበቁ ይገኛሉ፡፡ ከአገር ውስጥም የቢራ ፋብሪካዎችን ጨምሮ የመጠጥ ኢንዱስትሪው ውስጥ የሚንቀሳቀሱና በምግብ ማነቀነባበር መስክ የተሠማሩ፣ የሸንኮራ አገዳ አምራቾችና ሌሎችም ጨረታው ይፋ የሚወጣበትን ጊዜ ከሚጠባበቁት መካከል ናቸው፡፡

በኢትዮጵያ በሲሚንቶ ምርቶቹ የሚታወቀው ዳንጎቴ ኢንዱስትሪስ፣ መንግሥት ለሽያጭ ካቀረባቸው የስኳር ፋብሪካዎች መካከል ቢያንስ ሁለቱን ለመግዛት ፍላጎት እንዳለው የዳንጎቴ ግሩፕ ወኪል አቶ አዲስ ዓለማየሁ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ እንደ አቶ አዲስ ገለጻ፣ ዳንጎቴ ግሩፕ ጨረታው ይፋ የሚደረግበት ትክክለኛ ጊዜ መቼ እንደሆነ ብቻ በመጠባበቅ ላይ ይገኛል፡፡ ዳንጎቴ ከዚህ ቀደም በፖታሽ አምራችነት ለመሠማራት እንቅስቃሴ ጀምሮ እንደነበር ከሚጠቀሱለት የኢንቨስትመንት ፍላጎቶቹ መካከል ይመደባል፡፡ በኢትዮጵያ በዓመት እስከ 2.5 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ሲሚንቶ የማምረት አቅም ያለውን ፋብሪካ የገነቡት የዳንጎቴ ግሩፕ ባለቤት አሊኮ ዳንጎቴ፣ እኩል አቅም ያለው ተጨማሪ ፋብሪካ የመገንባት ፍላጎት እንዳላቸው አስታውቀው እንደነበር አይዘነጋም፡፡ በናይጄሪያና በሌሎችም አገሮች ውስጥ በተለያዩ የኢንዱስትሪ ምርቶች በተለይም በሲሚንቶ፣ በስኳር፣ በምግብ ሸቀጦችና በመሳሰሉት መስኮች የሚታወቀው ዳንጎቴ ግሩፕ፣ በነዳጅ ፍለጋና ማምረት ሥራም በናይጄሪያ በተለይ ትልቅ እንቅስቃሴ ላይ ይገኛል፡፡

እንዲህ ያሉ የውጭ ኩባንያዎችና ባለሀብቶች ፍላጎት የአገር ውስጥ ባለሀብቶችንና የዘርፉ ተዋንያንን ወደ ጎን እንዳያደርግ የሸንኮራ አገዳ አምራቾች የኅብረት ሥራ ዩኒየን አባላትና አክሲዮን በመሸጥ ላይ የሚገኘው የኢትዮ ስኳር ኢንዱስትሪ ማኑፋክቸሪንግ አክሲዮን ማኅበር ቦርድ አባላት አሳስበዋል፡፡ የወንጂ ሸዋ አገዳ አምራቾች ኅብረት ሥራ ማኅበር፣ ወንጂ ሸዋ ስኳር ፋብሪካን የመግዛት ፍላጎት እንዳለው አስታውቋል፡፡ በዚህም መንግሥት ለአገር ውስጥ በኮንትራት አገዳ የሚያመርቱ አርሶ አደሮች ትኩረት እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል፡፡ የኢትዮ ስኳር አክሲዮን ማኅበር ሥራ አስኪያጅ አቶ ቢተው ዓለሙና ሌሎችም የአክሲዮን ማኅበሩ አባላት መንግሥት ለአገር ውስጥ ባለሀብቶችና ኩባንያዎች ቅድሚያ የሚሰጥበትና የእኩል ተጠቃሚነት ድጋፍ የሚደርግበት ሥርዓት እንዲዘረጋ ጠይቀዋል፡፡ ብሩክ (ዶ/ር) ምላሽ ሲሰጡም መንግሥት ለአገር ውስጥ ባለሀብቶችና ኩባንያዎች ድጋፍ የማድረግ ፍላጎት እንዳለው ገልጸው፣ አገዳ አምራች አርሶ አደሮችም በሚያመቻቸው መንገድ ፋብሪካ ለመግዛት ቢመጡ እንደሚስተናዱ ተስፋ ሰጥተዋቸዋል፡፡

በኢትዮጵያ ስኳር ዘርፍ እንደ ዳንጎቴ ትልቅ ፍላጎት ያሳዩ ኩባንያዎች የሚሠማሩበት አንዱስትሪ፣ ከወዲሁ የሚመራባቸው የሕግና የአስተዳደር ማዕቀፎች መዘጋጀት ጀምረዋል፡፡ ከሰሞኑ በተካሄደውና የገንዘብ ሚኒስቴር በጠራው የሕዝብ ምክክር መድረክም፣ የስኳር ረቂቅ አዋጅን ጨምሮ የዘርፉ ፖሊሲና መሰል ጉዳዮች ተቃኝተዋል፡፡

ሚኒስቴሩ ዘርፉን እንዲያጠኑ የቀጠራቸው አማካሪዎችም ካቀረቧቸው ምክረ ሐሳቦች መካከል፣ የስኳር ኢንዱስትሪውን የሚመራ ቦርድ ይቋቋም የሚለው ሰፊ የመወያያ ጉዳይ ነበር፡፡ በዘጠኝ የቦርድ አባላት እንደሚተዳደር በረቂቅ ሕጉ የተጠቀሰው የስኳር ቦርድ፣ ከሚሰጡት ኃላፊነቶች መካከል የስኳር ዝቅተኛና ከፍተኛ የዋጋ ወለል መወሰን፣ ለአምራቾች ፈቃድ የመስጠትና የግልግል ዳኝነት የሚሰጥበት ሥርዓት የመዘርጋት ኃላፊነቶች ከዋና ዋናዎቹ መካከል ይመደባሉ፡፡ የኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን የስኳር ዘርፉን ከመምራት እንዲወጣ ተድርጎ፣ እንደ አንድ አምራች የቦርዱ አባል ሆኖ እንደሚካተት ተገልጿል፡፡

ተጠሪነቱ ለንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የሚሆነው የስኳር ቦርድ፣ የስኳርን ዋጋ ብቻም ሳይሆን የስኳር ተረፈ ምርቶችን የዋጋና የግብይት ጉዳይ ሊመለከት እንደሚችልም ተብራርቷል፡፡ የሕግ ጉዳዮችን በማማከር የተሳተፉት አቶ ጌታሁን ዋለልኝ የስኳር ዘርፉ ለፖለቲካ የተጋለጠ ከመሆኑም ባሻገር በመንግሥት ቁጥጥር ሥር ነበረ ብለው፣ ወደ ግሉ ዘርፍ በሚዛወርበት ወቅት የሚመራባቸው ሕጎችና የመወዳደሪያ ሜዳውን ለሁሉም በእኩል የሚመሩ አሠራሮች ከወዲሁ መዘርጋት እንዳለባቸው በመታመኑ አዋጅና ፖሊሲ ማርቀቅ እንዳስፈለገ ገልጸዋል፡፡

በአቶ ጌታሁንም ሆነ በኢኮኖሚ ባለሙያውና በዘርፉ የግል አማካሪነት በተሳተፉት ቴዎድሮስ መኮንን (ዶ/ር)፣ እንዲሁም በእንግሊዝ አማካሪ ኩባንያ ኤልኤምሲ ተወክለው በጥናቱ የተካፈሉት ሚስተር ማይክል ሒንጅ፣ ሐሳቦቻቸውን ካካፈሉባቸው መካከል የኤክሳይስ ታክስ ለአገር ውስጥ አምራቾች እንዲነሳ የጠየቁበት ይጠቀሳል፡፡

እንደ ቴዎድሮስ (ዶ/ር) ማብራሪያ፣ ከ33 በመቶ ያላነሰ የኤክሳይስ ታክስ የተጣለበት የስኳር ዘርፉ ሌሎችም የማምረቻ ወጪዎች ተደማምረው ከውጭ አምራቾች ጋር መወዳደር የማይችልባቸው ማነቆዎች ያሉበት በመሆኑ፣ የኤክሳይስ ታክሱ በአገር ውስጥ ለሚያመርቱ ኩባንያዎች እንዲነሳ ሐሳብ አቅርበዋል፡፡ በአንፃሩ ከውጭ በሚገባው ስኳር ላይ የኤክሳይስ ታክስ እንዲፀናበት ጠይቀዋል፡፡

በማብራሪያቸው መሠረት ከውጭ የሚገባው ስኳር የ33 በመቶ የኤክሳይስ ታክስን ጨምሮ፣ የአሥር በመቶ ሱር ታክስ፣ የአምስት በመቶ የጉምሩክ ታክስ፣ የሦስት በመቶ ዊዝሆልዲንግ ታክስ እንዲሁም የ15 በመቶ የተጨማሪ እሴት ታክስ ታክሎበት፣ በጠቅላላው የ87 በመቶ ታክስ ይከፈልበታል፡፡

ይህም ሆኖ በአሁኑ ወቅት አብዛኛው የአገሪቱ የስኳር ፍጆታ እየተሸፈነ የሚገኘው ከውጭ በሚገባ ስኳር በመሆኑ፣ ከምርት እጥረቱ ባሻገር ከውጭ የሚገባው ስኳር ይህንን ያህል ታክስ ተጥሎበትም ተወዳዳሪ መሆኑ፣ በዓለም የስኳር ገበያ ላይ የሚታየውን የተዛባና የሚዋዥቅ የዋጋ ሁኔታ እንደሚያሳይ አብራርተዋል፡፡ በመሆኑም የአገር ውስጥ የስኳር አምራቾች በዓለም ዋጋ መዋዠቅ ሳቢያ ጉዳት እንዳይደርስባቸው የሚከላከል ዝቅተኛ የመሸጫ ዋጋ እንዲቀመጥላቸው ማድረግ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ ሚስተር ማይክልም ይህንኑ ምክረ ሐሳብ አጠናክረዋል፡፡ ይሁን እንጂ ዝቅተኛም ሆነ ከፍተኛ የዋጋ መሸጫ ወለልን መወሰን ተገቢ አይደለም የሚለውን ጨምሮ፣ ለስኳር እንጂ አርሶ አደሮች ለሚያመርቱት የሸንኮራ አገዳ ዋጋ ማውጣት በአዲሱ አዋጅ አለመካተቱ ሊታሰብበት እንደሚገባም አምራቾቹን ወክለው በምክክሩ መድረክ የታደሙ አካላት ጠይቀዋል፡፡

እንዲህ ያሉ ጉዳዮች የተብላሉበት የስኳር የምክክር መድረክ ሌሎችም የአቅርቦትና የፍላጎት ክፍተቶች፣ ኢመደበኛ የስኳር ግብይቶችና ሌሎችም ጉዳዮች ተዳሰውበታል፡፡ እስካሁን የተዘጋጁ ሕጎችና የስኳር ኢንዱስትሪዎች ጠቅላላ የሀብትና ዕዳ መግለጫ ዝርዝር ሰነዶች መጠቃለላቸውን፣ በተለይም የስኳር ኢንዱስትሪው የጨረታና የቴክኒክ ሰነዶች በመጪው ወር ለሕዝብ ይፋ እንደሚደረጉ ይጠበቃል፡፡ ከጥር እስከ መጋቢት ባለው ጊዜ ውስጥም ስድስት ፋብሪካዎች ለጨረታ እንደሚቀርቡ ይጠበቃል፡፡  

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች