Monday, July 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹ኢትዮጵያ ከእኛ ጋር ያላትን ግንኙነት ዋጋ የምትሰጠው በጋራ ካለን ፍላጎት በመነጨ ነው›› ያሲን ሐጂ ሞሐሙድ፣ የሶማሌላንድ የውጭ ጉዳይና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትር

ያሲን ሐጂ ሞሐሙድ (ፕሮፌሰር)፣ የሶማሌላንድ የውጭ ጉዳይና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትር ናቸው፡፡ ሚኒስትር ሐጂ ሞሐሙድ ከአንድ ዓመት በፊት የተኳቸው የቦታው ተሿሚ ሳዓድ ሺሬ (ዶ/ር)፣ በሁለት ፕሬዚዳንቶች ሥልጣን ዘመን አገልግለው በአሁኑ ወቅትም አገሪቱን እየመሩ በሚገኙት በፕሬዚዳንት ሙሴ ቢሒ ካቢኔ ውስጥ በገንዘብ ሚኒስቴርነት ተሹመው እየሠሩ ነው፡፡ እሳቸው የተኳቸው ሚኒስትር ሐጂ ሞሐሙድ በሶማሌላንድ የምርጫ ወቅት በመሆኑ አገራቸው የምትከተለው ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ምንኛ ፍትሐዊና ነፃ የምርጫ ሥርዓት እንዳላት ለማሳየት የምትጣጣርበት ጊዜ ከመሆኑ ባሻገር፣ አገሪቱ በቀይ ባህር በኩል ካላት ስትራቴጂካዊ አቀማመጥ አኳያም የበርካታ አገሮች መናኸሪያ መሆን ጀምራለች፡፡ በአፍሪካ ቀንድ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች ላይ ትልቅ ሚና ያለው የበርበራ ወደብ ባለቤት እንደ መሆኗም፣ ኢትዮጵያን ጨምሮ የበርካታ አገሮች የትኩረት ማዕከል መሆኗ አልቀረም፡፡ በአንድ ወቅት የሞቃዲሾ ሶማሊያን በራሷ ፍላጎት ወዳና ፈቅዳ ብትቀላቀልም፣ እ.ኤ.አ. ከ1991 ጀምሮ ይህንን ውህደት በማውረድ ነፃና ሉዓላዊት አገር እንደሆነች አውጃለች፡፡ ሶማሊያ ግን አልተቀበለቻትም፡፡ ይህንን ተከትሎም የሶማሌላንድ ሉዓላዊ አገርነት በመላው ዓለም ሕጋዊ ዕውቅና እስካሁን ባያገኝም፣ በርካታ አገሮች ግን ፖለቲካዊና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶችን ከመመሥረት አልፈው በአሁኑ ወቅት በንግድና በኢንቨስትመንት እንቅስቃሴዎች ውስጥ መሳተፍ እየጀመሩ ነው፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የምግብ ፕሮግራም በየወሩ ወደ ኢትዮጵያ የሚጭነውን የዕርዳታ እህል የሚያጓጉዘውም በሶማሌላንድ በርበራ ወደብ ነው፡፡ ምንም እንኳ ለሶማሌላንድ ሉዓላዊ አገርነት ጉዳይ ኢትዮጵያ ዕውቅና ባትሰጥም፣ ከሞቃዲሾ ሊቃጣ የሚችል የፀጥታ ሥጋትን ግን በሶማሌላንድ በኩል እንደሚቀንስላት በርካቶች ያምናሉ፡፡ በሁለቱ አገሮች መካከል ሰፍኖ የቆየው የቅርብ ግንኙነትም በኢትዮጵያ አዲሱ አስተዳደር ወቅት ቸል ተብሏል የሚሉ ስሞታዎች በሶማሌላንድ ሕዝብ ዘንድ እየተበራከቱ መጥተዋል፡፡ ይህም አመለካከት በሚዲያ ዘገባ ተቃኝቷል፡፡ ሪፖርተር ዜናውን አስተናግዷል፡፡ ሚኒስትር ሐጂ ሞሐሙድ ግን የመንግሥታቸው አቋም ከዚህ የተለየ እንደሆነ በመግለጽ ዜናውን አስተባብለዋል፡፡ ሁለቱ አገሮች አሁንም ጥብቅ ግንኙነት እንዳላቸው፣ ዲፕሎማሲያዊ፣ ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ግንኙነቶች በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) አስተዳደር ወቅትም ሳይዛነፉ እንደቀጠሉ የገለጹት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ፣ ይህንና ሌሎችም ጉዳዮች በማንሳት በሶማሌላንድ ዋና ከተማ ሐርጌሳ ጽሕፈት ቤታቸው ከብርሃኑ ፈቃደ ጋር ያደረጉት ቆይታ እንደሚተለው ተጠናቅሯል፡፡

ሪፖርተር፡- የአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ለመካከለኛው ምሥራቅና ለምዕራቡ ዓለም አገሮች  የደራ የፖለቲካ ገበያ ሥፍራ እየሆነ መምጣቱ ይነገራል፡፡ ምሑራን ብሎም የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ፣ ይህ ጉዳይ እንደሚያሳስባቸው ሲጠቅሱና የእነዚህ አገሮች ተፅዕኖም በቀጣናው እንዳይንሰራፋ ሥጋት እንደነበረባቸው ሲገልጹ ቆይተዋል፡፡ ቀጣናው የፖለቲካ ገበያ ውስጥ ወድቋል የሚለውን እንዴት ይመለከቱታል?

ሐጂ ሞሐሙድ፡- አሁን እየታየ ባለው ዓለም አቀፋዊ ሁኔታ በተወሰነ ደረጃም ቢሆን በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ የሚታየው ነገር እውነትነት አለው፡፡ የአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ለበርካታ አገሮች ልዩ ጠቀሜታ ያለው የትኩረት መስህብ ሆኗል፡፡ አገሮች ለፀጥታ ሥጋት ሲሉም አካባቢውን በልዩ ትኩረት ይመለከቱታል፡፡ አካባቢው ከሚገኝበት ስትራቴጂካዊ አቀማመጥ የተነሳም ጭምር የምራብና የምሥራቅ አገሮች ዋና የትኩረት ማዕከል ሆኗል፡፡ በርካታ አገሮችም በዚህ አካባቢ ግንኙነቶችን በመመሥረት ፍላጎታቸውን የሚያስጠብቅ ተፅዕኖ ማሳደር ይፈልጋሉ፡፡ አካባቢው ምን ያህል ያለመረጋጋት ሥጋት ውስጥ እንደወደቀ ወይም ዓለም አቀፍ ፍላጎቶች የሚያሳድሩት ተፅዕኖ ምን ያህል የአፍሪካ ቀንድ አገሮችን ጫና ውስጥ እንደከተታቸው በውል አላውቅም፡፡ ይሁን እንጂ በሰፊው እንደሚባለው የአፍሪካ ቀንድ አካባቢ በዓለም አቀፍ ማኅበረሰቡ ዘንድ በእጅጉ የመናኸሪያ ማዕከል እየሆነ መጥቷል፡፡ ይህንን ነው ልል የምችለው፡፡

ሪፖርተር፡- በዚህ ስሱ በሆነው የአፍሪካ ቀንድ የፖለቲካ ቀጣና ውስጥ ኢትዮጵያና ሶማሌላንድ የዲፕሎማሲና የፖለቲካ ግንኙነቶችን በመፍጠር ለዓመታት በዚህ አግባብ ኖረዋል፡፡ አሁን ደግሞ አዲስ አስተዳደር ኢትዮጵያን እየመራ ይገኛል፡፡ ይህም ሆኖ በሁለቱ አገሮች መካከል የነበረው ግንኙነት በነበረበት እንደ ቀጠለ ነግረውናል፡፡ በደንብ ቢያብራሩልን?

ሐጂ ሞሐሙድ፡- እንደ እኔ ከሆነ ሁለቱ አገሮች የነበራቸው የዲፕሎማሲና ፖለቲካዊ ግንኙነት አሁንም በዚያው ልክ ተጠናክሮ እንደ ጠቀለ ነው፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ወደ ኃላፊነት መምጣት ተከትሎ ነገሮች ተለውጠዋል የሚለውን አመለካከት አልቀበልም፡፡ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር በተገናኘንበት ወቅትም በግልጽ እንዳስቀመጥንላቸው፣ በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ለመፍጠር የሚፈልጉትን የጋራ ትስስር በሙሉ እንደግፋለን፡፡ ሶማሌላንድም የዚህ ሒደት አካል እንደሆነች እናምናለን፡፡ በሁለቱ አገሮች በኩል ግልጽ እንዳደረግነው፣ የትኛውም ጥረትና ተነሳሽነት ሶማሌላንድን ማግለል እንደሌለበት ነው፡፡ ይህ ካልሆነ ግን ሒደቱ አይሳካም፣ ፖሊሲውም ትክክል አይሆንም፡፡ በአካባቢው ለሚካሄዱ የትኞቹም የጋራ ጥቅምና ፍላጎት ጥረቶች ስኬታማነት ሶማሌላንድ በአፍሪካ ቀንድ ውስጥ ወሳኝ በሆነ ስትራቴጂካዊ አካባቢ እንደ መገኘቷ፣ ለዚህ ዓይነቱ ጥረት ቁልፍ ቦታ አላት፡፡ ከቀጣናው አገሮች ጋር በትብብር ለመሥራት ደስተኞች ነን፡፡ አቋማችንም ይኸው ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ሶማሌላንድ በኢትዮጵያ ላይ ያደረባትን ሥጋት በማስመልከት ባለፈው ሳምንት ሪፖርተር ያወጣውን ዘገባ ተከትሎ በርካታ ስሞታዎች ሲደመጡ ከርመዋል፡፡ ይህ ሥጋት የመንግሥትም ለመሆኑ ከእርስዎ በፊት የነበሩት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርም ሲገልጹት የነበረ ጉዳይ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ወቅታዊ የውስጥ ፖለቲካ ትኩሳትም ሆነ በመሳሰሉት ጉዳዮች ሳቢያ ሥጋቶች ነበሩ፡፡ 

ሐጂ ሞሐሙድ፡- በኢትዮጵያ ውስጣዊ ፖለቲካዊ ጉዳዮችና ምን እየተካሄደ እንዳለ ያን ያህል የጠለቀ ዕውቀት የለንም፡፡ ይህም ቢሆን የኢትዮጵያውያን ጉዳይ በመሆኑ ጉዳዩን ለእነሱ እንተወዋለን፡፡ የእኛ ብቸኛው ትኩረት ከኢትዮጵያ ጋር ባለን ግንኙነት ላይ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ውስጣዊ የፖለቲካ ሁኔታ በግንኙነታችን ላይ ተፅዕኖ ያሳድራል ብለን አንሠጋም፡፡ የትኛውም አገር የራሱ ከፍታዎችና ዝቅታዎች ይኖሩታል፡፡ የጋራ ድንበር እንጋራለን፡፡ ይህም ከኢትዮጵያ በኩል ችግር ይፈጠርበታል የሚል ፍራቻ የለንም፡፡ ሶማሌላንድ በኢትዮጵያ ገሸሽ ተደርጋለች ብለን አናስብም፡፡ ኢትዮጵያ ከሶማሊያና ከኤርትራ ጋር የፈረመችውን የሦስትዮሽ ስምምነት በተመለከተም ምንም ሥጋት የለብንም፡፡ ኢትዮጵያ ከሶማሊያ ጋር መልካም ግንኙነት ይኑራት አይኑራት የማለት ሥልጣን የለንም፣ ልንልም አንችልም፡፡ ከኢትዮጵያ ጋር በሁሉም መስኮች እጅግ ጥሩ የሚባል ግንኙነት አለን፡፡

ስለሆነም በሦስትዮሹ ስምምነት ላይ ምንም ቅሬታ የለንም፡፡ ዘገባው ኢትዮጵያ ቆንስላ ጄኔራል ሳትሾም መቆየቷንም እንደ አንድ የሥጋት ምንጭ ያነሳል፡፡ ግልጽ ማድረግ የምፈልገው ጉዳይ ቢኖር፣ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታችን አሁንም ጠንካራ እንደሆነ ነው፡፡ እንደተነገረን ከሆነም በቅርቡ አዲስ ዲፕሎማት በሶማሌላንድ ለሚገኘው የኢትዮጵያ ቆንስላ ይሾማል፡፡ ስለጉዳዩ በዲፕሎማሲያዊና በሌሎችም የግንኙነት መንገዶች ግንኙነት እያደረግን ነው፡፡ ሁለታችንም የጋራ ፍላጎት አለን፡፡ ኢትዮጵያም የጋራ ፍላጎታችንን ማስጠበቅ ትፈልጋለች፡፡ በዘገባው የድንበር ላይ የፀጥታ ሥጋትም ተጠቅሷል፡፡ ይህ ብዙም የሥጋት ምንጭ  አይደለም፡፡ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት አለን፡፡ በርካታ ኢትዮጵያውያን ወደ ሌሎች አገሮች ለመሄድ በሶማሌላንድ በኩል ያቋርጣሉ፡፡ የተወሰኑትም እኛው ጋ መቆየትን በመምረጥ እየሠሩ ይኖራሉ፡፡ እርግጥ ሁለቱም አገሮች ሕገወጥ የሰዎችን እንቅስቃሴ ለመግታት እየሠሩ ነው፡፡ ይህንን ቢሆን እንደ ዲፕሎማሲያዊ ሥጋት አናየውም፡፡

ኢትዮጵያ በተጠንቀቅ የሚጠብቅ ሠራዊት የጋራ ድንበራችን ላይ አላት፡፡ ስደትና የሰዎች እንቅስቃሴ እንደ ፀጥታ ሥጋት መታየት የለበትም፡፡ ይሁን እንጂ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ለአሸባሪዎች ምልመላ አመቺ መሆኑ የታወቀ ነው፡፡ ከዚህም ባሻገር በስደተኞች ላይ የሚደርሰው አደጋም የሰብዓዊ ጉዳዮች ሥጋት ነው፡፡ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ለሉዓላዊ አገርነታችን ዕውቅና እንዲሰጠን እየጠየቅን ነው፡፡ ኢትዮጵያ ከእኛ ጋር ያላትን ግንኙነት ዋጋ የምትሰጠው በጋራ ካለን ፍላጎት በመነጨ ነው፡፡ በይፋ መግለጽ የምንፈልገው መንግሥታችን በኢትዮጵያ ላይ ምንም ዓይነት ሥጋት እንደሌለው ነው፡፡ ሰዎች ሐሳባቸውን ሊገልጹ ይችላሉ፡፡ የመሰላቸውን ሐሳብ መግለጻቸው መብታቸው ነው፡፡ የመንግሥታችን አቋም ግን በዜናው የተገለጸው አይደለም፡፡ ይህ ግልጽ መሆን አለበት፡፡

ሪፖርተር፡- ወደ በርበራ ወደብ ፕሮጀክት እናምራ፡፡ የማስፋፊያ ግንባታ እየተካሄደበት እንደሚገኝ ይታወቃል፡፡ ከዚህ ቀደም  የወደብ ልማቱ የሦስትዮሽ ስምምነት ከኢትዮጵያና ከዱባዩ ዲፒ ወርልድ ኩባንያ ጋር በተፈረመበት ወቅት፣ ሶማሊያ ተቃውሞ በማሰማት ስምምነቱ ውድቅ እንዲደረግ መጠየቋ ይታወሳል፡፡ በመሆኑም ኢትዮጵያና ሶማሌላንድ በፕሮጀክቱ ሳቢያ የገጠማቸው ፈተና አለ?

ሐጂ ሞሐሙድ፡- የበርበራ ወደብ ያለና የነበረ ነው፡፡ በአፍሪካ ቀንድ ስትራቴጂካዊ ቦታ ላይ የሚገኝ ወደብ ነው፡፡ ወደቡ ሶማሌላንድና ኢትዮጵያን ብቻ ሳይሆን፣ ለሌሎችም በአካባቢው ለሚገኙና ከዚያም ውጭ ላሉት አገሮች የሚያገለግል ነው፡፡ ሶማሊያ ለምን ስለሦስትዮሽ የወደብ ልማት ስምምነቱ ጉዳይ ጥያቄ እንዳነሳች አናውቅም፡፡ ኢትዮጵያ ጥቅሟን በሚገባ የምታስጠብቅበት መንገድ ላይ ትኩረት ታደርጋለች፡፡ ሶማሌላንድም እንደዚሁ፡፡ ሶማሊያ ሶማሌላንድ ግዛቴ ነች በማለት የምታቀርበው ስሞታ በወደቡ አስፈላጊነትና ጠቃሚነት ላይ ተፅዕኖ ያሳድራል ብለን አናምንም፡፡ ወደቡ ስትራቴጂካዊ ጠቃሚነቱን እንደያዘ ይኖራል፡፡  

ሪፖርተር፡- ወደቡ 30 በመቶ የኢትዮጵያን ገቢና ወጪ ዕቃዎች እንደሚያስተናግድ ይጠበቃል፡፡ ይህ እንዴት እንደሚከናወን ቢያስረዱን?

ሐጂ ሞሐሙድ፡- አዎን፡፡ ይህን ያህል ጭነት በወደቡ እንደሚስተናገድ  እንጠብቃለን፡፡ ከበርበራ ወደ ኢትዮጵያ የሚያገናኙ መንገዶች ሲታደሱና ሲገነቡ አይታችሁ ይሆናል፡፡ እንደ ወደቡ ሁሉ መንገዶችም እየተስፋፉ ነው፡፡ በመሆኑም በርከት ያሉ የኢትዮጵያ ገቢና ወጪ ሸቀጦች በበርበራ ወደብ በኩል እንደሚያልፉ ይጠበቃል፡፡ ወደቡ ለኢትዮጵያ ስትራቴጂካዊ በመሆኑ ለአገሪቱ በቀላሉ ተጨማሪ የባህር በር ዕድል እንድታገኝ አጋጣሚ የሚፈጥር ነው፡፡ ኢትዮጵያ ወደብ አልባ እንደ መሆኗና እንዳላት የሕዝብ ብዛት አኳያ ወደቡ ጠቃሚ ነው፡፡ ሶማሊያ ያሻትን ብትልም ፍላጎቷን የምታሟለበትን መንገድ የምታውቀው ግን  ኢትዮጵያ ነች፡፡

ሪፖርተር፡- የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ ኩባንያ የሆነው ዲፒ ወርልድ ከጂቡቲ ባይባረር ኖሮ ወደ በርበራ ወደብ በመምጣት ኢንቨስት ያደርግ ነበር ብለው ያስባሉ?

ሐጂ ሞሐሙድ፡- የበርበራ ወደብ ስትራቴጂካዊ በመሆኑ በርካታ አገሮችና ኩባንያዎች ፍላጎታቸውን ሲያሳዩ ቆይተዋል፡፡ ዲፒ ወርልድ ከመምጣቱ ቀደሞም ከሌሎች አገሮች ጋር እየተነጋገርን ነበር፡፡ ካለው ወሳኝ ስትራቴጂካዊ አቀማመጥ አኳያ በርካታ ዓለም አቀፍ ተዋንያን በበርበራ ላይ የረጅም ጊዜ ፍላጎት ነበራቸው፡፡

ሪፖርተር፡- የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ ወደ ሶማሌላንድ ያቀናችው ወታደራዊ የጦር ሠፈር በበርበራ ለማቋቋም እንደሆነ ይታወቅ ነበር፡፡ ቀደም ብለው ሲወጡ የነበሩ ግምቶችም ሶማሌላንድ የአሜሪካ የጦር ሠፈር በበርበራ እንዲኖር ትፈልግ እንደነበር ይጠቁማሉ፡፡ ይህ ምን ያህል እውነት ነው?

ሐጂ ሞሐሙድ፡- ቀደም ብለው የነበሩ ውይይቶች ነበሩ፡፡ በቀጣናው የነበሩ መግባባቶችም የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ በበርበራ የወታደራዊ ተቋማት ማዕከል ወይም የጦር ሠፈር ሊባል የሚችል ነገር መገንባት ይፈልጉ ነበር፡፡ በጊዜ ሒደት ግን ይህ ሐሳብ ተቀይሮ በአሁኑ ወቅት በበርበራ ኤርፖርት እየገነቡ ነው፡፡ ይህ ኤርፖርት ቀድሞ የነበረውን በማሻሻል እንደ አዲስ አገልግሎት መስጠት የሚቻልበት እንዲሆን እየተገነባ ነው፡፡ በተደረገው ስምምነት መሠረት ኤርፖርቱ ለንግድ ተግባር አገልግሎት የሚሰጥ እንደሚሆንና በቀጣናው ለሚገኙ አገሮችም ጭነቶችን ለማጓጓዝ የሚያስችል ይሆናል፡፡ ኤርፖርቱ በአብዛኛው የንግድ አውሮፕላኖች አገልግሎት የሚሰጡበት እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡

ሪፖርተር፡– ከወታደራዊ አገልግሎት ወደ ንግድ አገልግሎት እንዲለወጥ  የተደረገው የሶማሌላንድ ሕዝብ፣ እንዲሁም የፖለቲካ አካላት በኤምሬትስ ዕቅድ ላይ ባሰሙት ተቃውሞ ነው? ወይስ ኤምሬቶቹ ራሳቸው ወታደራዊ ሠፈራቸውን ወደ የንግድ አየር መንገድነት እንዲቀየር በመፈለጋቸው ነው?   

ሐጂ ሞሐሙድ፡-  ሐሳቡ ተቀይሯል፡፡ የተቀየረውም የሁለቱን አገሮች የጋራ ፍላጎት መሠረት በማድረግ ነው፡፡ ኤርፖርቱ በአብዛኛው ጭነቶችን በማዕከልነት የሚያስተናግድና የንግድ ግልጋሎቶች የሚቀርቡበት ይሆናል፡፡ የአውሮፕላን ጭነቶችን ከመካከለኛው ምሥራቅና ከሌሎችም አገሮች ወደ ቀጣናው የሚመላለሱበት ኤርፖርት እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡ የጭነት አገልግሎቱም ፈጣን በሆነ መንገድ ለኢትዮጵያ፣ ለደቡብ ሱዳን፣ ምናልባትም ለሶማሊያና ለሌሎችም አገሮች እንደ ፍላጎታቸው አገልግሎት ያቀርባል፡፡

ሪፖርተር፡- የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ሐርጌሳ እየበረረ ነው፡፡ ወደ በርበራ የቀጥታ በረራዎችን እንዲጀምር የሚያስችሉ ድርድሮች ተጀምረዋል?

ሐጂ ሞሐሙድ፡- መደበኛ ያልሆኑ ውይይቶች አሉ፡፡ አየር መንገዱ ፍላጎት እንዳለው ይፋዊ ባልሆኑ ውይይቶቻችን ወቅት ተገንዝብናል፡፡ ይሁን እንጂ እስካሁን ይህ ነው የሚባል መደበኛ ውይይት አልተደረገም፡፡ ፍላጎቱ እንዳለው ግን እናውቃለን፡፡ እኛም ወደ በርበራ የሚደረጉ በረራዎች እንዲጀመሩ ፍላጎት አለን፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በሶማሌላንድ ዋነኛው አገልግሎት ሰጪ ተቋም ነው፡፡ ሐርጌሳ እንደሚበረው ሁሉ ወደ በርበራም ቢመጣ መልካም ነው፡፡ ይህ ከማድረግ የሚያግደው ነገር እንደሌለ አምናለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- ሶማሌላንድ በንግድ፣ በኢንቨስትመንትና በፋይናንስ መስክ አዳዲስ ሕጎች እያወጣች ስለመሆኗ ሰምተናል፡፡ ይህም የውጭ ኩባንያዎችንና ባለሀብቶችን ለመሳብ እንደሆነ ተገልጿል፡፡ ይህ ምን ያህል ውጤታማ ያደርጋችኋል?

ሐጂ ሞሐሙድ፡- ሶማሌላንድ በጣም ነፃና ሊበራል ሥርዓት የምታራምድ በመሆኗ በዚሁ አግባብ ሕጎች አሏት፡፡ አሁን እየተደረገ ያለው ነባሮቹን ሕጎች አሻሽሎና አዳዲስ ይዘቶችን አካቶ ማፅደቅ ነው፡፡ ይህም የሚሆነው ነፃ ገበያን መሠረት በማድረግ ነው፡፡ ዓላማው ከጎረቤት አገሮችና ከዓለም ማኅበረሰብ ጋር በመተባበር መሥራት የምንችልበትን መንገድ ለማስፋት ነው፡፡ የንግድ ግንኙነታችንን ማስፋፋት እንፈጋለን፡፡ በዚህም የውጭ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ እንሻለን፡፡ የዓለም ማኅበረሰብም አሁን ያሉን ሕጎች የበለጠ ሕጋዊ እንዲሆኑና እንዲጠናከሩ  ይፈልጋል፡፡

ሪፖርተር፡- እንደ አገር ዕውቅና ባላገኛችሁበት ወቅት የውጭ ባለሀብቶች ወደ ሶማሌላንድ በመምጣት መሥራት ይፈልጋሉ ማለት ነው?

ሐጂ ሞሐሙድ፡- አዎን፡፡ በጣም ጠንካራ ፍላጎቶች አሉ፡፡ የውጭ ባለሀብቶች የሚፈልጉት ተስማሚ የንግድ ከባቢ ሁኔታዎች መኖራቸውንና ሕጎችም እነሱን የሚያግዙ መሆን ስለመቻላቸው ነው፡፡ አዎን ዕውቅና አግኝተን ቢሆን ኖሮ በርካቶች አሁን ከሚያደርጉትም በላይ ተበረታትተው በመጡ ነበር፡፡

ሪፖርተር፡- ለሶማሌላንድ እንደ አገር ዕውቅና የመስጠቱ ሒደት ሲበዛ የተጓተተና ረጅም ጊዜ ያስቆጠረ ቢሆንም አሁንም ድረስ አልተሳካም፡፡ በአንፃሩ እንደ ኤርትራና ደቡብ ሱዳን ያሉ አገሮች ግን ከሶማሌላንድ ትይዩ እንቅስቃሴ ቢጀምሩም ቀድመው ዕውቅናቸውን አግኝተዋል፡፡ ሶማሌላንድ ግን ሰሚ አላገኘችም፡፡

ሐጂ ሞሐሙድ፡- ይህንን መመለስ ያለበት የዓለም ማኅበረሰብ ነው፡፡ የዓለም ማኅበሰብ ለምን ለእኛ ዕውቅና ከመስጠት ወደ ኋላ እንደሚል አላውቅም፡፡ ሶማሌላንድ እንደ አገር ለመቆጠር የሚያበቋትን ሕጋዊ ሰነዶችና ቅድመ ሁኔታዎችን አሟልታለች፡፡ ሕዝባዊ ሪፈረንደም ተካሂዶ ሕዝቡ በግልጽ ፍላጎቱን አስታውቋል፡፡ ሶማሌላንድ ነፃና ሉዓላዊት አገር ነች ብሎ ወስኗል፡፡ በአንድ ነገር አጥብቀን እናምናለን፡፡ በጊዜ ሒደት ሶማሌላንድ ሉዓላዊነቷን ታገኛለች፡፡ በአንድ ወቅት በፍላጎታችን ከሶማሊያ ጋር ተዋህደን ነበር፡፡ ይሁን እንጂ የሶማሌላንድ ሕዝብ ነፃነቱን መቀዳጀት በመፈለጉ፣ ከሶማሊያ ጋር በፍላጎቱ እንደተዋሀደው ሁሉ በፍላጎቱ ነፃነቱን የመቀዳጀት መብት አለው፡፡  

ሪፖርተር፡- ሶማሊያ ግን በሶማሌላንድ ሉዓላዊ አገርነት የተስማማች አትመስልም?

ሐጂ ሞሐሙድ፡- እንደማስበው በጊዜ ሒደት እውነታውን እየተረዱት ነው፡፡ የዓለም ማኅበረሰብም ሉዓላዊነታችን ሳይረጋገጥልንም እኮ አብሮን እየሠራ ነው፡፡ የሁለትዮሽ ስምምነትና ዓለም አቀፍ ትብብሮችን እየፈረምን ነው፡፡ ችግር የለብንም፡፡ ሕጋዊ ዕውቅና ባናገኝም፣ ዕውቅናውን በተዘዋዋሪ መንገድ እያገኘን ነው፡፡ በጊዜ ሒደትም ተገቢውን ሕጋዊ ዕውቅና እንደምናገኝ እናምናለን፡፡

ሪፖርተር፡- ዕውቅና አለማግኘታችሁ ምን ያህል ዋጋ አስከፍሏችኋል?

ሐጂ ሞሐሙድ፡- የምንከፍለው ዋጋ ስፍር የለውም፡፡ ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት የብድር አገልግሎት እንዳይሰጡን የሚያደርግ ጫና ውስጥ እንገኛለን፡፡ ይህ ችግር አለብን፡፡ የሁለትዮሽ የብድር ስምምነት ለመፈረም ተቸግረናል፡፡ ይህ ትልቅ ችግር ነው፡፡ ዕውቅናውን ባለማግኘታችን የዲፕሎማሲያዊ ተልዕኳችን ላይም ጫና ይኖረዋል፡፡ ይህም ይሁን እንጂ አሁንም ድረስ እየታገልን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በተመድ ወይም በአፍሪካ ኅብረት በኩል የዕውቅና ዘመቻ የማድረግ ዕቅድ አላችሁ?

ሐጂ ሞሐሙድ፡- የቻልነውን ሁሉ እየሞከርን ነው፡፡ የዓለም ማኅበረሰብ ፍላጎታችንን እንዲገነዘብ ለማድረግ ጉዳያችንንም ለዓለም ለማሳወቅ እየጣርን ነው፡፡ በአፍሪካ ኅብረት በኩል እንዲሁም በቀጣናው በኩል የዲፕሎማሲ ግንኙነቶቻችንን በመጠቀም አጀንዳችንን ለማንቀሳቀስ እየጣርን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በመጪው ዓመት ባገኝዎ ሊነግሩን የሚችሉት አዲስ ስኬት ምን ሊሆን ይችላል? ምንስ ልንጠብቅ እንችላለን?

ሐጂ ሞሐሙድ፡- በመጪው ዓመት እንደ አገር ዕውቅና የምናገኝበትን ስኬት እናስመዘግባለን ማለት ይከብደኛል፡፡ ዕውቅና ባናገኝም አንከፋም፡፡ እስካሁን እንደነበርነው በጥንካሬና በፅናታችን እንቆያለን፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች ሥራቸውን በነፃነት ሳይፈሩና ሳይሸማቀቁ እንዲያከናውኑ ዋስትና የሚሰጣቸው ሕግ የለም›› አቶ አመሐ መኮንን፣ የሕግ ባለሙያና የመብት ተሟጋች

ለበርካታ የፖለቲካና የህሊና እስረኞች በፍርድ ቤት በመሟገት የሚታወቁት የሕግ ባለሙያ፣ ጠበቃና የመብት ተሟጋቹ አቶ አመሐ መኮንን የፈረንሣይና  የጀርመን መንግሥታት በጋራ ለሰብዓዊ መብቶች መከበር የላቀ...

‹‹የአጎራባች ክልሎች የሰላም ዕጦት በእኛ ላይ ሸክምና ጫና ፈጥሮብናል›› ከአቶ ባበከር ሀሊፋ፣ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የግብርና ቢሮ ኃላፊ

አቶ ባበከር ሀሊፋ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ ወንዶ ገነት ኮሌጅ በፎረስትሪ ሠርተዋል። ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተምረው አጠናቀዋል። ከ2002 ዓ.ም. እስከ 2003 ዓ.ም....

‹‹ሥራችን ተከብሮ እየሠራን ነው ብዬ አስባለሁ›› ወ/ሮ መሠረት ዳምጤ፣ የፌዴራል ዋና ኦዲተር

ቀደም ሲል በተለያዩ ተቋማት በኃላፊነቶች ሲሠሩ የቆዩትና በ2014 ዓ.ም. የፌደራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤትን በዋና ኦዲተርነት እንዲመሩ የተሾሙት  ወ/ሮ መሠረት ዳምጤ፣ በኦዲት ክፍተቶች ላይ...