Thursday, September 21, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በጥራጥሬና ቅባት እህሎች ወጪ ንግድ ከ650 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ተገኘ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የዘርፉ ውጤታማ ላኪዎች ዕውቅና ተሰጣቸው

ዓርብ ኅዳር 19 ቀን 2012 ዓ.ም. በተጀመረው ዘጠነኛው ዓለም አቀፍ የጥራጥሬና ቅባት እህሎች ኮንፈረንስ ላይ ይፋ በተደረገው መረጃ መሠረት በተሸኘው ዓመት ከጥራጥሬና ቅባት እህሎች የወጪ ንግድ 654 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ተገኝቷል፡፡ በዘርፉ ለተሰማሩ ውጤታማ ነጋዴዎችም ዕውቅና ተሰጧቸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ጥራጥሬ፣ ቅባት እህሎችና ቅመማ ቅመሞች አዘጋጆችና ላኪዎች ማኅበር ባዘጋጀው ዓለም አቀፍ ጉባዔ ወቅት እንደተገለጸው፣ የኢትዮጵያን ቅባት እህሎች ለሚገዙ 16 ዋና ዋና አገሮች ከቀረበው ከ261 ሺሕ ቶን ያላነሰ የቅባት እህል ምርት በጠቅላላው ከ388 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ተገኝቷል፡፡

እሥራኤል ከፍተኛ የቅባት እህሎችን በመግዛት ቻይናን አስከትላለች፡፡ እሥራኤል የ22.3 በመቶ የገበያ ድርሻ የያዘችበትን የ58 ሺሕ ቶን የቅባት እህሎች ግዥ ፈጽማለች፡፡ ለዚህም 92 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ ክፍያ ፈጽማለች፡፡ ቻይና በበኩሏ ከእሥራኤል ጋር ተቀራራቢ የምርት መጠን ከኢትዮጵያ ሸምታለች፡፡ ቻይና ከ56,948 ቶን ያላነሰ ምርት በ85.2 ሚሊዮን ዶላር መግዛቷን የማኅበሩ መረጃዎች አመላክተዋል፡፡ የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ በ47.4 ሚሊዮን ዶላር፣ የ29 ሺሕ ቶን የቅባት እህሎችን በመግዛት በሦስተኛ ደረጃ ተቀምጣለች፡፡ ቬትናም፣ ጃፓን፣ አሜሪካ፣ ሲንጋፖር፣ ቱርክ፣ ሳዑዲ ዓረቢያ፣ የመን፣ ሊባኖስ፣ ግሪክ፣ ሜክሲኮ፣ ጂቡቲ፣ ጀርመንና ሌሎችም የኢትዮጵያ የቅባት እህሎች መዳረሻ አገሮች መሆናቸው ታውቋል፡፡

በጥራጥሬ ምርቶች የወጪ ንግድ ረገድ ቀዳሚዋ ተቀባይ አገር የሆነችው ህንድ፣ ከጠቅላላው የጥራጥሬ ምርት ወጪ ንግድ የ32.5 በመቶ ድርሻ የያዘችበትን ግብይት ፈጽማለች፡፡ የ149 ሺሕ ቶን ምርት በ75.6 ሚሊዮን ዶላር ሸምታለች፡፡ ኬንያ ለ36 ሺሕ ቶን ምርት የ13 ሚሊዮን ዶላር ግዥ ፈጽማለች፡፡ ቱርክም በ20.8 ሚሊዮን ዶላር የ34.4 ሚሊዮን ዶላር ግዥ በመፈጸም ከግንባር ቀደሞቹ ተርታ ተቀምጣለች፡፡

የ2011 ዓ.ም. ግብይት በዚህ አግባብ የተስተናገደበት የቅባትና የጥራጥሬ ግብይት ላይ የላቀ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ላኪዎች የዕውቅና አሰጣጥ ሥነ ሥርዓት ተከናውኗል፡፡ የመጀመርያው ዕውቅና የሰጠውም ለቅባት እህል ላኪዎች ሲሆን፣ በዚህ ዘርፍ አምስት ድርጅቶች ዕውቅና አግኝተዋል፡፡ ኪዳነ ማርያም ገብረየሱስ አስመጪና ላኪ ኩባንያ 6‚726 ቶን በማቅረብና የ11 ሚሊዮን ዶላር ገቢ በማስገባት አምስተኛ ደረጃ አግኝቷል፡፡  በአራተኛ ደረጃ የተቀመጠው አልባር ትሬዲንግ የግል ኩባንያ ሲሆን፣ 7,395 ቶን በመላክ 12 ሚሊዮን ዶላር አስገብቷል፡፡ በሦስተኛ ደረጃ ኮማ አስመጪና ላኪ የግል ኩባንያ፣ አሥር ሺሕ ቶን በመላክ 14 ሚሊዮን ዶላር አስገብቷል፡፡ በሁለተኛ ደረጃ የተቀመጠው ዋርካ ትሬዲንግ ሐውስ የግል ኩባንያ 12 ሺሕ ቶን በመላክ 19 ሚሊዮን ዶላር ሲያስገኝ፣ በመጀመርያ ደረጃ የተቀመጠው በላይነህ ክንዴ አስመጪና ላኪ ኩባንያ፣ 13 ሺሕ ቶን ምርት በማቅረብ 21 ሚሊዮን ዶላር ማስገባት ችሏል፡፡

በዘር ላኪ ዘርፍም ዕውቅና የተሰጠ ሲሆን፣ በዚህ ንግድ ዘርፍ የተሸለሙት የህያ ሰዒድ ኡመር የተባሉ ነጋዴ ናቸው፡፡ 1,655 ቶን በማቅረብ ሁለት ሚሊዮን ዶላር አስገብተዋል፡፡

ለሁለት ቀናት በተካሄደውና በቅባት እህሎችና በጥሬጥሬ ምርቶች ላይ ባተኮረው  ኮንፈረንስ ላኪዎች፣ ገዢዎችና አምራቾች መካከል ያለው ግንኙነት የተጠናከረበት እንደነበር በኢትዮጵያ ጥራጥሬ፣ ቅባት እህሎችና ቅመማ ቅመም አዘጋጅቶ ላኪዎች ማኅበር ፕሬዚዳንት አቶ ኃይለ በርሄ ገልጸዋል፡፡

አቶ ኃይለ እንደገለጹት፣ በዚህ ዓመት በተዘጋጀው ኮንፈረንስ ላይ 600 ተሳታፊዎች ከፍለው ተሳትፈዋል፡፡ እንደ እሳቸው ገለጻ ከዚህ በፊት በነበሩት ኮንፈረንሶች ላይ ከ350 በላይ ተሳታፊዎች ተሳትፈው አያውቁም፡፡

አቶ ኃይለ በአሁን ወቅት ያለውን የጥራጥሬና የቅባት እህሎች ምርትን ከጥቂት ዓመታት በፊት ከነበረው ምርት ጋር ሲያነፃፅሩ በቅባት እህል ምርት 100,000 ቶን፣ በጥራጥሬ ደግሞ ከ200,000 ቶን የማይበልጥ እንደተመረተና በአሁኑ ወቅት ደግሞ በቅባት እህሎች እስከ 400 ሺሕ ቶንና በጥራጥሬ ደግሞ በሚሊዮን ቶኖች እንደሚመረት ገልጸዋል፡፡

ዕድገት እንዳለ ቢገልጹም የሚፈለገውን ያህል እንደማይመረት ተናግረዋል፡፡ የዚህንም ችግር ሲገልጹ፣ ‹‹እንደ አገር ችግራችን የአንዳንዱ ሔክታር የምናገኘው ምርታማነት በተፈለገው መጠን እየጨመረ ባለመሆኑ ነው፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹ስለዚህ በዚህ ኮንፈረንስ ከተለያዩ አገሮች ከመጡ ተሳታፊዎች ልምድ የተካፈልንበት ነው፤›› ሲሉም አክለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች