በዋጋ ግሽበት ላይ ወለም ዘለም ሳይባል ሊሠራበት ይገባል፡፡ ገበያው ይህ እንደሚያስፈልግ እየተናገረ ነው፡፡ ለዚህ አሳሳቢ ችግር የዛሬን ብቻ ሳይሆን፣ የነገንም ታሳቢ ያደረገ መፍትሔ በመዘርጋት ለተግባራዊነቱም ስለእውነት መሥራትን የሚጠይቅ ጊዜ መጥቷል፡፡ የግብርና ምርቶች፣ የሸቀጣ ሸቀጥና የአገልግሎት ዋጋዎች ሽቅብ እየወጡ ነው፡፡
በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንግሥት ተጠያቂ የሚደረግባቸው በርካታ ጉዳዮች የመኖራቸውን ያህል ያሻቸውን ዋጋ እየሠሩ መክበር የሚፈልጉ ነጋዴዎችም ለተንጋደደውና ልጓም ላጣው ዋጋ ግሽበት አስተዋጽኦ እያበረከቱ ነው፡፡ እህል ተራ የሄደ ሰው፣ በሁለትና በየሦስት ወራቱ የዋጋ ጭማሪ እያሳቀቀው መድረሻ አጥቷል፡፡ በየወፍጮ ቤቱ እናቶች ቁዘማ ላይ ናቸው፡፡ ምነው ምን ተገኘና ዋጋ ጨመራቹ ሲባሉ ‹‹ምን እናድርግ እኛም ጨምሮብን ነው፤›› ከማለት በቀር ማስረጃ አቅርቡ ቢሏቸው የማይገኝባቸው፣ በየሰበብ አስባቡ ዋጋ በእጥፍ የሚያንሩ በርክተዋል፡፡ የአቋራጭ አሳዳጁ አልቻል ብሏል፡፡ እህል ነጋዴው፣ ትራንስፖርት አቅራቢው፣ ቸርቻሪው፣ አከፋፋዩ፣ ደላላውና ሌላውም ዋጋ ከመጨመር በቀር ሌላ ሥራ ያላቸው አይመስሉም፡፡
በተደራጀና አግባብ ባለው መንገድ ገበያውን እያዩ ችግሮችን ከሥር መሠረታቸው የመቆጣጠርና ዕርምጃ የመውሰድ ልምድ እንብዛም በመሆኑ በላይ በላዩ የሚደረበው አበሳ እየበዛ ነው፡፡ የዋጋ ግሽበት የመንግሥት ፖሊሲ ችግር ወይም የዶላር እጥረት ስላለ ብቻ አይከሰትም፡፡
መንግሥትን በመፈታተን ወይም ገበያውን በመበረዝ ሆነ ብለው የሚንቀሳቀሱ አካላት ተፅዕኖ ይብዛም ይነስም ሌላው የዋጋ ግሽበት ሰበብ ሊሆኑ ይቻላሉ፡፡ ገበያውን ለመረበሽ የሚሞክሩ ጥሩ ማሰብ የራቃቸው ወገኖች አሉ፡፡ በግል ጥቅም አገር የሚያንበረክኩ፣ ጥቂት ማትረፍ እንደኪሳራ የሚከነክናቸው፣ ገበያውን በማጋጋልና ወፍ ዘራሽ ዋጋ መትከል ወደር ያላገኙ ደላሎች፣ ለዋጋ ንረት ብቻም ሳይሆን፣ ለሕዝቡ ብስጭትና ንዴትም ማጠንጠኛዎች ናቸው፡፡ በኢኮኖሚ ባለሙያዎች ሲጠቀሱ የምሰማቸው ዋና ዋና የዋጋ ግሽበት መንስዔዎች እንዳሉ ሁሉ፣ የዋጋ ግሽበት በሚፈለገው ደረጃ ላለመረጋጋቱ ብዙ ምክንያቶችም ይኖራሉ፡፡ የችግሩ ምንጭ ምንም ይሁን ምን መነሻውን በመለየት ገበያውን የማረጋጋቱ ሥራ በመንግሥት ሊታሰብበት ይገባዋል፡፡ መፍትሔ ማፈላለጉ ላይ ካልበረታ ችግሩ ብሶና አብጦ ፖለቲካዊ ይዘት እንዲላበስ ለሚፈልጉ ኃይሎች ሲሳይ ሊዳርገው ይችላል፡፡
በመሆኑም የዋጋና የግብይት ጉዳይ ከመንግሥት ዋና ዋና አጀንዳዎች መካከል አንዱ ሆኖ ሊሠራበት ይገባል፡፡ በትልልቅ አገሮች ውስጥ እኮ የገበያም የዋጋም ቁጥጥር ይደረጋል፡፡ በየገበያ ሱቁ ድንገት እየገቡ የዋጋ ዝርዝር የሚመረምሩ፣ የተለጠፈው ዋጋ ካለፈው ሳምንት በምን ያህል እንደተለወጠ የሚያጠኑና የመሳሰሉትን ክትትሎች የሚያደርጉ መንግሥታትን እዚህ መዘርዘር የሚያስፈልግ አይመስለኝም፡፡ በየአገራቱ የሚዞሩ የእኛ ባለሥልጣናት ይህ አይጠፋቸውምና፡፡
ይሁንና ለዋጋ ግሽበት በተደጋጋሚ ከምንጠቅሳቸው የፖሊሲ ግድፈቶችና ሌሎች ሰው ሠራሽ ችግሮች ባሻገር አንዳንዴም ተፈጥሮም ለዋጋ ግሽበት መንስዔ የምትሆንበት አጋጣሚዎች አለ፡፡
ከሰሞኑ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች እየታየ ያለው ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ ሊጠቀስ ይችላል፡፡ በቁጥጥር ሥር ያልዋለው የአንበጣ መንጋም ቢሆን ዓመታዊ የምርት መጠን ላይ ተፅዕኖ ሊያሳርፍ ይችላል፡፡ እንዲህ ያሉ ያልታሰቡ ክስተቶች ጉዳታቸው የከፋ እንዳይሆን ማሰብ አስፈላጊ ነው፡፡ በምርት ዘመኑ አዝመራው አምሮበት፣ ማሳው ዠረግጎ የተሻለ ምርት እንደሚገኝ በሚታሰበብበት የምርት መሰብሰቢያ ወቅት ያልተፈለገ ዝናብ በመምጣቱ ሳቢያ በቶሎ መሰብሰብ ካልተቻለና ከተበላሸ በዚያው ልክ ገበያ ሊዛባ እንደሚችል ምን ጥርጥር አለው፡፡
በዝናብ ምክንያት ሊደርስ የሚችለውን ጉዳት በአግባቡ ለመቀነስ ካልተቻለና ምርቱ ላይ ተፅዕኖ ካሳረፈ፣ ለዋጋ ግሽበት አዲስ ተፅዕኖ ፈጣሪ ሆኖ ብቅ ሊል መቻሉን ይረዳናል፡፡ ከግብርና ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ የአምበጣ መንጋው አሁንም ሙሉ ለሙሉ መቆጣጠር ያለመቻልን ነው፡፡ ይህንን ያልታሰበ የአምበጣ መንጋ ለመቆጣጠር ባልተቻለበት ወቅት ከሰሞኑ ጊዜውን ያልጠበቀው ዝናብ ምርት ሊያበላሽ ይችላል የሚለውን ሥጋት ከፍ አድርጓል፡፡ አሁንም ሰማዩ ዝም ካላለ የሚበላሸው ምርት አገራዊ የምርት መጠን ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ይፈጥራል፡፡ ይህ ችግር ገበሬውን ይጎዳል፡፡ ምናልባትም ለዋጋ ግሽበት ሌላ ሰበብ ሊሆን እንደሚችል ይጠቁመናል፡፡ ስለዚህ የደረሰ ሰብሎችን የመሰብሰቡን ሥራ ለገበሬ ብቻ መተው የማይችል መሆኑ ነው፡፡ ግብርና ሚኒስቴርና የክልል ግብርና ቢሮዎች ምርት በጊዜ ይሰብሰብ ከሚለው ማስታወቂያ ባሻገር ተባብሮ አደጋውን በመቀነሱ ሥራ ላይ ፈጣን ዕርምጃ ሊወሰዱ ይገባል፡፡
ምርት ለመሰብሰብ ሥራውም በባለሙያ የተደገፈና ኅብረተሰቡን ያሳተፈ ጭምር እንዲሆን ያስፈልጋል፡፡ ሌላው አስቸጋሪ ጉዳይ ደግሞ ያልተጠበቀው ዝናብ አሁንም ይቀጥላል በሚል በአንዳንድ አካባቢዎች ያልደረሱ ምርቶች ጭምር እየታጨዱ ነው መባሉ ነው፡፡ ስለዚህ እንዲህ ያለውን ጉዳይ በባለሙያ በታገዙ ድጋፍ መሰጠትንም ይጠይቃል፡፡ ከሁሉም በላይ ግን የደረሱ ምርቶች በገበሬው ብቻ በመሰብሰብ ወቅቱን ካልጠበቀው ዝናብ ማዳን ስለማይችል አማራቾችን መፈለግ ግድ ይሆናል፡፡ ለምሳሌ በቅርቡ አንዳንድ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ባሉበት አካባቢ አርሶ አደሩን ለመደገፍ ያደረጉት ዓይነት ጥረት በቶሎ መተግበር ይኖርበታል፡፡
የመከላከያ ሠራዊትም ተንቀሳቅሶ አጨዳ ያደረገበት አካባቢም እንዳለ ከመገናኛ ብዙኃን እየሰማን ነው፡፡ አሁን ከተለያዩ አካባቢዎች መረጃዎች እንደሚያሳዩት ደግሞ ወቅቱን ያልጠበቀው ዝናብ የደረሱ ሰብሎች ላይ ጉዳት ሊያደርስ የሚችልበት ዕድል በመሆኑ የግብርና ሚኒስቴር ከሌሎች አካላት ጋር በመሆን ይህንን ሥጋት ለመቀነስና ሰብሉ ሳይበላሽ እንዲሰበሰብ ማስተባበር ይኖርበታል፡፡ በወቅቱ ሰብሉን ካለመሰብሰብ ሊመጣ የሚችለውን ጉዳት ቀድሞ በማሰብ የተለያዩ አማራጮችን መውሰድ የግድ ነው፡፡ በአንዳንድ አካባቢዎች ተማሪዎች ለቀናት ከትምህርት ቤት ቀርተው አጨዳ መግባታቸው ያስገኘውን ውጤት በመገንዘብ እንዲህ ያለውን አሠራር በሌሎች ቦታም መተግበር ያስፈልጋል፡፡ አለበለዚያ እዚያ ብቻ የሚቀር ሳይሆን ሁሉንም ይነካካል፡፡ ይጎዳል፡፡
በትብብር ከተሠራ ምርት ሳይበላሽ መድረስ ከመቻሉም በላይ ለዋጋ መባባስ ምክንያት እንዳይሆን መከላከል ነውና ሁሉም ባለበት የበኩሉን ማለቱ ተገቢ ነው፡፡