Wednesday, July 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናበእስር ላይ የሚገኙት እነ ሜጀር ጄኔራል ክንፈ ዳኘው የ214.4 ሚሊዮን ብር አዲስ...

በእስር ላይ የሚገኙት እነ ሜጀር ጄኔራል ክንፈ ዳኘው የ214.4 ሚሊዮን ብር አዲስ ክስ ተመሠረተባቸው

ቀን:

የአገር መከላከያ ሚኒስቴር ሳይፈልግና ሳይጠይቅ እንዲሁም መመርያን በመጣስ ግምቱ 241,443,021 ብር የሆነ የጦር መሣሪያ ራዳር ግዥ በመፈጸም በመንግሥት ላይ ከባድ ጉዳት አድርሰዋል በማለት፣ የቀድሞ የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) ዋና ዳይሬክተር ሜጀር ጄኔራል ክንፈ ዳኘውን ጨምሮ በአራት ተጠርጣሪዎች ላይ ክስ ተመሠረተ፡፡

የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32(1ሀ)፣ 411(1ሐ) እና (3) ላይ የተደነገገውን በመተላለፍና በሐምሌ ወር 2003 ዓ.ም. ፀድቆ በሥራ ላይ የዋለውን የኮርፖሬሽኑን የግዥ መመርያ ወደ ጎን በመተው፣ ያለ ጨረታና የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ፍላጎት ከሁለት የቻይና ኩባንያዎች 111 ራዳሮች ግዥ እንዲፈጸም ማድረጋቸውን፣ የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ የመሠረተባቸው ክስ ያስረዳል፡፡

ግዥውን የፈጸመውና ከቻይና ኩባንያዎች ጋር አላግባብ የሆነ ውል የፈጸመው ሜቴክ መሆኑን፣ ከቻይና ናሽናል ኤሌክትሮኒክስ ኢምፖርት ኤክስፖርት ኮርፖሬሽን 8,581,092 ዶላር፣ ከኤሮስፔስ ሎንግ ማርች ኢንተርናሽናል ትሬድ ኩባንያ ደግሞ 10,236,700 ዶላር የራዳሮች ግዥ እንዲፈጸም ማድረጋቸውን ዓቃቤ ሕግ በክሱ ዘርዝሮ አስታውቋል፡፡

ግዥው እንዲፈጸም አድርገዋል በማለት ዓቃቤ ሕግ ክስ የመሠረተባቸው የቀድሞ የሜቴክ ዋና ዳይሬክተር ሜጀር ጄኔራል ክንፈ ዳኜ፣ የሃይቴክ ኢንዱስትሪ ሥራ አስኪያጅ ሌተና ኮሎኔል ፀጋዬ አንሙት፣ የቦርድ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ኮሎኔል ሸጋው ሙሉጌታና የሥነ ምግባርና የሕግ ጉዳዮች ኃላፊ የነበሩት ኮሎኔል መሐመድ ብርሃን ኢብራሒም ናቸው፡፡

ተከሳሾቹ ኃላፊነታቸውን ወደ ጎን በመተው ግዥው እንዲፈጸም ያደረጉት፣ በኢንዱስትሪው የኢንጂነሪንግ ቲም ለናሙና የመጣን ራዳር የመከላከያ ሠራዊት ባለበት አካባቢ ለሙከራ ይዞ ሄዶ፣ ራዳሩ ከመከላከያ ሠራዊት የትጥቅ ደረጃ አንፃር ዘመናዊ ያልሆነ፣ ወጣ ገባ ለሆነው የኢትዮጵያ መልክዓ ምድር የማያገለግል መሆኑን ዓቃቤ ሕግ ጠቅሷል፡፡

ሰውን፣ እንስሳትንና ሌሎች ግዑዝ ነገሮችን የማይለይ፣ ከቦታ ቦታ ለማንቀሳቀስ የሚያስቸግርና ሠራዊቱ ያለበት ሥፍራ የኤሌክትሪክ ኃይል የሌለበት በመሆኑ በፀሐይ ኃይል የሚሠራ መሆን ሲገባው በኤሌክትሪክ ቻርጅ የሚሠራ መሆኑንም አክሏል፡፡

በመሆኑም ለሙከራ ቀርበው የነበሩ ራዳሮች እንደማይሆኑ ከሠራዊቱ አስተያየት ተሰጥቶባቸው እያለ፣ 111 ራዳሮች ያላግባብ ተገዝተው ያለ አገልግሎት በሃይቴክ ኢንዱስትሪ መጋዘን ውስጥ እንዲቀመጡ መደረጋቸውን አስረድቷል፡፡ ተከሳሾቹ በፈጸሙት የመንግሥትን ሥራ በማያመች አኳኋን በመምራት ከባድ የሙስና ወንጀል ክስ መሥርቶባቸዋል፡፡

ተከሳሾቹ የክስ መቃወሚያ ካላቸው ለመጠባበቅ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 18ኛ ወንጀል ችሎት ለኅዳር 30 ቀን 2012 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የኤርትራ አቪዬሽን ባለሥልጣን የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራዎችን ማገዱን አስታወቀ

የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ጉዳዩን እያጣራሁ ነው ብሏል በኤርትራ ትራንስፖርትና...

[ክቡር ሚኒስትሩ ከተቋሙ የሠራተኞች ማኅበር አመራር ጋር እየተወያዩ ነው]

ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም! በአስቸኳይ እንደፈለጉኝ መልዕክት ደርሶኝ ነው የመጣሁት። አዎ።...

የሱዳን ጦርነትና የኢትዮጵያ ሥጋት

የሱዳን ጦርነት ከጀመረ አንድ ዓመት ከአራት ወራት አስቆጠረ፡፡ ጦርነቱ...

ግለሰብ ነጋዴዎችን በአስገዳጅነት የንግድ ምክር ቤት አባል ለማድረግ ያለመው ረቂቅ አዋጅ ተከለሰ

በምትኩ የንግድ ተቋማት በአስገዳጅነት የንግድ ምክር ቤት አባል ይሆናሉ...