በኢትዮጵያ በኢንቨስትመንት የተሠማሩ ማናቸውም ባለሀብቶች ለኢንቨስትመንት የሚያስፈልጋቸውን ብድር ከውጭ አገር አበዳሪዎች እንዲያገኙ የሚፈቅድ ረቂቅ አዋጅ ላይ በመወሰን ፓርላማው እንዲያፀድቀው ተላከ።
ረቂቅ አዋጁ በሥራ ላይ የሚገኘውን የኢንቨስትመንት አዋጅ የሚተካ ሲሆን፣ ኅዳር 20 ቀን 2012 ዓ.ም. የተሰበሰበው የሚኒስትሮች ምክር ቤት በረቂቅ አዋጁ ላይ በመወሰን ሕግ ሆኖ እንዲወጣ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንደላከው ታውቋል።
በረቂቅ አዋጁ ድንጋጌ መሠረት ማንኛውም የኢንቨስትመንት ፈቃድ አውጥቶ እየተንቀሳቀሰ ያለ ባለሀብት ከውጭ አገር አበዳሪዎች እንዲበደር የሚፈቅድ ቢሆንም፣ የውጭ ብድር መውሰድ የሚፈልግ ባለሀብት የብድር ስምምነት ከመዋዋሉ በፊት ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በማቅረብ ማስፈቀድና አግባብነት ባለው መመርያ መሠረት ማስመዝገብ እንዳለበት ቅድመ ሁኔታ ያስቀምጣል።
ረቂቅ አዋጁ በዓላማነት ካስቀመጣቸው ግቦች መካከል ወደ አገር ውስጥ የሚገባውን የውጭ ባለሀብቶች ኢንቨስትመንት መጠንና የተሳትፎ መስክ ማስፋት አንዱ ሲሆን፣ የውጭ ብድር መፈቀዱም በአገር ውስጥ ባለው የውጭ ምንዛሪ እጥረትና የኢንቨስትመንት ካፒታል ውስንነት እንዳይስተጓጎል ለማድረግ የታለመ መሆኑ ታውቋል። የውጭ ብድርን ብሔራዊ ባንክ በቅድሚያ አውቆ እንዲመዘግብ የተፈለገውም በአገሪቱ የውጭ ዕዳ ላይ ሊፈጥር የሚችለውን ጫና ለመቆጣጠር እንደሆነም የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
በሌላ በኩል ረቂቅ አዋጁ በኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት ዘርፍ የገንዘብ ሀብትን ሥራ ላይ ከማዋል ባለፈ የዕውቀት፣ የክህሎት፣ የቴክኖሎጂ ሽግግርና ሥርፀትን ማፋጠን ሌላው የዓላማው መዳረሻ አድርጓል።
በዚህም መሠረት የውጭ ኩባንያዎች ከአገር ውስጥ ባለሀብቶች ጋር የቴክኖሎጂ ሽግግር ትብብር ስምምነት በመፈጸም፣ በረቂቅ የኢንቨስትመንት ሕጉ የሚሸፈኑ ጥቅሞችን ማግኘት ይችላሉ።
በረቂቁ ድንጋጌ የቴክኖሎጂ ሽግግር ትርጓሜ የተሰጠው ሲሆን፣ “የቴክኖሎጂ ሽግግር ማለት ምርትን ለማምረት ወይም የአመራረት ሒደትን ተግባራዊ ለማድረግ ወይም ለማሻሻል ወይም አገልግሎትን ለመስጠት የሚረዳ ሥርዓት ያለው ዕውቀት ማስተላለፍ ሲሆን፣ የሥራ አመራርና የቴክኒክ ዕውቀት እንዲሁም የግብይት ሁኔታ ቴክኖሎጂንም ይጨምራል፡፡ ሆኖም ዕቃዎችን ብቻ ለመሸጥ ወይም ለማከራየት የሚደረግን ግንኙነት አይሸፍንም፤” ይላል።
ማንኛውም ባለሀብት ከኢንቨስትመንቱ ጋር በተያያዘ የሚዋዋለውን የቴክኖሎጂ ሽግግር ስምምነት በኮሚሽኑ ማስመዝገብ እንደሚኖርበት፣ ያልተመዘገበ የቴክኖሎጂ ሽግግር ስምምነት በኢንቨስትመንት ኮሚሽን ዘንድ ሕጋዊ ዕውቅና እንደማይኖረው ያመለክታል።
ማንኛውም ባለሀብት ለሕግ፣ ለሞራል፣ ለማኅበረሰብ ጤና ወይም ደኅንነት ተፃራሪ ካልሆነ በስተቀር በማናቸውም የኢንቨስትመንት መስክ መሠማራት እንደሚችል የሚደነግገው ረቂቁ፣ ለአገር ውስጥ ባለሀብቶች የተከለሉ ተብለው ከሚከለከሉ ዘርፎች በስተቀር፣ ሁሉም የኢንቨስትመንት መስኮች ለውጭ ባለሀብቶች ክፍት እንደሚሆኑ ይገልጻል።
ይህ ቢሆንም በአየር ትራንስፖርት አገልግሎት፣ በኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት ወይም ማስተላለፍ ወይም ማሠራጨት አገልግሎት፣ በኮሙዩኒኬሽን አገልግሎትና በፋይናንስ አገልግሎት ሥራዎች ላይ ለሚሰማሩ ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ የመስጠት፣ የማደስ፣ የማሻሻል፣ የመለወጥ፣ የመተካት፣ የመሰረዝና የኢንቨስትመንት ማስፋፊያ ወይም ማሻሻያ ፈቃድ የመስጠት ኃላፊነት በሕግ ሥልጣን የተሰጣቸው የመንግሥት ተቋማት መሆኑን ያመለክታል።