“ወርቃማ አክሲዮን” ድምፅን በድምፅ የመሻር መብት ያጎናፅፋል
የሚሸጠውን የልማት ድርጅት ሠራተኞች በቅናሽ ዋጋ አክሲዮን እንዲገዙ ሊፈቀድላቸው ይችላል
የሚኒስትሮች ምክር ቤት ቅዳሜ ኅዳር 20 ቀን 2012 ዓ.ም. ባካሄደው ስብሰባ በሙሉና በከፊል ለግሉ ዘርፍ በሽያጭ እንዲተላለፉ በታቀዱ የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ውስጥ፣ መንግሥት የ“ወርቃማ አክሲዮን” ባለቤት በመሆን ሽያጩን እንዲያከናውን የሚፈቅድ ረቅቅ አዋጅ አፀደቀ፡፡
መንግስት የ“ወርቃማ አክሲዮን” ባለቤት በመሆን የልማት ድርጅቶቹን እንዲሸጥ የሚፈቅደው ረቂቅ የሕግ ሰነድ የተዘጋጀው በገንዘብ ሚኒስቴር ሲሆን፣ ሰነዱም “ረቂቅ የፕራይቬታይዜሽን አዋጅ” የሚል ስያሜ የያዘ ነው፡፡
የሚኒስትሮች ምክር ቤት በቀረበለት በዚህ ረቂቅ አዋጅ ላይ ተወያይቶ እንዳፀደቀውና ሕግ ሆኖ እንዲወጣም ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንደተላከ፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ቃል አቀባይ ጽሕፈት ቤት ያወጣው መረጃ ያመለክታል፡፡
ሪፖርተር ያገኘው የረቂቅ አዋጁ ቅጂ “ወርቃማ አክሲዮን” የሚለውን ሐረግ ለዚሁ ዓላማ ብቻ እንዲውል በማድረግ ትርጓሜ ሰጥቶታል፡፡
በረቂቅ አዋጁ መሠረት “ወርቃማ አክሲዮን“ ማለት የመንግሥት የልማት ድርጅትን በመለወጥ የካፒታሉ አካል የሆነና በማናቸውም የቦርድ ውሳኔ ላይ ድምፅ የመስጠትና ድምፅን በድምፅ የመሻር መብቶችን ለመንግሥት የሚያጎናፅፍ፣ በአክሲዮን መመሥረቻ ጽሑፍ ውስጥ የተደነገጉ ልዩ መብቶችን የያዘ አክሲዮን ነው የሚል ትርጓሜ ተሰጥቶታል።
የ“ወርቃማ አክሲዮን” ባለቤትነትን መያዝ የሚችለው መንግሥት ብቻ እንደሆነ፣ ይህም የሕዝብ ጥቅም ያለባቸው የመንግሥት ልማት ድርጅቶች አብላጫ ወይም ወሳኝ የሆኑ አክሲዮኖች እንዲሸጡ በሚወሰንበት ጊዜ፣ መንግሥት “ወርቃማውን አክሲዮን” በመምረጥ ለራሱ ማስቀረት ያስችለዋል።
“ወርቃማ አክሲዮን” መንግሥት የሕዝብ ጥቅምን አያስጠብቅም ብሎ ባመነበት በማናቸውንም የቦርድ ውሳኔ ላይ ድምፅ የመስጠት፣ ድምፅን በድምፅ የመሻር መብት እንደሚያጎናፅፈውም የረቂቁ ድንጋጌ ያመለክታል።
የመንግሥት የልማት ድርጅትን ወደ ግል ማዘዋወር ያልተቻለ እንደሆነ፣ ተቆጣጣሪው ባለሥልጣን አግባብ ባላቸው የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ሕግ መሠረት ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ጥያቄ አቅርቦ ሲፀድቅለት የመንግሥት የልማት ድርጅቱ ሊፈርስ ይችላል፡፡
ረቂቁ ፕራይቬታይዜሽን የሚፈጸምባቸውን ሥልቶችንን የሚያስቀምጥ ሲሆን፣ የሥልቶቹ አተገባበርም በግልጽነት መርሆዎች ላይ የተመሠረተና ግቡም ለመንግሥት ተስማሚ የሆኑ ስምምነቶች ላይ መድረስ እንደሆነ ያመለክታል።
ከተዘረዘሩት የፕራይቬታይዜሽን ሥልቶች መካከልም በውድድር ላይ የተመሠረተ ጨረታ፣ ለሕዝብ ክፍት የሆነ ጨረታ፣ የአክሲዮን ገበያ ወይም ሌሎች ተስማሚ የግብይት መድረኮች፣ በረዥም ጊዜ ተከፋፍሎ የሚሸጥ የተሰበጣጠረ የአክሲዮን ግዥ ይገኙበታል። ከላይ የተዘረዘሩት የፕራይቬታይዜሽን ሥልቶች በዋናነት ተግባራዊ የሚደረጉ መሆናቸው እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ፕራይቬታይዜሽኑን እንዲያከናውን ሥልጣን የሚሰጠው ኤጀንሲ ከገንዘብ ሚኒስቴር ፈቃድ ማግኘት አለበት፡፡ ተስማሚና ለኢንዱስትሪው ደረጃ የሚመጥን የንግድ ወይም የስትራቴጂ ሽያጭን በተመለከተ በቅድሚያ በተመረጡ አነስተኛ ቁጥር ባላቸው የኮርፖሬት ኢንቨስተሮች ላይ ያነጣጠረ፣ ወይም ለውስጥ ሰዎች የሚደረጉ ሽያጮችን የመሳሰሉ ሌሎች የፕራይቬታይዜሽን ሥልቶችን መምረጥ እንደሚችል ድንጋጌው ያመለክታል።
ከዚህ በተጨማሪም ከሚሸጡት አክሲዮኖች ውስጥ የተወሰኑትን ለመንግሥት የልማት ድርጅት ሠራተኞች በቅናሽ ዋጋና በረዥም ጊዜ በሚፈጸም ክፍያ እንዲሸጡ ሊደረግ እንደሚችልም ተመልክቷል። ለዚህ ሲባልም የገንዘብ ሚኒስቴር ኤጀንሲው ጋር በመመካከር፣ ለመንግሥት የልማት ድርጅቱ ሠራተኞች ተለይተው የሚያዙትን የአክሲዮኖች ዋጋና መጠን እንዲወሰን በረቂቁ ሥልጣን ተሰጥቶታል።
የአክሲዮን ድርጅቶች ምሥረታን በተመለከተ በንግድ ሕጉ አንቀጽ 307(1) የተደነገገው ቢኖርም፣ አንድን የመንግሥት የልማት ድርጅት ለፕራይቬታይዜሽን ዝግጁ ለማድረግ በአንድ ባለአክሲዮን ባለቤትነት ወደሚያዝ የአክሲዮን ማኅበርነት እንዲለወጥ ሊደረግ እንደሚችልም በረቂቁ ተመልክቷል።
የልማት ድርጅቱ ወደ አክሲዮን ማኀበርነት በሚለወጥበት ወቅት የድርጅቱ ካፒታል በአክሲዮኖች ተከፋፍሎ አክሲዮኖቹ ወደ ግል ይዞታ በሽያጭ እስከሚዘዋወሩ ድረስ፣ በመንግሥት እንደሚያዙና ወደ አክሲዮን ማኅበርነት የተለወጠ የመንግሥት የልማት ድርጅትም ህልውናው እንደሚያከትም ይገልጻል። የልማት ድርጅትን በሙሉ ወይም የተወሰነ ክፍል፣ ወይም ንብረት ወይም የመንግሥት አክሲዮንን ወደ ግል ለማዘዛወር በቅድሚያ ዋጋው ገለልተኛ በሆነ ብቃት ባለው ባለሙያ እንዲተመን የሚደረግ መሆኑንም ያመለክታል።
በፕራይቬታይዜሽን የተገኘ ገቢ ሽያጩን ለማከናወን የወጣው ወጪ ተቀንሶ ለኢንዱስትሪ ልማት ፈንድ ገቢ እንደሚደረግም በረቂቁ የተደነገገ ሲሆን፣ በዚህ መሠረት እንዲሸጥ ቀርቦ ገዥ ያላገኘ የልማት ድርጅትን በተመለከተ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ቀርቦ የልማት ድርጅቱ እንዲፈርስ ውሳኔ ሊሰጥበት እንደሚችል ረቂቁ ይደነግጋል።
መንግሥት በሙሉና በከፊል እንዲሸጡ ውሳኔ ካሳለፈባቸው የልማት ድርጅቶች መካከል ኢትዮ ቴሌኮም፣ የስኳር ፋብሪካዎች፣ የኃይል ማመንጫዎች፣ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን፣ የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎትና የኢትዮጵያ አየር መንገድ እንደሚገኙበት ይታወሳል።