በሶማሌ ክልል ዋና ከተማ ጅግጅጋና ሌሎች ከተሞች ከሐምሌ 26 እስከ 30 ቀን 2010 ዓ.ም. በተፈጸመ የበርካታ ሰዎች ግድያ፣ አካል ጉዳት፣ የሃይማኖት ተቋማት ቃጠሎ፣ የንብረት ውድመት፣ ማፈናቀልና ሌሎችም ወንጀሎች ክስ በተመሠረተባቸው የክልሉ የቀድሞ ፕሬዚዳንት አቶ አብዲ መሐመድን ጨምሮ በ47 ተከሳሾች ላይ የምስክሮች ቃል መስማት ሊጀመር ነው፡፡
ከፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አራተኛ ወንጀል ችሎት ኅዳር 22 ቀን 2012 ዓ.ም. በሰጠው ትዕዛዝ እንዳስታወቀው፣ ክስ ተመሥርቶባቸው በፌዴራል ማረሚያ ቤት በሚገኙት አቶ አብዲና ሌሎችም ተከሳሾች ላይ፣ እንዲሁም በሌሉበት ክስ ቀርቦባቸው በጋዜጣም ጥሪ ቢደረግላቸው ሊቀርቡ ባልቻሉት ላይ የምስክሮች ቃል ከጥር 14 እስከ 22 ቀን 2012 ዓ.ም. ድረስ ይሰማል፡፡
ፍርድ ቤቱ ቀደም ባሉት ችሎቶች በሰጠው ትዕዛዝ አሥር ተጠርጣሪዎች በጋዜጣ እንዲጠሩ፣ ሦስት ተጠርጣሪዎች ደግሞ የፌዴራል ፖሊስና የክልሉ ፖሊስ ተባብረው ይዘው እንዲያቀርቡ ትዕዛዝ ሰጥቶ ነበር፡፡
በጋዜጣ የተጠሩት ባለመቅረባቸውና እንዲያዙ ትዕዛዝ ከተሰጠባቸው ውስጥ ሁለቱ ከአገር ውጪ መሆናቸው በመገለጹ፣ በሌሉበት የምስክሮች ቃል እንዲሰማ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡