የአፍሪካ ኅብረት ባዘጋጀው አፍሪካን ከኢቦላ የመቋቋም ፎረም ላይ ከ55 ሚሊዮን ዶላር በላይ ድጋፍና የተለያዩ ዕርዳታዎችን ለመስጠት የአፍሪካ ኅብረት አባል አገሮችና አጋሮች ቃል ገቡ፡፡
ሰኞ ኅዳር 22 ቀን 2012 ዓ.ም. በተካሄደውና በአፍሪካ ኅብረት ሊቀመንበር ሙሳ ፋቂ በተመራው መርሐ ግብር፣ በዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ እየተሠራጨ የሚገኘውን የኢቦላ ቫይረስ እስከወዲያኛው ለማስቆም የሚሆን ድጋፍ ከአፍሪካ ኅብረት አባል አገሮችና አጋር አገሮች ለመሰብሰብ ነበር፡፡
የአፍሪካ ኅብረት የማኅበራዊ ጉዳዮች ኮሚሽነር አሚራ ኤልፋዲል፤ መርሐ ግብሩ የተሳካ እንደነበርና ተሳታፊዎቹ በገንዘብ እንዲሁም ከገንዘብ ውጪ ያሉ ድጋፎችን ለማበርከት ቃል መግባታቸውን ገልጸዋል፡፡
ከሁሉም ተሳታፊዎች አንድነትን እንዳዩ የገለጹት ኮሚሽነሯ፣ መርሐ ግብሩ የዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎን መንግሥት ኢቦላን ለመከላከልና ለማጥፋት በሚያደርገው ዝግጁነትና አቅም ግንባታ ላይ ድጋፍ ለማድረግ ያለመ ነው ብለዋል፡፡
እሳቸው እንደገለጹት፣ ቃል ከተገባው 55 ሚሊዮን ዶላር ውስጥ ትልቁን ቦታ የያዘው የአውሮፓ ኅብረት ድጋፍ ነው፡፡ ቻይና አንድ ሚሊዮን ዶላር እንዲሁም የአፍሪካ ኅብረት አንድ ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ለማድረግ ቃል ከገቡት መካከል እንደሆኑ ታውቋል፡፡
ከገንዘብ ውጪ ስለተደረገው ድጋፍም ሲገልጹ፣ የተለያዩ የአፍሪካ ኅብረት አጋር አገሮች በሰው ኃይል፣ በሕክምና ቁሳቁሶች፣ በመድኃኒቶች እንዲሁም በሰው ኃይል አቅም ግንባታ ላይ ድጋፍ ለማድረግ ቃል ገብተዋል፡፡
በመጪው ጥር ወር ተመሳሳይ መርሐ ግብር እንደሚኖር፣ ይህም እንዲሁ የተለያዩ የአፍሪካ አገሮችን ለመደገፍ የሚካሄድ እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡
የኢቦላ ቫይረስ ለመጀመርያ ጊዜ የተከሰተው በ1976 ዓ.ም. ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት በአብዛኛው በማዕከላዊና ምዕራብ አፍሪካ አገሮች ገጠራማ አካባቢዎች እየተሠራጨ ይገኛል፡፡ በተለይ በዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ ሱዳን፣ ጋቦን፣ አይቮሪኮስት እንዲሁም ዩጋንዳ በሽታው በተደጋጋሚ ሲከሰት ታይቷል፡፡
የዓለም የጤና ድርጅት በቅርብ ባወጣው መረጃ መሠረት፣ እስካሁን በዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ብቻ 3‚313 ኬዞች ያጋጠሙ ሲሆን፣ ከዚህ መሀል 3‚195 ኢቦላ መሆኑ ተረጋግጧል፡፡ ከእነዚህም 2200 ሲሞቱ፣ 1078 ድነዋል፡፡ የተቀሩት በሕክምና ክትትል ላይ ናቸው ተብሏል፡፡