ከሃምሳ አምስት ዓመታት በፊት የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት የነበሩት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ሀንጋሪን ሲጎበኙ ቀልባቸውን የገዛ አንድ ነገር ተመለከቱ፡፡ ይህም በመዲናዪቱ ቡዳፔስት ሙዚቃን በዘመናዊ መሣርያ የሚቀረፁ ሙያተኞችን ማስተዋላቸው ነው፡፡ በዝምታ ማለፍ አልወደዱምና የሀንጋሪ መንግሥት በኢትዮጵያ ያለውን ባህላዊ ሙዚቃ በሳይንሳዊ ዘዴ የሚቀርፁ ባለሙያዎችን ልኮ እንዲሰንድላቸው ጠየቁ፣ እሺታንም አገኙ፡፡
ጃንሆይም በተጓዙበት በ1957 ዓ.ም. ሀንጋሪያውያኑ የምስልና የድምፅ ቀረፃ ባለሙያዎች ጊዮርጊ ማርቲን እና ባሊን ሳሮሲ ኢትዮጵያ በመምጣት በተለያዩ አካባቢዎች በመዘዋወር ሙዚቃን በምስል፣ በድምፅና በጽሑፍ ሰነዱ፡፡
የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር በድረ ገጹ እንደገለጸው፣ ሀንጋሪያውያን ሙያተኞቹ ጆርጅ ማርቲንና ባልቲን ሳሮሲ በወቅቱ በኢትዮጵያ የተለያዩ በርካታ ከተሞች በመዘዋወር ነበር ሲቀርፁ የቆዩት፡፡
በዚህም ከሦስት ሺሕ ሜትር በላይ ርዝመት ያላቸው የፊልም ክሮች፣ ከ40 ሰዓታት በላይ ድምፅ፣ ከ100 በላይ ምስሎችንና ከ200 ገጽ በላይ ጽሑፎችን ቀርፀው የነበረ ሲሆን በሀንጋሪ ዋና ከተማ ቡዳፔስት በሚገኘው በሀንጋሪ ሳይንስ አካዴሚ የሙዚቃ ጥናት ተቋም ውስጥ የባህላዊ ሙዚቃና ውዝዋዜዎች ቤተ መዛግብት ተቀምጦ የነበረ ነው፡፡
ኮነክቲንግ ኮሌክሽንስ (Connecting Collections) በተሰኘ ድረ ገጽ እንደተጻፈው፣ ጊዮርጊ ማርቲን የሀንጋሪን ባህላዊ ዳንሶች በማጥናትና በመመርመር የተጠመደ ባለሙያ ሲሆን፣ ከጃንሆይ የቀረበውን ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት ከባልደረባው ባሊን ሳሮሲ ጋር ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት ለሁለት ወራት ጥናትና ምርምሩን ሲያከናውን ቆይቷል፡፡ የባህላዊ ግንኙነት ተቋም የጉዟቸውን ወጪ ሲሸፍንላቸው የኢትዮጵያ መንግሥትም የአገር ውስጥ ጉዟቸውን አመቻችቶላቸዋል፡፡
ሁለቱ ባለሙያዎች ከግንቦት 30 እስከ ሐምሌ 26 ቀን 1957 ዓ.ም. በነበራቸው ቆይታ በስምንት ጠቅላይ ግዛቶች (ሸዋ፣ ወሎ፣ ትግራይ፣ ቤጌምድር፣ ጎጃም፣ ወለጋ፣ ከፋና ሐረርጌ) በአሥራ ሰባት ከተሞች (ደብረ ብርሃን፣ ደሴ፣ ሐይቅ፣ ውጫሌ፣ ውርጌሳ፣ ወልዲያ፣ ኮረም፣ መቐለ፣ አክሱም፣ እንዳ ሥላሴ፣ ጎንደር፣ ደብረ ማርቆስ፣ ለቀምት፣ ጅማ፣ ሐረር፣ ዓለማያና ድሬዳዋ) በመዘዋወር ባህላዊ ሙዚቃዎችን በምስልና በድምጽ፣ በጽሑፍ ሰንደዋል፡፡
ባለውለታዎቹ ሲገለጹ
ከ55 ዓመታት በፊት ኢትዮጵያ መጥተው በየጠቅላይ ግዛቱ በላንድሮቨር በመዘዋወር የኢትዮጵያን የባህል ሙዚቃና ሙዚቀኞችን ዳንኪረኞችን ያጠኑና የመረመቱት ሀንጋሪያውያን ባሊን ሳሮሲና ማርቲን ጊዮርጊ ናቸው፡፡
የፎክሎር ባለሙያው ሳሮሲ በአሁኑ ወቅት የ95 ዓመት አረጋዊ ሲሆኑ በሙዚቃ ሳይንስ፣ በቅመራ (ኮምፖዚሽን) እስከ ዱክትርና ድረስ ተምረዋል፡፡ የመላዋን ሀንጋሪ ባህላዊ ሙዚቃ ሰብሳቢው መሰነዳቸው ይወሳል፡፡ በ1975 ዓ.ም. ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት ጊዮርጊ በባህላዊ ዳንኪራነታቸው የሚታወቁና ‹‹ኢንጂነር ዳንሰር›› እስከ መሰኘት ደርሰዋል፡፡ የሀንጋሪን ሥነ ጽሑፍ፣ ሰዋስው፣ ኢትኖግራፊና የሙዚየም ጥናት ትምህርትን ተምረው አጠናቀዋል፡፡
ባህላዊ ውዝዋዜና ባህላዊ ሙዚቃዎችን የያዘ ተንቀሳቃሽ ምስልና ልዩ ልዩ ሰነዶች በዘመናዊ መንገድ ዲጂታላይዝ ተደርገ ለኢትዮጵያ መንግሥታቸውን ወክለው በስጦታ ያበረከቱት የሀንጋሪ አምባሳደር አቲላ ኮፓኒ ሲሆኑ፣ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ሒሩት ካሳው (ዶ/ር) ታሪካዊ ተንቀሳቃሽ ምስሎቹንና ሰነዶቹን ተረክበዋል፡፡
በርክክቡ ወቅት ሀንጋሪና ኢትዮጵያ ታሪካዊ ግንኙነታቸውን ይበልጥ ማጠናከር በሚችሉባቸው በተለይ በባህላዊ እሴቶችና በስፖርት ዘርፍ በጋራ መሥራት በሚችሉባቸው ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል፡፡ በቀጣይ እነዚህንና ሌሎች ትብብሮችን ለመፈጸም የሚያስችሉ የመግባቢያ ሰነዶች እንዲዘጋጁ መስማማታቸውን ሚኒስቴሩ አስታውቋል፡፡