Sunday, June 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹መንግሥት ሰብዓዊ ድጋፍ ለሚያደርጉ ድርጅቶች ነፃ መድረክ በመፍጠሩ የተሻለ ኃላፊነት ይጠበቅብናል›› አቶ ዳንኤል አበበ፣ የሲሲአርዲኤ ሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ

ከሠላሳ አምስት ዓመት በፊት፣ 1977 ዓ.ም. እንደማንኛውም ዓመት ተጠርቶ የሚታለፍ ቁጥር አይደለም፡፡ ያ ዘመን ለኢትዮጵያውያን የፍዳ፣ የረሃብና የጠኔ ምልክት ነበር፡፡ በዘመኑ የነበሩ፣ ያልነበሩም የሚያውቁት ክፉ ወቅት ነው፡፡ እስከ ሁለት ሚሊዮን የሚደርስ የሰሜኑ ነዋሪ በ1977 ዓ.ም. በድርቅ በረሃብ አልቋል፡፡ ኢትዮጵያ የዓለም መገናኛ ብዙኃንን ትኩረት የሳበችበት፣ ዜጎች በአጥንት ቀርተው ለሞት ሲያጣጥሩ የተቀረፁበት፣ አሰቃቂና የአገርን ገመና ደጅ ያዋለ ክስተት ነበር፡፡ ለሰብዓዊ ዕርዳታ ያደሩ ዜጎች ለዕርዳታ እጃቸውን ዘርግተዋል፡፡ የተለያዩ አገር በቀል ግብረ ሰናይ ድርጅቶች እየተቋቋሙ ጠኔ ያዳከመውን ወገን ለመርዳትም ጥረት ሲያደርጉ እንደነበር ታሪክ ያስታውሳል፡፡ ከእነዚህ ተቋማት መካከል የቀድሞው የክርስቲያን በጎ አድራጎት ድርጅት የአሁኑ  የክርስቲያን በጎ አድራጎትና ልማት ማኅበራት ኅብረት (ሲሲአርዲኤ) ተጠቃሽ ነው፡፡ ድርጅቱ በወቅቱ የሰብዓዊ አገልግሎትና የተለያዩ ድጋፎችን በማድረግ ሥራ መጀመሩን ከድርጅቱ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡ ኅብረቱ የሚሰጣቸውን አገልግሎቶች በተመለከተ ሔለን ተስፋዬ የድርጅቱን የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ ዳንኤል አበበን አነጋግራቸዋለች፡፡

ሪፖርተር፡- የክርስቲያን በጎ አድራጎትና ልማት ማኅበራት ኅብረት ከተቋቋመ ምን ያህል ጊዜ ሆነው?

አቶ ዳንኤል፡- ሲሲአርዲኤ ከተቋቋመ 47 ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡ ኅብረቱ ከ1977 ዓ.ም. በፊት በወሎና አካባቢው በ1965 ዓ.ም. እና በ1966 ዓ.ም ረሃብ በመከሰቱ ምክንያት የተቋቋመ ድርጅት ነው፡፡ በእነዚህ ጊዜያትም ከተለያዩ አጋር ድርጅቶች ጋር በመተባበር ሴት ሕፃናትን ብሎም ማኅበረሰቡን በመደገፍ እስካሁን እየሠራ ይገኛል፡፡ እንደ ማኅበር ከጊዜ ወደ ጊዜ ሥራዎቹንና ማኅበረሰቡ የሚያስፈልገውን ድጋፍ በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡  

ሪፖርተር፡- ምን ያህል አባል ድርጅቶች አሉት?

አቶ ዳንኤል፡- ክርስቲያን በጎ አድራጎትና ልማት ማኅበራት ኅብረት በሥሩ ከ400 የሚበልጡ አባል ድርጅቶች አሉት፡፡ ከአገር በቀል ድርጅቶች መካከል በጤና፣ በአካባቢ ጥበቃና በአየር ንብረት ለውጥ፣ በሲቪል ማኅበራት፣ በሰብዓዊ ቀውስ ላይ ከሚሠሩ ድርጅቶች ጋርም በጋራ የሚሠራ ሲሆን፣ በተጨማሪ አክሽን ኤይድና ሌሎች ዓለም አቀፍ ድርጅቶችን በውስጡ ይይዛል፡፡    

ሪፖርተር፡- አገር በቀል ድርጅቶችን በምን መልኩ ነው የምትደግፉት?

አቶ ዳንኤል፡- አገር በቀል ድርጅቶች የተዘረዘሩት ብቻ አይደሉም፣ ብዙ ናቸው፡፡  ቁሳዊና የገንዘብ ድጋፍ ይደረጋል፡፡ እንዲሁም ሌሎች ቴክኒካል ድጋፎችን በመስጠት ተቋማቱ ጠንካራ እንዲሆኑ ለማድረግ የሚጥር ድርጅት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ድርጅቶቹስ በምን መልኩ ነው ዕገዛ የሚያደርጉት?

አቶ ዳንኤል፡- አባል ድርጅቶች በገንዘብ ያግዙናል፡፡ ድርጅቶቹ በዛ ስለሚሉና የተለያዩ ሐሳብ ያላቸው በመሆኑ በቀላሉ ገንዘቡ ጥቅም ላይ ይውላል፡፡ ለምሳሌ ስምንት ዓይነት መድረኮች አሉን፡፡ ታዲያ መድረኮችን ማዘጋጀት ብቻ ሳይሆን እርስ በርስ እንዲተዋወቁና መረጃ እንዲለዋወጡ ሲሲአርዲኤ ድጋፍ ያደርግላቸዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ከተለያዩ ዓለም አቀፍ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ከሚገኘው ፈንድ ጥሩ እንቅስቃሴ ለሚያደርጉ አገር በቀል ድርጅቶች ድጋፍ በማድረግ ያበረታታል፡፡

ሪፖርተር፡- እነዚህ አባል ድርጅቶች የት ነው የሚገኙ?

አቶ ዳንኤል፡- አባል ድርጅቶቹ በአራቱም የኢትዮጵያ አቅጣጫዎች ይገኛል፡፡ ድርጅቶቹ ሐሳቦቻቸው የተለያየ ስለሆነ እንደተነሱበት ሐሳብ የምንሰጣቸው ድጋፎችም ይለያያል፡፡ ዓላማቸው በጎ ሥራ ስለሆነም ሁል ጊዜም ከጎናቸው ሆነን እንደግፋቸዋለን፡፡ እነዚህ ድርጅቶች የውኃ አቅርቦት፣ ለበረሃነት የተጋለጡ ቦታዎች የሚያለሙ፣ ገጠር ድረስ ገብተው የማኅበረሰብ ጤና ላይ የሚሠሩ ናቸው፡፡ እነዚህን ለማበረታታት፣ በቂ ችሎታና አቅም እንዲያገኙ በሲሲአርዲኤ በኩል ኃላፊዎቻቸው የድኅረ ምረቃ የትምህርት ዕድል እንዲያገኙ፣ የቴክኒካል ድጋፍ ጨምሮ የተለያዩ አቅምን ለማጎልበት ከዩኒቨርሲቲዎችና ምሁራን ጋር በመተባበር እነርሱን የማብቃት ሥራ እንሠራለን፡፡

ሪፖርተር፡- ይኼን ድጋፍ ካደረጋችሁ በኋላ ውጤቱን በምን መልኩ ነው የምታረጋግጡት?

አቶ ዳንኤል፡- የእያንዳንዱ አባል ድርጅት እንቅስቃሴ በሁለት ዓመት አንዴ የሚገመገምበት ሒደት አለ፡፡ ይኼን ሒደት የሚሠሩበት ቦታ ድረስ በመሄድ የማጣራት ሥራም ጭምር እንሠራለን፡፡ ግምገማ ብቻ ሳይሆን ድርጅቱን የመገምገሚያ መሥፈርት አውጥተን መልካም ተሞክሮ ያለውን ድርጅት የምንሸልምበት ሒደት ጭምር አለን፡፡ የተሸለሙ ድርጅቶችም መልካም ተሞክሯቸውን ለሌለው የሚያካፈሉበት ሁኔታ ይመቻቻል፡፡

ሪፖርተር፡- ውጤቱስ ምን ያህል ነው?

አቶ ዳንኤል፡- እስካሁን እጅግ በጣም ጥሩ ውጤት እያስመዘገብን ነው፡፡ ነገር ግን በመንግሥት ብዙም ዕይታ ውስጥ አልገባም፡፡

ሪፖርተር፡- ዕይታ ውስጥ ያልገባው ለምን ይመስላችኋል?

አቶ ዳንኤል፡- ዕይታ ውስጥ ያልገባው በሁለት ምክንያት ነው፡፡ ድርጅቱ በራሱ መንግሥት እንዲያውቀው ያደረገው ጥረት አነስተኛ መሆኑና ቀድሞ የነበረው የሲቪል ማኅበራት አዋጅ እንቅፋት ሆኖ መቆየቱ ነው፡፡ አሁን ግን የሲቪል ማኅበራት አዋጅ በመሻሻሉ በምንፈልገው መልኩ የሚዲያ ሽፋን ማግኘት እንችላለን፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ወጥተን ሥራችንን በአግባቡ እንድንሠራ ክፍት ሆኗል፡፡ ድርጅቱ ያሉት አባል ድርጅቶች ዘርፈ ብዙ ሥራ ነው የሚሠሩት፣ ለምሳሌ ገጠር ድረስ ዘልቀው ተላላፊ የሆኑና ያልሆኑ በሽታዎች ላይ ይሠራሉ፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን መንግሥት መድረስ ያልቻለባቸው ቦታዎች ድረስ የሚገቡ በመሆናቸው ለልማት የሚያደርጉት አስተዋጽኦ ከፍተኛ ስለሆነ የመንግሥት ዓይን እንዳይለየው እላለሁ፡፡ መንግሥት የሰብዓዊ ድጋፍ ለሚያደርጉ ድርጅቶች ነፃ መድረክ በመፍጠሩ ከዚህ የተሻለ ሥራና ኃላፊነት ይጠበቅብናል ብለንም እናምናለን፡፡ ከዚህ ቀደም የነበረው የበጎ አድራጎት ድርጅቶች የራሳቸው ሀብት እንዳያካብቱ የሚደነግግ ነበር፡፡ ይህ በመሻሻሉ ይበልጥ እንድንሠራ የሚደግፍ ይሆናል፡፡

ሪፖርተር፡- በማኅበረሰቡ ዘንድ ተቀባይነቱ እስከ ምን ድረስ ነው?

አቶ ዳንኤል፡- በማኅበረሰቡ ከፍተኛ ተቀባይነት አለው፡፡ ምክንያቱም መንግሥት መሠረተ ልማት ባላደረሰበት ቦታ ሄዶ የተለያዩ አገልግሎቶችን ይሰጣል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ማኅበረሰቡ ገምጋሚም፣ ተቺም፣ አበረታችም ነው፡፡ ጉድለት ሲገኝም ስለሚነግሩንና ስለምናስተካክል ተቀባይነቱ ከፍተኛ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ድጋፋችሁ ምን ያህል ነው?

አቶ ዳንኤል፡- ይኼ ድርጅት በዓመት ከ10 ቢሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ያደርጋል፡፡ መንግሥት ደግሞ በተለያዩ ነገሮች ድጋፍ ቢያደርግ፣ የበለጠ መሥራት ይቻላል፡፡ የመንግሥት ዓይን አይለየን እላለሁ፡፡ ድርጅቱ ዕምቅ መረጃ ስላለው ከመገናኛ ብዙኃን ጋር አብረን ብንሠራ በርካታ ለውጥ ማስመዝገብ እንችላለን፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ጦርነቱና ሒደቱ

ሦስት ሳምንታት ያስቆጠረው ሦስተኛው ዙር የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት አሁንም...

ወ/ሮ መሰንበት ሸንቁጤ የአዲስ አበባን ንግድና ዘርፍ ምክር ቤትን በፕሬዚደንትነት ለመምራት በተደረገው ምርጫ አሸነፉ

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤትን በፕሬዚደንትነት ለመምራት፣...

ኢትዮጵያ በ2023 የሚኖራት የውጭ ምንዛሪ ክምችት ለ18 ቀናት ግዢ መፈጸሚያ ብቻ እንደሚሆን አይኤምኤፍ ተነበየ

ኢትዮጵያ በ2023 የሚኖራት የውጭ ምንዛሪ ክምችት ለ0.6 ወር ወይም...

መንበሩ ካለመወረሱ በስተቀር መፈንቅለ ሲኖዶስ መደረጉን ቤተ ክህነት አስታወቀ

ቅዱስ ሲኖዶስ ከነገ ጀምሮ ውይይት እንደሚጀምር ተነገረ ‹‹እኛ ወታደርም ሆነ...