[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ ቢሯቸው ገባች]
- ምን ፈለግሽ?
- ምነው ክቡር ሚኒስትር?
- ሥራ ይዣለሁ፡፡
- ተቆጡኝ እኮ፡፡
- እኮ ለምን መጣሽ?
- እንዲህ ተቆጥተውኝማ እንዴት እነግርዎታለሁ?
- ታዲያ ለምን መጣሽ?
- እሱማ አንድ ነገር ልነግርዎት ነበር፡፡
- ምን?
- አዲሱ የተመሠረተውን ፓርቲ የተመለከተ ነው፡፡
- ምንድነው እሱ?
- ትንሽ ፈርቼ ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ምንድነው ያስፈራሽ?
- እንደ እኔ ዓይነቷን ጸሐፊ የሚቀንስ እየመሰለኝ ነው፡፡
- ለምን?
- ከዚህ በኋላ ሥራ የሚገኘው በብቃት ነው ሲባል ሰማሁ፡፡
- ታዲያ ምን ችግር አለው?
- እ…
- ምነው ደነገጥሽ?
- ኧረ ምንም፡፡
- ለነገሩ ሥጋትሽ ገብቶኛል፡፡
- እንዴት ክቡር ሚኒስትር?
- አንቺ እዚህ ቦታ ላይ የተቀመጥሽው በብቃትሽ አይደለማ፡፡
- እንዴት?
- እዚህ መሥሪያ ቤት ያለውን ዋነኛ የሙስና ኔትወርክ የመሠረትሽው አንቺ እንደሆንሽ አውቃለሁ፡፡
- እ…
- በዚያ ላይ ከዚህ ወደዚያ ወሬ እያመላለሽ ሠራተኛውን ታባያለሽ፡፡
- ኧረ እኔ እንደዚህ ዓይነት ሰው አይደለሁም፡፡
- ስለሁሉም ነገር መረጃ አለኝ፡፡
- እኔ እኮ የኢሕአዴግ ደጋፊ ነኝ፡፡
- እሱም እያበቃለት እንደሆነ አልሰማሽም?
- እ…
- ከዚህ በኋላ የፓርቲ ደጋፊ በመሆን ሥራ አይገኝም፡፡
- ምን አሉኝ?
- ብልፅግና ፓርቲ በብቃት ብቻ ነው የሚያምነው፡፡
- ምን ተሻለኝ ታዲያ?
- ራስሽን ማብቃት ነዋ፡፡
- ትምህርት እኮ ብዙም አይገባኝም፡፡
- ለነገሩ አንቺ ሴራ ነው የሚገባሽ፡፡
- እ…
- ሲቀጥል ሌብነት፡፡
- አይስደቡኝ እንጂ ክቡር ሚኒስትር?
- ይኼም ሲያንስሽ ነው፡፡
- ተው እንጂ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ከዚህ በኋላ ከሠነፎች ጋር መጓዝ አንችልም፡፡
- ወይ ጣጣ፡፡
- ስለዚህ በጊዜ አስቢበት፡፡
- ምኑን?
- ቀጣይ ቦታሽን፡፡
- ምን እያሉኝ ነው?
- ወስኛለሁ፡፡
- ምን ለማድረግ?
- ላባርርሽ!
[ለክቡር ሚኒስትሩ አንድ ደላላ ስልክ ደወለላቸው]
- ደስ ይላል ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ምኑ?
- ብልፅግና ነዋ፡፡
- ምኑን ወደድከው?
- ስሙ ራሱ ደስ ሲል፡፡
- ወደድከው?
- ምን ጥያቄ አለው?
- ለምን ወደድከው?
- በቃ ሁላችንም ልንበለፅግ ነዋ፡፡
- ዝም ብሎማ አይበለፀግም፡፡
- ማለት?
- ብልፅግና በሥራ ነው የሚመጣው፡፡
- እሱማ እንሠራለን፡፡
- አንተ መቼ ሠርተህ ታውቃለህ?
- ምን እያሉ ነው ክቡር ሚኒስትር?
- ያለፋህበትን አይደል እንዴ የምታጭደው?
- አልገባኝም?
- ሰዎችን ከባለሥልጣን ጋር አገናኘሁ ብለህ አይደል እንዴ ገንዘብ የምትቀበለው፡፡
- ምን ችግር አለው?
- ያለሥራ ገንዘብ እያገኘህ አገሪቱን ወደኋላ ታስቀራታለሃ፡፡
- ምን?
- ስማ ከዚህ በኋላ እያጭበረበሩ መክበር አይቻልም፡፡
- ማን ነው አጭበርባሪው?
- እንደ አንተ ዓይነቱ ነዋ፡፡
- ክቡር ሚኒስትር እኔ እኮ ለእርስዎ ብዙ ነገር እያሰብኩልዎት ነው፡፡
- ምንድነው የምታስብልኝ?
- እንዴት እንደሚበለፅጉ ነዋ፡፡
- እንዴት ነው የምበለፅገው?
- ይኸው እኔ የማውቃቸው በርካታ ባለሀብቶች አሉ፡፡
- እሺ፡፡
- የተለያዩ ጥያቄዎች ነው ያሏቸው፡፡
- እሺ፡፡
- ስለዚህ የባለሀብቶቹን ጥያቄዎች ይመልሳሉ ከዚያም የእርስዎ የሕይወት ጥያቄ ይመለሳል፡፡
- ትሰማኛለህ?
- ምነው ክቡር ሚኒስትር?
- አዲሱ ፓርቲ ለእንደ አንተ ዓይነቱ ሌባ ቦታ የለውም፡፡
- ምን?
- ከዚህ በኋላ እየሰረቁ ሀብት ማካበት ይቀራል፡፡
- ማን ሲሰርቅ አዩ?
- አንተ ነሃ፡፡
- ምን?
- ስለሁሉም እንቅስቃሴህ መረጃ አለኝ፡፡
- ክቡር ሚኒስትሩ እኔ የፓርቲው አባል መሆን እፈልጋለሁ፡፡
- የትኛው ፓርቲ?
- የብልፅግና ነዋ፡፡
- ለአንተ እንኳን ቦታ የለንም፡፡
- ለምን?
- ባይሆን ለአንተ የሚሆነውን ሌላ ፓርቲ አለ፡፡
- ምን የሚሉት?
- የሌቦች ፓርቲ!
[ለክቡር ሚኒስትሩ አንድ ባለሥልጣን ስልክ ደወሉላቸው]
- ብዙ ጥያቄ አለኝ ክቡር ሚኒስትር?
- የምን ጥያቄ?
- አዲሱ ፓርቲ ላይ ነዋ፡፡
- እኮ ምን ዓይነት?
- የሕዝባችን ጥያቄ መቼ ተመለሰ?
- ምን እያሉ ነው?
- መጀመሪያ የሕዝቡ ጥያቄ መመለስ አለበት፡፡
- የትኛው ሕዝብ?
- የክልላችን ሕዝብ፡፡
- የክልላችን ሕዝብ ጥያቄ እኮ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጥያቄ የተለየ አይደለም፡፡
- ቢሆንስ ምን ያስቸኩለናል?
- ምኑ ላይ ነው የቸኮልነው?
- ውህደቱ ላይ ነዋ፡፡
- ውህደቱ እኮ ለዓመታት ስንወያይበት የነበረ ነው፡፡
- እ…
- በአገሪቱ ጉዳይ አንዱ በዪ ሌላው ተመልካች መሆን የለበትም ስንባባል ነበር እኮ፡፡
- ብቻ እኔ አላማረኝም ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ምኑ ነው ያላማረህ?
- አሁን እየሄድንበት ያለው መንገድ፡፡
- ለምን?
- ምንም ሊገባኝ አልቻለም፡፡
- ለዓመታት የታገልንበት አጀንዳ እኮ ነው፡፡
- እ…
- ችግር በፈጠረው ሥርዓት መፍትሔ ማፍለቅ አይቻልም፡፡
- ማን ነው ያለው?
- አንተም ከዚህ በፊት ስትለው ነበር፡፡
- ሐሳቤን መቀየር አልችልም?
- ምንም አታስብ፣ አሁን የምንገነባው ሥርዓት የሐሳብ ልዩነትን የሚደግፍ ነው፡፡
- እኔ ግን ውህደቱን አልደግፍም ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ለምን እንደማትደግፈው ትነግረኛለህ?
- የሕዝባችን ጥያቄ አልተመለሰማ፡፡
- የኢትዮጵያ ሕዝብ ጥያቄ ሲመለስ እኮ ሁሉም ጥያቄ ይመለሳል፡፡
- የእኔስ ጥያቄ?
- ምንድነው የአንተ ጥያቄ?
- የሥልጣን ነዋ፡፡
- ኪኪኪ…
- ምን ያስቅዎታል ክቡር ሚኒስትር?
- ለሕዝቡ ነው የምታገለው አላልከኝም እንዴ?
- እኔስ የሕዝቡ አካል አይደለሁም እንዴ?
- አንድ ነገር ልንገርህ፡፡
- ምን?
- ከዚህ በኋላ በዚህች አገር አንድ ነገር ይቀራል፡፡
- ምን?
- ተረኝነት!
[ለክቡር ሚኒስትሩ የቀድሞ ሚኒስትር ስልክ ደወሉላቸው]
- አገር እያፈራረሳችሁ ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
- አገር እየነባን ነው እንጂ፡፡
- ማን ያፈረሰውን?
- እናንተ፡፡
- አሃዳዊ ሥርዓት በመገንባት ነው አገር የምትገነቡት?
- አሃዳዊውማ የእናንተ ነበር፡፡
- እ…
- አገሪቱን በአንድ ሐሳብ ረግጣችሁ ስትገዙ የነበራችሁት እኮ እናንተ ናችሁ፡፡
- ሕገ መንግሥቱን እየናዳችሁት እኮ ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
- እናንተ መቼ አክብራችሁት ታውቁና?
- እ…
- እንደፈለጋችሁ አልነበር እንዴ ስትፈነጩበት የነበረው?
- ግድ የለም አሁን ጊዜው የእናንተ ነው፡፡
- ጊዜው የሕዝቡ ነው፡፡
- እንዴት?
- የኢትዮጵያ ሕዝብ ተባብሮ በመሥራት የሚበለፅግበት ጊዜ ነው፡፡
- በእኛ ጊዜ አገሪቱ በ11 በመቶ ስታድግ እንደነበር እንዳይረሱ ክቡር ሚኒስትር?
- 11 በመቶ ያደገችው አገሪቱ ሳትሆን እናንተ ናችሁ፡፡
- እኛ እነማን ነን?
- ሌቦች ባለሥልጣናት ናችኋ፡፡
- ለማንኛውም እኛ አገር የማዳን ኮንፈረንስ እናዘጋጃለን፡፡
- የኮንፈረንሱን ስም ቀይሩት፡፡
- ምን እንበለው?
- ራስን የማዳን ኮንፈረንስ!