Tuesday, September 26, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

ጋዜጠኛ የተለየ ተጠያቂነት እንጂ የተለየ መብት የለውም

ወልደ አማኑኤል ጉድሶ

ኢትዮጵያ የምትባል አገርና ኢትዮጵያውያን የሚባሉ ሕዝቦች በኢትዮጵያ ምድር ከተፈጠሩ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የምናውቀውና የሰማነው የመጣብንን ወራሪ ኃይል ሁሉ በጋራ ተዋግተን፣ በጋራ አሸንፈን፣ የጋራ ድል በጋራ ከማጣጣም ውጪ እንዲህ እንዳሁኑ እርስ በርስ ስንተናኮል ወይም ስንገዳደል ታይቶም ተሰምቶም አይታወቅም፡፡ በኢትዮጵያዊነታችንና በአንድነታችን ዙሪያ እንዲህ ዓይነት ችግር አለባቸው ብሎ ያወራብንም ሆነ የጻፈብን ግለሰብም ሆነ ቡድን ስለመኖሩ እርግጠኛ አይደለሁም፡፡ ይህ እውነታ ህያው ታሪካችንም ውርሳችንም ስለመሆኑ ግን በኩራት ለመናገር የሚያሳፍረን አንዳች የታሪክ ጠባሳ የለብንም፡፡

አንድ በጦር ሜዳ ወይም በሰላም ቀጣና የተሰማራ ወታደር መሣሪያ በእጁ ስላለው ብቻ በሰላማዊ ሕዝብ ላይ አይተኩስም፣ እንዲያው አስፈላጊ ሆኖ ቢተኩስ እንኳን ወደ ሰማይ ይተኩሳል እንጂ የሰውን ሕይወት ለማጥፋት አነጣጥሮ አይተኩስም፡፡ ለዚህም ዋናው ምክንያት የሚተኩስበት ሰው ወንድሙ፣ እህቱ፣ እናቱ፣ አባቱ ወይም ሌላ ወገኑ ሊሆን ይችላልና ነው፡፡ ከሁሉም በላይ እርሱም ራሱ የተወለደውና የወጣው ከዚያው ከሚተኮስበት ኅብረተሰብ ስለሆነ ጥንቃቄ ስለሚያደርግ ነው፡፡ በሰላም ጊዜ ለኅብረተሰቡ ዘብ ይቆማል፡፡ በጦርነት ጊዜም መተኪያ የሌለ ሕይወቱን አሳልፎ የሚሰጠው ለዚሁ ሕዝብ ነው፡፡ ሁልጊዜና በሁሉም ቦታ የሕዝብ አገልጋይና የሕዝብ ልጅ ስለሆነም ጭምር፡፡

ጋዜጠኝነትም ኃላፊነትና ተጠያቂነት ካለባቸው ሙያዎች አንዱና ግንባር ቀደሙ እንጂ ከሌሎች ሙያዎች የተለየ መብት አሊያም ተጠቃሚነት ያለው ሙያ አይደለም፡፡ ጋዜጠኝነት ደንብና ሥርዓት ብሎም ሙያዊ ሥነ ምግባርን ተከትሎ የሚሠራ ክቡር ሙያ ነው፡፡ የጋዜጠኝነትን አስተምህሮ በጥንቃቄና በኃላፊነት ያለፉ ባለሙያዎች ጋዜጠኝነት ተጠሪነቱ ለሕዝብ መሆኑን ጠንቅቀው ያውቃሉ፡፡ እውነትና ትክክለኝነት በጋዜጠኝነት ሙያ ትልቅ ሥፍራ የሚሰጣቸው መሥፈርቶች መሆናቸውን በታላቅ ኃላፊነት ይገነዘባሉ፡፡

ሙያው እንደሚያስተምረው ጋዜጠኛው ተጠሪ ለሆነው ሕዝብ መረጃውን ይፋ ከማድረጉ ወይም ከማሠራጨቱ አስቀድሞ ማረጋገጥ ኃላፊነቱና ወርቃማ ሕግ መሆኑን እንዲሁም “እውነት”ም ዋና አስፈላጊ መሣሪያ መሆንዋን ማወቅ አለበት፡፡ የጋዜጠኛ ትልቁ ዳኛና አለቃ ኅሊናው ነው፡፡ ኅሊናው የማይቀበለውን ጭብጥ በሚዲያ ማሠራጨት የኅሊና ወንጀል ነው፡፡ ሕዝባዊ ተጠያቂነት እንዳለው፣ ከመረጃ ምንጮች ወይም መረጃ ሰጪዎች ተፅዕኖ ፍጹም ነፃ መሆኑን፣ ወገናዊነትን የማይከተል የሙያው ተዋናይ እንደሆነ፣ በአጀንዳው ዙሪያ ኅብረተሰቡ የባለቤትነት ስሜት ኖሮት እንዲወያይና የመፍትሔ ሐሳብ አፍላቂ እንዲሆን የሚያስችል፣ በዋናዎቹ ሕዝባዊና አገራዊ ርዕሰ ጉዳዮች የሚያተኩር፣ ብሎም በሽፋን ሰጪነቱ ሚዛናዊነቱን በጠበቁ ጭብጦች ዙሪያ ማተኮር እንዳለበት . . . ያስተምራል፡፡

እነዚህ ደንቦችና ሥነ ምግባሮች ዕውን የሚሆኑት በተለያዩ አገሮች እንደየአገሮቹ ነባራዊ ሁኔታ መሆኑ ቢታወቅም አስተምህሮው ግን የትም ሆነ መቼም አንድ ነው፡፡ እነዚህን ሒደቶች መጣስና ሙያዊ ሥነ ምግባር የሚጠይቀውን ኃላፊነትና ግዴታ መዘንጋት ከምንም በላይ በኅሊና ላይ በደል እንደማሸከም ነው፡፡ ይህንን ኃላፊነት መዘንጋት የሙያውን ብቻ ሳይሆን የዜግነት ግዴታ እንደ መርሳት ይቆጠራልና ልብ ማለት ይገባል፡፡

አንድ ጋዜጠኛ መጻፍ ስለሚችል ብቻ መረጃውን በወረቀቱ፣ በኮምፒውተሩ፣ በሞባይሉ፣ በሬዲዮ አሊያም በቴሌቪዥን ሲጠቀም እነዚህን ኃላፊነቶች ከዘነጋ ወይም አውቆ ችላ ካለ ሙያዊ፣ አገራዊና የዜግነት ግዴታውን እንደዘነጋ ይቆጠራል፡፡ አንድ ሰው መናገር ስለሚችል ብቻ ለፍላፊ መሆን እንደ ማለት ነው፡፡ በእርግጥ ከላይ በተጠቀሱት የሚዲያና የአክትቪዝም ዓይነቶች “የሚጽፉና የሚያስነብቡ“ ሁሉም ጋዜጠኞች ባይሆኑም ጋዜጠኞቹ ይህንኑ ሥርዓት አልበኝነት በሙያዊ ብቃታቸው ከማንም በላይ ራሳቸው ቢቻል በሙያ ማኅበር አማካይነት ወይም በሌላ ማረም፣ ማስተካከል፣ እንዲያውም በሰላ ብዕራቸው በርትተው መተቸት የሚጠበቅባቸው ይመስለኛል፡፡

ጋዜጠኛ በሕይወት ዘመኑ በሠራቸው ሥራዎቹ በተከታዩ ትውልድ በአዎንታዊነት የሚዘከር ቢሆን ይመረጣል፡፡ መሬት ውስጥ እንደተቀበረ ፈንጂ ጊዜውን ጠብቆ በመፈንዳት በኅብረተሰቡ መካከል ቂም በቀልንና ቁርሾ የሚቀሰቅስ ታሪክ ትቶ ማለፍ አይጠበቅበትም፡፡ የሌሎችን ግለሰባዊና ማኅበረሰባዊ ወይም የዜግነት መብት መንካት የለበትም፡፡ ይህንን ኃላፊነት መወጣት ያለመቻል የተሰጠውን የጦር መሣሪያ በኃላፊነትና በአግባቡ እንደማይጠቀም የጦር ሰው ጋር ይመሰላል፡፡

ብዕርና ጥይት አንድ ናቸውና ጋዜጠኛው እንዲህ ካልሆነ በጠላቶቹ እንጂ በሰላማዊ ሕዝብ እንዳይጠቀም የተሰጠውን የጦር መሣሪያ በወገኑ ላይ እንደደገነ ወይም እንደተኩሰ የጦር ሰው ጋዜጠኛውም እንዲሁ ይቆጠራል፡፡ ጥይት በጠላት ወይም በአስፈላጊው ዒላማ ላይ ከተነጣጠረ ቦታውን አይስትም፡፡ ያለቦታው ከተጠቀሙት ወይም ከባረቀ ግን የሰውን ሕይወት ያጠፋል፡፡ የንብረት ውድመት ያስከትላል፡፡ ከብዕር ያላግባብ የሚለቀቀው ቃላትም በአግባቡ ካልተጠቀሙ ዓላማውን ከሳተ በሰላማዊ ሕዝቦች መካከል እልቂት ያስከትላል፡፡ ሰላም ያደፈርሳል፡፡ አንድነትን ያናጋል፡፡ አብሮነትን ያበላሻል፡፡ እኔነትን በማጉላት እኛነትን ያሳንሳል፡፡

አሁን አገራችን ባለችበት ነባራዊ ሁኔታ የብዙዎቻችን ብዕር ሕዝባዊና አገራዊ ወገናዊነትን ችላ ያለ ወይም የዘነጋ ይመስላል፡፡ ከልማት ይልቅ ጥፋት ላይ ያነጣጠረ ነው፡፡ ከአንድነት ይልቅ ልዩነት ላይ ያተኮረ ነው፡፡ ከአገራዊ አንድነት ይልቅ ጽንፈኛ ብሔረተኝነት ላይ የወገነ ነው፡፡ ሲያስተሳስረን ከቆየ አኩሪ ታሪካችን፣ (በመጥፎ ጎን የሚነገሩ ነገር ግን ለዛሬዋ ኢትዮጵያ የማይጠቅሙ ትርክቶች እንዳሉ ሆኖ) ፍቅራችን፣ አብሮነታችን፣ በአጭሩ ማንም ምንም መቼም ሊለየን ከማይችለው ኢትዮጵያዊነታችን ያፈነገጠ እውነታ የሚዘክር እየሆነ ነው፡፡

ዛሬ ዛሬ “ብዕራችን“ና ሙያችን በአብዛኛው መልኩ ወዳልተፈለገ አቅጣጫ አነጣጥሯል፡፡ ተስፋ የሚያስቆርጥ ባይሆንም ኅብረተሰቡ ትክክለኛውን ከሐሰተኛው ለመለየት ወደሚቸገርበት ደረጃ ደርሷል፡፡ ለዚህም መንስኤውን እርግጠኛ ሆኖ መናገር የሚቻለው መንግሥትና መሪው የፖለቲካ ድርጅት ሲያካሂዱት የነበረው አገራዊ አጀንዳ በትክክል ወደፊት የማያራምድ መሆኑ ነው፡፡ ይህንን የተዘበራረቀ አካሄድ እንደ ዜጋ የምንጋራው ቢሆንም የታሪክ መዘውሩን ወደ ትክክለኛ አቅጣጫ ማዞር የሚቻለው ግን በእንደዚህ ዓይነት ወንጀለኛውንና ንጹኃኑን ዜጋ መለየት በማያስችለው የጅምላ አካሄድ አይመስለኝም፡፡ አይደለምም ደግሞ፡፡ ሥልጣኑ ቢሰጣቸው እንኳን መምራት የማይችሉ ወይም በጉልበት አመራሩን ወስደው መምራት ላቃታቸው አንዳንድ ፖለቲከኞች ጋዜጠኞቹ መሣሪያ እየሆኑ ማረጋገጫ በሌለበት ሁኔታ መለያየትንና መገዳደልን ማስከተላቸው ነው፡፡

እነዚህም አስመሳዮችና ኢትዮጵያዊ መሳይ ጋዜጠኞች ከፖለቲከኞች ጋር በመመሳጠር ለበጎ ልማት መዋል የሚገባውን ጊዜ፣ ዕውቀት፣ ሀብትና ጉልበት ለእኩይ ዓላማ እያዋሉ ነው፡፡ ለራሳቸው በአገር ውስጥና ውጪ አገር የተደላደለና የተሞሸረ ኑሮ እየኖሩ ደሃው እርስ በርስ እንዲገዳደልና እንዲሞት በማድረጋቸው በተወሰነ መልኩም ቢሆን ተሳክቶላቸዋል፡፡ ሌት ከቀን ለበጎ ነገር መዋል የሚገባውን አዕምሯዊ ኃይል እብደት አርግዘውበት የክፋት እንቁላሎችን እየፈለፈሉ ነው፡፡ ታዲያ እነዚህን ጋዜጠኞች ወይስ ጎጠኞች እንበላቸው!! በአጭሩ አወዛጋቢዎች ብንላቸው የሚቀል ይመስለኛል፡፡

እነዚህን ሕዝባዊ ተጠያቂነት እንዳለባቸው የማያውቁትን “ጋዜጠኞች” እውነተኞዎቹ ጋዜጠኞች በብዕራቸው አምርረው በመተቸት ሙያቸውንና ሙያዊ ሥነ ምግባራቸውን ማስከበር አለባቸው፡፡ ይህንን ማድረግ የሐሳብን ነፃነት ማስከበር እንጂ መጋፋት አይደለምና፡፡ አንድ ሰው በብዕሩ ሐሳቡን በነፃነት ማስከበር መቻሉን ማረጋገጥ ማለት የሌላውን ነፃነት ማጉደል ማለት አይደለም፣ እንዲህ በማድረግ ለምንስ የሌላውን የነገ ሕይወትና ውሳኔ ያበላሻል? ለምንስ የነገውን ምርጫና ዕድል ያደናቅፍበታል? አንድ የራሱን ነፃነት የሚፈልግ ሰው የሌላውን ነፃነት ለምን ይከለክላል፣ ለምንስ ያስከለክላል? እንደ ራሱ ሁሉ ሌላውም ሰው መሆኑን፣ ነፃነት፣ እኩልነትና ፍትህ . . . ፈላጊ መሆኑንስ እንዴት ይረሳል!

ዛሬ በብዕራችን አማካይነት አንገት የምናስደፋው ሰው ነገ በተራው ዕድሉን ካገኘ ጨቋኝ እንዲሆን ለምን ዕድል እንሰጣለን? ያልነበረብን ኢትዮጵያዊ ባህል ነው፡፡ ይህ ቂም በቀልና በደልም ነው፡፡ ይህንን በማድረጋችን የምንሻል ለዚህም ደግሞ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን የመጠቀም ዕድል ያገኘን ትውልዶች ስለመሆናችን ማሳያው ምንድር ነው? ለዚህ መፍትሔው መደነቃቀፍንና ማደናቀፍን፣ ማደናበርንና መደነባበርን ትተን ብዕራችንን ወደ አገራዊ የልማት፣ የዴሞክራሲና፣ የመደመር ፖለቲካ ከልብ ማዞር ነው፡፡

ጋዜጠኞች ኅብረተሰቡን ለአገራዊ ኢኮኖሚ ግንባታና የሐሳብ የበላይነት የሚጠቅመውን አጀንዳ መቅረጽ ይጠበቅባቸዋል፡፡ የሰፊው ሕዝብ ባለውለታዎች እንጂ “ባለጊዜዎች” መሆን አያስፈልግም፡፡ መጻፍ ስለቻሉ ብቻ የሚጻፈውን ጭብጥ ለትርምስና ብጥብጥ ፈጣሪዎች መሣሪያ መሆን ያለባቸው አይመስለኝም! እንደፈለግን ሳይሆን ተፈጥሯዊና ሙያዊ ግዴታ በሚፈቅደው ሥነ ምግባር መሠረት መመራት ያለብን ይመስለኛል፡፡

አስገራሚው ነገር ደግሞ አንዳንድ የአየር ሰዓት እየገዙ የተለያዩ ልሂቃንን የሚያወያዩ በተለይም የቴሌቪዥን ጋዜጠኞች የተወያዮችን በአብዛኛው አሉታዊ ባህርይ ሕዝብ እንዲያውቅ ከማድረግ ውጪ የጠቀሙት ነገር እምብዛም ነው፡፡ እንደ በረዶ ክምር የተቋጠረና የሚቀልጥ መርዝ በብልቃጥ ሞልተው እንደነሰንሱ ያስመስላልና፡፡

ጋዜጠኞች በጋዜጠኝነት ስም የሚያሰሙት ዜና፣ የሚያቀርቡት ፕሮግራም፣ የሚያስነብቡት መጣጥፍና ሌሎችም ሙያዊ ይዘቶች በተለይም በአገራችን ነባራዊ ሁኔታ የሚያፋቅሩን፣ የሚያከባብሩን፣ የሚያስተሳስሩንና የሚያቻችሉን መሆኑ ሁላችንንም ይጠቅማል እንጂ አይጎዳም፡፡ እንዲህ ዓይነቶቹ ባለሙያዎችና ተግባሮቻቸው ፈጣሪ ለያንዳንዳችን ለክቶ የሰጠንን የኮንትራት ዘመን በሕይወት መኖር ያስችለናል፡፡ ስማችን እንደየአቅማችን በተከታዩ ትውልድ ዘንድ በጥሩ ሁኔታ ይዘከራል፡፡ አውቀንም ሆነ ሳናውቅ በሠራነው “ስህተት” ቤተሰብ፣ ጓደኛ ወይም የቅርብ ዘመድ አያፍርም፣ አይኮነንምም፡፡ በታሪክ የሚያውቀን ሁሉ ወቃሽ ሳይሆን አሞጋሽና አወዳሽ ይሆናል፡፡ እንደዚህ ዓይነት በጎ ነገር ለማድረግ የግድ ወንድ፣ ሴት፣ ባለሥልጣን፣ ባለሙያ . . . መሆን አይጠበቅም፡፡ ሰብዓዊ ፍጡር ወይም በአጭር አነጋገር ሰው መሆን ብቻውን በቂ ነው፡፡ በጋዜጠኝነት ሙያችንና በነፃ ብዕራችን ለአገራችን ሁለንተናዊ ዕድገት ተሟጋቾች እንጂ አደናቃፊዎች መሆን ለማን እንዲበጅ ነው!!

ለኢትዮጵያችን ኋላ መቅረትና መደህየት፣ ለሕዝባችን ተመጽዋችነት ሌት ተቀን የሚሠሩ ወደጅ መሳይ ጠላቶች እንዳሉንስ ለምን እንዘነጋለን!! ብንጎዳና እርስ በርስ ብንጠፋፋ ተጠቃሚዎች እነማን ሊሆኑ እንደሚችሉስ እንዴት አርቀን ማየት ያቅተናል፡፡ ጋዜጠኛ መስለው መርዝ የሚረጩብን “ጭንቅላቶችስ” መነሻቸው የኢትዮጵያዊነትን ክቡር ባህልና ጨዋነት የተከተለ ነውን? በጊዜያዊ ጸብ ብንጣላና ብንጨቃጨቅ እንኳን ለእንደዚህ ዓይነት መገዳደል የሚያበቃን አንድም ምክንያት ሊኖር አይገባም፡፡ ቢኖር እንኳን በውይይት የመፍታት ጥንታዊና ባህላዊ ትሩፋቶች እያሉን ለምን ወደ መገዳደልና መጠፋፋት ቅስቀሳ እንሄዳለን? ይህ የጋዜጠኝነት ሙያዊ ተልዕኮም ዓላማም አይደለም፡፡

የታሪካዊ ጠላቶቻችንን ተልዕኮ ይዘው ታሪካችንን ሊያደፈርሱ የሚሞክሩ ግለሰቦችንና ቡድኖችን በብዕራችን ማሳፈር አለብን፡፡ ይህንን ኃላፊነት ለማንም የምንተወው ወይም የምንሰጠው ሳይሆን የሁላችንም አገራዊ ኃላፊነትና ግዴታ ነው፡፡ እስከ ዛሬ  ለውጪ ጠላቶቻችን እጃችንንና መብቶቻችንን አሳልፈን እንዳልሰጠን ሁሉ ለውስጥ ጠላቶቻችንም አንፍቀድ፡፡ በቃችሁ እንበል፡፡ የማንነጣጠል የአንድ አገር ዜጎች መሆናችንን በየአጋጣሚው ሁሉ በፍቅር እናስረዳቸው፡፡ ልዩነታችንን በውበት አጅበንና በአንድነት ጥላ ሥር ተሰባስበን ከንቱ ሴራቸው እንዲከስም በተባበረ ሁኔታ እንቁም፡፡ እኛ ከምንነግራቸው በላይ ከንቱ መሆናቸውን ራሳቸው በራሳቸው እንዲውቁ በሰላማዊ መንገድና በብዕራችን እንጠቁም፡፡

አንድ ትልቅ አጽንኦት ሊሰጥ የሚገባው ወሳኝ ጉዳይ ቢኖር ኅብረተሰቡም በራሱ በሁሉም ሚዲያ በተለይም በፌስቡክ የተጻፈው ጭብጥ ሁሉ ትክክል ነው ብሎ መውሰዱን ማሻሻል አለበት፡፡ አንዳንድ ችግር ያለባቸው የሚዲያ ሰዎች ወይም አክቲቪስቶች የጻፉት ነገር ትክክል ነው ወይስ አይደለም የሚል አቅም እንዲኖራቸው አስተማሪ መረጃ መስጠት ተገቢ ነው፡፡ “ጦር ከፈታው ወሬ የፈታው” ይባል የለ!! በጥቅሉ ጋዜጠኞችና የተግባቦት ባለሙያዎች ከምንም በላይ የሚወክሉትን የመገናኛ ተቋምና ሙያቸውን በኃላፊነት የሚያስከብሩና የሚሞግቱለት እንጂ የሚያስወግዙ መሆን አይጠበቅባቸውም፡፡ ያለችን አንድ አገርና ያሉን ደግሞ በአንድነት ኅብር የተገመዱ ሕዝቦች ናቸውና፡፡ ከፊት ለፊታችን የተጋረጡብንን የጋራ ፈተናዎች በጋራ የምንሻገር መሆናችንን በተግባር ማሳየት ይጠበቅብናል፡፡ መንገዳገድ መውደቅ አይደለምና፡፡

በመጨረሻም ጋዜጠኛ የተለየ ተጠያቂነት እንጂ የተለየ መብት ያለው ባለሙያ አይደለም፡፡ ሕግና ሥርዓት እንዲሰፍን የሚታገሉ፣ ልዩነትን አክብረው የደመቀ አንድነት እንዲኖር የሚሞግቱ፣ ያለፈውን ቁርሾ ትተን የወደፊቱን አብሮነት ከፍ አድርገን እንድናየው ከልብ ሌት ከቀን የሚሠሩ ጋዜጠኞችና የተግባቦት ባለሙያዎች እንደነበሩና አሁንም እንዳሉ ብረዳም፣ የሙያው ባለቤቶች ነንና ሙያችንን ማስከበር ይጠበቅብናል፡፡ ይህንን ማድረግ ማለት ደግሞ ሙያዊ ነፃነትን መጋፋት አይደለም፡፡ እስቲ በእንደዚህ ዓይነት መድረኮች እንከራከር፡፡ ሰላም!

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles