Thursday, June 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ፅናት ያስከብራል!

ሰላም! ሰላም! አንዱ በቀደም ሰተት ብሎ በጠዋቱ ቤቴ መምጣት። ከተዋወቅን እኮ ሳምንት አልሞላንም። የእኔ ውድ ማንጠግቦሽ ግን፣ ‹‹እንኳን ሰባት ቀን ሰባት ደቂቃ ቆሞ የሚያወራህ በጠፋበት በዚህ ጊዜ እንዲህ አትበል፤›› እያለች ለምሳ የቆጠበችውን ለእንግዳው ጨምራ ቁርስ ታቀርባለች። ምናለበት አንድ ጉርሻ ብጎርስ? ምናለበት አንድ ጊዜ ቡናዬን ፉት ብል? ‹‹አንበርብር ዛሬ ሰባ ሺሕ ብር ካላበደርከኝ መታነቄ ነው፤›› አይለኝ መሰላችሁ? ማንጠግቦሽም ይህን ስትሰማ የምሳ ፍጆታችንን ማባከኗ ሳይነዳት አይቀርም። ምን እኮ በቃ ሳንወድ በግድ ጋቭሮባውያንን ሆንን እናንተ። አጅሬ ዋ ብዬ መቅረቴን አላየ፣ እጄ ላይ በቀመር የጠቀለልኩት አጓጊ ጉርሻ መፍረሱን አላየ ብቻ፣ ‹‹እነዚህ ሰዎች በዚህ ወር አንድ ነገር ከላደረግኩ ልጅቷን ይገድሏታል፤›› ይለኛል። ‹‹ኧረ ማን ነው ገዳይ? ማን ነው ተገዳይ? አንተስ የማን ገላጋይ ነህ?›› ብዬ ሳልጨርስ፣ ‹‹አንበርብር ስንቴ ነው የምነግርህ? የሚስቴ ቤተሰቦች ናቸዋ። እሷ (ሚስቱ) እርጉዝ ናት ብዬሃለሁ። ቤተሰቦቿ ይኼን ሲያውቁ ጠቅልል ብለዋል። እኔም እሷም የምንፈልገው ይኼንኑ ነው። ግን እነሱ ተደግሶ ተሠርጎ ነው ብለው ደረቁ። ቢያንስ አንድ ሁለት በሬ መግዛት የለብኝም?›› ብሎ ዓይን ዓይኔን ያየኛል። ግለሰብ ቀርቶ መንግሥት የሚመሩ ሰዎች ዓይን ለዓይን መተያተት አንደፍር ባሉበት በዚህ ጊዜ፣ ጭራሽ ዓይኑን ሳይገረብብ ሲያፈጥብኝ በእጅጉ ደነቀኝ፡፡ ዘንድሮ ምን የማይደንቅ አለ አትሉኝም!

ወይ ዘንድሮ! ሰው እንዲህ የሩቁን ማየት እየተሳነው በየሜትሩ ጉድጓድ የሚገባበት ዘመን ይሁን? እሺ የሆነውስ ይሁን። ግን እንዴት ያለ ኃፍረተ ቢስነት ቢጠናወተን ነው እንዲህ ገመና ከመሸፈን፣ በአንዴ በገመና ወደ መሸቀል የኮበለልነው? የምሬን እኮ ነው። እንዴት ተስፋ አድርጎኝ እንደ መጣ ሳስብ ደግሞ ልቤ አልችል አለ። ‹‹ቆይ እስኪ ጊዜ ስጠኝ፤›› ብዬ ከሸኘሁት በኋላ እግሩ ከመውጣቱ ማንጠግቦሽ ትኩር ብላ እያየችኝ፣ ‹‹ለእኛ ሠርግ እንኳን በሬ በግ እንዳልታረደ አስታውስ፤›› ብላ ወደ ጓዳዋ ገባች። ለነገሩ የተረሳው ጋብቻችን ብዙ የሚያስታውሰን ነገሮች ቢኖሩም፣ ገመና ከታች የሆነው ፍቅራችን አንድ ቀን አሳስቶን አደባባይ አውጥቶ አነታርኮን አያውቅም፡፡ ኑሮአችንን ለመምራት የሚያጨቃጭቁን ጉዳዮች ቢኖሩም የተሻለ መፍትሔ ያቀረበ ሁሌም አሸናፊነቱ ይፀናለታል እንጂ፣ እንዲያው በደፈናው እያኮረፉ ፍቅርን ቅራሪ ማድረግ አለመደብንም፡፡ በዚህ ደግሞ ለውድ ባለቤቴ ታላቅ ክብር እሰጣለሁ፡፡ አክብራ ያስከበረችኝ ናትና፡፡ ክብር ልዩነትን በፀጋ ማስተናገድ ለሚችሉ ሁሉ ይሁን!

አረፋፍጄ ከቤት ስወጣ የወጣቱን ታሪክ ካስተዋወቀኝ ሰው ወሬውን ስሰማ፣ ይህች አሁን ቤተሰቦቿ ድል ባለ ድግስ በወግ ውሰዳት የሚሉት ገና የሃያ ዓመት ወጣት ናት። ‹‹ለመሆኑ አልተማረም?›› ብዬ ስጠይቅ፣ ‹‹ኧረ በሕግ የመጀመርያ ዲግሪ አለው፡፡ ምነው ስንት ጊዜ አላጫወትኩህም እንዴ?›› ተባልኩ። ምንድነው ይኼ አሥር ጊዜ ‘አጫውቼህ የለም ወይ’ እያሉ መደጋገም ብዬ በስጨት አልኩ። ጨዋታ እንደ ጋብቻ የሰማንያ ሕግ ሆነ እንዴ? የምር። ‹‹አጫውቻለሁና ሰምተሃልና የገባህበት ገብተህ ሸክሜን ተሸከም ብሎ ነገር አለ እንዴ?›› እያልኩ ስነጫነጭ አዛውንቱ ባሻዬ ሰምተው፣ ‹‹ብሎ ብሎ ደግሞ ሰው በዚህ መጣብህ?›› አሉኝ። ‹‹በየቱ?›› ስላቸው፣ ‹‹ኧረግ አንተስ እውነትም ልብህ ጠፍቷል፤›› ብለው ፈገግ እያሉ፣ ‹‹ክርስቶስ ቃሌን አንዴ ሰምቶ እንዳልሰማ ሆኖ የተመለሰ፣ ያፈገፈገ ሰው ፍርዱ በራሱ ላይ ነው ብሎ ነበር። ይኼ መቼም መንፈሳዊ ነገር ስለሆነ አግባብነቱ ያመዝናል። እኔን የሚገርመኝ ግን ይኼኛው ነገር ነው። የዘመኑ ሰው ቃል ምን እንደሆነ በቅጡ ሳያውቅ የትም እየማለ፣ የትም እየተገዘተ ይቆይና የታሪኬ ባለዕዳ ካልሆንክ፣ የሕመሜ ተጋሪ ካልሆንክ ይል ይዟል። እንኳንም የመንግሥተ ሰማይ መዝጊያ በአንድ ፈጣሪ እጅ ሆነ፤›› እያሉ አበስኩ ገበርኳቸውን ቀጠሉ። አንዳንዴ ባሻዬ እንዲህ ሲያወሩ ቃል በቃል መከታተል ያቅተኛል። በተለይማ ብድር ተጠይቄ? ‹‹ማን ጠየቀህ?›› አሉኝ ባሻዬ። ለካስ እሳቸው እየሰሙኝ ኖሯል በልቤ ያወራሁ የመሰለኝ። ታሪኩን ሳጫውታቸው ዝም ብለው ሲያደምጡ ቆይተው፣ ‹‹ምን ያስጨንቅሃል ታዲያ? የሚቻልህ ከሆነ አበድረው። ካበደርከውም መልስ የማትለው ከሆነ ጭምር ማለቴ ነው፤›› ሲሉኝ ጥያቸው ጠፋሁ። እንዲያማ ብለን መስሎን ስንቱ በትከሻችን ላይ ተንፈራጦ የከበረው፡፡ ስንቱን ከድህነት ወለል አንስተን ያከበርነው፡፡ መልሱ ምን ሆነ ብትሉኝ ጥጋብ ነው ምላሼ!

ለነገሩ በባሻዬ አልፈርድም። እሳቸውም በደህናው ጊዜ ልባቸው መንግሥተ ሰማይን ናፋቂ ስለሆነ የዚህ ዓለም ነገር በፊታቸው የተናቀ ነው። ለእኛ ደግሞ ሌላ ነው። ‘እያለህ ካልሆነ ከሌለህ የለህም’ የተዘፈነው ለምሳሌ ለእኛ ለእኛ ዓይነቱ በሁለት ልብ ለሚያነክስ ከንቱ ነው። ማስጠንቀቂያውን ብሰማና የለኝም ብል ደግሞ ንፉግ፣ ቆጥቋጣ፣ ገብጋባ፣ ራስ ወዳድ…’ ብዙ ብዙ መሰል ስሞች ጀርባዬ ላይ ሲለጠፉ ይታዩኛል። እኛ ደግሞ እንደምታውቁት የመለጣጠፍ ችግር የለብንም። አንስቼ ብሰጥ የማንጠግቦሽ ጉምጉምታና የእኔ ድካም መና መቅረት ብቻ ስቀመጥ ስነሳ ሰላሜን ሊነሱት ነው። ይኼን እያሰብኩ አንድ ሥራ መጣ። ያበደ ዘመናዊ ሕንፃ ይሸጣል ተባልኩ። ወዲያው አካባቢውን አጣርቼ ሳበቃ ለአራት ቤት ፈላጊ ደንበኞች ደወልኩ። ሁለቱ አላነሱም፣ አንዱ ስልኩ አይሠራም። አንደኛው ‘ሃሎ?’ አለ። የነገርኩትን ሰማ። ጊዜ ሳያጠፋ አገኘኝና ሕንፃውን ሄዶ አየ። ወገኖቼ እኛ ወሬ ላይ ተጥደን ልብ የገዙት ጥሪት እየያዙ ነው፡፡ ሌላው ቢቀር ከወሬው ቀንሰን ልጆቻችንን ብናስተምር እኮ ምንኛ ፅድቅ ነበር!

ብታምኑም ባታምኑም ገዥው የዕለቱ ዕለት ሰባ ሚሊዮን ብር በባንክ ወደ ባለቤቶቹ ከአካውንቱ እንዲዛወር አደረገ። ያንተስ ሲለኝ ደለብ ያለ ኮሚሽኔን በእጄ ሰጥቶ፣ ሌላውን ወደ አካውንቴ እንዲያስገባው ነገርኩት። ወዲያው ከላዩ ላይ ወስጄ ለሙሽራው ሰጥቼ ተገላገልኩ። ግን እንዲያው ሲያስበው ራሷን ያልቻለች፣ በቤተሰብ ጥገኝነት ሥር ያለች ታዳጊ አባብሎ ዘልዝሎ ለጥብስ ሲያደርስ እንዴት ሰው አዋዜውን አያስብም? ነገን ማሰብ ማንን ገደለ? ምንስ አለኝ ምንስ የለኝም ማለት ማንን ገደለ?’  ብዬ የባሻዬን ልጅ ብጠይቀው፣ ‹‹ይኼ ሀሉ ሰው እንዲህ ማሰብ ቢችል እንኳን በግለሰብ ደረጃ እንደ አገር የብድር ድር ላያችን ላይ ያደራብን ነበር?›› ብሎ ልክ አስገባኝ። ለካ እንደ ግለሰብ በአበዳሪነቴ ስታበይ እንደ ማኅበረሰብ ተረጂነቴን ስቼው ነበር። ያንን ያህል የብድር ተራራ ተጭኖብን፣ በርካታ ሚሊዮን ወጣቶች የሥራ ያለህ እያሉ እየለመኑ፣ ሰላም ያጡ የሰላም ያለህ እያሉ እየጮሁ፣ ፍትሕ፣ ነፃነትና እኩልነት የናፈቃቸው ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እየፀለዩ… ከአገር በላይ እኔ የሚሉ ሰዎችን ድርጊት ስሰማ ያመኛል!

እናላችሁ ሰሞኑን የማስበው በገንዘብ አቅም ራስን ከመቻል በፊት በአስተሳሰብ ራስን ስለመቻል ሆኗል። የእናንተን ባላውቅም የብዙ ሰዎችን ውድቀትና ስኬት ስታዘብ፣ ሚስጥሩ በአስተሳሰብ ራሳቸውን የቻሉና ያልቻሉ መሆናቸው ይከሰትልኛል። እኛ ደግሞ እንደምታውቁት ከአለባበስ፣ ከሜክአፕ፣ ከምንነዳው መኪና፣ ከውፍረትና ከክሳታችን አልፈን በብሔርና በሃይማኖት ለሚመዝኑን እጅ እየሰጠን ነው። ይኼን ትታችሁት በቀደም አንድ ከባድ የጭነት መኪና ላሻሽጥ ደንበኛዬን እየጠበቅኩ ካፌ ተቀምጬ፣ ሁለት ወንድማማቾች ሲነጋገሩ የሰማሁትን ላጫውታችሁ። አንደኛው አጥባቂ ሃይማኖተኛ ይመስላል። አንደኛው ደግሞ ልዝብ መሆኑ ነው። በማን ዓይን? በአጥባቂው ዓይን። እናም ይመክረዋል። ‹‹አንተ እስከ መቼ ነው ዕድሜህን፣ ገንዘብህንና ዕውቀትህን አልባሌ ቦታ የምትጨርሰው? መቼ ነው ሰው የምትሆነው? መቼ ነው ወደ ፈጣሪ ፀጋ የምትመጣው? እስካሁን እኮ የኖርከው ሁሉ ከንቱ ነው፤›› ይለዋል። ከንቱነት በየቦታው በተዘራበት በዚህ ዘመን መካሪ አያሳጣ ያሰኛል!

ተተቺው በትህትናና በየዋህነት፣ ‹‹ለእኔ ስለምታስብ እንዲህ እንደምትለኝ አውቃለሁ። ግን እኔ የራሴ የሆነ ከፈጣሪ ጋር የምገናኝበት መንገድ አለኝ። የግድ የአንተን መምሰል የለበትም። እኔንም አንተንም ፈጣሪ እኩል ነው የሚያየን። ምናልባት አንተ ጠንካራ እምነት ሊኖርህ ይችላል። እኔ ደግሞ ደካማ ልመስል እችላለሁ። ነገር ግን ሁሉንም የሚያውቀው ፈጣሪ ነው። የአንተን ምክርና ሐሳብ እረዳለሁ፣ እቀበለዋለሁ። ግን በሕይወቴ ዘመን የማደርገውን ሁሉ ማድረግ የምፈልገው በራሴ ጊዜና ውሳኔ እንዲሆን ስለምፈልግ ታገሰኝ፤›› ይለዋል። ያኛው አይሰማውም። ‹‹አልገባህም። ዛሬ ወደ ትክክለኛው መንገድ ካልተመለስክ ከዚህ ካፌ ተነስተህ ስትሄድ ሰይጣን በመኪና አደጋ ሊወስድህ ይችላል፤›› ሲለው ተተቺው በዝምታ ተነስቶ መኪናውን አስነስቶ ተፈተለከ። እኔ አልኩኝ፣ ‘እስከ መቼ ይሆን በቡድን ፍረጃ፣ በቡድን አስተሳሰብ፣ በቡድን ብያኔ ሕይወታችን እየተቃኘ ስንራብ አንድ ላይ ስንጠግብ አንድ ላይ፣ ስንፀድቅ አንድ ላይ፣ ስንኮነን አንድ ላይ… መሆኑ የሚያከትመው?’ የዴሞክራሲያችንም ማነቆ ዋነኛ እንከኑ የሚጀምረው በቤተሰብ መሀል መሰለኝ። ከተሳሳትኩ አርሙኝ ብያለሁ! የሆነ ሆኖ ግን አሁንም እላለሁ በንፁህ ልቦና መመካከሩ አይከፋም!

በሉ እንሰነባበት። እናውራው ብንል የእኛ ነገር አያልቅም። ብቻ እኔን የሚገባኝ ብዙ ብዙ መከርከም ያለበት ነገር እንዳለ ነው። ከባሻዬ ልጅ ጋር ትናንት አመሻሽ ላይ አንድ አንድ ልንል ወደ ግሮሰሪያችን እያመራን ሳለን አንድ ሰውነቱ በጣም የተጎሳቆለ ወጣት መጥቶ ፊታችን ወደቀ። ‹‹እናንሳው?›› ስለው የባሻዬ ልጅ፣ ‹‹ኧረ እረፍ የት ታውቀዋለህ?›› አለኝ። ትተነው ወደ ግሮሰሪያችን ገባን። የግሮሰሪያችን ታዳሚ የዚያን ምስኪን መጨረሻ እርስ በርሱ ትከሻ ለትከሻ እየተንጠራራ ይከታተላል። አንዱ፣ ‹‹ይኼ ጫት ምናምኑ እኮ ነው እንዲህ የሚያደርገው፤›› ይላል። ‹‹የለም ይኼማ የአዕምሮ በሽታ ነው። ቢታከም እኮ ይድናል። አካሚው ሳይጠፋ አሳካሚው ነው የጠፋው፤›› ይላል። ‹‹የምን የአዕምሮ በሽታ ነው ደግሞ እሱ። ገና ለገና ዘመናዊ ነን ለማለት ሲሉ የሰሙትን መደጋገም አይደብራችሁም እንዴ? ይኼ አንድ ሁለት የሌለው የሰይጣን ሥራ ነው። ፀበል ቢሄድ በቃው። ተገላገለ፤›› ይላል ወዲያ ማዶ ከባሻዬ ልጅ ጀርባ። እኔና የባሻዬ ልጅ ተያይተን ተሳሳቅን። አንዱ የየዕምሮ በሽታ ነው ሲል አንዱ ‘ሱስ’ ነው ሲል፣ አንዱ ሰይጣን ነው ሲል የጋለ ንትርክ ተነስቶ አረፈው። በማያነታርከው የምንነታረከው እኮ ከመረጃ እጥረት ወይም ከሐሰተኛ መረጃ መብዛት ሊሆን እንደሚችል መገንዘብ ያቃተን በዝተናል፡፡ በአንድ ወቅት አንድ ሰው ድንገት ደርሶ መንግሥትን በግልጽ ይሳደባል፡፡ አንዱ ይኼማ የታወቀ ሰላይ ነው ሲል፣ ሌላው አውቀዋለሁ በቅርቡ ከአማኑኤል የወጣ ወፈፌ ነው ይላል፡፡ በዚህ መሀል አንዱ ድንገት ይደርስና ሰላም ሲለው ሰውየው በተኮላተፈ የሰካራም አንደበት ስድቡን እየቀጠለ ሰላምታ የሰጠውን ሰው እጁን ይዞ ጅን ግዛልኝ አለው፡፡ ይኼኔ የሁለቱን ሰዎች የተሳሳተ ወሬ ሲያዳምጥ የነበረ፣ ‹‹አንተ የታወቀ ሰላይ ነው አልክ፣ አንተ ደግሞ የለየለት ወፈፌ ነው አልክ፣ ግን ሰውየው ሰክሮ ነው የሚሳደበው መረጃችሁ ምንድነው?›› ሲላቸው ሁለቱም አንገታቸውን አቀርቅረው በአንድ ድምፅ ‹ግምት ነው!› ሲሉት፣ ‹‹ለካ ፌስቡክ ላይ በግምት እየጻፋችሁ ነው ሕዝብ የምታጋድሉት?›› ያላቸው አይረሳኝም፡፡ ለነገሩ የስንቱን ወሬኛ አሉባልታ አስታውሰን እንችላለን!

ምሁሩ የባሻዬ ልጅ፣ ‹‹አየህ የአስተሳሰብ ልዩነትና የግንዛቤ እጥረት ምን ያህል እንደሚያጃጅለን። እንግዲህ ይኼ ሁሉ ሰው በየፊናው ትክክል ነኝ ካለ ችግር ነው። ታዲያ እንዴት ሆኖ ነው አገር በዘመናዊ ፖሊሲና አመራር ብቻ የሚለወጠው? በተጨባጭ ማስረጃ መተማመን ዘበት በሆነበት ጎዳና ድክ ድክ ብለው የሚያድጉትስ እንዴት ብለህ ተስፋ ትጥልባቸዋለህ?›› ሲለኝ ቆም ብዬ አሰብኩ። እስኪ እናንተም ቆም በሉና አሰላስሉ። አዕምሮ ካልተለወጠ እኮ ሌላው ዘበት ነው ጎበዝ። በተለይ በዚህ አንዱን ጥሎ ሌላውን አንጠልጥሎ ዓይነት የወየበ አስተሳሰብ ለመቀየር ከዕውቀት ውጪ ሌላ መላ ያለው አልመሰለኝም። ትምህርቱም እንምታዩት ገለባ የሆነ ይመስላል፡፡ ከስማቸው በፊት የተለያዩ ማዕረጎችን የለጠፉ ተንታኝ ተብዬዎች ደግሞ ትንታኔ ይለቁባችኋል፡፡ ትናንት አክብራችሁ ላይ የሰቀላችኋቸው እንደ ላባ ቀለው ትንሽ ሲሆኑ ስታዩ ታፍራላችሁ፡፡ ኢትዮጵያ ስንትና ስንት ጀግኖችን ያፈራች የአስተዋዮች አገር እንደነበረች እየተረሳ፣ እያደር የሚቀሉ ነፍሶችን ስትታዘቡ ግራ ትጋባላችሁ፡፡ ይህን ጊዜ ነው ታዲያ ቁጭት ውስጣችሁ እየተፈጠረ ያለፉትን ዘመናት የምታስታውሱዋቸው፡፡ ለአገራቸው ምናቸውንም ሳይሰስቱ መስዋዕትነት የከፈሉ መምህራን፣ ሐኪሞች፣ ወታደሮች፣ ወጣቶች፣ ሴቶች፣ አርሶ አደሮች፣ የእምነት አገልጋዮች፣ ታታሪ ሠራተኞች፣ ወዘተ ስታስቡ ታዝናላችሁ፡፡ ይህን ጊዜ ነው ታዲያ እኔስ ማን ነኝ መባል ያለበት፡፡ እኔ ደላላው አንበርብር ምንተስኖት ምንም ደላላ ብሆን በሀቅ ለአገር መሥራትና ሕዝብን ማገልገል ታላቅ ኩራት ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ይህ እምነቴ እስከ መቃብር አብሮኝ እንዲወርድ ፍላጎቴ ፅኑ ነው፡፡ ፅናት ካለ ደግሞ የታሰበው ሁሉ ይሳካል፡፡ መፈክሬ ደግሞ ፅናት ያስከብራል ነው፡፡ ለዓላማ መፅናትን የመሰለ ምን አለ? መልካም ሰንበት! 

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት