በአማራ ክልል በማዕከላዊ ጎንደር ዞን በጭልጋ ወረዳና በአካባቢው በመስከረም ወር 2012 ዓ.ም. በተከሰተ ግጭት፣ በሞቱ 43 ሰዎችና ከቀዬአቸው በተፈናቀሉ ከስምንት ሺሕ በላይ አባወራዎች የተጠረጠሩ 156 ግለሰቦች ተከሰሱ፡፡
በወንጀል ድርጊት የተጠረጠሩት ግለሰቦች የፍርድ ቤት ሒደታቸው በተለያየ ደረጃ ላይ መሆኑን፣ በ14 ግለሰቦች ላይ ተጨባጭ ማስረጃ በመቅረቡ የቅጣት ውሳኔ ተላልፎባቸው ወደ ማረሚያ ቤት መውረዳቸውን፣ የጎንደር ከተማ አዴፓ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሞላ መልካሙ ገልጸዋል፡፡
ቀሪዎቹ ተከሳሾች ጉዳያቸው ገና በፍርድ ቤት እየታየ መሆኑን፣ 27 ተጠርጣሪዎች ምርመራ እየተካሄደባቸው እንደሆነና የ17 ተጠርጣሪዎች ምርመራ ተጠናቆ ወደ ፍርድ ቤት መላኩንም አክለዋል፡፡ 98 ተጠርጣሪዎች ላይ ማስረጃ መቅረብ ባለመቻሉ በነፃ መሰናበታቸውን ኃላፊው ገልጸዋል፡፡
በወቅቱ በተከሰተው ግጭት ከሞትና አካል መጉደል በተጨማሪ፣ በ145 አባወራዎች ቤትና ንብረት ላይ ጉዳት መድረሱንና ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያለው ንብረት መውደሙን አቶ ሞላ አስረድተዋል፡፡
በወቅቱ ተከስቶ የነበረውን ግጭት ወጣቶች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የከተማው የሰላምና የልማት ሸንጎዎች፣ አመራሩና የፀጥታ ኃይሎች ተረባርበው ባያስቆሙት ከፍተኛ የሆነ ጉዳት ሊያደርስ ይችል እንደነበርም ኃላፊው አክለዋል፡፡
በወቅቱ በተከሰተው አለመረጋጋትና የሰላም ዕጦት በንግድ፣ በኢንቨስትመንትና በቱሪዝም እንቅስቃሴ ላይ ከፍተኛ የሆነ አሉታዊ ተፅዕኖ ፈጥሮ እንደነበርም ጠቁመዋል፡፡ በማዕከላዊ ጎንደር በወቅቱ ተከስቶ የነበረውን ግጭት በሚመለከት መዘገባችን ይታወሳል፡፡