Wednesday, July 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናዕጣ የወጣላቸው የ20/80 የጋራ መኖሪያ ቤቶች ዕድለኞች በችግር ላይ ነን አሉ

ዕጣ የወጣላቸው የ20/80 የጋራ መኖሪያ ቤቶች ዕድለኞች በችግር ላይ ነን አሉ

ቀን:

ከአሥር ወራት በፊት የካቲት 27 ቀን 2011 ዓ.ም. በኢንተርኮንቲኔንታል ሆቴል ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ (ኢንጂነር) በተገኙበት ዕጣ የወጣላቸው ከ32 ሺሕ በላይ የ20/80 የጋራ መኖሪያ ቤቶች ዕድለኞች፣ ቤቶቹ እስካሁን ተላልፈው እንዳልሰጧቸውና በችግር ላይ መሆናቸውን ገለጹ፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የቁጠባ ቤቶች ልማት ኢንተርፕራይዝ የተገነቡ በ13ኛው ዙር ዕጣ የወጣባቸው 1,248 ስቱዲዮ፣ 18,823 ባለአንድ መኝታ ቤት፣ 7,127 ባለሁለት መኝታ ቤትና 5,455 ባለሦስት መኝታ ቤቶች መሆናቸው ይታወሳል፡፡

ዕጣው የደረሳቸው ዕድለኞች የሚጠበቅባቸውን የቅድሚያ ክፍያ ለመፈጸም ተዘጋጅተው እየተጠባበቁ ቢሆንም፣ ላለፉት አሥር ወራት ምንም ዓይነት ጥሪ እንዳልተደረገላቸውና ምን እየተደረገ እንደሆነ የሚያውቁት ነገር ባለመኖሩ ግራ መጋባታቸውን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

ባለሁለት መኝታ ቤትና ባለአንድ መኝታ ቤት ከደረሳቸው ግሰቦች ውስጥ መሆናቸውን የሚናገሩት አቶ ፍፁም ሰለሞን፣ ወ/ሮ አዳነች ጋቢሳ፣ አቶ ቆቱ ጋዲሳ፣ ወ/ሮ ፍሬሕይወት አዳነና አቶ ገብረ ዮሐንስ በንቲ፣ የቤቶቹ ዕጣ ከወጣበት ከየካቲት 27 ቀን 2011 ዓ.ም. እስከ የካቲት 30 ቀን 2011 ዓ.ም. ድረስ እንቅልፍ አልነበረንም ይላሉ፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ‹‹ዕድለኛ ሆኜ ይሆን ወይስ አልደረሰኝም?›› የሚል ጥያቄ በአዕምሯቸው ሲያሰላስሉና መረጃውን አግኝተው እስከሚገላገሉ ድረስ፣ በጭንቀት በማሳለፋቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ዕድለኞቹ ዕጣው እንደደረሳቸው ካረጋገጡ በኋላ፣ ሩጫቸው ቅድሚያ ክፍያው ስንት እንደሆነና በቆጠቡት ላይ የሚያስጨምራቸው ስንት እንደሆነ፣ ወይም የቆጠቡት በቂ መሆኑን ለማረጋገጥ እንደነበር አክለዋል፡፡

የቆጠቡት በቂ የሆነላቸው ከተጨማሪ ጭንቀት ሲላቀቁ፣ ተጨማሪ ገንዘብ የሚያስፈልጋቸው ከወዳጅ ዘመዳቸው ፈላልገው ከአስተዳደሩ ጋር የሚፈራረሙበትን ቀን ሲጠባበቁ አሥር ወራት እንደሞላቸው ይናገራሉ፡፡

የቤትን ችግር የማያውቅ በተለይ የአዲስ አበባ ተከራይ ነዋሪ ስለሌለ አበዳሪዎቻቸው እየቸገራቸውም ቢሆን እስካሁን ዝም እንዳሏቸው የሚናገሩት ዕድለኞቹ፣ አስተዳደሩ ቁርጡን ቢነግራቸው ቢያንስ የተበደሩትን ለመመለስ እንደሚችሉ ተናግረዋል፡፡ ከኑሮ ውድነቱ ጋር በየሦስት ወሩ የሚጨመረው የቤት ኪራይ አማሯቸው ባለበት ወቅት፣ ከልጆቻቸው ጉሮሮ እየቀነሱ የቆጠቡለት ቤት ዕድለኛ በመሆናቸው ደስታቸው ከፍተኛ የነበረ ቢሆንም፣ ደስታቸው ከቀናት ያላለፈ መሆኑንና የኑሮ ውድነቱና የቤት ኪራይ ተደራርበው በከፍተኛ ችግር ውስጥ እንደወደቁ ገልጸዋል፡፡

በወቅቱ በተለይ ኮዬ ፈጬ አካባቢ ከተገነቡ ቤቶች ጋር በተያያዘ ተከስቶ የነበረው አለመግባባት እንኳን የት እንደደረሰ፣ ዕጣ የደረሳቸው ነዋሪዎች ዕጣ ፈንታ ምን እንደሆነ አስተዳደሩ መግለጽ ሲገባው ዝም ማለቱንና ስለቤቶቹ አጠቃላይ ሁኔታ ምንም ዓይነት መረጃ ማግኘት እንዳልቻሉም ጠቁመዋል፡፡ በአዲስ አበባና ኦሮሚያ ክልል መካከል ስለተፈጠረው የወሰን አከላለል ሁኔታ አጥንቶ የመፍትሔ ሐሳብ ያቀርባል የተባለ ኮሚቴ ከተለያዩ አካሎች ተውጣጥቶ መቋቋሙ ቢነገርም፣ እስካሁን ምን እንደሠራና ምን ውጤት እንዳቀረበ እንኳን ማወቅ አለመቻላቸው እንዳሳዘናቸው ተናግረዋል፡፡

መንግሥትና የሚመለከተው አካል በተለይ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ የኅበረተሰብ ክፍሎችን ባለቤት ለማድረግ፣ በመንግሥት ዕገዛና በነዋሪዎች መዋጮ የተገነቡ ቤቶች ለዕድለኞች በወቅቱና በአግባቡ እንዲተላለፉላቸው ጠይቀዋል፡፡

የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ጨምሮ በአዲስ አበባ ከተማ የሚገነቡ የቤቶች ልማት የሚቆጣጠረውን የአስተዳደሩ ቤቶች ልማት ቢሮ ኃላፊ ሰናይት ዳምጠው (ኢንጂነር)፣ የ13ኛው ዙር የ20/80 የጋራ መኖሪያ ቤቶች ዕጣ ዕድለኞች የሚያነሱትን አቤቱታ በሚመለከት ማብራሪያ እንዲሰጡ ሪፖርተር ለማግኘት በተደጋጋሚ ያደረገው ጥረት አልተሳካም፡፡ የአስተዳድሩ ቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን ሥራ አስኪያጅ አቶ ደሳለኝ ተረፈ በተለይ የ40/60 እና 20/80 የጋራ መኖሪያ ቤቶችን በሚመለከት ለሚነሱ ጥያቄዎች ምላሽ መስጠት ያለባቸው ቢሆንም፣ እሳቸውንም ለማግኘት ተደጋጋሚ ጥረት ቢደረግም ማግኘት አልተቻለም፡፡

የካቲት 27 ቀን 2011 ዓ.ም. ዕጣ የወጣባቸው 32,653 የ20/80 የጋራ መኖሪያ ቤቶችና 18,576 የ40/60 የጋራ መኖሪያ ቤቶች መሆናቸው ይታወቃል፡፡ የ20/80 ቤቶችን በሚመለከት በተለይ ኮዬ ፈጬ ለነበሩ የልማት ተነሺዎች ያለ ዕጣ ቤት እንደሚሰጣቸው ምክትል ከንቲባ ታከለ በዕጣ አወጣጡ ሥነ ሥርዓት ላይ የተናገሩ ቢሆንም፣ በነጋታው ተቃውሞ መነሳቱ ይታወሳል፡፡ ተቃውሞው የወሰን አከላለል ጥያቄም ጭምር በማስነሳቱ ከከተማ አስተዳደሩና ከኦሮሚያ ክልል የተውጣጡ ኮሚቴዎች ተሰይመው እንዲያጠኑና የመፍትሔ ሐሳብ እንዲያቀርቡ የተባለ ቢሆንም፣ እስካሁን ምን ላይ እንደተደረሰ የታወቀ ነገር የለም፡፡

የ40/60 የጋራ መኖሪያ ቤቶችን በሚመለከት መቶ በመቶ ክፍያ የፈጸሙ ግለሰቦች ዕጣ መውጣቱን ተቃውመው የሕግ ጥያቄ በማቅረባቸው፣ በዕጣው ለጊዜው የታገደ ቢሆንም፣ ቆይቶ በከሰሱት ልክ ብቻ ታግዶ ቀሪው ለባለ ዕድለኞቹ እንዲተላለፍ ፍርድ ቤት ውሳኔ በማሳለፉ፣ ዕድለኞቹ ከአስተዳደሩ ጋር ውል መፈጸማቸው ይታወሳል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የኤርትራ አቪዬሽን ባለሥልጣን የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራዎችን ማገዱን አስታወቀ

የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ጉዳዩን እያጣራሁ ነው ብሏል በኤርትራ ትራንስፖርትና...

[ክቡር ሚኒስትሩ ከተቋሙ የሠራተኞች ማኅበር አመራር ጋር እየተወያዩ ነው]

ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም! በአስቸኳይ እንደፈለጉኝ መልዕክት ደርሶኝ ነው የመጣሁት። አዎ።...

የሱዳን ጦርነትና የኢትዮጵያ ሥጋት

የሱዳን ጦርነት ከጀመረ አንድ ዓመት ከአራት ወራት አስቆጠረ፡፡ ጦርነቱ...

ግለሰብ ነጋዴዎችን በአስገዳጅነት የንግድ ምክር ቤት አባል ለማድረግ ያለመው ረቂቅ አዋጅ ተከለሰ

በምትኩ የንግድ ተቋማት በአስገዳጅነት የንግድ ምክር ቤት አባል ይሆናሉ...