Tuesday, February 27, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

ለመተማመን መደማመጥ ይቅደም!

በኢትዮጵያ የፓርቲ ፖለቲካ ሥራ ውስጥም ሆነ በሌሎች መስኮች የተሰማሩ ወገኖች፣ ለመደማመጥና ለመተማመን ቅድሚያ መስጠት አለባቸው፡፡ ሰዎች እንዴት ሳይነጋገሩ ይግባባሉ? መነጋገር ሲኖር የልዩነቶች መንስዔ ይታወቃል፡፡ ችግሮች ሲፈጠሩ መንስዔያቸው ሳይታወቅ መፍትሔ ፍለጋ አይገባም፡፡ የችግሮችን መንስዔ ለማወቅ ደግሞ መነጋገርን የመሰለ ነገር የለም፡፡ መነጋገር ሲቻል በሰከነ መንገድ መደማመጥ ይለመዳል፡፡ መደማመጥ ባህል ሲሆን መተማመን ይጀመራል፡፡ ለምሳሌ በየትኛውም ሙያ ወይም የሥራ መስክ ውስጥ ሠራተኞች ወይም ባለሙያዎች ውጤታማ መሆን የሚችሉት፣ ከዕቅድ ጀምሮ አፈጻጸም ድረስ በሚኖራቸው መስተጋብር ነው፡፡ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ትልቁ ጉድለት የመነጋገር ባህል አለመለመዱ ነው፡፡ ተፎካካሪን እንደ ጠላት ማየትና ማሳደድ ለዓመታት የተፀናወተ ልማድ ነው፡፡ የተለያየ ዓላማ ያላቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች አመራሮች በሕዝብ ግፊት መገናኘት ሲጀምሩ በጥርጣሬ የተሞሉ ስለሆኑ፣ ግንኙነታቸው ዘለቄታዊ ሳይሆን ጊዜያዊ ይሆናል፡፡ ግንባር ወይም ቅንጅት ቢፈጥሩ እንኳ አብረው አይዘልቁም፡፡ ቢዘልቁም አንዱ የበላይ ሌላው የበታች ሆነው ነው፡፡ በመሠረታዊ ጉዳዮች ላይ ተነጋግረው የጋራ ችግሮችን ለመፍታት ከሚጥሩ ይልቅ አሉባልታ ይበትናቸዋል፡፡ በጠረጴዛ ዙሪያ በሚደረጉ ውይይቶች ሊፈቱ የሚችሉ ችግሮች በወሬ በሚበረግጉ ሰዎች ምክንያት ከአንድ ትውልድ ወደ ሌላው እየተሻገሩ የጥላቻ፣ የቂም በቀልና የሴረኝነት መነሻ ይሆናሉ፡፡ መደማመጥ በሌለበት መተማመን ስለማይኖር የአገር ችግሮች የመፍትሔ ያለህ እያሉ ዓመታት ይነጉዳሉ፡፡ አሀዳዊና ፌዴራሊስት እየተባባሉ መካሰስ ፋይዳ የለውም፡፡

በኢትዮጵያ ውስጥ የብሔር ጥያቄ በይፋ ለውይይት ከቀረበ ከሃምሳ ዓመታት በኋላ፣ ጥያቄው በአግባቡ መልስ አግኝቶ መስማማት አለመቻሉ ከሚገርሙ ጉዳዮች መካከል ተጠቃሽ ነው፡፡ ለአገር በቀል ችግር መፍትሔው አገራዊ መሆን ሲገባው ከባህር ማዶ በተገለበጡ ውኃ የማይቋጥሩ ንድፈ ሐሳቦች በኢትዮጵያ ምድር መከራ ወርዷል፣ በሺዎች የሚቆጠሩ አልቀዋል፡፡ ኢትዮጵያን ሁሉንም በእኩልነት የምታስተናግድ አገር ለማድረግ በጋራ መሥራት እየተቻለ፣ መለስተኛ ቅራኔዎችን ከመጠን በላይ በመለጠጥ በጠላትነት መተያየት ቀጥሏል፡፡ በኢትዮጵያ ምድር ኅብረ ብሔራዊ ሥርዓት መገንባት  እየተቻለ፣ ዛሬም ‹‹ከእንቁላሉና ከዶሮዋ ማን ይቀድማል?›› የሚለው ዓይነት አሰልቺ ንትርክ መባባሱ ያስገርማል፡፡ ኢትዮጵያ ከ80 በላይ ብሔር ብሔረሰቦች የሚኖሩባት አገር መሆኗ እየታወቀ የአንድ ብሔር የበላይነት ሊመጣ ነው ማለት ዕብደት የመሆኑን ያህል፣ ብዝኃነትን ባለመቀበል ኅብረ ብሔራዊ አገር ስለመሆኗ መጠራጠርም የለየለት ወፈፌነት ነው፡፡ ይልቁንም ኢትዮጵያ ምን ዓይነት ፌዴራሊዝም ይጠቅማታል? የምርጫ ሥርዓቷ ምን ቢሆን ትጠቀማለች? የፖለቲካ ምኅዳሩ እንዴት ቢደላደል አሳታፊነቱ የበለጠ ይጨምራል? የፖለቲካ ፓርቲዎች በምን ዓይነት ጥንካሬ ላይ ቢገኙ ሕዝቡ የተሻሉ አማራጮችን ያገኛል? በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚ፣ በማኅበራዊና በውጭ ጉዳይ ምን ዓይነት ፖሊሲዎች ያስፈልጋሉ? ወዘተ ላይ ማተኮር ይመረጣል፡፡ ይህንን ማድረግ የሚቻለው ግን መወያየት፣ መደማመጥና መተማመን ሲኖር ብቻ ነው፡፡ በሰለቹ ትርክቶች መናጀስ ኋላቀርነት ነው፡፡

ግለሰቦች ያዋጣናል የሚሉትን የፖለቲካ ፓርቲ በአባልነት የመቀላቀል፣ የመደገፍና ሐሳባቸውን በነፃነት የመግለጽ መብት አላቸው፡፡ ሌሎችም እንዲሁ ባሻቸው ፓርቲ ሲደራጁና ሐሳባቸውን ሲገልጹ መብታቸውን ማክበር ይጠበቅባቸዋል፡፡ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችም ሆኑ አባላትና ደጋፊዎች ትኩረት ማድረግ የሚገባቸው በራሳቸው የውስጥ ጉዳይ ላይ ቢሆንም፣ ከሌሎች ጋር ለሚኖራቸው መስተጋብርም ትኩረት ሊሰጡ ይገባል፡፡ አንድ የፖለቲካ ፓርቲ የፈለገውን ርዕዮተ ዓለም በመምረጥ ደንቡንና ፕሮግራሙን እንደሚቀርፀው ሁሉ፣ ስለሌላው ምርጫና ፍላጎት ግን አያገባውም፡፡ የሚያገባው ጉዳይ ቢኖር በጋራ በሚወስኑበት አገራዊ ውይይትና ድርድር ላይ ብቻ ነው፡፡ የሚፎካከሩበት የፖለቲካ ምኅዳርና የሚዳኙዋቸው የፓርቲ ፖለቲካ ሕጎች የመነጋገሪያ አጀንዳ ሲሆኑ፣ የፓርቲ ውስጣዊ ጉዳዮች ግን ለፓርቲውና ለአባላቱ ይተዋሉ፡፡ የፖለቲካ ተንታኝና አክቲቪስት ነን የሚሉትም በፓርቲ የውስጥ ጉዳይ ላይ ከሚያተኩሩ ይልቅ፣ ውጫዊ ግንኙነቱ ላይ አፅንኦት ቢሰጡ ውይይቱም ሆነ ድርድሩ ቀና ይሆናል፡፡ ፓርቲዎች ምን ዓይነት አጀንዳ ወይም ፖሊሲ ይዘው ሕዝብ ዘንድ ቀረቡ የሚለው ርዕስ ለውይይት ይመጥናል፡፡ የፓርቲዎቹ ውስጣዊ ጉዳይ ነፀብራቅ የሆኑ ፖሊሲዎች ዳኝነት የሚያገኙት በመራጩ ሕዝብ ብቻ ነውና፡፡ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ የተንሰራፋ አንዱ ችግር ይህ ነው፡፡ አገርን በማዳን፣ በሕዝብ ሰላምና ደኅንነት ስም የፓርቲዎችን ልዩነት በማጦዝ ችግር መፍጠርም ተገቢ አይደለም፡፡ ነገር ግን ራስን ለውይይት፣ ለድርድርና ለመተማመን ማዘጋጀት የተሻለ ነው፡፡ ለአገር ሰላም የሚበጀውም ይኸው ነው፡፡

ኢትዮጵያ ከፊቷ የተጋረጡ በርካታ ችግሮች ያሉባት አገር ናት፡፡ የአገር ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ወገኖች በሙሉ ለመነጋገርና ለመደማመጥ ጊዜ መስጠት አለባቸው፡፡ በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ፅኑ የሆነ የምግብ ችግር አለ፡፡ የኑሮ ውድነቱ እየባሰበት ነው፡፡ የሥራ አጥነቱ መጠን በፍጥነት እያሻቀበ ነው፡፡ የአገሪቱ የዕዳ ጫና ከባድ ነው፡፡ ጥራት ያለው የትምህርትና የጤና አገልግሎት ተደራሽነት በጣም ዝቅተኛ ነው፡፡ በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት በተፈጥሮ ሀብቶች ላይ ከፍተኛ ጉዳት እየደረሰ ነው፡፡ በገጠርም ሆነ በከተማ የሚኖሩ በርካታ ሚሊዮኖች ከድህነት ወለል በታች ይኖራሉ፡፡ በተቃራኒው ግን በአግባቡ የሚያሠሩ ፖሊሲዎች ከተነደፉ የአገሪቱ የሰው ኃይልና የተፈጥሮ ሀብቶች ከበቂ በላይ ናቸው፡፡ በዚህ ወሳኝ ጊዜ በሰከነ መንገድ መነጋገርና መደማመጥ ያስፈልጋል፡፡ ፖለቲከኞች ምኅዳራቸው በሥርዓት ተመሥርቶ ሰላማዊ የፖለቲካ ፉክክር እንዲፈጠር፣ ልዩነቶቻቸውን አስታርቀው በጋራ መሥራት አለባቸው፡፡ በተለያዩ መስኮች የተሰማሩ ምሁራንና ልሂቃን ለፖሊሲዎች ግብዓት የሚሆኑ ድጋፎችን የማበርከት ኃላፊነት አለባቸው፡፡ መንግሥት ግብዓቶችን ተቀብሎ ተግባራዊ እንዲያደርጋቸው ተደራጅተው ጫና ማሳደር ይጠበቅባቸዋል፡፡ ለአገራቸው ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከት የሚችሉ ልምድ ያካበቱ ወገኖች በማሰባሰብ ጭምር አገራዊ ኃላፊነት መወጣት ግዴታቸው ነው፡፡ በተጨማሪም በአገሪቱ የመነጋገርና የመደማመጥ፣ እንዲሁም የመተማመን ባህል እንዲጎለብት ግፊት ማድረግ አለባቸው፡፡ በር ዘግቶ መብሰልሰል አያዋጣም፡፡ በከንቱ የባከኑ ዓመታት ያስቆጫሉ፡፡

በሌላ በኩል ባሉት ችግሮች ላይ ተጨማሪ ችግሮች በመቀፍቀፍ ላይ የተጠመዱ ወገኖችም፣ አንድ ጉዳይ ላይ አጽንኦት ቢሰጡ መልካም ነው፡፡ የሚፈልጉትን ዓላማ ለማሳካት ሲነሱ፣ የሕዝብን ሕይወትና የአገርን ህልውና አደጋ ውስጥ ከሚከት ድርጊት መታቀብ አለባቸው፡፡ በእነሱ ምክንያት ንፁኃን ሲገደሉ፣ ንብረታቸው ሲዘረፍና ሲወድም፣ ሲፈናቀሉና የአገር ሰላም ሲታወክ ለጊዜው ከሕግ ተጠያቂነት ቢያመልጡም፣ ከታሪክ ተጠያቂነት የሚታደጋቸው ግን የለም፡፡ ከሕግ ለጊዜው ቢሰወሩም ቆየት ብሎ ፍትሕ ደጃፍ ላይ መገተራቸውም አይቀሬ ይሆናል፡፡ በ21ኛው ክፍለ ዘመን በሥልጡን የፖለቲካ መንገድ ቢጓዙ የሚጠየቁት አንድ ነገር ብቻ ነው፡፡ እሱም የሕዝብን ቀልብ የሚስብ አጀንዳ ነው፡፡ ሕዝብ የሚፈልገው ሰላሙን በዘለቄታዊነት የሚያረጋግጥለት፣ ከድህነት አረንቋ ውስጥ የሚያወጣውና ነገን ብሩህ የሚያደርግለት ፖሊሲ ነው፡፡ ይህ ነው የሚባል አማራጭ ፖሊሲ ሳያቀርቡ መፎከር ዋጋ የለውም፡፡ አንዴ ቢሳካ እንኳ መድገም አይቻልም፡፡ ዘለቄታዊና አስተማማኝ የሆነ የሕዝብ ተቀባይነት ማግኘት የሚቻለው ግን ለውይይት፣ ለድርድርና ለመተማመን ዝግጁ የሆነ አደረጃጀትና ሥምሪት ሲኖር ነው፡፡ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ኃይሎችም ሆኑ በዙሪያቸው ያሉ ወገኖች ከተራ ብሽሽቅ፣ እሰጥ አገባ፣ ሐሜት፣ አሉባልታና ለትዝብት ከሚዳርጉ ድርጊቶች መታቀብ ይኖርባቸዋል፡፡ ኢትዮጵያን ታላቅ አገር አድርጎ በሰላም፣ በነፃነት፣ በፍትሕና በእኩልነት ለመኖር የሚያስችል ሥርዓት ዕውን ማድረግ የዘመኑ ትውልድ ኃላፊነት ነው፡፡ ኃላፊነትን አለመወጣት ለፀፀት ይዳርጋል፡፡ ፀፀት ደግሞ መፍትሔ ሆኖ አያውቅም፡፡ ስለዚህ ለመተማመን መደማመጥ ይቅደም!    

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

የመጣንበትና አብረን የምንዘልቅበት የጋራ እሴታችን ለመሆኑ ነጋሪ ያስፈልጋል ወይ?

በኑረዲን አብራር በአገራችን ለለውጥ የተደረጉ ትግሎች ከመብዛታቸው የተነሳ ሰላም የነበረበት...

አልባሌ ልሂቃንና ፖለቲከኞች

በበቀለ ሹሜ በ2016 ዓ.ም. ኅዳር ማክተሚያ ላይ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ...

አሜሪካ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ተገቢነት ቢኖረውም ከጎረቤት አገሮች ጋር በሚደረግ ንግግር መሆን አለበት አለች

መንግሥትን ከፋኖና ከኦነግ ሸኔ ጋር ለማነጋገር ፍላጎቷን ገልጻለች የኢትዮጵያ የባህር...

ሕወሓት በትግራይ ጦርነት ወቅት በፌዴራል መንግሥት ተይዘው ከነበሩት አባላቱ መካከል ሁለቱን አሰናበተ

በሕወሓት አባላት ላይ የዓቃቤ ሕግ ምስክር የነበሩት ወ/ሮ ኬሪያ...

የኤሌክትሪክ ኃይል ለታንዛኒያ ለመሸጥ የሚያስችል ስምምነት ለመፈጸም የመንግሥት ውሳኔ እየተጠበቀ ነው

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ለታንዛኒያ የኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭ ለማከናወን የሚያስችለውን...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ሰብዓዊ ቀውሶችን ማስቆም ተቀዳሚ ተግባር ይሁን!

በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ከአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ተወክለው ከመጡ ሰዎች ጋር ያደረጉት ውይይት፣ በአማራ ክልልም ሆነ በሌሎች ሥፍራዎች የሚካሄዱ ግጭቶች ምን...

የበራሪው የኅብረተሰብአዊት ኢትዮጵያ ጀግና ጄኔራል ለገሠ ተፈራ ቅርሶችን የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተረከበ

በቀድሞው የኢትዮጵያ መንግሥት (1967-1983) ዘመን የኅብረተሰብአዊት ኢትዮጵያ ጀግና ሜዳይ የየካቲት 1966 1ኛ ደረጃ ኒሻን ተሸላሚ የነበሩ የአየር ኃይል ጀት አብራሪው የብርጋዴር ጄኔራል ለገሠ ተፈራ...

የዜጎች በነፃነት የመንቀሳቀስ መብት ዘላቂ መፍትሔ ይበጅለት!

ሰሞኑን በአዲስ አበባ የተካሄደው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ በተጠናቀቀ ማግሥት፣ መንግሥት ልዩ ትኩረት የሚሹ በርካታ ጉዳዮች እየጠበቁት ነው፡፡ ከእነዚህ በርካታ ጉዳዮች መካከል በዋናነት የሚጠቀሰው...