Monday, December 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናግብፅ በህዳሴ ግድብ የውኃ ሙሌት ኢትዮጵያ የቅኝ ግዛት ስምምነት እንድትቀበል ግፊት ማድረጓ...

ግብፅ በህዳሴ ግድብ የውኃ ሙሌት ኢትዮጵያ የቅኝ ግዛት ስምምነት እንድትቀበል ግፊት ማድረጓ ተገለጸ

ቀን:

በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የውኃ ሙሌትና አለቃቀቅን በተመለከተ ኢትዮጵያ፣ ግብፅና ሱዳን የጋራ ስምምነት ላይ እንዲደርሱ በአሜሪካ ታዛቢነት የተጀመረው ውይይት ግቡን እንዲመታ ከማድረግ ይልቅ፣ ኢትዮጵያ ፈራሚ ያልሆነችበትን የቅኝ ግዛት ስምምነት እንድትቀበል ለማድረግ ግብፅ ግፊት እያደረገች ነው ተባለ፡፡ በዚህ የግብፅ መንግሥት ያልተገባ አካሄድ ምክንያትም ባለፈው ሳምንት መጀመሪያ ላይ በግብፅ ከተማ ለሁለት ቀናት የተካሄደው የሦስቱ አገሮች ውይይት ስምምነት ሳይደረስበት ያለመግባባት መጠናቀቁን፣ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው የኢትዮጵያ መንግሥት ኃላፊዎች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

ተቋርጦ የነበረው የሦስቱ አገሮች ውይይት በአሜሪካ መንግሥትና በዓለም ባንክ ታዛቢነት ከሳምንታት በፊት በአዲስ አበባ ይጀመር የነበረው የውይይት መንፈስ፣ ከዚህ ቀደም ከነበሩት ሁሉ እጅግ አዎንታዊ የነበረና በበርካታ መሠረታዊ ጉዳዮች ላይም ስምምነት የተደረሰበት እንደነበር የሚገልጹት ኃላፊዎቹ፣ ባለፈው ሳምንት በካይሮ በቀጠለው ውይይት ወቅት ግን ግብፅ ወደ ቀድሞ አቋሟ በመመለስ የውይይቱን መንፈስ ያደፈረሰችበት እንደነበር አመልክተዋል፡፡

በአዲስ አበባ በነበረው ስብሰባ ሦስቱም አገሮች በታዛቢዎች ፊት ግድቡን ከአራት እስከ ሰባት ዓመታት ባለው ጊዜ ለመሙላት መሠረታዊ ስምምነት አድርገው እንደነበር ያስታወሱት ኃላፊዎቹ፣ በግብፅ በተካሄደው ስብሰባ አዲስ አበባ ላይ ከተደረሰው መሠረታዊ ስምምነት በመነሳት በዚያው መንፈስ መነጋገር አለመቻሉን ተናግረዋል፡፡ ወደ ስምምነት ለመምጣት ይቅርና በአዲስ አበባው ውይይት ግድቡን ከአራት እስከ ሰባት ዓመት ለመሙላት ተደርሶ የነበረውን ስምምነት የሚያፈርስ ሐሳብ በግብፅ በኩል ዳግም መቅረቡን አስረድተዋል፡፡

በግብፅ በኩል የተነሳው ሐሳብ አዲስ አለመሆኑን የተናገሩት ኃላፊዎቹ፣ የግድቡ ውኃ ሙሌት በሚከናወንባቸው ዓመታት ቢያንስ 40 ቢሊዮን ሜትር ኩብ ውኃ ወደ ግብፅ መፍሰሱን ኢትዮጵያ እንድታረጋግጥ፣ በግብፅ የሚገኘው የአስዋን ግድብ የውኃ መጠን ከፍታ 165 ሜትር ላይ ካልደረሰ ኢትዮጵያ ውኃ መያዝ እንደማትችል ዳግም መጠየቋን ተናግረዋል፡፡

ይህ ማለት ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድቡን ውኃ መሙላት እንዳትችል የሚያደርግ ብቻ ሳይሆን፣ ሌሎች የዓባይ ገባሪዎችንም እንዳታለማ በእጅ አዙር የሚጠመዝዝና የዓባይን ውኃ በዋናነት ለግብፅ የሚሰጠውን የቅኝ ግዛት ስምምነት ኢትዮጵያ እንድትቀበል ተድበስብቦ የቀረበ ሐሳብ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ በአጠቃላይ ግብፅ ወደ ስምምነት ለመምጣት የሚደረገውን ጥረት ውስጥ እየተሳተፈች እንደሆነ በማስመሰል፣ ኢትዮጵያ በቅኝ ግዛት ወቅት የተፈረመውን የግብፅ የውኃ ድርሻ እንድትቀበል ጫና ማድረግ ላይ ትኩረት ማድረጓን አክለዋል፡፡

ኢትዮጵያ ፈጽሞ በዚህ ሴራ ውስጥ እንደማትወድቅ የሚናገሩት ኃላፊዎቹ፣ እ.ኤ.አ. በ1956 በግብፅና በሱዳን የተፈረመው የውኃ ክፍፍል ስምምነት የላይኛው ተፋሰስ አገሮች ውኃውን ለመጠቀም ሲፈልጉ ለግብፅና ለሱዳን በተሰጠው የውኃ ኮታ ላይ ውይይት ተመሥርቶ በሚደረግ ስምምነት ተጠቃሚ መሆን እንደሚችሉ የሚገልጸውን አንቀጽ እንኳን፣ ግብፆች አጢነውት እንደማያውቁ ጠቁመዋል፡፡

በመሆኑም ግብፅ በትብብር ወደ ስምምነት ለመምጣት ፍላጎቱ እንደሌላት ጠቋሚ መሆኑን ያመላክታል ብለዋል፡፡ ውይይቱ ያለ ስምምነት ቢጠናቀቅም ከሳምንታት በኋላ ሌላ ዙር ውይይት በሱዳን እንደሚቀጥል ገልጸዋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ የዓረብ አገሮች ፓርላማ ኅብረት ለኢትዮጵያ ፓርላማ የኢትዮጵያ መንግሥት የግብፅን ታሪካዊ የውኃ ድርሻ ሊያከብር ይገባል በማለት ያወጣውን የውሳኔ ሐሳብ የሚገልጽ ደብዳቤ በማውገዝ፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ታገሰ ጫፎ የምላሽ ደብዳቤ መላካቸው ታውቋል፡፡

አፈ ጉባዔ ታገሰ በጻፉት ደብዳቤ የዓረብ ፓርላማ ባወጣው የግብፅ ታሪካዊ የውኃ ድርሻ እንዲከበር በማለት ከግብፅ ጎን ሲቆም፣ ስለኢትዮጵያ መብት ምንም አለማለቱ እንዳሳዘናቸው ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ አባል ስላልሆነችበት የቅኝ ግዛት ስምምነት ልትጠየቅ እንደማይገባት በላኩት ደብዳቤ የገለጹት አፈ ጉባዔ ታገሰ፣ የውኃ ሀብቷን ለማልማት የሚከለክላት ምንም ዓይነት ዓለም አቀፍ ስምምነት ሳይኖር በወንድማማችነትና በትብብር መንፈስ ግብፅ እንድትሳተፍ በማድረጓ ልትመሠገን እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

የዓረብ አገሮች ፓርላማ ኅብረት ከዚህ ተቃራኒ የሆነ አቋም ማራመዱ ተገቢ እንዳልሆነ ጠቅሰው፣ አቋሙን እንዲያርምና ከእንዲህ ዓይነት የትብብር መንፈስን ከሚያፈረስ ተግባርም እንዲቆጠብ አሳስበዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በዓለም አቀፍ ደረጃ ሕይወታቸውን በኤድስ ምክንያት ላጡ ሰዎች 35ኛ ዓመት መታሰቢያ

ያለፍንበትን እያስታወስን በቁርጠኝነት ወደፊት እንጓዝ - በኧርቪን ጄ ማሲንጋ (አምባሳደር) በየዓመቱ...

እዚያ ድሮን… እዚህ ድሮን…

በዳንኤል ካሳሁን (ዶ/ር) ተዓምራዊው የማዕበል ቅልበሳ “በሕግ ማስከበር” ዘመቻው “በቃ የተበተነ...

ለፈርጀ ብዙ የማንነት ንቃተ ህሊናችን የሚጠቅሙ ጥቂት ፍሬ ነገሮች

በበቀለ ሹሜ ከጨቅላነት ጅምሮ ያለ የእያንዳንዳችን የሰብዕና አገነባብ ከቤተሰብ እስከ...