Friday, December 8, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በ57 ሚሊዮን ዶላር የሚካሄደው የአፍሪካ አዳራሽ ዕድሳት ሲጠናቀቅ ለሕዝብ ክፍት ይደረጋል ተባለ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የአዲስ አበባ አስተዳደር ለማስፋፊያ 3‚100 ካሬ ሜትር ቦታ ሰጥቷል

አፍሪካ ኅብረት የተካው የቀድሞውን የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን ለመመሥረት ጥድፊያ የተገነባውና ለአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ዋና አዳራሽ ሆኖ ሲያገለግል የቆየው አፍሪካ አዳራሽ በቅርስነት እንዲጠበቅ የሚያስችለው መሠረታዊ ጥገና እንዲደረግለት፣ 56.9 ሚሊዮን ዶላር በጀት እንደተያዘለትና ዕድሳቱም በሁለት ዓመታት ውስጥ ተጠናቆ ለሕዝብ ክፍት እንደሚደረግ ተገለጸ፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ከአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ዋና ጸሐፊ ቬራ ሶንግዌ (ዶ/ር)፣ እንዲሁም ከአዲስ አበባ ከተማ የመሬት ልማትና ማኔጅመንት ኤጀንሲ ጋር በተፈራረሙት ስምምነት መሠረት፣ ከአፍሪካ አዳራሽ ዕድሳት ጋር አብሮ ለሚካሄድ የማስፋፊያ ሥራ 3‚100 ካሬ ሜትር ቦታ ተለግሷል፡፡ ከሁለት ዓመታት በኋላ መሠረታዊ የጥገና ሥራው እንደሚጠናቀቅ የሚጠበቀውና አፍሪካ አዳራሽ በመባል የሚታወቀው ታሪካዊው ሕንፃ፣ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመን የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን መሥራች ጉባዔ እንዲያስተናግድ የተገነባ ነው፡፡

ዓርብ ኅዳር 26 ቀን 2012 ዓ.ም. በአፍሪካ አዳራሽ ውስጥ በተካሄደው የስምምነት ሥነ ሥርዓት ወቅት አቶ ገዱ እንዳስታወሱት፣ 32 የአፍሪካ መሪዎች በተገኙበት የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን ለመመሥረት ያስቻለው ስምምነት ተፈርሞ ድርጅቱም በይፋ ተመሥርቷል፡፡ 

በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ብቻም ሳይሆን በአፍሪካ ታሪካዊ ከሚሰኙ ቅርሶች አንዱ ነው ያሉት የዕድሳት ሥራውን በዋና ኃላፊነት የሚመሩት ሚስተር አንቶኒዮ ባዮ ሲሆኑ፣ ዘመናዊ ቴክሎጂዎችን በማካተትና ሕዝብ እንዲጎበኘው ለማድረግ የሚያስችሉ ተጨማሪ ግንባታዎች እንደሚካተቱበት አብራርተዋል፡፡

የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ዋና ጸሐፊ በበኩላቸው፣ የአፍሪካ አዳራሽ በኢትዮጵያ መንግሥት ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በችሮታ የተሰጠ ከመሆኑም በላይ በባለቤትነት የሚያስተዳድረውም እሳቸው የሚመሩት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ነው፡፡ ዋና ጸሐፊዋ ለሪፖርተር እንደገለጹት የአፍሪካ አዳራሽ ዕድሳትና የተሰጠው መሬት፣ ሕንፃውን ሸገርን ከማስዋብ ፕሮጀክት ጋር በማያያዝ ለአዲስ አበባ ከተማ ቱሪዝም መዳረሻ በመሆን አስተዋጽኦ ለማበርከት ያስችለዋል፡፡

የአፍሪካ አዳራሽን በማደስ ሥራ ሒደት በአማካሪ ቦርድ ውስጥ ከተካተቱ በርካታ የለጋሽ አገሮች ተወካዮችና አምባሳደሮች መካከል አንጋፋዋ ዲፕሎማት ቆንጂት ሥነ ጊዮርጊስ (አምባሳደር) ትውስታቸውን አጋርተዋል፡፡ እንደ እሳቸው ገለጻ ከሆነ፣ የመጀመሪያው የአፍሪካ አንድነት መሥራች ጉባዔ ሲካሄድ እሳቸው በወጣት ዲፕሎማትነት ሰነዶችን ለጉባዔተኞች የማሠራጨት ሚና ተሰጥቷቸው ነበር፡፡ በየጊዜው የተከናወኑ የመሪዎችን ውሳኔዎችና ክርክሮች ያስተናገደው የአፍሪካ አዳራሽ፣ የአፍሪካን ታሪኮች የሚዘክር ቅርስ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡

በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ችሮታ በተሰጠው ቦታ ላይ ግንባታው የተካሄደው የአፍሪካ አዳራሽ ሕንፃ፣ የግንባታ ሒደቱ 18 ወራት ብቻ በመውሰድ ግንባታው በተጀመረ በአንድ ዓመት ተኩል ጊዜ እ... 1961 ዓ.ም. መጠናቀቁን ድርሳናት አስፍረዋል፡፡አፍሪካ አዳራሽ 75 ሺሕ ካሬ ሜትር ቦታ ያካተተ ግዙፍና ዘመናዊ ሕንፃ ነው፡፡ ከዚህ ቦታ ውስጥ 3,600 ካሬ ሜትር የስብሰባ አዳራሾች ያረፉበት፣ 5,500 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ የተገነቡ ጽሕፈት ቤቶች፣ እንዲሁም 4,700 ካሬ ሜትር ቦታ የሚሸፍኑ ጠቅላላ አገልግሎት የሚሰጡ ልዩ ልዩ ሕንፃዎችን ያካተተ ትልቅ ተቋም ነው፡፡

የአፍሪካ አዳራሽ ዕድሳት ... 2018 ተጀምሮ 2021 እንዲጠናቀቅና ለአገልግሎት ክፍት እንዲደረግ ታቅዶ እንደነበር መዘገባችን አይዘነጋም፡፡ የወቅቱ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ዋና ጸሐፊ ካርሎስ ሎፔዝ (ዶ/ር) ከቀድሞው የኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት ሙላቱ ተሾመ (/ር) ጋር በሕንፃው ዕድሳት ጉዳይ ላይ በመወያየት፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔ ለሕንፃው ዕድሳት የሚያስፈልገውን ወጪና የጊዜ ሰሌዳ ማፅደቁን ለፕሬዚዳንቱ አስረድተዋቸው ነበር፡፡ የዕድሳት ወጪውንም ተመድ ከአባል መንግሥታት በሚዋጣ ገንዘብ ሊገነባ እንደሚችል ዋና ጸሐፊው አስታውቀው ነበር፡፡ ይሁንና ይህንን ገንዘብ በመዋጣት የአፍሪካ አገሮች በራሳቸው እንዲያሳድሱት በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን በኩል ጥያቄ ሲቀርብላቸው ቆይቷል፡፡ ይሁን እንጂ የዕድሳት ወጪው ሙሉ በሙሉ እንዳልተገኘ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

የመጀመሪያውን መሥራች የአፍሪካ አንድነት ጉባዔ አሳክቶ አጀብ አሰኝቶ የቆየውአፍሪካ አዳራሽ፣ ከጥቂት ዓመታት በኋላ 800 ያህል ተጨማሪ ጽሕፈት ቤቶችን ያካተተ ባለ ስድስት ፎቅ ሕንፃ ... 1975 ታክሎለታል፡፡ በቅርቡም አዲስ አበባን ከብራሰልስና ከኒውዮርክ በመቀጠል በተመድ የሥራ ሥምሪት ረገድ በርካታ ኤጀንሲዎች የሚንቀሳቀሱባት ለመሆኗ ማሳያ የሆነ ተጨማሪ ሕንፃ፣ በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ግቢ ውስጥ ተገንብቶ ለአገልግሎት በቅቷል፡፡

በቀድሞው የዓለም ሎሬት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ ገናና የጥበብ ሥራ በሆነውና 150 ካሬ ሜትር ስፋት ባለው የመስታወት ላይ ሥዕል ያጌጠው ይህ ሕንፃ፣ ‹‹ቶታል ሊበሬሽን ኦፍ አፍሪካ›› የሚል ስያሜ ከያዘው ከዚህ ሥዕል ባሻገር፣ በርካታ የጠቢቡ ሥራዎችም በኪነ ሕንፃው ዙሪያ ይገኛሉ፡፡ በአፍሪካ ብቻም ሳይሆን በዓለም ከሚጠቀሱ ዘመን አይሽሬ ሕንፃዎች አንዱ የሆነው አፍሪካ አዳራሽ፣ ለዕድሳት ዝግ ከተደረገበት ከሁለት ወራት ወዲህ እስከሚጠናቀቅበት እ.ኤ.አ. እስከ 2022 ድረስ ተዘግቶ እንደሚቆይ ቢታወቅም፣ ለበርካቶች የጉብኝት መዳረሻ ሆኖ ሲያገልግል ቆይቷል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች