Friday, December 8, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትለኢትዮጵያ ታዳጊዎች የተዘረጋው የስፔኖች ፕሮጀክት

ለኢትዮጵያ ታዳጊዎች የተዘረጋው የስፔኖች ፕሮጀክት

ቀን:

ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ በርካቶች “ካታላን” ሲባል መጀመሪያ ወደ አዕምሮዋቸው የሚመጣው የባርሴሎና እግር ኳስ ክለብ እንደሚሆን መናገር እንደሚቻል ይገምታሉ፡፡ በስፔን በተለይም በካታላን ዘንድ እንደ ባርሴሎና ሁሉ በስፖርቱ ትልቅ ዕውቅናና ስም ስላለው “አሴዴ ጋቫ ካታላን” የቅርጫት ኳስ ክለብ መኖሩን የሚናገሩት የክለቡ ፕሬዚዳንት ሚስተር ዣቪ እስቴባንና ልዑካናቸው፣ በኢትዮጵያ ቅርጫት ኳስ ላይ ያተኮረ የታዳጊ ወጣቶች ፕሮጀክት መክፈታቸውን ይናገራሉ፡፡

ሚስተር ዣቪና ልዑካናቸው ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ የመጡት ከአሥር ዓመት በፊት ሲሆን፣ ምክንያት የሆኗቸው ደግሞ ከጉዲፈቻ ጋር በተያያዘ ቀደም ብለው ኢትዮጵያን በሚያውቁ አንዲት ግለሰብ አማካይነት ነው፡፡ በወቅቱ በሰሜን ኢትዮጵያ ወልዲያና አካባቢው ለትምህርት ቤቶች የሚሆኑ ቁሳቁሶችን ከማቅረብ ጀምሮ ታዳጊ ወጣቶች የሚያዘወትሩባቸው መለስተኛ የቅርጫት ኳስ ሜዳዎችና ተያያዥ መሠረተ ልማቶችን በመገንባት የጀመሩት ፕሮጀክት፣ ከክልሉ ኃላፊዎች ዘንድ የሚፈልጉትን ያህል ተቀባይነት ሊያገኝ ባለመቻሉ ፕሮጀክቱ ሊቋረጥ መቻሉን ያወሳሉ፡፡

በአማራ ክልል ያጡት ተቀባይነት ብዙም እንዳላስከፋቸው የሚናገሩት ሚስተር ዣቪ፣ የወልዲያው ፕሮጀክት ከተቋረጠ በኋላ፣ ከኢትዮጵያ ቅርጫት ኳስ ፌዴሬሽን ጋር ግንኙነት አድርገው ፕሮጀክቱን በደቡብ ክልል ወልቂጤና ሐዋሳ እንዲሁም በአዲስ አበባ የካ ክፍለ ከተማ ላይ አቋቁመው በአሁኑ ወቅት፣ ፕሮጀክቱ ከፍ ባለ ደረጃ የሚንቀሳቀስበት ደረጃ ላይ መድረሱን ያስረዳሉ፡፡ ከሰሞኑም የፕሮጀክቱን አጠቃላይ ይዘትና እንቅስቃሴ በሚመለከት ከወልቂጤና ሐዋሳ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር የሁለትዮሽ ስምምነት ማድረጋቸውን ጭምር ያብራራሉ፡፡

ፕሮጀክቱ በዋናነት የኢትዮጵያ ቅርጫት ኳስ አሁን ከሚገኝበት ደረጃ ከፍ ማለት ይችል ዘንድ የስፖርቱ መገኛ ከሆኑ ትምህርት ቤቶች፣ ዩኒቨርሲቲዎችና ከሌሎችም ተቋማት ጋር ትስስር ፈጥሮ፣ ተቋማቱም በባለቤትነት እንዲያስተዳድሩት የሙያና የቁሳቁስ ድጋፍ ማድረግን እንደሚያካትት የሚናሩት ሚስተር ዣቪ፣ በስፔን እግር ኳሱን ጨምሮ ሁሉም ስፖርቶች አሁን ለደረሱበት ደረጃ የበቁት እ.ኤ.አ ከ1992 የባርሴሎና ኦሊምፒክ በኋላ መንግሥትና የስፖርቱ ባለድርሻ አካላት በጋራ ቁጭ ብለው፣ ሥልጠናው ከትምህርት አሰጣጡ ጋር ተዛምዶና ተጣጥሞ መሄድ እንዳለበት መተማመን ላይ ከደረሱ በኋላ ነው፡፡ ስፖርት እንደ አንድ የልማት ተቋም ሆኖ መቀጠል እንዳለበት፣ ሙያው በወጣቱ ዘንድ ቅቡል ሆኖ ለማኅበረሰቡ ሊያበረክት የሚችለውን ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጠቀሜታ እንዲረዳ ተደርጓል፣ ውጤትም አስገኝቷል በማለት ሒደቱን ያስረዳሉ፡፡

የአሴዴ ጋቫ ካታላን ክለብ ፕሬዚዳንትና ልዑካናቸው ከሰሞኑ ወልቂጤና ሐዋሳ እንዲሁም በአዲስ አበባ ተንቀሳቅሶ ፕሮጀክቶቹ የሚገኙበትን ሁኔታ በመገምገም ትጥቅና መሰል እገዛዎችን አድርጓል፡፡ ፕሮጀክቱ በወልቂጤ ቀደም ሲል ባስገነባቸው መለስተኛ የቅርጫት ኳስ ሜዳዎች በሥልጠና ላይ ለሚገኙ ታዳጊ ወጣቶች አሠልጣኞች የሙያ ማሻሻያ ሥልጠና እንዲያገኙ፣ ተጨማሪ ማዘውተሪያዎች እንዲገነቡ፣ እያንዳንዱ ማዘውተሪያ ሴቶችን ያማከለ እንዲሆን ከከተማ አስተዳደሩና ከዩኒቨርሲቲ ኃላፊዎች ጋር ተነጋግሮ መግባባት ላይ ደርሷል፡፡ የኢትዮጵያ ቅርጫት ኳስ ፌዴሬሽን ለዚህ የአንበሳውን ድርሻ እንደሚይዝ ጭምር ያስረዳሉ፡፡

የሐዋሳውን ፕሮጀክት በተመለከተ፣ ከዓምና ጀምሮ 12 ቡድኖች ከተለያዩ ትምህርት ቤቶች በሁለቱም ጾታ ስድስት ወንዶችና ስድስት ሴቶች የሚወዳደሩባቸው መለስተኛ (ሚኒ) ሜዳዎች ተዘጋጅተው ውድድር እንዲጀምሩ ስለመደረጉም የክለቡ ፕሬዚዳንት ተናግረዋል፡፡

የልዑካን አባላቱ በጉብኝታቸው ወቅት ማለትም በወልቂጤም ሆነ በሐዋሳ እንዲሁም በአዲስ አበባ ተግዳሮት ሆኖ የተመለከቱት፣ ተመሳሳይ የማዘውተሪያ ችግር መኖሩን ነው፡፡ በማዘውተሪያ ደረጃ ከቅርጫት ኳስ በተሻለ እግር ኳስ ላይ ማዘውተሪያዎች በበቂ ደረጃም ባይሆን የሚሻል ነገር መታዘባቸውን ያስረዱት ሚስተር ዣቪ፣ “በጣም በሚገርም ሁኔታ አዲስ አበባን ጨምሮ በአንዳንድ ክልሎች ስታንዳርዳቸው በታላላቅ አገሮች ደረጃ የሚታይ ግዙፍ የስታዲየሞች ግንባታ እየተከናወነ ነው፡፡ አቅሙ ካለ ጥሩ ነው፣ ይሁንና ቅድሚያ ለሚሰጠው ቅድሚያ መስጠት ላይ ክፍተት አይቻለሁ፡፡ በኢትዮጵያ አሁን ባለው ሁኔታ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባው አነስተኛ ለሆኑ ማዘውተሪያዎች ነው፡፡ በካታላን በተለይ ቅዳሜና እሑድ በቅርጫት ኳስ ብቻ ብንመለከት፣ በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ታዳጊዎች በመለስተኛ ማዘውተሪያዎች ስፖርቱን እንዲያዘወትሩ ይደረጋል፤” ይላሉ፡፡

በማሳያነት የሦስት ዓመት ሴት ልጅ እንዳለቻቸው የሚናገሩት የክለቡ ፕሬዚዳንት፣ “ሕፃኗ የቅርጫት ኳስ አዘውታሪ ነች፡፡ በኢትዮጵያም ይህ ዓይነቱ አሠራር መለመድና መዘውተር ይኖርበታል፡፡ ጤናማና ነገን ማለም የሚችሉ ታዳጊዎች ማፍራት የሚቻለው በዚህ መንገድ ነው፡፡ እንደተረዳሁት በኢትዮጵያ ብዙዎቹ ትምህርት ቤቶች ማዘውተሪያ የላቸውም፣ እዚህ ላይ መንግሥትም ሆነ የሚመለከታቸው ወገኖች ለአገሪቱ ስፖርት ብቻ ሳይሆን፣ አካሉ በስፖርት የፈረጠመ ጤናማና አምራች ዜጋ ለማፍራት ያን ያህል ወጪ ለማይጠይቁ ለመለስተኛና ለአነስተኛ ማዘውተሪያዎች ትኩረት ሊሰጡ ይገባል፤” በማለት የአገራቸውን ተሞክሮ ይናገራሉ፡፡

ኢትዮጵያውያን ፅናት የሚጠይቁ እንደ አትሌቲክስ ለመሰሉ ስፖርቶች ካልሆነ፣ ቅርጫት ኳስን ጨምሮ ለሌሎች ስፖርቶች የብዙዎቹ ታዳጊዎች ተክለ ሰውነት የሚመጥን እንዳልሆነ የሚያምኑ አሉ፡፡

የአሴዴ ጋቫ ካታላን ክለብ ፕሬዚዳንት ግን ለዚህ አባባል የሰጡት መልስ፣ “እውነት ነው ኢትዮጵያ በሩጫው ዓለም አቀፍ ዕውቅናና ክብር ያተረፉ ታላላቅ አትሌቶችን የምታፈራ አገር ነች፡፡ እንደተባለው ሩጫ ፅናት የሚጠይቅ ስፖርት ነው፣ ቅርጫት ኳስም በተመሳሳይ ፅናትን ይጠይቃል፡፡ ሌሎችም ስፖርቶች እንደዚሁ፡፡ ቀደም ሲል እንደገለጽኩት ካታላን እ.ኤ.አ ከ1992 የባርሴሎና ኦሊምፒክ በፊት እግር ኳሱን ጨምሮ ቅርጫት ኳሳችን አሁን ያለበት ደረጃ ላይ አልነበረም፡፡ ከዚያን በኋላ መደረግ ያለበትን ሁሉ አደረግን ተሳካልን፣ ገና ብዙ ይቀረናል፡፡ በኢትዮጵያም የዚህ ተመሳሳይ አስተሳሰብ መምጣት ይኖርበታል፡፡ አሁን ባለው አስተያየት ከመስጠት ባለፈ ለቅርጫት ኳሱም፣ ለእግር ኳሱም ሆነ ለሌሎቹ ስፖርቶች ማድረግ ያለብን ሁሉ አድርገናል ግን አልተሳካልንም፣ ከሆነ አላውቅም፡፡ እኔ እስካየሁት ድረስ ገና ብዙ ሥራ ይጠብቃችኋል፤” ብለው ተዘዋውረው እንዳረጋገጡት ከሆነ፣ የብዙዎቹ ታዳጊዎች ችግር የተሰጥዖና የፅናት ሳይሆን በትኩረት ያልተሠራባቸው መሆኑን ነው በማለት ያስረዳሉ፡፡

ከቅርጫት ኳስ ፕሮጀክት ጋር በተገናኘ ከወልቂጤ፣ ከሐዋሳና ከአዲስ አበባ በተጨማሪ፣ በኦሮሚያ ክልል ጅማ ከተማ ላይ አንድ ፕሮጀክት ለማቋቋም፣ ከጅማ ከተማ ከንቲባ ጋር መስማማታቸው የክለቡ ፕሬዚዳንት ሳይገልጹ አላለፉም፡፡ እንደ ሚስተር ዣቪ ከሆነ፣ የጅማ ከተማ ከንቲባ አቶ መኪዩ መሐመድ በ2012 የውድድር ዓመት በኢትዮጵያ ቅርጫት ከኳስ ፕሪሚየር ሊግ መወዳደር የሚችል አንድ የሴቶች ቡድን ለማቋቋም ከተማ አስተዳደሩ ወስኗል፡፡ ፕሮጀክቱን በተመለከተ ደረጃውን የጠበቀ እንዲሆን አስፈላጊው እገዛ እንደሚያደርጉላቸው ቃል የገቡላቸው ስለመሆኑ ጭምር አስረድተዋል፡፡  

ስፖርቱ ካደረጃጀት ጀምሮ ሙያተኞች የማሠልጠን ብቃት፣ የትምህርት አሰጣጥ ዘዴን አሁን ላይ ካለው ነባራዊ እውነታ ጋር ማጣጣም እንደሚያስፈልግ የሚያስረዱት ሚስተር ዣቪ፣ ከቅርጫት ኳስ በተጨማሪ ቀጣይ ትኩረታቸው የእግር ኳስ ፕሮጀክት ማቋቋም እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

ለዚህም ፕሮጀክት እገዛ የሚያደርጉላቸውን የካታላን ተቋማት በሚመለከት ሚስተር ዣቪ ሲያስረዱ፣ ባርሴሎና ውስጥ ባርሴሎናን ጨምሮ ለሌሎችም ክለቦች ታዳጊዎችን በመመገብ ትልቅ ዕውቅና ያለው ጁፒተር የታዳጊዎች ፕሮጀክትን በብቸኝነት ይጠቅሳሉ፡፡ ፕሮጀክቱ መላው ካታላውያን እምነት የሚጥሉበት መሆኑ ብቻ ሳይሆን፣ ታዳጊዎችን ወደ ፕሮጀክቱ የሚያስገባው ከአራት ዓመት ጀምሮ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ለምንጀምረው ፕሮጀክት የተቋሙ ኃላፊዎችና ሙያተኞች ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጡ በማድረግ ስለፕሮጀክቱ ምንነት እንዲያስረዱና ፕሮጀክቱም እንዲከፈት እገዛ እንደሚያደርጉ መተማመኛ ስለማግኘታቸው ጭምር ያስረዳሉ፡፡

በካታላን ላሜሲያና እስፓኞል የተሰኙ ፕሮጀክቶች እንዳሉ ያስረዱት ሚስተር ዣቪ፣ ጁፒተር ከእነዚህ የሚለየው ወደ ተቋሙ የሚገቡ ታዳጊዎች ተሰጥዖ አላቸው የላቸውም ብሎ ሳይሆን፣ ለሁሉም እኩል ዕድል በመስጠት ነው፡፡ ላሜሲያና እስፓኞል ግን ከሁሉም ዓለማት የሚመለምሏቸው ታዳጊዎች ታለንት ያላቸው መሆን ይኖርበታል፣ ዕድሜያቸውን በተመለከተም ከስምንት ዓመት በላይ መሆን ይጠበቅባቸዋል በማለት ፕሮጀክቶቹ ከጁፒተር ፕሮጀክት ጋር ያላቸውን ልዩነት ያስረዳሉ፡፡

እንደ ክለቡ ፕሬዚዳንት፣ (እሳቸው የስፔንን ስፖርት የሚገልጹት ካታላን እያሉ ነው) ይሁንና ለስፔን ስፖርት አሁን ለደረሰበት ደረጃ ቁልፍ ሚና መጫወት የቻለው፣ በአገሪቱ ለታዳጊዎች የሚሰጠው ትኩረት ተሰጥዖ አለው የለውም በሚል ሳይሆን፣ ከመጀመሪያው ለሁሉም ታዳጊዎች እኩል ዕድል በመስጠት እንደየ ዝንባሌያቸው ትክክለኛው ከታች ጀምሮ ተገቢው ሥልጠናና ክትትል ማድረግ በመቻሉ ነው፡፡

ይህንኑ በቀጣይ ወደ ኢትዮጵያ ማምጣት ይቻል ዘንድ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ወጣቶች አካዲሚ እንዲሁም ሌሎች ጉዳዩ የሚመለከታቸው መንግሥታዊ ተቋማት ከእሳቸውና ልዑካናቸው ጋር በጋራ ለመሥራት ፈቃደኛ ከሆኑ በሁሉ ነገር እገዛ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን ጭምር አስረድተዋል፡፡           

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...