Thursday, December 7, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በቴሌኮም ማማ ምርቶቹ የሚታወቅ ኩባንያ የኢትጵያን ገበያ የመቀላቀል ፍላጎት እንዳለው አስታወቀ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ኢትዮጵያ 1.5 ቢሊዮን ዶላር የሚጠይቁ የቴሌኮም ማማዎች እንደሚተከሉ ተገምቷል

ሔሊዮስ ታወርስ የተሰኘውና በአፍሪካ ሰፊ የቴሌኮም መሠረተ ልማት አውታሮች ግንባታ ላይ ጉልህ የገበያ ድርሻ በመያዝ የሚጠቀሰው ኩባንያ፣ በኢትዮጵያ የቴሌኮም ማማዎችን ለመገንባት እንደሚፈልግ አስታወቀ፡፡

የኩባንያው ኃላፊዎች ኅዳር 25 ቀን 2012 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከቴሌኮም ዘርፍ ባለድርሻ አካላት ጋር ባካሄዱት ስብሰባ ወቅት እንዳስታወቁት፣ በኢትዮጵያ እየተካሄደ በሚገኘው የቴሌኮም ዘርፍ ማሻሻያ መሠረት፣ ሁለት የግል ኦፕሬተሮች እንደሚገቡ መንግሥት ይፋ ማድረጉን ተከትሎ በርካታ ኩባንያዎች እየመጡ ነው፡፡ ምንም እንኳ ሔሊዮስ ታወርስ ዋና ሥራው ከኔትወርክት ኦፕሬተርነት ውጪ ባለው የማማ ግንባታ ሥራ ላይ ቢያተኩርም፣ ከኦፕሬተሮች ጋር በመሆን በገበያው ውስጥ የመሰማራት ፍላጎቱን ይፋ አድርጓል፡፡

የኩባንያው ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሚስተር ካሽ ፓንዲያና የፋይናንስ ዘርፍ ዋና ኃላፊው ሚስተር ቶም ግሪንውድ እንዳስታወቁት፣ በኢትዮጵያ እየተስፋፋ በሚገኘው የቴሌኮም ኢንዱስትሪ ውስጥ የመሠረተ ልማት ግንባታውም በከፍተኛ ደረጃ እያደገ እንደሚመጣ ይገመታል፡፡ በዚህ መሠረት ከሦስት እስከ አምስት ዓመታት ባሉት ጊዜያት ውስጥ በኢትዮጵያ ከ10 ሺሕ ያላነሱ የቴሌኮሙዩኒኬሽን ማማዎችን መትከል እንደሚያስፈልግ ኃላፊዎቹ ይገልጻሉ፡፡

ለዚህም የ1.5 ቢሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልግ አክለዋል፡፡ ለእያንዳንዱ የቴሌኮም ማማ መትከያ ቦታ 10 ካሬ ሜትር ስፋት ያለው መሬት እንደሚያስፈልግም ተብራርቷል፡፡ በዚህም መሠረት 100 ሺሕ ካሬ ሜትር ቦታ ለማማ መትከያ ማዘጋጀትም ይጠበቃል፡፡ እስካሁን ባለው መረጃ በኢትዮጵያ ከስምንት ሺሕ ያላነሱ ማማዎች ለቴሌኮም አግልግሎት እየሰጡ እንደሚገኙ መረጃዎች ጠቅሰዋል፡፡ 

ከመደበኛው የማማ መሠረተ ልማት ዝርጋታ በተጓዳኝ በሕንፃዎች፣ በመንገዶች፣ በባቡር መንገዶች፣ በኤርፖርቶች፣ በመጋዘኖችና በሌሎችም አመቺ ሥፍራዎች ላይ የሚገጠሙ የቴሌኮም በተለይም የሞባይል ሲግናሎችን ለመቀበልና ለማሠራጨት የሚያስችሉ አውታሮችን የሚዘረጋው ሔሊዮስ ታወርስ፣ የራሱን መሠረተ ልማቶች መዘርጋት ብቻም ሳይሆን በግዥ ከተላለፉለት በአሁኑ ወቅት አገልግሎት እየሰጡ የሚገኙትንም ማማያዎች የመግዛት ፍላጎት እንዳለው ሚስተር ፓንዲያ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ እንደ ዋና ሥራ አስፈጻሚው ከሆነ፣ ኩባንያው ዋናው ተግባሩ ማማዎች ላይ የተመረኮዘ በመሆኑ በኦፕሬተርነት የመሳተፍ ዕቅድ የለውም፡፡ በኢትዮ ቴሌኮም ውስጥም የመሳተፍ ዕቅድ አልያዘም፡፡ ሆኖም ኢትዮ ቴሌኮም በከፊል ወደ ግል የሚዛወርበት አካሄድ የማማ ሽያጮችን ታሳቢ ካደረገ ሔሊዮስ ሳያቅማማ የመግዛትና የማስተዳደር ፍላጎት መያዙን አስታውቀዋል፡፡

ወደ ኢትዮጵያ ገበያ በሰፊው የመግባት ፍላጎት እንዳለው ቢያስታውቅም ሥጋት ያላቸው ጉዳዮችንም አንፀባርቋል፡፡ በኢትዮጵያ ያለው አንፃራዊ የፀጥታ ሥጋት ለሥራው እንቅፋት ሊሆንበት እንደሚችል ያወሱት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፣ አብረውት ሊሠሩ ከሚችሉት ኩባንያዎችም ጋር ይህንኑ ሥጋት ተጋርቷል፡፡ ኤምቲኤን የተሰኘው የሞባይል ኔትወርክ ኦፕሬተርም ሆነ ቮዳኮም ኩባንያ፣ ለቴሌኮም ሥራ ፈታኝ ካሏቸው መካከል የፀጥታና የሰላም ዕጦት ችግሮች ቀዳሚ ሆነዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት፣ የመሬትና የፋይናንስ ችግሮችም ተካተዋል፡፡

የጀርመን የኢንቨስትመንት ባንክን የቴሌኮም ዘርፍ በመወከል በስብሰባው የተሳተፉት ቤትራም ድሬየር በበኩላቸው፣ እንደ ሔሊዎስ ላሉ ኩባንያዎች የሚሰጡ ብድሮች ተመላሽ እንዲደረጉ የሚያስችል በውጭ ምንዛሪ የሚፈጸም ክፍያና ገንዘቡም ወደ ጀርመን መላክ ስለሚችልበት አግባቡ ማረጋገጫ ማግኘት እንደሚፈልግ፣ ከ10 እስከ 15 ዓመታት ፀንቶ የሚቆይ የመሬት ሊዝ ስምምነት፣ የፀጥታ ዋስትናና ሌሎችም ጉዳዮች በኢትዮጵያ የቴሌኮም መሠረተ ልማት ግንባታን ፈታኝ ሊያደርጉት እንደሚችሉ ገልጸዋል፡፡

እ.ኤ.አ. በ2009 የተመሠረተው ሔሊዮስ ታወርስ በአሁኑ ወቅት ከ7‚000 በላይ ማማዎችን በመትከል በተለይም በጋና፣ በዴሞክቲክ ኮንጎ፣ በኮንጎ ብራዛቪልና በታንዛንያ በሰፊው አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝና በቅርቡም የደቡብ አፍሪካ ገበያን እንደተቀላቀለ መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡

ሔሊዮስ የሞባይል ኔትወርክ ኦፕሬተሮችን መግባት የሚጠባበቅ ሲሆን፣ ቮዳኮምና ኤምቲኤንን ጨምሮ በርካቶች ከጥቂት ወራት በኋላ የሚካሄደውን ጨረታ በመጠባበቅ ላይ እንደሚገኙ ይታወቃል፡፡ በአገሪቱ ዋና ዋና ከተሞች እንደሚስፋፋ የሚጠበቀው የ4ጂ ኔትወርክ ዝርጋታም ለበርካታ ተዋንያን በጉጉት የሚጠበቅ የገበያ ሲሳይ ነው፡፡   

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች