Monday, July 22, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

መንገዶች ባለሥልጣን በስድስት ቢሊዮን ብር ለሚገነቡ አራት መንገዶች ስምምነት ተፈራረመ

ተዛማጅ ፅሁፎች

መንገዶችን ለፖለቲካ ዓላማ ማበላሸትና ግንባታዎችን ማስተጓጎል እንዲቆም ጠይቋል

የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን በ2012 ዓ.ም. ለማስገንባት ካቀዳቸው 78 የመንገድ ፕሮጀክቶች መካከል ከ6.1 ቢሊዮን ብር በላይ የሚጠይቁ የአራት መንገዶችን ግንባታ ለማስጀመር ከተመረጡት ተቋራጮች ጋር ሐሙስ ኅዳር 25 ቀን 2012 ዓ.ም. ተፈራርሟል፡፡

በጠቅላላው 299 ኪሎ ሜትር የሚሸፍኑት አራቱ መንገዶች፣ የሐሙሲት እስቴ፣ ጩለሴ ሶያማ የሎት 2፣ የአደሌ ግራዋና ጎዴ ቀላፎ ሎት 1 ፕሮጀክት ሲሆኑ፣ በሦስት ዓመት ተኩል ጊዜ ውስጥ እንደሚጠናቀቁ በስምምነቱ ወቅት ተገልጿል፡፡ የመንገድ ግንባታው ስምምነት ከዚህ ቀደም ከተደረጉ ስምምነቶች የተለየ ድባብ ነበረው፡፡ እንደ ከዚህ ቀደሙ የባለሥልጣኑ ከፍተኛ ኃላፊዎችና ግንባታዎችን ለማከናወን የተመረጡ ተቋራጮች ብቻ ሳይሆኑ፣ አራቱም መንገዶች በሚያልፉባቸው አካባቢዎች የሚገኙ ነዋሪዎችን የወከሉ የአገር ሽማግሌዎችና የወረዳ አመራሮች ታድመው ነበር፡፡ ይህም ስምምነቱን የተለየ አድርጎታል፡፡ ይህ የሆነበት ምክንያት የመንገድ ግንባታው በአግባቡ እንዲካሄድ፣ ሕዝቡም ለሥራው ተባባሪ እንዲሆን ለማስቻል እንደሆነ ተገልጿል፡፡ ከዚህም ባሻገር ፕሮጀክቶቹን ለማስጀመር ከዓመታት በፊት ቢታቀድም፣ ግንባታቸው እስካሁን ባለመጀመሩ ሳቢያ፣ የሕዝብ እሮሮ ሲቀርብባቸው የቆዩ መንገዶችም በመኖራቸው ይህንን ችግር ላለመድገምና ለሕዝቡ ጥያቄም ምላሽ ለመስጠት መንገዶቹ ወደ ግንባታ እንዲገቡ ማስፈለጉ ተብራርቷል፡፡ መንገዶቹ በሚዘረጉባቸው አካባቢዎች የሚገኙ ነዋሪዎች በተጓተቱ ግንባታዎች ሳቢያ በተደጋጋሚ አቤቱታ ሲያቀርቡ እንደቆዩ፣ ቀን ወጥቶላቸው ፕሮጀክቶቹን ለማስጀመር የሚያስችሉ ስምምነቶች መፈረማቸውም ትልቅ ቁም ነገር እንደሆነ የባለሥልጣኑ ኃላፊዎች ገልጸዋል፡፡

የግንባታ ስምምነቶቹ ሲፈረሙ በመንገዶች ባለሥልጣን ጽሕፈት ቤት የተገኙ የየአካባቢው ተወካዮች፣ የፕሮጀክቶቹ መዘግየት ሆድ ሲያስብሳቸው እንደቆየ በመግለጽ የመንገዶቹ ግንባታ ስምምነቶችን ለማየት በመብቃታቸው ግን ምሥጋናቸቸውን አሰምተዋል፡፡ እንደሚገነቡ ቃል ተገብቶላቸው በሰበብ አስባቡ በዘገዩት አራት የመንገድ ፕሮጀክቶች በተቀመጠላቸው ጊዜ ሰለዳ መሠረት ቢሳኩ ኖሮ የሁለተኛውን የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ የመንገድ ዘርፍ ልማት ግቦች ለማሳካት ያስችሉ ነበር፡፡  ለአራቱም መንገዶች ግንባታ የወጡትን ጨረታዎች ያሸነፉት የቻይና ተቋራጭ ናቸው፡፡

የሐሙሲት እስቴ መንገድ ፕሮጀክት በአማራ ክልል የሚካሄድ ሲሆን፣ ከአዲስ አበባ 595 ኪሎ ሜትር ርቆ የሚካሄድ ነው፡፡ የ76.6 ኪሎ ሜትር ርዝማኔ ያለውን ይህን ፕሮጀክት በአስፋልት ኮንክሪት ደረጃ ለመገንባት የ1.39 ቢሊዮን ብር ወጪ ይጠይቃል፡፡ የሐሙሲት እስቴ መንገድን ለመገንባት ጨረታውን በማሸነፍ የውል ስምምነት የፈረመው ኒንሺያ ኮሙዩኒኬሽን ኮንስትራክሽን ካምፓኒ (ኤንሲሲሲ) የሚባል የቻይና ሥራ ተቋራጭ ነው፡፡

በደቡብ ክልል የሚገነባውና 79.5 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው ጩላሴ ሶያማ (የሎት ሁለት) የሚባለው መንገድ ነው፡፡ ይህንን መንገድ በአስፋልት ኮንክሪት ደረጃ ለመገንባት በ1.8 ቢሊዮን ብር ወጪ ለመገንባት ጨረታ በማሸነፍ ስምምነት የፈረመው ቻይና ሬልዌይ 14 የተባለ ሥራ ተቋራጭ ነው፡፡ (የሎት ሁለት) ቹለሴ ሶያማ የመንገድ ፕሮጀክት የጎን ስፋት በከተማ የመንገድ ትከሻን አካቶ 40 ሜትር የሚለጠጥ ሲሆን፣ የገጠር መንገድ ትከሻን ጨምሮ ሰባት ሜትር ስፋት ይኖረዋል፡፡ የግንባታ ወጪውም በመንግሥት አቅም ይሸፈናል፡፡

ሦስተኛው ፕሮጀክት በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ሐረርጌ ውስጥ የሚገነባውና ከአዲስ አበባ 501 ኪሎ ሜትር ርቆ ከአደሌ ግራዋ ድረስ የሚዘልቀው መንገድ ነው፡፡ ይህ መንገድ 55 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው ሲሆን፣ ግንባታውን በአስፋልት ኮንክሪት ደረጃ ለማካሄድ በ1.43 ቢሊዮን ብር የውል ስምምነት የወሰደው የቻይና ተቋራጭ ሂቤ የሚባል ኩባንያ ነው፡፡

መንገዱ ተገንብቶ ሲጠናቀቅ አደሌ፣ ቆሬ፣ አምበር፣ ቢፍቱ፣ ዳዌ፣ ቁርፋ፣ አራሚቱና ግራዋ ከተሞች የሚያገናኝ ይሆናል ተብሏል፡፡ የአደሌ ግራዋ የመንገድ ፕሮጀክት የጎን ስፋት በከተማ የመንገድ ትካሽን ጨምሮ 19 ሜትር ሲሆን፣ በገጠር ትካሽን ጨምሮ ሰባት ሜትር ስፋት ይኖረዋል ተብሏል፡፡ የዚህንም መንገድ የግንባታ ወጪ በኢትዮጵያ መንግሥት የሚሸፈን እንደሆነ ታውቋል፡፡

በአራተኛው ተዋዋይ የሚገነባው መንገድ በሶማሌ ክልል የሚገኘው ጎዴ – ቀላፎ – ፍርፍር (ሎት አንድ) ጎዴ ቀላፎ ፕሮጀክት ነው፡፡ 88.5 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለውን ይህን መንገድ በአስፋልት ኮንክሪት ደረጃ ለመገንባት የተዋዋለው ቻይና ሬልዌይ ሰቨንስ ግሩፕ ሲሆን፣ ለግንባታ ያሸነፈበት ዋጋም 1.53 ቢሊዮን ብር ነው፡፡ የመንገዱ የጎን ስፋት በከተማ የመንገድ ትከሻን ጨምሮ አሥር ሜትር ሲሆን፣ በገጠር የመንገድ ትከሻን አካቶ ስምንት ሜትር ስፋት ይኖረዋል፡፡ የዚህ መንገድ የግንባታ ወጪም በኢትዮጵያ መንግሥት ይሸፈናል፡፡ የጎዴ ቀላፎ (ሎት አንድ) ግንባታን ለማጠናቀቅ የሦስት ዓመት ከስድስት ወራት ጊዜ ተሰጥቶታል፡፡

መንገዶቹ ካላቸው ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጠቀሜታ አንፃር ታይቶ በአሁኑ ወቅት በአስፋልት ኮንክሪት ደረጃ እንዲገነቡ ታቅዶ ውል ስምምነቱ ተፈርሟል፡፡ በስምምነቶቹ ወቅት ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ሀብታሙ ተገኘ (ኢንጂነር) በብርቱ ሊታሰብበት እንደሚገባ ያስጠነቀቁት ጉዳይ፣ የመንገድ ሥራዎቹ በተያዘላቸው ጊዜ ውስጥ እንዲጠናቀቁ ለማስቻል ኅብረተሰቡ አስተዋጽኦ እንዲያበርክት ነው፡፡ ‹‹መንግሥት እየተፈተነ ነው፡፡ ግንባታዎችን የሚያስተጓጉሉ ድርጊቶች መታረም አለባቸው፤›› ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፣ መንገዶቹ  ከሚገነቡባቸው አካባቢዎች የመጡ የአገር ሽማግሌዎችና የወረዳ አመራሮችም የዓመታት ጥያቄዎቻቸው እንዲመለሱላቸው በሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ላይ ከሚደረጉ አደናቃፊ ተግባራት እንዲከላከሉ ጠይቀዋል፡፡ የመንገድ ልማት የሕዝብ ሀብት እንደሆነ በመግለጽ፣ ‹‹ምንም ዓይነት የፖለቲካ ፍላጎት ቢኖር፣ የመንገድ ልማት ሕዝብ መሆኑን በመገንዘብ ሥራው በተያዘለት ጊዜና በጥራት ተገንብቶ እንዲያልቅ ሁሉም ኃላፊነቱን መወጣት አለበት፤›› ብለዋል፡፡ ከደቡብ፣ ከአማራና ከሶማሌ ክልል የመጡ የአገር ሽማግሌዎችና አመራሮች መንገዶቹ ያለ ችግር እንዲገነቡ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንደሚያበረክቱ በተወካዮቻቸው በኩል ቃል ገብተዋል፡፡

የመንገድ ፕሮጀክቶቹ ከስምምነት ፊርማ ባሻገር በአስቸኳይ ወደ ሥራ እንዲገቡላቸው ጠይቀዋል፡፡ የመንገዶቹ ግንባታ በሚጠናቀቅበት ወቅት የግብርና ምርቶችንም ሆነ ሌሎች ምርቶችን ካለ ምንም ችግር ወደ ገበያ ለማውጣት ያስችላል፡፡ በተጨማሪም ከዚህ በፊት በአካባቢ የነበረውን የተቀላጠፈ የትራንስፖት ችግር በመቅረፍ የአካባቢ ኅብረተሰብ በተመጣጣኝ ዋጋ ወደ ፈለገው ቦታ የሚንቀሳቀስበትን ሁኔታ በማመቻቸት ከፍተኛ ጠቀሜታ ያበረክታሉ ተብሎ ታምኗል፡፡

የመንገዶቹ ግንባታ በሚጠናቀቅበት ወቅት ከዚህ በፊት በአካባቢው የነበረውን የትራንስፖርት ችግር በመቅረፍ የአካባቢ ኅብረተሰብ በቀላሉ ወደ ፈለገው ቦታ የሚንቀሳቀስበትን ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር ከመሆኑም ባሻገር፣ በኢንቨስትመንት የተሰማሩ ባለሀብቶች ያመረቱትን ምርት ወደ ገበያ ለማውጣት እንዲችሉና ሌሎች ባለሀብቶችም በአካባቢው ኢንቨስት ለማድረግ ተነሳሽነትን ከመፍጠር አኳያ የዚህ መንገድ መገንባት ጉልህ ሚና ይኖረዋል ተብሏል፡፡

እዚህን አራቱ መንገዶች የሚገነቡት አራቱ የቻይና ኮንትራክተሮች ተወካዮችም ለመንገዱ በተያዘላቸው ጊዜ ለማጠናቀቅ የተቻላቸውን ጥረት እንደርጋለን ብለዋል፡፡  በዕለቱ መንገዶች ውስጥ የሐሙሲት እስቴ መንገድ ፕሮጀክትን የማማከርና የቁጥጥር ሥራውን የሚያከናውኑት ከሃቲምና አልሃሚን አማካሪ መሐንዲሶች ከኮር አማካሪ መሐንዲሶች ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ድርጅት ጋር በጋራ በመሆን ነው፡፡ የጎዴ ቀላፎ ፕሮጀክትን ደግሞ አማካሪ ሆኖ እንዲሠራ የተመረጠው ስታዲዮም መሐንዲሶች አማካሪ ድርጅት ሲሆን፣ ለሁለቱ የመንገድ ፕሮጀክቶችን አማካሪ ድርጅት ለመቅጠር በጨረታ ሒደት ላይ ስለመሆኑ ለማወቅ ተችሏል፡፡ የሐሙሲት እስቴ የመንገድ ፕሮጀክት የጎን ስፋት በከተማ የመንገድ ትከሻን ጨምሮ ሰባት ሜትር ሲሆን፣ በገጠር ትከሻን ጨምሮ ሰባት ሜትር ስፋት ይኖረዋል፡፡ ለዚህ መንገድ ፕሮጀክት ማስፈጸሚያ ወጪም የዓረብ ባንክ ከአፍሪካ ልማት ባንክ በመተባበር ይሸፍናል ተብሏል፡፡

የመንገዶቹን የግንባታ ስምምነት በባለሥልጣኑ በኩል ሀብታሙ (ኢንጂነር) የፈረሙ ሲሆን፣ ተቋራጮቹን የየኩባንያዎቹ ሥራ አስኪያጆችና ተወካዮቻቸው ፈርመዋል፡፡  ከአራቱ ሁለቱ ለኢትዮጵያ የመንገድ ግንባታ ዘርፍ አዲሶች መሆናቸውም ታውቋል፡፡

በግንባታ ስምምነቱ ላይ ጨረታዎቹን በማሸነፍ ግንባታዎቹን የተረከቡት አራቱ ተቋራጮች በሙሉ የቻይና ኩባንያዎች መሆናቸው፣ የአገር ውስጥ ኩባንያዎች ለምን አልተካተቱም የሚል ጥያቄ አስነስቷል፡፡ ዋና ዳይሬክተሩም ይህንኑ በማመን ወደፊት በሚኖሩ ፕሮጀክቶች ላይ የአገር በቀል ተቋራጮች እንደሚሳተፉ ገልጸዋል፡፡ ‹‹ከዚህ በኋላ 78 ያህል ፕሮጀክቶች ስላሉ በእነዚህ ፕሮጀክቶች ውስጥ አገር በቀል ኮንትራክተሮች ይካተታሉ፤›› ብለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች